ሴቶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?
የወጣቶች ጥያቄ
ሴቶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?
እሷን ለመማረክ ያላደረግኩት ጥረት የለም። ስለ ራሴ ብዙ ነገር ነግሬያታለሁ፤ ስላሉኝ ነገሮች፣ ስለሄድኩባቸው ቦታዎችና ስለማውቃቸው ሰዎች ሁሉ አጫውቻታለሁ። ለጓደኝነት ብጠይቃት ዓይኗን ሳታሽ እሺ እንደምትለኝ እርግጠኛ ነኝ!
ምነው መሬት ተከፍታ በዋጠችኝ! በዘዴ ብነግረውም ሊገባው አልቻለም። ሳላስቀይመው ጭውውታችንን ማቆም የምችለው እንዴት ነው?
ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት በሚያስችልህ ዕድሜ ላይ ነህ እንበል። ከምትማርክህና የአንተ ዓይነት እምነት ካላት ወጣት ጋር ጓደኝነት ብትመሠርት ደስ ይልሃል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ይሁንና ከዚህ በፊት የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ያደረግከው ሙከራ ሁሉ እንዳልተሳካ ይሰማሃል።
አንዲትን ወጣት የበለጠ ለማወቅ ከፈለግክ ልታስብባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? ልታስታውሳቸው የሚገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችስ የትኞቹ ናቸው?
መጀመሪያ ማድረግ የሚኖርብህ ነገር
ከአንዲት ወጣት ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት ጥያቄ ከማቅረብህ በፊት ልታዳብራቸው የሚገቡ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮች አሉ፤ እነዚህን መሠረታዊ ነገሮች ማዳበርህ ከማንኛውም ሰው ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት እንድትችል ይረዳሃል። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ተመልከት።
▪ መልካም ምግባር እንዲኖርህ ጥረት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “[ፍቅር] ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም” በማለት ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 13:5) መልካም ምግባር ያለህ መሆኑ ሌሎችን እንደምታከብርና የክርስቶስ ዓይነት ባሕርይ እያዳበርክ እንደሆነ ያሳያል። ይሁን እንጂ መልካም ምግባር ሌሎችን ለመማረክ ስትል የምትለብሰውና ቤት ስትገባ ግን የምታወልቀው ልብስ አይደለም። ‘ከቤተሰቦቼ ጋር ባለኝ ግንኙነት መልካም ምግባር እንዳለኝ አሳያለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በቤት ውስጥ መልካም ምግባር ከሌለህ ከሌሎች ጋር በምትሆንበት ጊዜ ጥሩ ጠባይ እንዳለህ ለማሳየት ብትሞክር እያስመሰልክ እንደሆነ ያስታውቃል። አስተዋይ የሆነች ወጣት ደግሞ እውነተኛ ማንነትህን ለማወቅ ቤተሰቦችህን የምትይዝበትን መንገድ እንደምትመለከት አትዘንጋ።—ኤፌሶን 6:1, 2
ሴቶች ምን ይላሉ? “በር እንደ መክፈት ባሉ ትናንሽ ነገሮች እንዲሁም ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቦቼም ጭምር ደግነትና አሳቢነት እንደማሳየት ባሉ ትላልቅ ነገሮች ምግባረ መልካም መሆኑን የሚያሳይ ወንድ ይማርከኛል።”—የ20 ዓመቷ ቲና“ገና ከመተዋወቃችን ‘የወንድ ጓደኛ አለሽ?’ ወይም ‘ግብሽ ምንድን ነው?’ እንደሚሉት ያሉ የግል ሕይወቴን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን የሚጠይቀኝ ሰው ይደብረኛል። እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ያሸማቅቁኛል።”—የ19 ዓመቷ ካቲ
▪ የግል ንጽሕናህን ጠብቅ። ንጽሕናህን በሚገባ መጠበቅህ ለሌሎች ብቻ ሳይሆን ለራስህም አክብሮት እንዳለህ ያሳያል። (ማቴዎስ 7:12) ለራስህ አክብሮት ካለህ ሌሎችም እንደሚያከብሩህ ጥርጥር የለውም። በአንጻሩ ግን ለንጽሕናህ ትኩረት የማትሰጥ ከሆነ አንዲትን ወጣት ለመማረክ የምታደርገው ጥረት መና ይቀራል።
ሴቶች ምን ይላሉ? “ከእኔ ጋር ለመቀራረብ ይፈልግ የነበረ አንድ ወጣት መጥፎ የአፍ ጠረን ነበረው። ይህን ደግሞ በፍጹም ችላ ብዬ ማለፍ አልቻልኩም።”—የ24 ዓመቷ ኬሊ
▪ ከሰዎች ጋር የመወያየት ችሎታ አዳብር። ከሰዎች ጋር በመወያየት ረገድ ጥሩ ችሎታ ማዳበር ዘላቂ የሆነ ዝምድና ለመመሥረት ወሳኝ ነው። ይህም አንተ ስለምትወዳቸው ነገሮች ብቻ ሳይሆን ጓደኛህ ስለሚወዳቸው ነገሮችም ማውራትን ይጨምራል።—ፊልጵስዩስ 2:3, 4
ሴቶች ምን ይላሉ? “ነፃ ሆኖ ማውራት የሚችልና ከዚህ ቀደም የነገርኩትን ነገር የሚያስታውስ እንዲሁም አንዳንድ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ውይይታችን እንዲቀጥል የሚያደርግ ወንድ ይማርከኛል።”—የ20 ዓመቷ ክሪስቲን
“ወንዶችን የሚማርካቸው የሚያዩት ነገር ሲሆን ሴቶችን ግን በበለጠ የሚማርካቸው የሚሰሙት ነገር ይመስለኛል።”—የ22 ዓመቷ ሎራ
“ስጦታ መቀበል ያስደስታል። ሆኖም አንድ ወንድ ጥሩ ውይይት ማድረግ መቻሉና የሚናገረው ነገር የሚያጽናና ብሎም የሚያበረታታ መሆኑ ይበልጥ ይማርከኛል።”—የ21 ዓመቷ ኤሚ
“ቀልድ ከሚያውቅ ሆኖም ለማስመሰል ሳይሞክር ቁም ነገር ያለው ጨዋታም መጫወት ከሚችል ወንድ ጋር ጓደኝነት ብመሠርት በጣም ደስ ይለኛል።”—የ24 ዓመቷ ኬሊ
ከላይ ያሉትን ምክሮች ተግባራዊ ማድረግህ ከሌሎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት እንድትመሠርት ያስችልሃል። ይሁን እንጂ ከአንዲት ወጣት ጋር የፍቅር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ እንደሆንክ ከተሰማህ ምን ማድረግ አለብህ?
የሚቀጥለው እርምጃ
▪ ቅድሚያውን ውሰድ። ከጓደኞችህ መካከል አንዷ ጥሩ የትዳር ጓደኛ ልትሆን እንደምትችል ካሰብክ ይህን ስሜትህን ግለጽላት። ግልጽና ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ሐሳብህን ንገራት። እምቢ እንዳትልህ ስለምትፈራ እንዲህ ማድረጉ ሊያስጨንቅህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም ቅድሚያውን ወስደህ ስሜትህን መግለጽህ በራሱ እንደጎለመስክ የሚያሳይ ማስረጃ ነው።
ሴቶች ምን ይላሉ? “የሰውን ልብ ማንበብ አልችልም። ስለሆነም አንድ ወንድ የበለጠ ሊያውቀኝ ከፈለገ ስሜቱን በግልጽ ሊነግረኝ ይገባል።”—የ23 ዓመቷ ኒና
“ለተወሰነ ጊዜ ጓደኛሞች ሆናችሁ ከቆያችሁ በኋላ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ሲነሳ ግራ ሊያጋባ ይችላል። ይሁንና አንድ ወንድ ከተራ ጓደኝነታችን ባለፈ ከእኔ ጋር በደንብ ለመተዋወቅ እንደሚፈልግ ቢነግረኝ አከብረዋለሁ።”—የ25 ዓመቷ ሄለን
▪ ውሳኔዋን አክብርላት። ጓደኛህ ያቀረብክላትን ጥያቄ ባትቀበለውስ? በውስጧ የሚሰማትን የምታውቀው እሷ እንደሆነችና ‘አልፈልግም’ ያለችው የምሯን እንደሆነ በማመን ውሳኔዋን አክብርላት። ይሁን እንጂ እሺ እንድትልህ ለማድረግ መነዝነዝህን ከቀጠልክ ጉልምስና እንደሚጎድልህ ታሳያለህ። ያቀረብከውን ጥያቄ እንደማትቀበለው በግልጽ ብትነግርህም ካልሰማህ፣ እንዲያውም በሰጠችው ምላሽ የምትበሳጭ ከሆነ በእርግጥ የምታስበው ስለ እሷ ፍላጎትም ጭምር ነው ወይስ ስለ ራስህ ብቻ?—1 ቆሮንቶስ 13:11
ሴቶች ምን ይላሉ? “‘አልፈልግም’ የሚል ቁርጥ ያለ መልስ ከሰጠሁት በኋላ ደጋግሞ የሚጠይቀኝ ወንድ ያበሳጨኛል።”—የ20 ዓመቷ ካሊን
“ከእሱ ጋር ጓደኝነት የመመሥረት ፍላጎት እንደሌለኝ የገለጽኩለት ቢሆንም የስልክ ቁጥሬን እንድሰጠው ይወተውተኝ ነበር። ላስቀይመው አልፈለግኩም። ደግሞም ስሜቱን ለመግለጽ የሚያስችለውን ድፍረት ለማግኘት ተጨንቆ ሊሆን እንደሚችል ይሰማኛል። መጨረሻ ላይ ግን ጠንከር ብዬ ስሜቴን መንገር አስፈልጎኛል።”—የ23 ዓመቷ ሳራ
ማድረግ የሌለብህ ነገር
አንዳንድ ወጣት ወንዶች፣ ሴቶች እንዲወዷቸው ማድረግ እንደማያስቸግራቸው ይሰማቸዋል። እንዲያውም የብዙ ሴቶችን ትኩረት መሳብ የሚችለው ማን እንደሆነ ለማሳየት ከእኩዮቻቸው ጋር ይፎካከሩ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ያለው ድርጊት ደግነት የጎደለው ከመሆኑም ሌላ መጥፎ ስም እንድታተርፍ ያደርግሃል። (ምሳሌ 20:11) የሚከተሉትን ሐሳቦች ተግባራዊ ማድረግህ መጥፎ ስም ከማትረፍ ያድንሃል።
▪ ከማሽኮርመም ተቆጠብ። አንድ ወንድ የሚሸነግሉ ቃላት በመናገርና በሰውነት እንቅስቃሴው ጭምር አንዲትን ሴት ያሽኮረምም ይሆናል። ይህ ሰው እንዲህ የሚያደርገው ከእሷ ጋር ትዳር የመመሥረት ዓላማ እንደሌለው እያወቀ ነው። እንዲህ ያለው አድራጎትና ዝንባሌ “ሴቶችን . . . እንደ እኅቶች በፍጹም ንጽሕና አስተናግዳቸው” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጋር ይጋጫል። (1 ጢሞቴዎስ 5:2) የማሽኮርመም ልማድ ያላቸው ወንዶች ለትዳር ጓደኝነት ይቅርና ጥሩ ጓደኞች ለመሆን እንኳ አይበጁም። አስተዋይ የሆኑ ሴቶች ይህን ማየት አያስቸግራቸውም።
ሴቶች ምን ይላሉ? “አንድ ወንድ ባለፈው ወር ለጓደኛችሁ የተናገረውን ነገር ለእናንተም እየደገመ ሲሸነግላችሁ መስማት በጣም ያስጠላል።”—የ25 ዓመቷ ሄለን
“አንድ የሚያምር ልጅ እኔን ለማሽኮርመም ይሞክር ጀመር፤ በአብዛኛው ያወራ የነበረው ስለ ራሱ ነው። አንዲት ልጅ ከእኛ ጋር ተቀላቅላ ማውራት ስትጀምር ከእሷም ጋር ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ሞከረ። አሁንም ሌላ ወጣት ወደ እኛ ስትመጣ እሷንም ማሽኮርመም ጀመረ። በጣም የሚያስጠላ ነገር ነው!”—የ20 ዓመቷ ቲና
▪ በስሜቷ አትጫወት። ከተቃራኒ ጾታ ጋር የሚኖርህ ጓደኝነት ከአንድ ወንድ ጋር ካለህ ወዳጅነት ምንም እንደማይለይ አድርገህ አታስብ። እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ ይህን አስብ፦ አንድ ጓደኛህ አዲስ የገዛው ሙሉ ልብስ በጣም እንዳማረበት ብትነግረው ወይም ዘወትር ከእሱ ጋር ብታወራና ሚስጥርህን ብታካፍለው በእሱ እንደተማረክህ አድርጎ እንደማያስብ የታወቀ ነው። ሆኖም አንዲትን ሴት አለባበሷን ብታደንቅላት ወይም ደግሞ ሁልጊዜ ከእሷ ጋር ብታወራና ሚስጥርህን ብትነግራት ከእሷ ጋር የፍቅር ጓደኝነት የመመሥረት ፍላጎት እንዳለህ አድርጋ ማሰቧ አይቀርም።
ሴቶች ምን ይላሉ? “ወንዶች፣ የሴት ጓደኞቻቸውን የሚይዙበት መንገድ የወንድ ጓደኞቻቸውን ከሚይዙበት መንገድ የተለየ መሆን እንዳለበት የሚገነዘቡ አይመስለኝም።”—የ26 ዓመቷ ሺረል
“አንድ ወንድ ስልክ ቁጥሬን ይወስድና መልእክት ይልክልኛል። ታዲያ . . . ይህ ምን ማለት ነው? አንዳንድ ጊዜ በስልክ መልእክት በመለዋወጥ ብቻ ጓደኝነት ልትመሠርቱ ሌላው ቀርቶ ፍቅር ሊይዛችሁ ይችላል፤ ሆኖም የስልክ መልእክት በመላላክ ብቻ ምን ያህል ማውራት ይቻላል?”—የ19 ዓመቷ ማለሪ
“አንድ ወንድ በተለይ አሳቢ ከሆነና ከእሱ ጋር ማውራት የማይከብድ ከሆነ አንዲት ሴት በቀላሉ ልትወደው እንደምትችል ወንዶች የሚረዱ አይመስለኝም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምትገባው ለመወደድ ከመጠን ያለፈ ጉጉት ስላላት ላይሆን ይችላል። ብዙ ሴቶች የሚያፈቅሩት ሰው ለማግኘት ይፈልጋሉ፤ በመሆኑም ለእነሱ የሚስማማ ወንድ ለማግኘት ንቁ ሆነው ይመለከታሉ።”—የ25 ዓመቷ አሊሰን
እውነታውን ተቀበል
ሁሉም ሴቶች እንደሚወዱህ አድርገህ ማሰብህ ከእውነታው የራቀ ከመሆኑም ሌላ ራስ ወዳድ መሆንህን የሚያሳይ ነው። ይሁንና ለሚከተለው ሐሳብ ትኩረት ከሰጠህ የሚወዱህ ሴቶች እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም፦ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውጫዊ ማንነትህ ሳይሆን ውስጣዊ ማንነትህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “አዲሱን ስብዕና” የማዳበርን አስፈላጊነት የሚያጎላ መሆኑ ምንም አያስገርምም።—ኤፌሶን 4:24
የ21 ዓመቷ ኬት፣ ሁኔታውን ጠቅለል አድርጋ ስታስቀምጥ እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ወንዶች፣ ሴቶችን ለመማረክ ለየት ያለ አለባበስ ወይም ቁመና ሊኖራቸው እንደሚገባ አድርገው ያስባሉ። ይህ በተወሰነ መጠን እውነት ቢሆንም ብዙ ሴቶችን ይበልጥ የሚማርካቸው አንድ ወንድ ጥሩ ባሕርያት ያሉት መሆኑ ይመስለኛል።” *
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.10 ስሞቹ ተቀይረዋል።
^ አን.38 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 3 ተመልከት።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
▪ ለራስህ አክብሮት እንዳለህ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?
▪ የአንዲትን ወጣት ሐሳብና ስሜት እንደምታከብርላት እንዴት ማሳየት ትችላለህ?
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መልካም ምግባር፣ ሌሎችን ለመማረክ ስትል የምትለብሰውና ቤት ስትገባ ግን የምታወልቀው ልብስ አይደለም