ለልጆቻችሁ ሕይወት ጥሩ መሠረት ጣሉ
ለልጆቻችሁ ሕይወት ጥሩ መሠረት ጣሉ
ካናዳ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው
▪ “ቴሌቪዥን ግሩም የማስተማሪያ መሣሪያ ሊሆን ይችላል” በማለት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በተሰኘው ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ ይናገራል። ይሁን እንጂ “ለሰዓታት ቴሌቪዥን ፊት ተደቅኖ መቆየት” ልጆች የፈጠራና የመማር ችሎታቸውን እንዳያሳድጉ እንዲሁም ጥሩ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዳይኖራቸው በማድረግ “በአካላዊና በአእምሯዊ ጤንነታቸው ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።”
ጋዜጣው እንደዘገበው በሲያትል፣ ዋሽንግተን በሚገኝ የልጆች ሆስፒታል ውስጥ የሚሠሩ ተመራማሪዎች የ2,500 ልጆችን ቴሌቪዥን የመመልከት ልማድ ካጠኑ በኋላ “ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሕፃናት ቴሌቪዥን ብዙ በተመለከቱ መጠን ሰባት ዓመት ሲሆናቸው ትኩረትን ለመሰብሰብ ችግር የመጋለጣቸው አጋጣሚ ከፍተኛ እንደሚሆን ደርሰውበታል።” እንደነዚህ ያሉት ልጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጡዎችና ትዕግሥት የለሾች እየሆኑ የሚመጡ ከመሆኑም ሌላ ትኩረታቸውን የመሰብሰብ ችሎታቸው እየቀነሰ ይሄዳል። የሥነ ልቦና ምሑር የሆኑት ዶክተር ጄን ሂሊ የተባሉ ሴት እንደተናገሩት “ትኩረት የመሰብሰብ ችግር እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠላቸው ልጆች ያሏቸው ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን ቴሌቪዥን እንዳይመለከቱ ካደረጉ በኋላ ችግሩ ጉልህ መሻሻል እንዳሳየ ተገንዝበዋል።”
ወላጆች ልጆቻቸው ቴሌቪዥን በማየት የሚያጠፉትን ጊዜ ለመቀነስ ምን ማድረግ ይችላሉ? ዘገባው የሚከተሉትን የመፍትሔ ሐሳቦች አቅርቧል፦ ልጃችሁ በየቀኑ መቼና ለምን ያህል ጊዜ ቴሌቪዥን መመልከት እንደሚችል ገደብ አብጁ። ቴሌቪዥንን ለሞግዚትነት አትጠቀሙበት። ከዚህ ይልቅ ልጃችሁ በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ ሥራዎች እንዲጠመድ አድርጉ። ልጃችሁ ሊመለከታቸው የሚችላቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ምረጡ፤ ፕሮግራሙ ካለቀ በኋላ ደግሞ ቴሌቪዥኑን ዝጉት። በተቻለ መጠን የመረጣችሁትን ፕሮግራም ከልጃችሁ ጋር ሆናችሁ እዩና ስላያችሁት ነገር ተነጋገሩ። በመጨረሻም፣ እናንተ ራሳችሁ ቴሌቪዥን በመመልከት ለምታሳልፉት ጊዜ ገደብ አብጁ።
ልጆች የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩና ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸው መርዳት ጊዜ፣ ቆራጥነትና ራስን መገሠጽ ይጠይቃል። እንዲህ ማድረጉ ከሚያስገኘው ጥሩ ውጤት አንጻር ምንም ያህል ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም። “ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም” የሚለው የጥንት ምሳሌ የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት ያረጋግጣል። (ምሳሌ 22:6) ልጆችን ትክክለኛ በሆኑ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ኮትኩቶ ማሳደግ የዚህ ሥልጠና አቢይ ክፍል ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ጥሩ ሥነ ምግባር ለመቅረጽ ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተሰኘውን መጽሐፍ ውጤታማ በሆነ መንገድ ይጠቀሙበታል። በእርግጥም ወላጆች ልጃቸው ገና ሕፃን ሳለ ጀምሮ ከእሱ ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት መመሥረታቸውና ትኩረት መስጠታቸው ለዘለቄታው እንደሚክስ የተረጋገጠ ነው። ለወላጆች ልጃቸው አድጎ የተከበረና ኃላፊነት የሚሰማው ጎልማሳ ሰው ሲሆን ከማየት የበለጠ ምን የሚያረካ ነገር ይኖራል?