መድኃኒቶችን በአግባብ መውሰድና አላግባብ መጠቀም
መድኃኒቶችን በአግባብ መውሰድና አላግባብ መጠቀም
አንጂ የምትባል አንዲት ልጅ ወላጆቿ ታናሽ ወንድሟ የሚወስደው መድኃኒት የምግብ ፍላጎቱን እንደቀነሰው ሲያወሩ ሰማች። አንጂ የክብደቷ ነገር በጣም ያሳስባት ስለነበር የወንድሟን መድኃኒት እያሰለሰች በድብቅ መውሰድ ጀመረች። ወላጆቿ እንዳያውቁባት ለማድረግ ስትል ተመሳሳይ መድኃኒት የሚወስድ አንድ ጓደኛዋ ጥቂት ኪኒኖች እንዲሰጣት ጠየቀችው። *
ብዙዎች በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኙ መድኃኒቶችን አላግባብ የሚጠቀሙት ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት በቀላሉ የሚገኝ መሆኑ ሲሆን ማንኛውም ሰው እንዲህ ያሉ መድኃኒቶችን ቤቱ ውስጥ እንደልብ ሊያገኝ ይችላል። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ብዙ ወጣቶች ሐኪም ሳያዝላቸው መድኃኒት መውሰዳቸው ሕገወጥ እንዳልሆነ የሚሰማቸው መሆኑ ነው። ሦስተኛው ምክንያት በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኙ መድኃኒቶች የአደገኛ ዕፆችን ያህል መርዛማ አይደሉም ብለው ስለሚያስቡ ነው። አንዳንድ ወጣቶች ‘ይህ መድኃኒት ለአንድ ትንሽ ልጅ ከታዘዘ ምንም ጉዳት አያስከትልም ማለት ነው’ ብለው ያስባሉ።
በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚገኝ መድኃኒት በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ጤንነትን ሊያሻሽል፣ ደስታን ሊጨምር አልፎ ተርፎም ከሞት ሊያድን እንደሚችል የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ አላግባብ ከተወሰደ የአደገኛ መድኃኒቶችን ያህል ጎጂ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው የማነቃቃት ባሕርይ ያለው መድኃኒት አላግባብ መውሰዱ የልብ ድካም ወይም የሰውነት መንዘፍዘፍ (seizures) ሊያስከትልበት ይችላል። ሌሎች መድኃኒቶችም የአንድን ሰው አተነፋፈስ ሊያዛቡ ወይም ውሎ አድሮ ደግሞ ሞት ሊያስከትሉ ይችላሉ። በተጨማሪም አንድ መድኃኒት ከሌሎች መድኃኒቶች ወይም ከአልኮል መጠጥ ጋር ከተወሰደ ጎጂ ውጤት ሊኖረው ይችላል። በ2008 መጀመሪያ ላይ አንድ ታዋቂ ተዋናይ “የማረጋጋት ባሕርይ ያላቸው ስድስት ኪኒኖችን፣ የእንቅልፍ እንክብሎችንና የሥቃይ ማስታገሻ መድኃኒቶችን አንድ ላይ በመውሰዱ ምክንያት” እንደሞተ አሪዞና ሪፑብሊክ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
መድኃኒቶችን አላግባብ መውሰድ የሚያስከትለው ሌላው አደጋ ደግሞ ሱሰኛ የሚያደርግ መሆኑ ነው። አንዳንድ መድኃኒቶች ከመጠን በላይ ወይም ለተሳሳተ ዓላማ ሲወሰዱ እንደ ሕገ
ወጥ መድኃኒቶች ሁሉ በአንጎል ውስጥ የደስታ ስሜት የሚፈጠርበትን ቦታ ያነቃቃሉ፤ ይህ ደግሞ በጊዜ ሂደት ግለሰቡ ለመድኃኒቱ ከፍተኛ አምሮት እንዲያድርበት ሊያደርገው ይችላል። ይሁን እንጂ መድኃኒቶችን አላግባብ መውሰድ ቀጣይነት ያለው የደስታ ስሜት ከማስገኘት ወይም ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንዲቋቋሙ ከመርዳት ይልቅ ችግሮችን ያባብሳል። ውጥረት ሊጨምር፣ የመንፈስ ጭንቀት ሥር እንዲሰድ ሊያደርግ፣ ጤንነትን ሊያቃውስ፣ የመድኃኒት ጥገኛ ሊያደርግ፣ ሱስ ሊያስይዝ ወይም በአንድ ሰው ላይ እነዚህን ነገሮች በሙሉ ሊያስከትል ይችላል። መድኃኒት አላግባብ የሚጠቀሙ ሰዎች በቤት ውስጥ፣ በትምህርት ቤት፣ ወይም በሥራ ቦታ ለችግር መዳረጋቸው አይቀሬ ነው። ታዲያ አንድ ሰው መድኃኒቶችን በአግባቡ እየወሰደ ወይም አላግባብ እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ለይተን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?በአግባቡና መውሰድ ሲባል ምን ማለት ነው? አላግባብ መውሰድስ?
በአጭር አነጋገር፣ መድኃኒትን በአግባቡ እየወሰድክ ነው የሚባለው የሕክምና ምርመራ መረጃዎችህን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሐኪም በሰጠህ መመሪያ መሠረት ስትወስድ ነው። ይህም መድኃኒቱን በትክክለኛው መጠን፣ በሰዓቱ፣ በተገቢው መንገድና ለሚፈለገው ዓላማ መውሰድን ይጨምራል። እንደዚያም ሆኖ የማይፈለጉ ወይም ያልተጠበቁ ምልክቶች ይታዩ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመህ ወዲያውኑ ሐኪምህን አማክር። ሐኪምህ ሌላ መድኃኒት ሊያዝልህ ይችላል። ይህ መመሪያ የሐኪም ትእዛዝ ለማያስፈልጋቸው መድኃኒቶችም ይሠራል። እነዚህ መድኃኒቶች የግድ የሚያስፈልጉህ ከሆነ ብቻ ውሰድ፤ እንዲሁም በላያቸው ላይ የሰፈረውን መመሪያ በጥብቅ ተከተል።
ሰዎች ራሳቸውን ለአደጋ የሚያጋልጡት መድኃኒቶችን ለተሳሳተ ዓላማ ሲጠቀሙ፣ መጠኑን እንደፈለጋቸው ሲያዛቡ፣ ለሌላ ሰው የታዘዘ መድኃኒት ሲወስዱ ወይም መድኃኒቱን በተሳሳተ መንገድ ሲውጡ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ኪኒኖች የያዙት ንጥረ ነገር ከሰውነት ጋር ቀስ በቀስ መዋሃድ ስላለበት እንዳለ እንዲዋጡ መመሪያ ይሰጣል። ይሁን እንጂ መድኃኒቶችን አላግባብ የሚወስዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ እነዚህን መድኃኒቶች
አድቅቀው ወይም አኝከው ይውጣሉ። አሊያም ፈጭተው በአፍንጫቸው ይስባሉ፤ ወይም ደግሞ በውኃ አሟምተው መድኃኒቱን በመርፌ ይወስዱታል። እንዲህ ያለው አወሳሰድ መድኃኒቶቹ የሚሠሩበትን ሂደት ያፋልሳል። እንዲህ ማድረጉ የመድኃኒቱን ኃይል ይጨምር ይሆናል፤ ሆኖም ይህ ወደ ሱሰኝነት የሚያደርስ የመጀመሪያው እርምጃ ሊሆን ይችላል። የከፋው ነገር ደግሞ ለሞት ሊዳርግ የሚችል መሆኑ ነው።በሌላ በኩል ግን በሐኪም የታዘዘለትን መድኃኒት በተገቢው መንገድ እየወሰደ ያለ ሰው ሱስ እየያዘው መሆኑን ይገነዘብ ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ሳይውል ሳያድር ሁኔታውን ለሐኪሙ ማሳወቅ ይኖርበታል። ሐኪሙም መድኃኒቱን ያዘዘበትን የመጀመሪያውን የጤና እክል ሳይዘነጋ በመድኃኒቱ ሳቢያ የተከሰተውን ችግር ማስተካከል የሚችልበትን መንገድ መፈለግ ይኖርበታል።
እንደ ወረርሽኝ እየተዛመተ ያለው መድኃኒቶችን አላግባብ የመጠቀም ችግር በምን ዓይነት ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር የሚጠቁም ነው። ፍቅር ሊሰፍንበትና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከሚያስከትለው ውጥረት እፎይታ ሊገኝበት ይገባ የነበረው ቤተሰብ ችግር ላይ ወድቋል። ጤናማ የሆኑ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ እሴቶች እንደተዳከሙ ሁሉ ለሕይወት ሊኖር የሚገባው አክብሮትም ጠፍቷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ሌላው ምክንያት ደግሞ ብዙ ሰዎች ስለወደፊቱ ጊዜ ብሩሕ ተስፋ የማይታያቸው መሆኑ ነው። ብዙዎች ስለወደፊቱ ጊዜ ሲያስቡ የሚታያቸው ጨለማ ብቻ ነው። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች የሚኖሩት ለዛሬ ብቻ ነው፤ እንዲሁም ስለሚያስከትልባቸው ጉዳት ሳይጨነቁ ደስታ ያስገኛል ብለው የሚያስቡትን ነገር በሙሉ ያሳድዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ራእይ በሌለበት ሕዝብ መረን ይሆናል” በማለት ይናገራል።—ምሳሌ 29:18
ወላጅ ከሆንክ በዓለም ላይ እየተዛመተ ካለው ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ውድቀት ቤተሰብህን ለመጠበቅ እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። ታዲያ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ትክክለኛ መመሪያ እንዲሁም ስለመጪው ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው? የሚቀጥሉት ርዕሰ ትምህርቶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችን ጤንነት አስመልክቶ ከተዘጋጀ ድረ ገጽ ላይ የተወሰደ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሰዎች ለመመርቀን የማይወስዱት ነገር የለም
አንዳንድ ሰዎች ለመመርቀን ሲሉ የማይወስዱት ነገር የለም ማለት ይቻላል። በተለይ ጎጂ ከሆኑት ድርጊቶች መካከል ለጽዳት የሚያገለግሉ ፈሳሾችን፣ የጥፍር ቀለሞችን፣ ቫርኒሾችን፣ ቤንዚንን፣ ኮላን፣ የላይተር ጋዝን፣ የሚነፉ ቀለሞችንና ሌሎች በቀላሉ የሚተኑ ነገሮችን ማሽተት ይገኙበታል። አንድ ሰው እነዚህን ነገሮች በአፍንጫው ሲስብ ያሸተተው ነገር በፍጥነት ወደ ደም ሥሩ ስለሚገባ ወዲያውኑ የተለየ ስሜት ይሰማዋል።
ሌላው ጎጂ ድርጊት ደግሞ የአልኮል ይዘት ያላቸውን ወይም እንቅልፍ የሚያስወስዱ የሐኪም ትእዛዝ የማያስፈልጋቸው መድኃኒቶችን አላግባብ መጠቀም ነው። እንዲህ ያሉ መድኃኒቶች በከፍተኛ መጠን ከተወሰዱ የስሜት ሕዋሳትን በተለይ ደግሞ የመስማትና የማየት ችሎታን ስለሚያዛቡ ግራ መጋባት፣ የቁም ቅዠት፣ መደንዘዝና የሆድ ሕመም ሊያስከትሉ ይችላሉ።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“መድኃኒት ማግኛ ዘዴዎች”
“ሱሰኞችና መድኃኒት አላግባብ የሚጠቀሙ ሰዎች ‘መድኃኒት ማግኛ ዘዴዎችን መፈላለጋቸው’ በጣም የተለመደ ነገር ነው” በማለት ፊዚሺያንስ ዴስክ ሪፈረንስ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። “መድኃኒት ለማግኘት ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል በድንገተኛ ሕክምና ስም ወይም የሥራ መውጫ ሰዓት ላይ ሐኪም ቤት መሄድ፣ ተገቢ ምርመራ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ ወይም ሪፈራል ሲጻፍላቸው ፈቃደኛ አለመሆን፣ መድኃኒት የታዘዘበትን ወረቀት በተደጋጋሚ ጊዜ ‘መጣል’፣ መድኃኒት የታዘዘበትን ወረቀት ለማስተካከል መሞከርና ከዚያ በፊት የነበራቸውን የሕክምና መረጃ ለማቅረብ ወይም ቀደም ሲል የመረመራቸውን ሐኪም አድራሻ ለመስጠት ማመንታት ይገኙበታል። ተጨማሪ የመድኃኒት ማዘዣ ወረቀቶችን ለማግኘት ወደተለያዩ ሐኪሞች መሄድ መድኃኒት አላግባብ በሚጠቀሙና ሱሰኛ በሆኑ ሰዎች ዘንድ የተለመደ ነገር ነው።”
ብዙውን ጊዜ አላግባብ ጥቅም ላይ ከሚውሉ የመድኃኒት ዓይነቶች መካከል ሦስቱ የሚከተሉት ናቸው፦
▪ አፒዮይድስ—ሕመም ለማስታገስ የሚታዘዙ መድኃኒቶች
▪ ማዕከላዊውን የነርቭ ሥርዓት የሚያረጋጉ መድኃኒቶች—ለጭንቀት ወይም ለእንቅልፍ ችግር የሚታዘዙ ባርቢቹሬትስ እና ቤንዞዳያዜፒንስ የሚባሉ የመድኃኒት ዓይነቶች (ብዙውን ጊዜ ሴዴቲቭ ወይም ትራንኩላይዘር በመባል ይታወቃሉ)
▪ የሚያነቃቁ መድኃኒቶች—ሐሳባቸውን የመሰብሰብና የመረጋጋት ችግር ላለባቸው፣ በቁም እያሉ ድንገት ከባድ እንቅልፍ ለሚይዛቸው ወይም ከመጠን በላይ ለወፈሩ ሰዎች የሚታዘዙ *
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.24 የአሜሪካ ብሔራዊ የአደገኛ መድኃኒቶች መቆጣጠሪያ ተቋም ካወጣው መረጃ ላይ የተወሰደ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚወሰዱ መድኃኒቶችን ጉዳት በማያስከትል መንገድ ለመጠቀም የሚረዳ መመሪያ
1. የአወሳሰድ መመሪያዎቹን በጥንቃቄ ተከተል።
2. ሐኪምህን ሳታማክር የምትወስደውን መጠን አትጨምር ወይም አትቀንስ።
3. የታዘዘልህን መድኃኒት በራስህ ፈቃድ አታቋርጥ።
4. በባለሞያ ካልተነገረህ በስተቀር ክኒኖቹን ፈጭተህ ወይም ሰብረህ አትውሰድ።
5. መድኃኒቱ መኪና ስታሽከረክር ወይም ሌላ እንቅስቃሴ ስታደርግ የሚያስከትለውን ውጤት ለማወቅ ጥረት አድርግ።
6. መድኃኒቱ ከአልኮል መጠጥ ወይም በሐኪምም ሆነ ያለ ሐኪም ትእዛዝ ከሚወሰዱ ሌሎች መድኃኒቶች ጋር ሲወሰድ የሚያስከትለውን ነገር ጠይቀህ ተረዳ።
7. ከዚያ በፊት መድኃኒቶችን ወይም ሌሎች ነገሮችን አላግባብ ትወስድ ከነበረ ለሐኪምህ ንገረው።
8. ለሌላ ሰው የታዘዘ መድኃኒት አትውሰድ፤ የራስህንም ቢሆን ለሌሎች አትስጥ። *
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.36 የዩናይትድ ስቴትስ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር በሰጠው ምክር ላይ የተመሠረተ።