በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሃርፒ ንስር—ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ የሚኖር አዳኝ ወፍ

ሃርፒ ንስር—ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ የሚኖር አዳኝ ወፍ

ሃርፒ ንስር—ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ የሚኖር አዳኝ ወፍ

ኢኳዶር የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

ይህን ግዙፍ ወፍ የተመለከቱ የደቡብ አሜሪካ የቀድሞ አሳሾች በጣም ሳይደነቁ አልቀሩም። በዚህም የተነሳ በግሪካውያን አፈ ታሪክ ውስጥ በምትጠቀሰው ግማሽ ወፍ ግማሽ ሰው እንደሆነች በሚነገርላት ሃሪፒ በምትባል አስፈሪ ፍጥረት ስም ሰየሙት።

ዛሬም ቢሆን ሰዎች የሃርፒ ንስርን ግዙፍነት ሲመለከቱ ይገረማሉ። ቁመቱ 91 ሴንቲ ሜትር ሲሆን ክንፉ ሲዘረጋ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሁለት ሜትር ርዝመት አለው። በማዕከላዊና በደቡባዊ አሜሪካ በሚገኙ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ውስጥ የሚኖረው ይህ ወፍ፣ በዓለም ውስጥ ካሉት ትልቅና ኃይለኛ የሚባሉ ንስሮች መካከል አንዱ ነው። በግዙፍነት እንስቷ ንስር የምትበልጥ ሲሆን እስከ 9 ኪሎ ግራም የሚመዝን ክብደት ሊኖራት ይችላል።

ከሰውነቱ መጠን አንጻር ሲታይ ሃርፒ ንስር ትላልቅና ጠንካራ ጥፍሮች አሉት፤ ጥፍሮቹ 13 ሴንቲ ሜትር እስኪደርሱ ድረስ የሚያድጉ ሲሆን ይህ ደግሞ ከቦልድ ንስር ጥፍሮች በሁለት እጥፍ ይበልጣል። በተጨማሪም ናሽናል ጂኦግራፊክ ቱዴይ እንደገለጸው የሃርፒ ንስር ጥፍሮች በጣም ጠንካራ ከመሆናቸው የተነሳ ንስሩ “ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ ካሉት ዛፎች ላይ ነጥቆ የሚወስዳቸውን እንደ ስሎዝና ጦጣ ያሉ እንሳሳት አጥንት [የሚሰብር] ሲሆን በአብዛኛው እንስሶቹ ወዲያውኑ ይሞታሉ።” ሃርፒ ንስር በጣም ግዙፍ እንዲሁም የማይደፈር መሣሪያ የታጠቀ ቢሆንም ሲበር አንዳች ድምፅ ስለማያሰማ በአንድ ሰው አናት ላይ ቢያልፍ እንኳ ማለፉ ላይታወቅ ይችላል።

ሊጠፋ የተቃረበ ወፍ

ሰዎች ሃርፒ ንስርን የሚፈሩበት ምንም ምክንያት ባይኖራቸውም ንስሩ ግን ሰውን የሚፈራበት ምክንያት አለው። ሕገወጥ አደንና መኖሪያው የሆነው ደን መመናመን ይህ ወፍ ሊጠፉ ከተቃረቡ እንስሳት ተርታ ውስጥ እንዲመደብ አድርገውታል፤ አሁን ይህንን ወፍ ጫካ ውስጥ እንደ ልብ ማየት አይቻልም። ሃርፒ ንስርን ከመጥፋት ለመታደግ ፓናማ ይህ ወፍ ብሔራዊ አርማ እንዲሆን የወሰነች ሲሆን በሕገወጥ አዳኞች ላይ ከባድ ቅጣት ማስፈጸም ጀምራለች።

ሃርፒ ንስርን ከመጥፋት ለመታደግ ኢኳዶርም የበኩሏን ጥረት እያደረገች ነው። የጓያክዊል ታሪካዊ ፓርክ የእንስሳት ሐኪም የሆኑት ዶክተር ያራ ፔሳንቴስ ከንቁ! መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ሃርፒ ንስሮች አራት ወይም አምስት ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ለመራባት አይችሉም። ለመራባት በሚችሉበት ጊዜም እንኳ እንቁላል የሚጥሉት በሁለት ዓመት አንዴ ሲሆን በአንድ ጊዜ የሚጥሉት እንቁላል ከአንድ ወይም ከሁለት አይበልጥም። በፍጥነት የሚራቡ አለመሆናቸው እነዚህን ወፎች ከመጥፋት ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ ያደርገዋል። ሆኖም በፓርኩ ውስጥ አንዲት ጤናማ ጫጩት ማስፈልፈል እንደተቻለ ዶክተር ያራ ፔሳንቴስ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ሰዎች እንስሳትን ከመጥፋት ስለመታደግ መጨነቅ የማያስፈልጋቸው ጊዜ ሩቅ አይደለም። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ በቅርቡ ምድርን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር ከመሆኑም በላይ ፕላኔታችንንም ሆነ በውስጧ ያሉትን አስደናቂ ፍጥረታት ለከንቱ እንዳልፈጠራቸው በማያሻማ መንገድ ያሳያል።—መዝሙር 104:5፤ ኢሳይያስ 45:18

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ንስር ላይ መለያ ምልክት ለማሠር ማዘጋጀት

[ምንጭ]

Pete Oxford/Minden Pictures

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Tui De Roy/Roving Tortoise Photos