በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሠላሳ ዓመታት በድብቅ የትርጉም ሥራ ማከናወን

ለሠላሳ ዓመታት በድብቅ የትርጉም ሥራ ማከናወን

ለሠላሳ ዓመታት በድብቅ የትርጉም ሥራ ማከናወን

ኦና ሞጽኩቴ እንደተናገረችው

ሚያዝያ 1962 ‘በማኅበረሰቡ ላይ ወንጀል ፈጽመሻል’ በሚል ክስ በክላይፔዳ፣ ሊትዌኒያ ፍርድ ቤት ቀረብኩ፤ ፍርድ ቤቱ በሰው ተጨናንቆ ነበር። የታሰርኩት በጥቅምት ወር ሲሆን ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ማከናወኔ በሶቭየት መንግሥት ላይ ወንጀል እንደመፈጸም ተቆጥሮ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፎች በድብቅ በመተርጎሜ ተይዤ ለእስር ልዳረግ የቻልኩት እንዴት እንደሆነ እስቲ ላውጋችሁ።

በ1930 በባልቲክ ባሕር አቅራቢያ በምዕራብ ሊትዌኒያ ተወለድኩ። እናቴ እኔን ከመውለዷ በፊት፣ ልጇ መነኩሲት እንድትሆን እንደምትፈልግ በመግለጽ ወደ አምላክ ጸልያ ነበር። ያም ቢሆን በአንድ ወቅት “በቅዱስ ጴጥሮስም ሆነ በማንኛውም በድን የሆነ ጣዖት ፊት በፍጹም አልጸልይም” አለችኝ። በዚህም ምክንያት ከትምህርት ቤት ወደ ቤቴ ስመለስ ክርስቶስ ተሰቅሎ የሚያሳይ ምስል መንገድ ላይ ካጋጠመኝ የምሳለም ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ግን ተንበርክኬ አልጸልይም ነበር።

ከ1939 እስከ 1945 በተካሄደው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተመለከትኩት ለመግለጽ የሚያዳግት የጭካኔ ድርጊት በጣም ረበሸኝ። ጀርመኖች ሊትዌኒያን ወረዋት በነበረበት ወቅት አንድ ቀን ከአክስቴ ጋር ሆኜ በጫካ ውስጥ ፍራፍሬ እየለቀምኩ ሳለ ሁለት ትላልቅ ጉድጓዶች ተመለከትን፤ በጉድጓዶቹ አካባቢ ትኩስ ደም ተረጫጭቶ ይታይ ነበር። ቴስ እና ሣራ የተባሉትን የትምህርት ቤት ጓደኞቼን ጨምሮ የተወሰኑ አይሁዳውያን በቅርቡ እንደተገደሉ እናውቅ ስለነበር ቦታው በርካታ አይሁዳውያን የተቀበሩበት መሆን አለበት ብለን አሰብን። ባየሁት ነገር በጣም በመደንገጤ “አምላክ ሆይ፣ አንተ በጣም ጥሩ ሆነህ ሳለ እንዲህ ያለ ዘግናኝ ግፍ እንዲፈጸም ለምን ትፈቅዳለህ?” በማለት ምርር ብዬ ተናገርኩ።

በ1949 በክላይፔዳ በቤታችን አቅራቢያ በሚገኘው ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ሙዚቃ መማር ጀመርኩ። በ1950 ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት በድብቅ ከሚንቀሳቀስ የተማሪዎች ቡድን ጋር ተቀላቀልኩ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን እንቅስቃሴያችን ስለታወቀ እኔና ሌሎች 12 የቡድኑ አባላት ተያዝን። በክላይፔዳ በሚገኝ ወኅኒ ቤት የታሰርኩ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘሁት እዚያ እያለሁ ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተማርኩ

በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኝ አንዲት ሴትም ከእኛ ጋር ታሰረች። ይህቺ ሴት በክፍሉ ውስጥ የነበርነውን ሰባት ወጣት ሴቶች በፈገግታ ትመለከተን ነበር። እኔም እንዲህ ስል ጠየቅኳት፦ “ብዙውን ጊዜ ሰዎች እስር ቤት ሲገቡ ያዝናሉ፤ በአንቺ ፊት ላይ ግን ፈገግታ ይነበባል! የእኔ እመቤት፣ የታሰርሽበትን ምክንያት ልትነግሪን ትችያለሽ?”

ሴትየዋ “በእውነት ምክንያት ነው” በማለት መለሰች።

እኔም “እውነት ደግሞ ምንድን ነው?” ብዬ ጠየቅኳት።

ሴትየዋ፣ ሊዲያ ፔልድዡስ ትባላለች። ጀርመናዊ ስትሆን የታሰረችውም የይሖዋ ምሥክር በመሆኗ ነበር። ከሊዲያ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሰፋ ያለ ውይይት አደረግን። ሊዲያ የነገረችን አስደሳች የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት፣ እኔም ሆንኩ አብረውኝ ከታሰሩት ወጣቶች መካከል ሦስቱ ሕይወታችንን እንድንለውጥ አድርጎናል።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ እውቀት እያደገ ሄደ

የሶቭየትን መንግሥት በመቃወም በድብቅ ባከናወንኩት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ምክንያት ከ25 ዓመት እስራት በተጨማሪ ለ5 ዓመት በግዞት እንድኖር ተፈረደብኝ። በተለያዩ እስር ቤቶችና በሳይቤሪያ የጉልበት ሥራ በሚሠራባቸው ካምፖች ውስጥ ያገኘኋቸው የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ ያለኝ እውቀት እንዲያድግ ረዱኝ። እንደ ሊዲያ ሁሉ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮችም የታሰሩት በእምነታቸው ምክንያት ነበር።

በእነዚያ ዓመታት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ እውቀት ከማደጉም ባሻገር እምነቴን ለሌሎች ማካፈል ጀመርኩ። ራሴን ለአምላክ መወሰኔን በጥምቀት የማሳየት አጋጣሚ ባላገኝም ሌሎች እስረኞችም ሆኑ የወኅኒ ቤቱ ባለሥልጣናት የይሖዋ ምሥክር እንደሆንኩ ይሰማቸው ነበር። ለስምንት ዓመታት ከታሰርኩ በኋላ በ1958 ከእስር ተለቀቅኩ። ወደ ሊትዌኒያ ስመለስ ጤንነቴ በጣም የተጎዳ ቢሆንም በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት ተጠናክሮ ነበር።

በድብቅ የትርጉም ሥራ ማከናወን ጀመርኩ

በወቅቱ በሊትዌኒያ የቀሩት የይሖዋ ምሥክሮች በጣም ጥቂት ነበሩ። ሌሎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ታስረው አሊያም በግዞት ወደ ሳይቤሪያ ተወስደው ነበር። በ1959 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ከሳይቤሪያ ተመለሱ፤ እነዚህ ወንድሞች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ወደ ሊትዌኒያ ቋንቋ እንድተረጉም ሐሳብ አቀረቡልኝ። ሥራው ከባድ ቢሆንም እንደ ትልቅ መብት ስለቆጠርኩት በደስታ ተቀበልኩት።

በመጋቢት ወር 1960 የትርጉም ሥራ የጀመርኩ ሲሆን በሐምሌ ወር በዱቤሳ ወንዝ ውስጥ በድብቅ ተጠመቅኩ። የሶቪየት ኅብረት የደኅንነት ኮሚቴ (ኬጂቢ) የይሖዋ ምሥክሮችን ይቃወም ስለነበር ራሴን ለማስተዳደር ሥራ ማግኘት አልቻልኩም፤ በዚህም ምክንያት ለእምነቴ ጥሩ አመለካከት ከነበራቸው ከወላጆቼ ጋር መኖር ጀመርኩ። የአባቴንና የጎረቤቶቻችንን ላሞች እጠብቅ ነበር። ከብቶቹን እየጠበቅኩ የትርጉም ሥራዬንም አከናውን ነበር። በአረንጓዴ የሣር ምንጣፍ በተሸፈነው ውብ መስክ ላይ ጉቶ ላይ ተቀምጬ እግሮቼ ላይ በማስደገፍ የትርጉም ሥራዬን ሳከናውን የሚያምር ቢሮ ውስጥ ሆኜ እንደምሠራ ይሰማኝ ነበር።

ይሁንና ገላጣ በሆነው መስክ ላይ የትርጉም ሥራውን ሳከናውን የኬጂቢ ወኪሎች ወይም መረጃ የሚያቀብሏቸው ሰዎች ሊያዩኝ ስለሚችሉ እንዲህ ማድረጉ አደገኛ እንደሆነ አስተዋልኩ። በመሆኑም በድብቅ የትርጉም ሥራውን ማከናወን የምችልበት ቦታ ሲገኝ ከአባቴ ቤት ወጣሁ። አንዳንድ ጊዜ በከብቶች በረት ውስጥ ሆኜ ሥራዬን አከናውን ነበር፤ ከብቶቹ በአንዱ ክፍል ሲሆኑ እኔ ደግሞ በሌላኛው ክፍል ውስጥ ሆኜ የተረጎምኩትን በታይፕ እጽፍ ነበር።

በአካባቢያችን የኤሌትሪክ ኃይል ስላልነበረ የምሠራው ቀን ቀን ነበር። የጽሕፈት መሣሪያው ጽምፅ እንዳይሰማ ለማድረግ ከበረቱ ውጭ በነፋስ የሚሠራ መሣሪያ ተተከለ። ሲመሽ ወደ ቤት ገብቼ እራቴን ከበላሁ በኋላ ወደ በረቱ ተመልሼ ጭድ ላይ እተኛለሁ።

በጥቅምት ወር 1961 ሃይማኖትን የማስፋፋት ሥራ እንደማከናውን ስለታወቀ እኔና ሌሎች ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ታሰርን። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደጠቀስኩት በ1962 ፍርድ ቤት የቀረብኩት በዚህ ምክንያት ነበር። ባለሥልጣናቱ ጉዳያችን በግልጽ ሸንጎ እንዲታይ ስለፈቀዱ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ለተሰበሰቡት በርካታ ሰዎች ምሥክርነት የመስጠት አጋጣሚ በማግኘታችን ተደሰትን። (ማርቆስ 13:9) የሦስት ዓመት እስራት የተፈረደብኝ ሲሆን በታሊን፣ ኢስቶኒያ ወደሚገኝ እስር ቤት ተላክሁ። እኔ እስከማውቀው ድረስ በወቅቱ በእምነቴ ምክንያት በዚያ ወኅኒ ቤት የታሰርኩት እኔ ብቻ ነበርኩ። የከተማው ባለሥልጣናት ይጎበኙኝ የነበረ ሲሆን እኔም ስለ እምነቴ እነግራቸው ነበር።

የትርጉም ሥራውን እንደገና ጀመርኩ

በ1964 በኢስቶኒያ ከሚገኘው ወኅኒ ቤት ከተለቀቅሁ በኋላ ወደ ሊትዌኒያ ተመለስኩ። በዚያም ጽሑፎቻችንን መተርጎም የቀጠልኩ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የምተረጉመው ከሩሲያኛ ወደ ሊትዌኒያ ቋንቋ ነበር። ከባድ የሥራ ጫና ነበረብኝ። ሌሎች የሚያግዙኝ ቢሆንም ወደ ሊትዌኒያ ቋንቋ በመተርጎሙ ሥራ ሙሉ ጊዜዬን የማሳልፈው እኔ ብቻ ነበርኩ። አብዛኛውን ጊዜ ከሰኞ እስከ እሁድ ሙሉ ቀን እሠራ ነበር። ይሖዋ ባይረዳኝ ኖሮ እንዲህ ያለውን ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ኃይል አይኖረኝም ነበር።

የማከናውነው ሥራ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ስለምገነዘብ ምንጊዜም ቢሆን በጣም እጠነቀቅ ነበር። ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች እኔን ለመደበቅ እንዲሁም የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ለማሟላትና እንዳልያዝ ለመጠበቅ አብዛኛውን ጊዜ የራሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውን ደህንነት አደጋ ላይ ይጥሉ ነበር። በዚህ መንገድ ተባብረን መሥራታችን በጣም እንድንቀራረብ አድርጎናል። ሥራዬን በማከናውንበት ወቅት ሌሎች ሰዎች ለመንግሥት እንዳይጠቁሙብኝ ያረፍኩበት ቤተሰብ አባላት አካባቢውን ይቃኙ ነበር። አንድ ሰው ሲመጣ ካዩ ሙቀት ወደየክፍሉ የሚመጣበትን ቧንቧ ሁለት ጊዜ በብረት በመምታት ያስጠነቅቁኛል። ይህንን የማስጠንቀቂያ ድምፅ ስሰማ ሥራዬን ሊያጋልጥ የሚችል ማንኛውንም ነገር በፍጥነት እደብቃለሁ።

ሥራዬን የማከናውንበት ቤት እየተሰለለ እንደሆነ ካወቅን በፍጥነት ወደ ሌላ ቦታ እሄዳለሁ። በወቅቱ ያለ ፈቃድ የጽሕፈት መሣሪያ ይዞ መገኘት እንደ ከባድ ወንጀል ስለሚታይ የጽሕፈት መሣሪያውን ወደ አዲሱ የሥራ ቦታዬ የሚወስድልኝ ሌላ ሰው ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ወደ አዲሱ ቦታ የምሄደው በምሽት ነበር።

በወቅቱ ይሖዋ ጥበቃ እንዳደረገልኝ ምንም ጥርጥር የለውም። ባለሥልጣናቱ ምንም ዓይነት ማስረጃ ማግኘት ባይችሉም ምን እንደምሠራ ያውቁ ነበር። ለምሳሌ፣ በ1973 ስምንት የይሖዋ ምሥክሮች ፍርድ ቤት ቀርበው በነበረበት ወቅት አቃቤ ሕጉ ለጥያቄ ጠራኝ። “ሞጽኩቴ፣ ባለፉት ዓመታት ውስጥ ምን ያህል ጽሑፍ አዘጋጅተሻል?” የሚል ቀጥተኛ ጥያቄ አቀረበልኝ።

እኔም እንዲህ ዓይነቱን ጥያቄ ልመልስ እንደማልችል ነገርኩት። ከዚያም “ታዲያ ምን ዓይነት ጥያቄ ባቀርብልሽ ነው መልስ የምትሰጪኝ?” በማለት ጠየቀኝ።

እኔም “ከዚህ ሥራ ጋር ተያያዥነት የሌለው ጥያቄ ከጠየቅኸኝ እመልስልሃለሁ” አልኩት።

የለውጥ ነፋስ

በ1980ዎቹ ዓመታት መገባደጃ አካባቢ በሊትዌኒያ ሁኔታዎች መለወጥ ጀመሩ። ከመንግሥት ባለሥልጣናት ተደብቀን ሥራችንን ማከናወናችን ቀረ። በ1990 ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችም የትርጉም ሥራውን ማከናወን ጀመሩ። ከዚያም መስከረም 1, 1992 በክላይፔዳ አነስተኛ የትርጉም ቢሮ ተቋቋመ፤ እኔም በዚህች ከተማ መኖር ጀመርኩ።

በአጠቃላይ በ16 የተለያዩ ቦታዎች ሆኜ ለ30 ዓመታት ያህል የትርጉም ሥራዬን አከናውኛለሁ። የራሴ ቤት አልነበረኝም። ያም ቢሆን ሥራችን ያስገኘውን ፍሬ በመመልከቴ በጣም ደስተኛ ነኝ! በአሁኑ ጊዜ በሊትዌኒያ ወደ 3,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ። በአንድ ወቅት በበረቶችና በቤቶች ጣሪያ ሥር ባለው ቦታ ተደብቄ አከናውነው የነበረው የትርጉም ሥራ፣ ዛሬ በካውናስ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ምቹ በሆነው የሊትዌኒያ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እየተከናወነ ነው።

ወደ 60 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት በክላይፔዳ ቀዝቃዛ በሆነው ወኅኒ ቤት ውስጥ ከሊዲያ ጋር የተገናኘንበትን ወቅት እስካሁን አስታውሰዋለሁ። ያ አጋጣሚ ሕይወቴን ለውጦታል! ታላቁ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ ስለ እሱና ስለ ዓላማዎቹ እውነቱን እንዳውቅ አጋጣሚ ስለሰጠኝ ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ፤ ፈቃዱን ለማድረግ ሕይወቴን ለእሱ መወሰን በመቻሌም ይሖዋን አመሰግነዋለሁ!

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሊዲያ በወኅኒ ቤት ሳለን ለአራታችን ያስተማረችን አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሕይወታችንን ለውጦታል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የሶቪየት ጋዜጣ በ1962 ፍርድ ቤት በቀረብኩበት ወቅት ችሎቱ የተከናወነበትን መንገድ ዘግቦ ነበር

[በገጽ 14 እና 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብያዝ ወኅኒ ልወርድ እንደምችል እያወቅሁ ከተረጎምኳቸው ጽሑፎች አንዳንዶቹ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሊዲያ በወኅኒ ቤት ሳለን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዳውቅ ረዳችኝ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1956 በከባሮፍስክ፣ ሩሲያ በሚገኝ እስር ቤት በነበርኩበት ወቅት ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች (በስተግራ) ስለ አምላክ ይበልጥ እንዳውቅ ረድተውኛል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእገዳው ሥር እጠቀምበት የነበረው የጽሕፈት መሣሪያ