ለእርዳታ ጥሪህ ምላሽ የሚሰጥህ ማን ነው?
ለእርዳታ ጥሪህ ምላሽ የሚሰጥህ ማን ነው?
አንድ ቁልፍ ስንጫን በአምቡላንሳችን ላይ የተገጠሙት የአደጋ ምልክት መብራቶች እየተብለጨለጩ በአካባቢው ባሉት መኪኖችና ሕንፃዎች ላይ ማንጸባረቅ ይጀምራሉ። ጆሮ የሚበሳው የአምቡላንሱ ጩኸት መኪኖችንም ሆነ እግረኞችን ስለሚያስቆም ብዙም ሳንቸገር በመኪኖቹ መሃል ሰንጥቀን በማለፍ የተጠራንበት ቦታ መድረስ እንችላለን።
ከሃያ ለሚበልጡ ዓመታት ፓራሜዲክ ሆኜ ሠርቻለሁ፤ በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ የጤና ባለሙያዎች፣ የታመሙና አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ሆስፒታል እስኪደርሱ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን የሕክምና እርዳታ ይሰጣሉ። * በዚህ ሥራ ላይ በማንኛውም ሰዓት ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ቀላል ወይም በጣም አሠቃቂ አደጋዎች በሥራዬ ላይ የሚያጋጥሙኝ ሲሆን ውጤቱም በጣም የሚያስደስት አሊያም እጅግ አሳዛኝ ሊሆን ይችላል።
ኅብረተሰቡን በመርዳት ረገድ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ
ፓራሜዲክ ሆነው የሚሠሩ ሰዎች በካናዳ በሕክምናው ዘርፍ የጎላ ሚና ይጫወታሉ። አንድ ሰው ሆስፒታል እስኪደርስ ድረስ እነዚህ ባለሙያዎች የሚያደርጉለት የሕክምና እርዳታ ሕይወቱን ሊያድንለት ወይም ቢያንስ አደጋው አሊያም ሕመሙ የሚያስከትለውን ሥቃይና ጉዳት ሊቀንስለት ይችላል። *
በብዙ ቦታዎች ዓመቱን ሙሉ የ24 ሰዓት የፓራሜዲክ አገልግሎት ማግኘት ይቻላል። በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሚሠሩት ለከተማው ማዘጋጃ ቤት፣ ለግል ድርጅት ወይም ለአንድ ሆስፒታል የድንገተኛ ሕክምና ክፍል ሊሆን ይችላል። አንዳንዶቹ ሥራቸውን የሚያከናውኑት ከአምቡላንስ አገልግሎት ወይም ከእሳት አደጋ ክፍል ጋር በመሆን ነው።
የተለየ ሥልጠና የተሰጣቸው እነዚህ ወንዶችና ሴቶች የእርዳታ ጥሪ እንደደረሳቸው ወዲያውኑ ለሥራ ይንቀሳቀሳሉ። እነዚህ ባለሙያዎች በማንኛውም ሰዓት፣ ያለ ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የእርዳታ ጥሪ ሊደርሳቸው ይችላል። አንድ ሰው ፓራሜዲክ ለመሆን ምን ዓይነት ሥልጠና እንደሚሰጠው እስቲ እንመልከት።
ሕይወት ለማትረፍ የሠለጠኑ ሰዎች
በካናዳ ውስጥ ፓራሜዲክ ለመሆን የሚሰጠው ሥልጠናና ሙያውን ለመግለጽ የሚያገለግሉት ቃላት እንደየግዛቱ ቢለያዩም የፓራሜዲክ ሙያ አብዛኛውን ጊዜ በአራት ደረጃዎች ይከፈላል። እነዚህም ለድንገተኛ አደጋ የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ ባለሙያ፣ የመጀመሪያ እርዳታ የሚሰጥ ባለሙያ፣ ከፍተኛ ደረጃ የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ ባለሙያ እና አስጊ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ሰዎች እርዳታ የሚሰጥ ባለሙያ ናቸው። የተለያዩ የመንግሥት
አካላትና የሕክምናው ዘርፍ ባለሥልጣናት፣ ፓራሜዲክ ሆኖ ለመሥራት የሚፈልግ ሰው አስፈላጊውን ሥልጠና እንደወሰደ የሚያረጋግጥ የምሥክር ወረቀት እንዲኖረው ይጠብቁበታል።እኔ በምኖርበት በካናዳ መሠረታዊ የሆነው ሥልጠና በክፍል ውስጥ እንዲሁም በሆስፒታልና በአምቡላስ ውስጥ ለብዙ ሰዓታት የሚሰጠውን ትምህርት ይጨምራል። በሥልጠናው ወቅት የአንድን ሰው የጤና ሁኔታ የሚጠቁሙትን ምልክቶች ማንበብ፣ ኦክስጅን ለመስጠት የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን መጠቀም እንዲሁም ልባቸው እና ሳምባቸው መሥራት ላቆመ ሰዎች እርዳታ መስጠት የምንችልበትን መንገድ ተምረናል። ከዚህም በተጨማሪ ፋሻ ማሰር፣ አጥንቱ ለተሰበረ ሕመምተኛ መደገፊያ ማድረግ እንዲሁም የበሽተኛው አከርካሪ እንዳይንቀሳቀስ የሚያደርግ መሣሪያ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ ሠልጥነናል።
ከዚህም በላይ በተለያዩ ሆስፒታሎች ድንገተኛ ክፍል፣ ልዩ የሕክምና ክትትል በሚደረግበት ክፍል እንዲሁም በማዋለጃ ክፍል ውስጥ ለ300 ሰዓታት ያህል ጠቃሚ ሥልጠና ተሰጥቶናል። ለመጀመሪያ ጊዜ በማዋለጃ ክፍል ውስጥ የሠራሁበትን ቀን ፈጽሞ አልረሳውም፤ አንድ ልዩ ተአምር ሲሠራ እኔም የተወሰነ ድርሻ እንደነበረኝ ሆኖ ተሰማኝ! ይህ ገጠመኝ ከሌሎች ሁኔታዎች ጋር ተዳምሮ ለቀጣዩ ሥልጠና አዘጋጅቶኛል። ከዚያ በኋላ የወሰድኩት ሥልጠና አደጋ በሚያጋጥምበት ጊዜ ልምድ ያላቸው ሁለት የፓራሜዲክ ባለሙያዎች መመሪያ እየሰጡኝና እያገዙኝ በአምቡላንስ ውስጥ ከ300 ሰዓታት በላይ መሥራትን ይጨምራል። የጽሑፍና የተግባር ፈተናዎችን ካለፍኩ በኋላ ለድንገተኛ አደጋ የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ ባለሙያ ለመሆን የሚያስችለኝን የምሥክር ወረቀት አገኘሁ፤ በአሁኑ ጊዜ በዚህ ሙያ የተሠማራ ሰው የመጀመሪያ እርዳታ የሚሰጥ ባለሙያ ተብሎ ይጠራል።
ለበርካታ ዓመታት በገጠርም ሆነ በከተማ አካባቢዎች ሠርቻለሁ። ሕይወት አድን የሆነው አዲሱ ሙያዬ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለመገንዘብ በሥራው ላይ ብዙ መቆየት አላስፈለገኝም፤ አንድ ቀን በግንባታ ሙያ ላይ የተሠማራ አንድ ሰው ደረቱ አካባቢ ሕመም ስለተሰማው ወደ ሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍል መጣ። ብዙም ሳይቆይ ግን የሰውየው ልብ መምታቱን አቆመ። ከዶክተሮችና ከነርሶች ጋር በመሆን ልቡና ሳምባው መሥራት እንዲጀምር የሚያስችለውን እርዳታና መድኃኒቶችን ሰጠነው። በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ልቡ እንደቀድሞው መምታቱን የቀጠለ ሲሆን ሰውየው ያለ መሣሪያ እርዳታ በራሱ መተንፈስ ቻለ። ከዚያም ልዩ የሕክምና ክትትል ወደሚደረግበት ክፍል ተዛወረ። በማግስቱ ወደዚህ ክፍል ተላክሁ፤ በዚያ የነበረው ሐኪምም፣ አልጋው ላይ ቁጭ ብሎ ከሚስቱ ጋር ከሚያወራ አንድ ሕመምተኛ ጋር አስተዋወቀኝ። መጀመሪያ ላይ ሰውየው ማን እንደሆነ አላወቅኩትም ነበር፤ እሱ ግን “ረሳኸኝ እንዴ? ትናንት እኮ ሕይወቴን አድነህልኛል!” አለኝ። በዚህ ወቅት ምን እንደተሰማኝ መግለጽ ያቅተኛል።
የመጨረሻው ሥልጠና፣ ሕመምተኞችን የምይዝበትን መንገድ ከሚገመግም ሐኪም ጋር ያለማቋረጥ ለ12 ሰዓት መሥራትን የሚጠይቅ ነበር። ከዚያም ቀጣዩን የጽሑፍና የተግባር ፈተና ካለፍኩ በኋላ ከፍተኛ ደረጃ የሕክምና እርዳታ የሚሰጥ ባለሙያ ለመሆን የሚያስችለኝን የምሥክር ወረቀት አገኘሁ።
በፓራሜዲክ ሙያ የሠለጠኑ ሰዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በአንድ የሕክምና ዳይሬክተር ሥር ሆነው ነው፤ ይህ ባለሙያ የሕክምና ባለሙያዎችን ካቀፈ አንድ ኮሚቴ ጋር በመተባበር የሕክምና አሰጣጥ መመሪያዎችን ወይም እቅዶችን ያወጣል። በፓራሜዲክ ሙያ የተሰማሩ ሰዎች አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚሰጡት እነዚህን መመሪያዎች መሠረት በማድረግ ነው፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከተመረጡ ሐኪሞች ጋር በራዲዮ ወይም በስልክ እየተነጋገሩ ሥራቸውን ያከናውናሉ። በዚህም ምክንያት እነዚህ ባለሙያዎች የሐኪሞች ዓይን፣ ጆሮና እጅ እንደሆኑ ተደርገው ይገለጻሉ። በግል ቤት ወይም ሕዝብ በሚበዛባቸው ሕንፃዎች ውስጥ አሊያም ደግሞ የመኪና አደጋ በደረሰበት ቦታ ላይ የተለያየ ዓይነት ሕክምና መስጠት ያስፈልግ ይሆናል። ይህም ኦክስጅንና መድኃኒት መስጠትን እንዲሁም የሕመምተኛው የልብ ምት እንዲስተካከል መርዳትን አልፎ ተርፎም የመተንፈሻ ቱቦ ወደ ሰውነቱ ማስገባትንና ቀዶ ጥገና ማድረግን ሊጨምር ይችላል።— “የፓራሜዲክ ባለሙያ የሚያገኛቸው ሥልጠናዎች” የሚለውን ገጽ 15 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።
ከሥራው ጋር የተያያዙ አደገኛና አስቸጋሪ ሁኔታዎች
አደገኛና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መጋፈጥ የአንድ ፓራሜዲክ የዕለት ተዕለት ሕይወት ክፍል ነው። በማንኛውም ዓይነት የአየር ሁኔታ፣ አንዳንድ ጊዜም አደገኛ በሆነ ቦታ ወይም ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሥራውን ያከናውናል። ሌላው ቀርቶ የእርዳታ ጥሪ
ወደተደረገበት ቦታ ለመድረስ ሲባል መኪና በፍጥነት ማሽከርከር በራሱ አደገኛ ሊሆን ይችላል።በዚህ ሙያ ላይ የተሰማራን ሰዎች፣ ደምንና ከሰውነት የሚወጡ ፈሳሾችን መንካት ለሚያስከትለው አደጋ እንዲሁም ለተላላፊ በሽታ የተጋለጥን ነን። ራሳችንን ለመጠበቅ እንደ አስፈላጊነቱ ጓንት፣ ጭምብል፣ መነጽር ወይም የፊት መሸፈኛና ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጁ ልብሶችን እንጠቀማለን።
ለሕመምተኞች የምናደርገው እንክብካቤ ከቤተሰቦቻቸውና ከጓደኞቻቸው ሌላው ቀርቶ ምንም ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር መነጋገርን ይጨምራል። እነዚህ ሰዎች ስሜታቸው በጣም ከመረበሹ የተነሳ ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ ወይም ያልተጠበቀ ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት አብረው የኖሩ ባልና ሚስት በሞት ሲለያዩ ማየት በጣም ያሳዝናል። ለአንድ ሰው፣ የትዳር ጓደኛውን ሞት ማርዳት ቀላል አይደለም። በአንድ ወቅት ለአንዲት ሴት ባለቤቷ ማረፉን ስነግራት በቡጢ መታችኝ። ከዚያም ከቤቷ ወጥታ እየጮኸችና እያለቀሰች ወደ መንገዱ ሮጠች። ከኋላዋ ተከትዬ ስደርስባት ወደ እኔ ተመልሳ ተጠመጠመችብኝና ምርር ብላ አለቀሰች።
ስሜታቸው የተረበሸ ወይም የአልኮል መጠጥ አሊያም ዕፅ የወሰዱ ሰዎችን ለማረጋጋት ስንጥር ርኅራኄና አዘኔታ ማሳየት ብሎም ዘዴኛ መሆን ይኖርብናል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ መገመት ያዳግታል። ስሜታቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው ሕመምተኞች ሥራዬን በማከናውንበት ጊዜ መተውኛል፣ ተፍተውብኛል እንዲሁም በሌሎች መንገዶች አንገላተውኛል።
ሥራችን፣ ፍጹም በማይመች ሁኔታ ውስጥም ጭምር ሁልጊዜ ከባድ ነገሮችን ማንሳት ስለሚጠይቅ አድካሚ ነው። ሕመምተኞችን ለመርዳት አጎንብሰን ወይም ተንበርክከን ረዘም ላለ ጊዜ መሥራት ሊኖርብን ይችላል። ሥራችንን ስናከናውን ጉዳት ይደርስብናል። ብዙውን ጊዜ ወገባችን፣ ትከሻችንና ጉልበታችን ይጎዳል። አንዳንድ ጊዜ የሚደርሰው ጉዳት በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ፓራሜዲክ ሥራውን ለማቆም ሊገደድ ይችላል። ከዚህም ሌላ በፈረቃ መሥራት የሚጠበቅብን ሲሆን ይህም አድካሚ ነው።
በተጨማሪም ሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ ለሚገኝ ታማሚዎች እንክብካቤ ማድረግ በአእምሮም ሆነ በስሜት ላይ ውጥረት ያስከትላል። የፓራሜዲክ ባለሙያ የሆነ ሰው አስጨናቂ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙት ወቅት መረጋጋት፣ ነገሮችን ማመዛዘንና ማስተዋል የታከለበት ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። የፓራሜዲክ ባለሙያዎች፣ ሰዎች ሲሠቃዩና መከራ ሲደርስባቸው ይመለከታሉ። አሰቃቂ የሆነ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የሚያጋጥሟቸው ከመሆኑም ሌላ ለእነዚህ ሰዎች እርዳታ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በፋብሪካ ውስጥ ሲሠራ አደጋ ያጋጠመው አንድ ወጣት ከአእምሮዬ አይጠፋም። ሰውነቱ ከሆዱ በታች ተጨፍልቆ እንዳልነበር ሆኗል፤ ይህ ወጣት ሕይወቱን እንድናተርፍለት እኔንና የሥራ ባልደረባዬን ተማጸነን። የሚያሳዝነው እኛም ሆንን አብረውን የነበሩት ሐኪሞችና ነርሶች የተቻለንን ያህል ብንጥርም አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሕይወቱ አለፈ።
አንዳንድ ጊዜ በጣም እንድናዝን የሚያደርጉ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። አንድ ቀን ማለዳ ላይ አንድ ቤት በእሳት በመያያዙ ለእርዳታ ተጠራን። ባልየው ሥራ አድሮ ወደ ቤቱ ሲደርስ ሚስቱ የሦስት ዓመት ሴት ልጃቸውን ይዛ በእሳት ከተያያዘው ቤታቸው ሸሽታ ስትወጣ አገኛት። ሆኖም ከአራት ወር እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሌሎች ሦስት ልጆቹና አያታቸው የእሳት አደጋ ሠራተኞች እስኪደርሱ ድረስ ከቤቱ መውጣት አልቻሉም ነበር። ከበርካታ የፓራሜዲክ ባለሙያዎች ጋር ሆነን የእነዚህን ሰዎች ሕይወት ለማትረፍ ከፍተኛ ጥረት ብናደርግም አልተሳካልንም።
ይህንን ሁሉ ስታነቡ ‘ታዲያ አንድ ሰው በዚህ ሙያ ለመሰማራት የሚፈልገው ለምንድን ነው?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። እኔም ራሴን እንዲህ ብዬ የጠየቅኩባቸው ጊዜያት አሉ። እንዲህ ሲሰማኝ ኢየሱስ፣ ጉዳት የደረሰበትን ሰው ለመርዳት ሲል በፈቃደኝነት ብዙ ነገር ስላደረገው ደግ ሳምራዊ የተናገረውን ምሳሌ አስታውሳለሁ። (ሉቃስ 10:30-37) የፓራሜዲክ ባለሙያ የሆነ ሰው፣ አንድ ግለሰብ ለሚያሰማው የእርዳታ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ሲል ስለ ራሱ ሳያስብ ግለሰቡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ያደርጋል። እኔ በግሌ የፓራሜዲክ ሙያ እርካታ የሚያስገኝ ሥራ ሆኖልኛል፤ ያም ሆኖ ሙያዬ አስፈላጊ የማይሆንበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ። እንዲህ ያልኩት “ታምሜአለሁ” የሚል አንድም ሰው የማይኖርበት ጊዜ በቅርቡ እንደሚመጣ አምላክ ቃል ስለገባ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ‘ሞትና ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም’ በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሰጥቷል። (ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:4)—በካናዳ የሚኖር የፓራሜዲክ ባለሙያ እንደተናገረው
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 ፓራሜዲክ ሆኖ የሚሠራ አንድ ክርስቲያን ስለሚያጋጥሙት ሕሊናውን ሊረብሹ የሚችሉ ነገሮች ለማወቅ የሚያዝያ 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 29ን እንዲሁም የሚያዝያ 1, 1975 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 215-216ን ተመልከት።
^ አን.5 በአንዳንድ አገሮች የአምቡላንስ አገልግሎት የፓራሜዲክ ባለሙያዎችን አይጨምርም። ሕመምተኛውን በተቻለ ፍጥነት ሆስፒታል የማድረሱ ኃላፊነት የሚወድቀው አምቡላንሱን በሚያሽከረክረው ሰው ላይ ነው።
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ሰውየው ማን እንደሆነ አላወቅኩትም ነበር፤ እሱ ግን “ረሳኸኝ እንዴ? ትናንት እኮ ሕይወቴን አድነህልኛል!” አለኝ። በዚህ ወቅት የተሰማኝን ስሜት መግለጽ ያቅተኛል
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ስሜታቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው ሕመምተኞች ሥራዬን በማከናውንበት ጊዜ መተውኛል፣ ተፍተውብኛል እንዲሁም በሌሎች መንገዶች አንገላተውኛል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
የፓራሜዲክ ባለሙያ የሚያገኛቸው ሥልጠናዎች
አንድ ፓራሜዲክ፣ ሕመምተኛው ያለምንም ችግር መተንፈስ እንዲችል ማለትም አየር ወደ ሳምባው እንዲገባ የሚረዳውን ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል ሥልጠና አግኝቷል። ይህን ለማድረግ፣ በሕመምተኛው አፍና ጉሮሮ በኩል ለስላሳ የሆነ የፕላስቲክ ቱቦ ወደ አየር ቧንቧው ማስገባት ያስፈልግ ይሆናል። አሊያም ደግሞ በሕመምተኛው አንገት በኩል በቀጥታ ወደ አየር ቧንቧው ትልቅ ቱቦ (ካቴተር) ማስገባት ያስፈልግ ይሆናል፤ ይህንንም ለማድረግ መርፌ፣ ቀጭን ቱቦ (ካቴተር)፣ ቀጭን ሽቦ እንዲሁም የቀዶ ሕክምና ቢላ ያስፈልጋል። የሕመምተኛው ሳምባ መሥራቱን በማቆሙ ሕይወቱ አስጊ ሁኔታ ላይ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የፓራሜዲክ ባለሞያው በሕመምተኛው ደረት በኩል መርፌና መተንፈሻ ቱቦ ማስገባት ይኖርበታል።
የፓራሜዲክ ባለሙያዎች ኢንትራቬነስ ቴራፒ የሚባለውን ሕክምና መስጠት እንዲችሉም ይሠለጥናሉ። በመርፌ በመጠቀም በሕመምተኛው የደም ሥር ውስጥ ካቴተር ያስገባሉ። በዚህ በኩል እንደ ሳላይን ሶሉሽን ያሉ ፈሳሾችን መስጠት ይቻላል። አሊያም ደግሞ ወደ ሕመምተኛው መቅኒ ፈሳሽ ለማስገባት የሚረዳ መሣሪያ በቀጥታ አጥንቱ ውስጥ ይገባል።
የፓራሜዲክ ባለሙያ የሆነ ሰው የሕመምተኛው የልብ ምት ትክክል መሆኑን ለማወቅ በሚረዳ ካርዲያክ ሞኒተር/ዲፌብሪሌተር በተባለ መሣሪያ ይጠቀም ይሆናል። በተጨማሪም ይህ መሣሪያ የሕመምተኛው ልብ መምታቱን ካቆመ ወይም በጣም በፍጥነት የሚመታ ከሆነ የልብ ምቱን ለማስተካከል ይረዳል። የሕመምተኛው ልብ በጣም ቀስ ብሎ የሚመታ ከሆነ ደግሞ ይህ መሣሪያ ለጊዜው የልብ ምቱን ለማስተካከል ያግዛል።
[ምንጭ]
ሁሉም ፎቶዎች፦ Taken by courtesy of City of Toronto EMS
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Taken by courtesy of City of Toronto EMS