ለረጅም ጊዜ ለፀሐይ መጋለጥህ ሊያሳስብህ ይገባል?
ለረጅም ጊዜ ለፀሐይ መጋለጥህ ሊያሳስብህ ይገባል?
“የኦዞን ሽፋን መሳሳት ይበልጥ ግልጽ በሆነበትና በመላው ዓለም ያሉ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሰዎች ለፀሐይ በሚያጋልጥ መዝናኛ መካፈል በሚመርጡበት በዚህ ዘመን ከልክ በላይ ለአልትራቫዮሌት ጨረር መጋለጥ የሚያስከትለው የጤና ቀውስ በጣም አሳሳቢ ችግር እየሆነ ነው።”—የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ዶክተር ጆንግ-ዉክ
ነጭ የቆዳ ቀለም ያለው ማርቲን የሚባል ከሰሜን አውሮፓ የመጣ ሰው በጣሊያን የባሕር ዳርቻ ላይ ከአንድ የመናፈሻ ጃንጥላ ሥር ጋደም ብሎ እያለ እንቅልፍ ወሰደው። ከእንቅልፉ ሲነቃ የጃንጥላው ጥላ ሸሽቶ ስለነበር እግሮቹ ከመጠን በላይ ለፀሐይ ተጋልጠው ነበር፤ በዚህም ምክንያት እግሮቹ ያበጡ ከመሆኑም በላይ በጣም ቀይ ሆነው ነበር። ማርቲን እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ሆስፒታል ድንገተኛ የሕክምና ክፍል መሄድ ነበረብኝ። እግሮቼ እጥፍ ዘርጋ አልል ከማለታቸውም ሌላ አብጠው ሁለት ቋሊማዎች መስለው ነበር። በቀጣዮቹ ሁለትና ሦስት ቀናት በከባድ ሕመም ስሠቃይ ቆየሁ። መቆምም ሆነ እግሮቼን ማጠፍ አልችልም ነበር። ቆዳዬ በጣም ከመወጠሩ የተነሳ ይፈነዳል ብዬ ፈርቼ ነበር።”
ብዙዎች፣ ለፀሐይ እንዳይጋለጡ መፍራት የሚገባቸው እንደ ማርቲን ያሉ ነጭ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው ብለው ያስባሉ። ጠቆር ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ሰዎች የፀሐይን ትኩሳት የመቋቋም አቅማቸው የተሻለ ቢሆንም እነሱም የቆዳ ካንሰር ሊይዛቸው ይችላል። እንዲያውም እነሱን የሚይዛቸው ካንሰር ብዙውን ጊዜ ሳይታወቅ አደገኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል። ለፀሐይ ከመጠን በላይ መጋለጥ ከሚያስከትላቸው አደጋዎች መካከል የዓይን መጎዳትና በሽታን የመከላከል አቅም መዳከም የሚገኙበት ሲሆን አንድ ሰው እነዚህ ጉዳቶች እንዳሉበት የሚገነዘበው ጉዳቱ ከደረሰበት ከረጅም ጊዜ በኋላ ሊሆን ይችላል።
እርግጥ ነው፣ በጥቅሉ ሲታይ ወደ ምድር ወገብ በተጠጋን መጠን የአልትራቫዮሌት ጨረር እየጨመረ ይሄዳል። ስለዚህ በተለይ በሐሩርና ከፊል ሐሩራማ በሆኑ ክልሎች የሚኖሩ እንዲሁም ወደ እነዚህ አካባቢዎች የሚጓዙ ሰዎች ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው አንደኛው ምክንያት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚቀርበው ዘገባ መሠረት የኦዞን ሽፋን እየሳሳ መምጣቱ ነው። ለፀሐይ ከልክ በላይ መጋለጥ ከሚያስከትላቸው አደጋዎች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።
በዓይን ላይ የሚደርስ ጉዳት
በምድር ዙሪያ ከ15 ሚሊዮን የማያንሱ ሰዎች ለዓይን መታወር ዋነኛ መንስኤ በሆነው ለዓይን ሞራ ግርዶሽ (ለዓይን ሌንስ ጉም መልበስ) ተዳርገዋል። የዓይን ሞራ ግርዶሽ የሚከሰተው በዓይናችን ሌንስ ውስጥ ያሉት ፕሮቲኖች እርስ በርስ ተወሳስበው ሌንሱን እንደ ጉም የሚያለብስ ቀለም በሚፈጥሩበት ጊዜ ነው። የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ ለረዥም ዓመታት ለአልትራቫዮሌት ጨረር በመጋለጥ ከሚመጡት የዓይን ጉዳቶች መካከል አንዱ ነው። እንዲያውም ለዓይን ሞራ ግርዶሽ ከተዳረጉት ሰዎች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ችግሩ የተከሰተባቸው ወይም የተባባሰባቸው ለረጅም ጊዜ ለፀሐይ በመጋለጣቸው እንደሆነ ይገመታል።
የሚያሳዝነው፣ ለዓይን ሞራ ግርዶሽ ከሚጋለጡት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ የሚኖሩት በምድር ወገብ አካባቢ ነው፤ ይህ አካባቢ ደግሞ ድሆች የሚበዙባቸው በርካታ ታዳጊ አገሮች የሚገኙበት ክልል ነው። በመሆኑም በአፍሪካና በእስያ እንዲሁም በመካከለኛውና በደቡብ አሜሪካ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆች ለዓይነ ስውርነት የተዳረጉት ሞራውን በቀዶ ሕክምና ለማስወጣት የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው ነው።
በቆዳ ላይ የሚደርስ ጉዳት
በዓለም ዙሪያ ካንሰር ካለባቸው ሰዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በቆዳ ካንሰር የተጠቁ ናቸው። በየዓመቱ 130,000 የሚያህሉ ሰዎች ሜላኖማ በተባለው በጣም አደገኛ የቆዳ ካንሰር እንደሚያዙ ሪፖርት ይደረጋል። በተጨማሪም በየዓመቱ ከሁለት እስከ ሦስት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ቤዛል ሴል ካርሲኖማ እና ስኩዌመስ ሴል ካርሲኖማ በሚባሉት የቆዳ ካንሰር ዓይነቶች ይያዛሉ። በየዓመቱ በቆዳ ካንሰር ምክንያት ወደ 66,000 የሚጠጉ ሰዎች እንደሚሞቱ ይገመታል። *
የፀሐይ ብርሃን ቆዳህን ሊጎዳው የሚችለው እንዴት ነው? ለፀሐይ ከልክ በላይ መጋለጥ የሚያስከትለው የተለመደውና በብዙዎች ዘንድ የታወቀው ጉዳት ኤርቲማ የተባለው በፀሐይ መለብለብ ምክንያት የሚመጣ የቆዳ መቅላት ነው። ይህ ጉዳት ለቀናት ሊቆይ ይችላል፤ ምናልባትም በቆዳው ላይ የሚወጣው እንደ ቡግር ያለ ነገር ይፈርጥና ቆዳው ይላጥ ይሆናል።
ቆዳ በፀሐይ ሲለበለብ የአልትራቫዮሌት ጨረር በላይኛው የቆዳ ሽፋን ላይ ያሉትን አብዛኞቹን ሴሎች የሚገድላቸው ሲሆን በውስጠኛው የቆዳ ክፍል ላይ ደግሞ ጉዳት ያደርሳል። አንድ ሰው ከመጠን በላይ ለፀሐይ በመጋለጡ ምክንያት የቆዳው ቀለም ከተለወጠ ቆዳው ጉዳት ደርሶበታል ማለት ነው። የቆዳ ካንሰር ሊከሰት የሚችለው የሴሎቹን እድገትና ወደ ሌላ ሴል የሚከፈሉበትን ሂደት የሚቆጠጠረው ዲ ኤን ኤ ጉዳት ሲደርስበት ነው። በተጨማሪም የፀሐይ ብርሃን ቆዳን እንዲሻክርና እንዲቆረፍድ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ግለሰቡ ያለ ዕድሜው ቆዳው እንዲሸበሸብ አልፎ ተርፎም ቆዳው በቀላሉ እንዲበልዝ ያደርጋል።
በሽታን በመከላከል አቅም ላይ የሚደርስ ጉዳት
የአልትራቫዮሌት ጨረር ከመጠን በላይ ወደ ቆዳ በሚገባበት ጊዜ የሰውነት በሽታን የመከላከል ሥርዓት በእጅጉ እንደሚዛባ ጥናቶች አመልክተዋል። ይህ ደግሞ ሰውነት ራሱን ከአንዳንድ በሽታዎች የመከላከል አቅሙን ሊያዳክምበት ይችላል። በመጠኑም እንኳ ለፀሐይ መጋለጥ ባክቴሪያ፣ ፈንገስ፣ ጥገኛ ተሕዋስያንና ቫይረሶች ለሚያስከትሉት ኢንፌክሽን የመጋለጥ አጋጣሚን እንደሚጨምር ታውቋል። ብዙ ሰዎች ፀሐይ ላይ መቆየት ኸርፐር ሲምፕሌክስ በሚባል ቫይረስ የሚመጣው ሽፍታ በተደጋጋሚ እንዲወጣባቸው እንደሚያደርግ አስተውለዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣው አንድ ዘገባ እንደገለጸው አልትራቫዮሌት ቢ (UVB) ተብሎ የሚጠራው የጨረር ዓይነት “የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም የሚያዳክም ይመስላል፤ በሽታን የመከላከል አቅም ከተዳከመ ሰውነት ኸርፐስ ሲምፕሌክስ የሚባለውን ቫይረስ መቋቋም ስለማይችል ፀሐይ ላይ በመቆየት የሚመጣው ሽፍታ ያገረሻል።”
ከካንሰር ጋር በተያያዘ ደግሞ የፀሐይ ጨረር በሁለት መንገድ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። የመጀመሪያው፣ በዲ ኤን ኤ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ሰውነት እንዲህ ዓይነቱን ጉዳት ለመጠገን የሚረዳውን ተፈጥሯዊ ችሎታ ማዳከም ነው።
እንግዲያውስ ራሳችንን ከልክ በላይ ለፀሐይ እንዳናጋልጥ ጥንቃቄ ማድረጋችን ብልኅነት ነው። ካልሆነ ግን ጤንነታችን አልፎ ተርፎም ሕይወታችን አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.10 የቆዳ ካንሰርን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሰኔ 8, 2005 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 3-10ን ተመልከት።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ቆዳህን ከጉዳት መጠበቅ የምትችልበት መንገድ
▪ ከጧቱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ የአልትራቫዮሌት ጨረር ኃይለኛ ስለሚሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ለፀሐይ እንዳትጋለጥ ጥንቃቄ አድርግ።
▪ ጥላ ባለበት ሥፍራ ለመቆየት ጥረት አድርግ።
▪ እጆችህንና እግሮችህን በደንብ ሊሸፍን የሚችል ሰውነት ላይ የማይጣበቅ ልብስ ልበስ።
▪ ዓይኖችህን፣ ጆሮችህን፣ ፊትህንና ማጅራትህን ፀሐይ እንዳያገኛቸው ሰፊ ባርኔጣ አድርግ።
▪ ሁለቱን የአልትራቫዮሌት ጨረር ዓይነቶች (UVA እና UVB) ከ99 እስከ 100 በመቶ ሊከላከሉ የሚችሉ ጥራት ያላቸውና ዓይንን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍኑ የፀሐይ መነፅሮችን ብታደርግ በዓይንህ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በእጅጉ መቀነስ ትችላለህ።
▪ የፀሐይ ጨረር የመከላከል ኃይሉ ቢያንስ 15 የሚሆን መከላከያ ቅባት ተጠቀም፤ እንዲሁም ይህን ቅባት በየሁለት ሰዓቱ በደንብ ተቀባ።
▪ ሰውነትን ለማጠየም የሚረዱ የፀሐይ አምፑሎችና የፀሐይ አልጋዎች፣ ቆዳን ሊጎዳ የሚችል የአልትራቫዮሌት ጨረር ስለሚያመነጩ እንዲህ ያሉ መሣሪያዎችን ከመጠቀም መቆጠብ እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።
▪ በተለይ ሕፃናትና ልጆች ቆዳቸው በቀላሉ ጉዳት ሊደርስበት ስለሚችል ተገቢውን ጥንቃቄ አድርግላቸው።
▪ ፈጽሞ ፀሐይ ላይ አትተኛ።
▪ በቆዳህ ላይ ጠቆር ያለ ወይም ጠቃጠቆ ነገር አሊያም ሽፍታ ከወጣብህና ሁኔታው አሳሳቢ እንደሆነ ከተሰማህ ሐኪም ቤት ሂድ።