በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሌላ ሰው የታዘዘ መድኃኒት በድብቅ መውሰድ

ለሌላ ሰው የታዘዘ መድኃኒት በድብቅ መውሰድ

ለሌላ ሰው የታዘዘ መድኃኒት በድብቅ መውሰድ

ሊና የምትባል አንዲት ሴት “በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኙ መድኃኒቶችን መውሰድ የጀመርኩት ገና የ14 ዓመት ልጅ እያለሁ ነው” በማለት ተናግራለች። * አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ቀጭንና ማራኪ መሆን አለብኝ ብዬ አስብ ስለነበር የቤተሰባችን ሐኪም ለመክሳት የሚረዱ መድኃኒቶችን አዘዘልኝ። ስለራሴ ጥሩ ስሜት የሚኖረኝ ወንዶች እንዳደነቁኝ ሲሰማኝ ብቻ ነበር። ውሎ አድሮ ሱስ የሚያስይዙ አደገኛ መድኃኒቶችን መውሰድ የጀመርኩ ሲሆን አኗኗሬም በተመሳሳይ ሥነ ምግባር የጎደለው ሆነ። ሁልጊዜ ከፍተኛው የምርቃና ደረጃ ላይ ለመድረስ እጣጣር ነበር።”

ሚራ የተባለች አንዲት ሴት በኃይለኛ የራስ ምታት ትሠቃይ ስለነበር ሐኪሟ የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት አዘዘላት። ከጊዜ በኋላ ሚራ ለራስ ምታቷ ብቻ ሳይሆን ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣውን ሱሷን ለማርካት ስትል ተጨማሪ መድኃኒቶችን መውሰድ ጀመረች። ከዚህም በላይ ለሌሎች የቤተሰቧ አባላት የታዘዙ መድኃኒቶችን ትወስድ ጀመር።

አዎ፣ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ወጣቶችና ጥቂት የማይባሉ ትልልቅ ሰዎች ስሜታቸውን ለማረጋጋት፣ የሚሰማቸውን ጭንቀት ለማስታገስ፣ ንቁ ለመሆን፣ ውፍረት ለመቀነስ ወይም ለመመርቀን ሲሉ በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኙ መድኃኒቶችን አላግባብ እየወሰዱ ነው። ብዙውን ጊዜ አላግባብ የሚወሰዱት፣ በብዙዎች ቤት የማይጠፉ መድኃኒቶች ናቸው፤ ከእነዚህ መካከል የሕመም ማስታገሻዎች፣ የእንቅልፍ ኪኒኖች፣ የሚያነቃቁ እንክብሎችና የመሳሰሉት ይገኙበታል። * ከዚህም ሌላ የሐኪም ትእዛዝ የማያስፈልጋቸው፣ ለእንቅልፍ የሚረዱ እንዲሁም ለሳልና ለአለርጂ የሚወሰዱ መድኃኒቶችንም ይጨምራል።

ችግሩ መጠነ ሰፊ ከመሆኑም በላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በደቡብ እስያ በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኙ መድኃኒቶችን አላግባብ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ሕገ ወጥ መድኃኒቶችን ከሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር እየበለጠ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ያለ ሐኪም ትእዛዝ የማይገኙ መድኃኒቶችን አላግባብ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ካናቢስን ሳይጨምር ሁሉንም ሕገወጥ ዕፆችና መድኃኒቶች ከሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ይበልጣል ለማለት ይቻላል። አንድ ጋዜጣ በቅርቡ ባወጣው ዘገባ መሠረት ከ12 እስከ 17 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል “በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኙ መድኃኒቶችን አላግባብ የሚጠቀሙ ወጣቶች ቁጥር ኮኬይን፣ ሄሮይንና ሜታምፋትሚንስ የሚባሉትን አደንዛዥ ዕፆች ከሚወስዱ ወጣቶች አጠቃላይ ቁጥር ይበልጣል።” በእርግጥም በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኙና አላግባብ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ተፈላጊነት በጣም ከፍተኛ መሆኑ መድኃኒቶችን አስመስለው የሚሠሩ ድርጅቶች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

ታዲያ አላግባብ የሚወሰዱ መድኃኒቶችም ሆኑ ሕገወጥ መድኃኒቶች ከሚያስከትሉት አደጋ ራስህንም ሆነ ልጆችህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉት ርዕሰ ትምህርቶች በዚህ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 በዚህ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተለውጠዋል።

^ አን.4 በእነዚህ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርቶች ውስጥ የተጠቀሱት አብዛኞቹ መሠረታዊ መመሪያዎች ሕገወጥ መድኃኒቶችን ከመውሰድና የአልኮል መጠጦችን አላግባብ ከመጠጣት ጋር በተያያዘም ይሠራሉ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“አንድ ሰው ከፍተኛ የመድኃኒት አምሮት ካደረበት፣ ሳይታመም መድኃኒት የሚወስድ ከሆነ እንዲሁም ጉዳት ያስከተለበት ወይም የሚያስከትልበት ቢሆንም እንኳ መውሰዱን ከቀጠለ የመድኃኒት ሱሰኛ ሆኗል ማለት ነው” ሲል ፊዚሺያንስ ዴስክ ሪፈረንስ የተሰኘ አንድ መጽሐፍ ገልጿል። ራስን መግዛት አለመቻልና ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት አእምሮት የሱሰኝነት ዓይነተኛ መገለጫ ናቸው።

አንዳንድ ሕመምተኞች እንደ ኦፖይድ ያሉ ኦፒየም ያለባቸውና በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኙ መድኃኒቶችን ሲያቆሙ የሕመም ምልክቶች ይታዩባቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ የተለመደ ሁኔታ በመሆኑ እንደ ሱስ ተደርጎ መታየት የለበትም።

አንድ ሰው የሚወስደውን የመድኃኒት መጠን ጨምሮም እንኳ ሥቃዩ የማይታገስለት መሆኑ ሰውነቱ መድኃኒቱን እንደተላመደ ያሳያል።