ወላጆች ልጆቻችሁን ከአደጋ ጠብቁ!
ወላጆች ልጆቻችሁን ከአደጋ ጠብቁ!
ሁኔታው የሚያሳስባቸው ወላጆች “ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ወጣቶች መድኃኒት በድብቅ የሚወስዱት ለምንድን ነው?” ብለው መጠየቃቸው ተገቢ ነው። ለዚህ ጥያቄ የተለያዩ መልሶች መስጠት ይቻላል። አንዳንድ ወጣቶች ሁልጊዜ ደስ እንዲላቸው፣ ሌሎቹ ደግሞ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ትምህርታቸውን ማጥናት ወይም ጭንቀታቸውን መርሳት ይፈልጋሉ። አንዳንዶቹም አካላዊ ወይም ስሜታዊ ሥቃይ ሊኖርባቸው ስለሚችል ይህን የማስታገሥ ፍላጎት አላቸው። ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት የሚያንስ ትንንሽ ልጆች እንኳ በሐኪም ትእዛዝ ብቻ የሚወሰዱ መድኃኒቶችን አላግባብ እንደሚጠቀሙ የታወቀ ነው፤ ምናልባትም እንዲህ ዓይነቶቹን መድኃኒቶች አላንዳች ጥያቄ የሚያገኙት በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩት ድረ ገጾች መካከል አንዱን ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑትን ተጠቅመው በማዘዝ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ደግሞ ጓደኞቻችን ከሚሏቸው ሰዎች ላይ ኪኒኖችን ይገዛሉ። ወላጅ ከሆንክ ልጆችህን እንዲህ ካለው አደገኛ ሁኔታ ለመጠበቅ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
ከሁሉ በፊት በሐኪም ትእዛዝም የሚወሰዱትንም ሆነ ሕገወጥ መድኃኒቶችን መጠቀም የሚያስከትለውን አደጋ ከልጆቻችሁ ጋር በግልጽ ተወያዩ። በተጨማሪም ሐኪም ያዘዘላችሁን መድኃኒት ልጆች በማይደርሱበት ቦታ አስቀምጡ፤ ምናልባትም መድኃኒት የምታስቀምጡበትን መሳቢያ መቆለፍ ይኖርባችሁ ይሆናል። በቤታችሁ ውስጥ ምን ዓይነት መድኃኒት እንዳላችሁና ምን ያህል እንደቀራችሁ ክትትል አድርጉ። አንድ
መድኃኒት የማይፈለግ ከሆነ በጥንቃቄ አስወግዱት። በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ልጃችሁ የያዘው ሳል ከለቀቀውም በኋላ መድኃኒቱን መውሰዱን ከቀጠለ ስለ ሁኔታው ጠይቁት። የልጃችሁን የኢንተርኔትና የገንዘብ አጠቃቀም እንዲሁም የሚያደርጋቸውን የደብዳቤ ልውውጦች ነቅታችሁ ተከታተሉ። በመጨረሻም በጓደኛ ምርጫው፣ በአካሉ ወይም በጠባዩ አሊያም በትምህርት ቤት ውጤቱ ላይ የሚታዩትን ድንገተኛ ለውጦች ነቅታችሁ ተከታተሉ።አንድ ልጅ መድኃኒት አላግባብ የመውሰድ ችግር ቢኖርበትስ?
ልጃችሁ ከመድኃኒት ጋር በተያያዘ ችግር ካለበት ወይም አለበት ብላችሁ ከጠረጠራችሁ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? የሚሰማችሁን ስጋት ከልጃችሁ ጋር ፍቅርና ደግነት በሚንፀባረቅበት መንገድ መወያየት ያስፈልጋችኋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል” ይላል። (ምሳሌ 20:5) መድኃኒት አላግባብ የመጠቀም ችግር እንዳለበት የምትጠረጥሩትን ልጅ እውነቱን እንዲያወጣ ማግባባት በቀላሉ ሊበጠስ በሚችል ገመድ ከጉድጓድ ውስጥ በባልዲ ውኃ ከመቅዳት ጋር ይመሳሰላል። የሚኮንኑ ቃላት በመናገር ወይም በመቆጣት ልጃችሁ ሐቁን እንዲናገር የምታውጣጡት ከሆነ የሐሳብ ግንኙነት ገመዳችሁን ልትበጥሱት ትችላላችሁ። ዓላማችሁ ሁለት ነገሮችን ማወቅ መሆኑን አስታውሱ። የመጀመሪያው ልጁ ችግር ያለበት መሆን አለመሆኑን ማወቅ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ችግር ካለበት በዋነኝነት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን መለየት ነው። ብዙውን ጊዜ ምክንያቶቹ ቀጥሎ ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱን ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑትን የሚያካትቱ ናቸው።
▪ መጥፎ ጓደኞችና የእኩዮች ተጽዕኖ። መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 15:33 ላይ “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” ይላል። ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው ከሚችሉ መጥፎ ጓደኞች ጋር መግጠም ያለውን አደጋ እንዲገነዘቡ የሚረዷቸው ከመሆኑም በላይ ጥሩ ጓደኞች እንዲመርጡ ይረዷቸዋል። (ምሳሌ 13:20) ምናልባትም እናንተ ወላጆች ጥሩ ልጆችን በቤታችሁ በመጋበዝ ወይም በቤተሰብ ደረጃ ለሽርሽር ስትወጡ አብረዋችሁ እንዲሄዱ በማድረግ ልጆቻችሁን ልትረዷቸው ትችላላችሁ።
▪ ውጥረት። ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ሰዎች ስኬታማ እንዲሆኑ የሚደረግባቸው ጫና እንዲህ ቀላል አይደለም፤ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸው ተግተው እንዲሠሩ በመጫን ችግሩን ያባብሱታል። * የልጆቻችሁን ጠንካራና ደካማ ጎን ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ? ለልጆቻችሁ ሊደረስበት የሚችል ምክንያታዊ ግብ ታወጡላቸዋላችሁ? እንዲሁም ግቦቻቸው ላይ እንዲደርሱ ትረዷቸዋላችሁ? የአንድ ልጅ መንፈስ እንዲደቆስና የመንፈስ ጭንቀት እንዲይዘው ሊያደርግ ከሚችል ልጁን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ባሕርይ ሙሉ በሙሉ ትርቃላችሁ? አንድ የማይካድ ነገር አለ፤ ልጆች በቤት ውስጥ ስሜታዊ ፍላጎታቸው ካልተሟላላቸው የሚጓጉለትን ፍቅርና እውቅና ከቤት ውጪ ለማግኘት መጣራቸው አይቀርም። በተጨማሪም ጥበበኛ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ በቤታቸው ውስጥ ጥሩ መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲሰፍን ለማድረግ ይጥራሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” ብሏል።—ማቴዎስ 5:3
▪ የሥነ ምግባር አቋም መጥፋት። አንዳንድ ወጣቶች መድኃኒት አላግባብ የሚጠቀሙት ወላጆቻቸው ስድ ስለሚለቋቸው ነው። ምሳሌ 29:15 ‘መረን የተለቀቀ ልጅ እናቱን ያሳፍራል’ ይላል። ልጆች ግልጽ የሆነ የሥነ ምግባር አቋም ሲቀመጥላቸው ለጊዜው ቢነጫነጩም እንኳ ይበልጥ እንዲረጋጉና በወላጆቻቸው እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ስለሚያደርግ መመሪያ ማግኘታቸው ያስደስታቸዋል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ለልጆቻቸው ምክንያታዊ መመሪያዎችን እንዲያወጡና ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ ማበረታቻ ይሰጣል። (ኤፌሶን 6:4) ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ወጥ የሆነ አቋም እንዲኖራቸው እንዲሁም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ጥብቅ እንዲሆኑ ያበረታታል። የአምላክ ቃል “አዎ ካላችሁ አዎ ይሁን፤ አይደለም ካላችሁ አይደለም ይሁን” ይላል።—ያዕቆብ 5:12
እርግጥ ነው፣ ልጃችሁ መድኃኒት አላግባብ የመውሰድ ችግር እንዳለበት ካወቃችሁ በጉዳዩ ላይ ከጤና ባለሞያ ጋር መወያየቱ አስተዋይነት ነው። ከሱስ መላቀቅ ከባድ ከመሆኑም በላይ የባለሞያ ምክር የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ቤተሰባችሁ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ጉባኤ አባል ከሆነ የጉባኤ ሽማግሌዎችን ድጋፍ መጠየቅ ይኖርባችኋል። (ያዕቆብ 5:13-16) እነዚህ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንዶች ልጃችሁ በፍጥነት ከሱስ እንዲላቀቅ የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ እንድታውሉ ሊረዷችሁ ይችላሉ።
የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት አንዳንድ ተጨማሪ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያብራራ እንዲሁም የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ስለተሰጠን አስደናቂ ተስፋ የሚገልጽ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.7 በገጽ 14 ላይ የሚገኘውን “ውጥረት የበዛባቸው ልጆች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል።”—ምሳሌ 20:5
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በመድኃኒት አላግባብ ለመጠቀም አደጋ ሊጋለጡ የሚችሉ ወጣቶች
▪ መድኃኒት ወይም የአልኮል መጠጥ አላግባብ የሚጠቀም የቤተሰብ አባል የነበራቸው
▪ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ወይም ለራሳቸው ዝቅተኛ ግምት የሚሰማቸው
▪ ከሌሎች ጋር ተግባብተው መኖር እንደማይችሉ ወይም በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ እንዳልሆኑ የሚሰማቸው
▪ ዘወትር የድካም ስሜት የሚጫጫናቸው፤ የእንቅልፍ ችግር ያለባቸው
▪ ጠበኞችና፣ ሥልጣን ባላቸው አካላት ላይ የማመፅ ባሕርይ ያላቸው *
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.21 ቲን ሄልፕ ለሕትመት ባበቃው መረጃ ላይ የተመሠረተ።