‘ሥራ በጣም ይበዛብኛል!’
‘ሥራ በጣም ይበዛብኛል!’
በኦሎምፒክ ላይ የሚወዳደሩ ክብደት አንሺዎች በየቀኑ አዲስ ሪከርድ ለማስመዝገብ ጥረት አያደርጉም። በየጊዜው አነስ ያሉ ክብደቶችን እያነሱ ልምምድ በማድረግ ከፍተኛ ክብደት ለማንሳት የሚያስችላቸውን ጥንካሬ ያገኛሉ። ልምምድ ባደረጉ ቁጥር የመጨረሻ አቅማቸውን የሚጠቀሙ ከሆነ በጡንቻቸውና በመገጣጠሚያቸው ላይ አደገኛ ውጥረት ሊፈጠር ስለሚችል በዚህ ስፖርት የመቀጠል አጋጣሚያቸው በአጭሩ ይቀጫል።
አንተም ተማሪ እንደመሆንህ መጠን በትምህርት ቤት ትጋት የተሞላበት ጥረት ታደርግ ይሆናል። ከበድ ያለ የቤት ሥራ ሲሰጥህ ወይም ለፈተና ስትዘጋጅ ተጨማሪ ጥረት ለማድረግ ፈቃደኝነቱም ሆነ ችሎታው ይኖርህ ይሆናል። * ይሁንና በእያንዳንዱ ቀን ጊዜህ በሙሉ በትምህርትና በምታከናውናቸው ሌሎች ሥራዎች የተጣበበ ከሆነስ? በዚህ ጊዜ የአመጋገብ ሥርዓትህ ይቃወስ ወይም ጥሩ እንቅልፍ አይወስድህ ይሆናል። ነጋ ጠባ ከፍተኛ ውጥረት የሚያጋጥምህ መሆኑ የኋላ ኋላ ለበሽታ ሊዳርግህ ይችላል። ምናልባትም አሁን ያለህበት ሁኔታ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ይሆናል። *
ማለቂያ የሌለው የቤት ሥራ
በጃፓን የምትኖረው ሂሮኮ * የተባለች የ15 ዓመት ተማሪ እንዲህ ብላለች፦ “ክፍል እየጨመርኩ በሄድኩ ቁጥር የሚሰጠኝ የቤት ሥራ እየበዛና ይበልጥ ከባድ እየሆነ ይሄዳል። የቤት ሥራውን ሠርቶ ለመጨረስ ረጅም ጊዜ ይወስዳል። ማድረግ የምፈልጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሆኖም የቤት ሥራውን አጠናቅቄ በነጋታው ማስረከብ አለብኝ። አንዳንድ ጊዜ ጭንቅ ይለኛል።” በሩሲያ የምትኖረው የ14 ዓመቷ ስቭዬትላነ የሚሰጣትን የቤት ሥራ በተመለከተ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “የቤት ሥራዬን መጨረስ ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነብኝ መጥቷል። የምማራቸው የትምህርት ዓይነቶች ቁጥር በየዓመቱ ይጨምራል፤ አስተማሪዎቹ ደግሞ ብዙ ነገር አንብበን እንድንመጣ ይጠብቁብናል። በተጨማሪም እያንዳንዱ አስተማሪ እሱ የሚያስተምረው የትምህርት ዓይነት ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማዋል። ለሁሉም ጊዜ ማብቃቃትና ሁሉንም ሠርቶ መጨረስ በጣም ከባድ ነው።”
ለቤት ሥራ ይህን ያህል ክብደት የሚሰጠው ለምንድን ነው? በብራዚል የሚኖረው የ18 ዓመቱ ዢልቤርቶ “አስተማሪዎች ከባድ ፉክክር ለሚበዛበት የሥራው ዓለም ሊያዘጋጁን እንደሚፈልጉ ይናገራሉ” ሲል ጽፏል። ምክንያቱ ይህ ቢሆንም እንኳ የሚሰጥህ የቤት ሥራ ብዛት ልትጨርሰው ከምትችለው በላይ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ምናልባት ለቤት ሥራ ያለህን አመለካከት በመቀየርና የተደራጀህ ለመሆን የሚያስችሉህን ጠቃሚ እርምጃዎች በመውሰድ ያለብህን ውጥረት መቀነስ ትችላለህ።
በየጊዜው እየጨመረብህ የሚመጣውን የቤት ሥራ ትልቅ ሰው በምትሆንበት ጊዜ ስኬታማ እንድትሆን የሚያስችል ሥልጠና እንደምታገኝበት አድርገህ ቁጠረው። የቤት ሥራ መሥራት መክብብ 2:24
መቼም የምትላቀቀው ነገር መስሎ ባይታይህም በትምህርት የምታሳልፋቸው ዓመታት ከምታስበው በላይ ቶሎ ያልፋሉ። ራስህን ችለህ ለመኖር መሥራት በምትጀምርበት ጊዜ ተማሪ በነበርክበት ወቅት ይሰጡህ የነበሩትን ከባድ የቤት ሥራዎች ሠርተህ በማጠናቀቅህ ደስ ይልሃል። በትምህርት ባሳለፍካቸው ዓመታት ጠንክረህ መሥራትህ ‘እርካታ’ ያስገኝልሃል።—ትጉና ጠንቃቃ እንዲሁም የተደራጀህ በመሆን የሚሰማህን ውጥረት በእጅጉ መቀነስ ትችላለህ። (“ ውጥረትን ለመቀነስ የሚረዱ ተግባራዊ ዘዴዎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) የቤት ሥራህን በጥንቃቄ የመሥራትና በሰዓቱ የማድረስ ልማድ ካዳበርክ አስተማሪዎችህ እምነት ሊጥሉብህና አንተን የመርዳት ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል። ከአስተማሪዎችህ መካከል ከአንዱ ጋር እንዲህ ዓይነት ጥሩ ግንኙነት አለህ እንበል። አንድ ያልጠበቅከው ነገር ቢገጥምህና የቤት ሥራውን በሰዓቱ ማጠናቀቅ እንደማትችል አስቀድመህ ብትነግረው የሚተባበርህ አይመስልህም? ከአምላክ አገልጋዮች አንዱ የሆነው ዳንኤል “ታማኝ፣ ጠንቃቃና በሥራው እንከን የሌለበት” ሰው ነበር። ዳንኤል ሥራውን በትጋት የሚያከናውን ሰው መሆኑ የንጉሡን ምስጋናና አመኔታ እንዲያገኝ አስችሎታል። (ዳንኤል 6:4) የቤት ሥራህን የምታከናውንበትን መንገድ በተመለከተ የዳንኤልን ምሳሌ የምትከተል ከሆነ አስተያየት እንዲደረግልህ በምትፈልግበት ጊዜ ተቀባይነት ልታገኝ ትችላለህ።
ክፍል ውስጥ በትኩረት ማዳመጥህ፣ የቤት ሥራህን መሥራትህና የሚሰጡህን ፕሮጀክቶች በሰዓቱ ማጠናቀቅህ ከትምህርት ጋር በተያያዘ ከሚያጋጥምህ ውጥረት ሁሉ እንድትገላገል ያስችልሃል? በፍጹም፤ ምክንያቱም በተወሰነ መጠን ውጥረት እንዲሰማህ የሚያደርገው የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያለህ ፍላጎት ሊሆን ይችላል። ከትምህርት ቤት ሥራ ለመገላገል አቋራጭ መንገድ ከመፈለግ ይልቅ ከትምህርቱ እውቀት የመቅሰምና ጥቅም የማግኘት ልባዊ ፍላጎት ይኖርህ ይሆናል።
እንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት ጠቃሚና አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ ጎጂና አላስፈላጊ የሆነ ጭንቀት ሊያጋጥምህ ይችላል።
ተጨማሪ እንቅስቃሴዎች ጊዜ ያሳጣሉ
ሁልጊዜ መኪናውን በኃይል የሚያሽከረክርን አንድ ሰው ለማሰብ ሞክር። በከፍተኛ ፍጥነት እየበረረ መጥቶ ቁም የሚል ምልክት ሲያይ ድንገት ፍሬን እንቅ አድርጎ ይይዛል። ከዚያም ነዳጅ በኃይል ሰጥቶ በከፍተኛ ፍጥነት ይፈተለካል። እንዲህ ያለው ሹፌር የሚያሽከረክራት መኪና መጨረሻዋ ምን የሚሆን ይመስልሃል? በመኪናዋ ሞተር ላይም ሆነ በሌሎች የመኪናዋ ክፍሎች ላይ ጉዳት የማድረሱ አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። ምናልባትም ይህ ከመሆኑ በፊት ከባድ አደጋ ሊከሰትና መኪናዋ ከጥቅም ውጭ ልትሆን ትችላለች።
ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ሰዓት በፊትና በኋላ ሰውነታቸውም ሆነ አእምሯቸው እስኪደክም ድረስ ብዙ ነገር ለማከናወን ይሯሯጣሉ። ደኒዝ ክላርክ ፖፕ የተባሉ ዶክተር በአንዳንድ ተማሪዎች ላይ ያካሄዱትን ጥናት አስመልክተው ዱዊንግ ስኩል በተባለው መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን ሐሳብ ጽፈዋል፦ “እነዚህ ልጆች በትምህርት የሚያሳልፉትን ቀን የሚጀምሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሥራ ከመግባታቸው ከአንድ ወይም ከሁለት ሰዓት በፊት ነው። በቀኑ መገባደጃ ላይ ደግሞ እግር ኳስ ከተጫወቱ፣ ዳንስ ከተለማመዱ፣ በተማሪዎች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ከተገኙ፣ በትርፍ ጊዜያቸው ተቀጥረው የሚሠሩትን ሥራ ከጨረሱና የቤት ሥራቸውን ካጠናቀቁ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ በጣም አምሽተው ይተኛሉ።”
ተማሪዎች በየቀኑ እንዲህ ዓይነት በጥድፊያ የተሞላ ሕይወት የሚመሩ ከሆነ ራሳቸውን ችግር ላይ ይጥላሉ። ከሚያጋጥማቸው ከባድ ውጥረት የተነሳ ለሆድ ዕቃ መታወክና ለራስ ምታት ሊጋለጡ ይችላሉ። የማያቋርጥ የድካም ስሜት በሽታ የመከላከል አቅማቸውን እያዳከመው ሲሄድ በቀላሉ ሊታመሙ ይችላሉ። ከዚያም እንደበፊቱ መሮጥ ያቅታቸዋል፤ የቀድሞ ብርታታቸውን መልሰው ለማግኘት ደግሞ ብዙ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ያንተስ ሁኔታ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል?
ጥሩ ግቦች ላይ ለመድረስ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ መልካም ሊሆን ቢችልም ምንም ያህል ጠንካራ ብትሆን በቀን ውስጥ ማከናወን የምትችለው ነገር ገደብ አለው። መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚል ጠቃሚ ምክር ይሰጣል። (ፊልጵስዩስ 4:5) “ምክንያታዊ” የሚለው ቃል “ጽንፈኛ ያልሆነ ወይም ከገደቡ የማያልፍ” እና “ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታ ያለው” የሚሉ ሁለት ትርጉሞች አሉት። ምክንያታዊ የሆነ ሰው በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ውሳኔዎች አያደርግም። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ዛሬ ባለው ተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ በሳል አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ሲሆን ይህ ደግሞ በዋጋ ሊተመን የማይችል ጠቀሜታ አለው። ስለዚህ ጤንነትህን መጠበቅ እንድትችል ምክንያታዊ በመሆን ከዚህ በፊት ታከናውናቸው የነበሩ እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ አንዳንድ ነገሮችን አስወግድ።
ሀብት ማሳደድ
ይሁን እንጂ አንዳንድ ወጣቶች ምክንያታዊ መሆናቸው ግባቸው ላይ ለመድረስ ከመርዳት ይልቅ እንቅፋት የሚሆንባቸው ይመስላቸዋል። እንዲህ ያሉ ተማሪዎች ለስኬት ቁልፉ ከፍተኛ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ መያዝና ሥራው የተለያዩ ንብረቶች
እንዲያፈሩ ማስቻሉ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ከላይ የተጠቀሱት ፖፕ፣ በጥናታቸው ውስጥ ካካተቷቸው ወጣቶች መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ ያለ አመለካከት እንዳላቸው ተገንዝበዋል። ዶክተሯ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፦ “እነዚህ ተማሪዎች እንቅልፍ የሚተኙበት ተጨማሪ ጊዜ ቢያገኙና ጤንነታቸው ቢሻሻል ደስ ባላቸው ነበር፤ ሆኖም ከትምህርት፣ ከቤተሰብ፣ ከሥራ ግዴታዎችና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያላቸው ፕሮግራም በጣም የተጣበበ መሆኑ ይህን ለውጥ እንዲያደርጉ እድል አይሰጣቸውም። በተጨማሪም ከጓደኞቻቸው ጋር የበለጠ ጊዜ ቢያሳልፉ፣ ሌሎች ነገሮችን ቢያደርጉ ወይም ለጥቂት ቀናት እረፍት ቢወስዱ ይወዱ ነበር፤ ይሁንና አብዛኞቹ እነዚህን ሁሉ እያደረጉ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ይዘው መቀጠል እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። ከሁለት አንዱን መምረጥ እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። ደግሞም አሁን ከሚያገኙት ደስታ ይልቅ ወደፊት የሚያገኙት ስኬት ይበልጥባቸዋል።”ሕይወታቸው በሩጫ የተሞላ እንዲህ ዓይነት ተማሪዎች በአንድ ወቅት ኢየሱስ ለተናገረው ለሚከተለው ጥበብ ያዘለ ሐሳብ ትኩረት መስጠት ይበጃቸዋል፦ “አንድ ሰው ዓለሙን ሁሉ የራሱ ቢያደርግ፣ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ለነፍሱ ምትክ የሚሆን ምን ነገር ሊሰጥ ይችላል?” (ማቴዎስ 16:26) ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ሲል በዚህ ዓለም ውስጥ ግብ አድርገን የምንከታተላቸው ነገሮች በአካላችን፣ በስሜታችንና በመንፈሳዊነታችን ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሥዋዕት ልንከፍልላቸው የሚገቡ እንዳልሆኑ እያስጠነቀቀ ነበር።
የሥነ ልቦና ሐኪም የሆኑት ማደለን ለቫይን ዘ ፕራይስ ኦቭ ፕሪቭሌጅ በተባለ መጽሐፋቸው ላይ “ገንዘብ፣ ትምህርት፣ ሥልጣን፣ ዝናና ቁሳዊ ነገሮች ደስታ ከማጣት ወይም ከስሜት ቀውስ ሊያስጥሉን እንደማይችሉ ሐቁን አምነን መቀበል ይኖርብናል” ሲሉ ጽፈዋል። ፖፕ ደግሞ የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል፦ “ብዙ ልጆችና ወላጆች ስኬትን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ፍጽምና ደረጃ ላይ ለመድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ ተመልክቻለሁ።” አክለውም “ጥረት ማድረግ የሚኖርብን በአእምሮም ሆነ በአካል እንዲሁም ለነገሮች ባለን አመለካከት ረገድ ጤናማ ሆነን ለመገኘት ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
ከገንዘብ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ነገሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል ስሜታዊና አካላዊ ጤንነታችን፣ ጥሩ ሕሊና መያዛችንና ከፈጣሪያችን ጋር ያለን ወዳጅነት ይገኙበታል። እነዚህ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ የአምላክ ስጦታዎች ናቸው። ዝና ወይም ሀብት ለማግኘት ስትሉ እነዚህን ነገሮች አንዴ ካጣችኋቸው መልሳችሁ ላታገኟቸው ትችሉ ይሆናል። ይህን በአእምሯችሁ ይዛችሁ ኢየሱስ ምን ብሎ እንዳስተማረ ልብ በሉ፦ “አምላክ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያውቁ እንዴት ደስተኞች ናቸው! መንግሥተ ሰማይ የእነሱ ነውና።”—ማቴዎስ 5:3 ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ
ብዙ ወጣቶች ይህን እውነታ ተቀብለዋል። በትምህርት በሚያሳልፏቸው ዓመታት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ቢያደርጉም ከፍተኛ ውጤት ማምጣትና ቁሳዊ ሀብት ማካበት ዘላቂ ደስታ እንደማያስገኝ ይገነዘባሉ። እንዲህ ያሉ ግቦችን ማሳደድ አላስፈላጊ ውጥረት እንደሚያስከትልባቸው ያውቃሉ። እነዚህ ተማሪዎች ወደፊት እውነተኛ ደስታ ማግኘታቸው የተመካው “አምላክ እንደሚያስፈልጋቸው” ተገንዝበው ይህን ፍላጎት በማርካታቸው ላይ መሆኑን ተረድተዋል። የዚህ መጽሔት አዘጋጆች ወይም በአካባቢህ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ ጋር ለመቀራረብ ያለህን ፍላጎት በማርካት ደስታ ማግኘት የምትችልበትን መንገድ ሊያሳዩህ ፈቃደኞች ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጡ ወይም በቂ ጥረት የማያደርጉ ተማሪዎችን በተመለከተ በሚያዝያ 1999 ንቁ! ገጽ 20-22 ላይ የወጣውን “ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . የትምህርት ውጤቴን ማሻሻል እችላለሁን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.3 በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በጥር 1994 ንቁ! ገጽ 17-19 ላይ የወጣውን “የወጣቶች ጥያቄ . . . የቤት ሥራ ይበዛል ምን ባደርግ ይሻላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.5 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ምንም ያህል ጠንካራ ብትሆን በቀን ውስጥ ማከናወን የምትችለው ነገር ገደብ አለው
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ስለ ፈጣሪህ እውቀት እያካበትክ መሄድህ ከየትኛውም ትምህርት የላቀ ጥቅም አለው
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ውጥረትን ለመቀነስ የሚረዱ ተግባራዊ ዘዴዎች
❑ የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ወረቀቶችንና ማስታወሻ ደብተሮችን በማገላበጥ ብዙ ጊዜ ታጠፋለህ? አንዳንድ ሰዎች በተሻለ መንገድ የተደራጁ ለመሆን እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ረገድ ሌሎች ሰዎች ሐሳብ እንዲሰጡህ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል።
❑ ዛሬ ነገ የማለት ልማድ አለህ? የተሰጠህን ሥራ ከጊዜው በፊት አጠናቅቀህ ለመጨረስ ጥረት በማድረግ ራስህን ፈትሽ። የምታገኘው የእፎይታና የእርካታ ስሜት ከፍተኛ ደስታ የሚያመጣልህ ከመሆኑም በላይ የቤት ሥራህን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ እንድታቆም ሊያነሳሳህ ይችላል።
❑ በትምህርት ሰዓት ላይ ስትሆን ብዙ ጊዜ ሐሳብህ እየተከፋፈለ ያስቸግርሃል? እስቲ ለአንድ ወር ያህል ይህን ለማድረግ ሞክር፦ በክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት በትኩረት አዳምጥ፤ እንዲሁም በሌላ ጊዜ እንድትጠቀምበት ጥሩ ማስታወሻ ያዝ። እንዲህ ማድረግህ የሚሰጥህን የቤት ሥራ መሥራት ይበልጥ ቀላል እንዲሆንልህ እንደሚያደርግ መመልከት ትችላለህ። በዚህ ረገድ የምታገኘው ጥሩ ውጤት ከትምህርት ጋር በተያያዘ የሚሰማህ ውጥረት እንዲቀንስ ያደርጋል።
❑ ብዙ ጊዜና ጥረት የሚጠይቁ ቢሆኑም የእውቀት አድማስህን ለማስፋት ስትል የምትወስዳቸው ተጨማሪ ኮርሶች አሉ? እነዚህን ኮርሶች መውሰድህ የግድ አስፈላጊ ነው? በጉዳዩ ላይ ከወላጆችህ ጋር ተነጋገር። ስለ ትምህርት ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት ያለው ሰው ሐሳብ እንዲሰጥህ ጠይቅ። እነዚህ ተጨማሪ ኮርሶች ትምህርትህን ማጠናቀቅ እንድትችል ያን ያህል አስተዋጽኦ እንደማያበረክቱ ታስተውል ይሆናል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ምናባዊ የመከላከያ ግንብ
“ለባለጠጋ ሰው ሀብቱ እንደ ጸናች ከተማ ናት፣ በአሳቡም እንደ ረጅም ቅጥር።” (ምሳሌ 18:11 የ1954 ትርጉም) በጥንት ዘመን ሰዎች ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ረጃጅም ቅጥሮች ወይም ግንቦች ይሠሩ ነበር። እስቲ ዙሪያውን በግንብ በታጠረ ከተማ ውስጥ እንደምትኖር አድርገህ አስብ፤ ይሁንና ግንቡ ምናባዊ ነው። ግንቡ አለ ብለህ ራስህን ለማሳመን የፈለግከውን ያህል ጥረት ብታደርግም ያ ግንብ በምንም ዓይነት መንገድ ከጠላቶችህ ሊያስጥልህ አይችልም።
ለጥቃት በተጋለጠ ቦታ እንደሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ሀብት የሚያሳድዱ ወጣቶችም መጨረሻቸው ሐዘን ነው። ወላጅ ከሆንክ ልጅህ በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ እንዳይያዝና ምናባዊ ግንብ ባለው ከተማ ውስጥ መኖር እንዳይጀምር አስፈላጊውን እርዳታ መስጠትህ ተገቢ ነው።
በዚህ ረገድ ልጅህን ማሳመን እንድትችል ቀጥሎ የቀረቡት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ እውነቶች ይረዱሃል፦
▪ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ሀብት፣ ከሚያስገኛቸው መፍትሔዎች ይልቅ የሚያስከትላቸው ችግሮች ይበዛሉ። “የሀብታም ሰው ብልጽግና . . . እንቅልፍ ይነሣዋል።”—መክብብ 5:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10
▪ አንድ ሰው በጥሩ እቅድ የሚኖር ከሆነ ደስተኛ ለመሆን የግድ ሀብታም መሆን አያስፈልገውም። “የትጉህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል።”—ምሳሌ 21:5፤ ሉቃስ 14:28
▪ አንድ ሰው ፍላጎቶቹን ሊያሟላለት የሚችል መጠነኛ ገቢ ካለው ረክቶ መኖር ይችላል። “ድኽነትንም ሆነ ብልጽግናን አትስጠኝ።”—ምሳሌ 30:8 *
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.43 ፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ሊሆን የሚችልበትን መንገድ በተመለከተ በግንቦት 2003 ንቁ! ገጽ 14-15 ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት ይቻላል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከአቅም በላይ ለመሥራት መሞከር ለጥሩ ውጤት አያበቃም
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሚሰጥህን የቤት ሥራ እንደ ሸክም ሳይሆን ለሥራው ዓለም የሚጠቅም ሥልጠና እንደምታገኝበት አድርገህ ተመልከተው