መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው ዘገባ ጋር የሚስማማ ደረሰኝ
መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው ዘገባ ጋር የሚስማማ ደረሰኝ
▪ በ1870ዎቹ ዓመታት በዘመናዊቷ ባግዳድ፣ ኢራቅ አቅራቢያ 5.5 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ከሸክላ የተሠራ ጽላት በቁፋሮ ተገኝቶ ነበር። በቪየና፣ ኦስትሪያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚካኤል ዩርሳ በ2007 በብሪቲሽ ሙዝየም ውስጥ ምርምር ሲያደርጉ ይህንን ጽላት ተመለከቱት። ፕሮፌሰር ዩርሳ፣ በጽላቱ ላይ ናቦሠርሰኪም (በባቢሎናዊ አጠራሩ ናቡሻሩሱኪን) የሚል ስም ያገኙ ሲሆን ይህ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በኤርምያስ 39:3 ላይ ከተጠቀሰው የባቢሎን ባለሥልጣን መጠሪያ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን አስተዋሉ። *
ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. በጠፋችበት ወቅት ናቦሠርሰኪም ከንጉሥ ናቡከደነፆር አዛዦች አንዱ የነበረ ሲሆን በጽላቱ ላይ በሠፈረው ሐሳብ መሠረት “ዋና ጃንደረባ” ተብሎ ይጠራ ነበር። ዋና ጃንደረባ የሚለው የማዕረግ ስም በአንድ የተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚሰጠው ለአንድ ሰው ብቻ ነው፤ ይህም በጽላቱ ላይ የተጠቀሰው ሠርሰኪምና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ሠርሰኪም አንድ ሰው መሆናቸውን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።
ናቦሠርሰኪም የባቢሎናውያን ዋነኛ አምላክ ወደሆነው ወደ ማርዱክ ወይም ሜሮዳክ ቤተ መቅደስ ወርቅ እንደወሰደ ጽላቱ ይገልጻል፤ የሜሮዳክም ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። (ኤርምያስ 50:2) ደረሰኙ የተዘጋጀው በናቡከደነፆር የግዛት ዘመን በ10ኛው ዓመት፣ በ11ኛው ወር፣ ከወሩ በ18ኛው ቀን ነው። እርግጥ ነው፣ ናቦሠርሰኪም ወደ ቤተ መቅደሱ የወሰደው ወርቅ ከዓመታት በኋላ ኢየሩሳሌም ከመበዝበዟ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። (2 ነገ. 25:8-10, 13-15) ያም ቢሆን ፕሮፌሰር ዩርሳ እንደተናገሩት “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ሰው በባቢሎን ወደሚገኝ ቤተ መቅደስ ወርቅ የወሰደበትን ቀን በትክክል የሚጠቅስ እንዲህ ያለ ጽላት መገኘቱ በጣም አስገራሚ ነው።” ቴሌግራፍ የተባለው የብሪታንያ ጋዜጣ እንደዘገበው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በተያያዘ በሚደረገው ዘመናዊ የአርኪኦሎጂ ምርምር ውስጥ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ግኝቶች አንዱ እንደሆነ የተገለጸው ይህ ጽላት “በብሉይ ኪዳን ውስጥ የሚገኙት ታሪካዊ መጻሕፍት በእውነታ ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ የሚገልጸውን አመለካከት ይደግፋል።”
ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት በአርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች ላይ የተመካ አይደለም። ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ በተለይም በውስጡ የያዛቸው ትንቢቶች ከዚህ የበለጠ ጠንካራ ማስረጃዎች ናቸው። (2 ጴጥሮስ 1:21) ለአብነት ያህል፣ ይሖዋ አምላክ የኢየሩሳሌም ሀብት በሙሉ “ወደ ባቢሎን ተማርኮ [እንደሚወሰድ]” በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል ከ100 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት አስነግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 39:6, 7) በተመሳሳይም በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት አምላክ የሚከተለውን ትንቢት አስነግሮ ነበር፦ “የዚህችን ከተማ [የኢየሩሳሌምን] ሀብት ሁሉ . . . ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣለሁ፤ እነርሱም ዘርፈው ወደ ባቢሎን ይዘውት ይሄዳሉ።”—ኤርምያስ 20:4, 5
ኢየሩሳሌምን ከዘረፏት ጠላቶች አንዱ ናቦሠርሰኪም ሲሆን ከላይ የተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሲፈጸም ተመልክቷል። እንዲያውም ናቦሠርሰኪም ይወቀውም አይወቀው በትንቢቱ ፍጻሜ ላይ ተካፋይ ነበር።
[የግርጌ ማስታወሻዎች ]
^ አን.2 የ1954 ትርጉም የዕብራይስጡ የማሶራውያን ቅጂ የተጠቀመበትን ሥርዓተ ነጥብ በመከተል ኤርምያስ 39:3ን “ሳምጋር ናቦ፣ ሠርሰኪም፣ ራፌስ” በማለት አስቀምጦታል። ይሁን እንጂ አናባቢ ሳይጨመርበት የሚጻፈው የዕብራይስጥ ጽሑፍ “ሳምጋር፣ ሬፌስ [ወይም ዋና አዛዡ] ናቦሠርሰኪም” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል፤ ይህ ዓይነቱ አተረጓጎም በጽላቱ ላይ ከሰፈረው ጽሑፍ ጋር ይስማማል።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Copyright The Trustees of the British Museum