በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሕሙማን የመምረጥ መብት አላቸው

ሕሙማን የመምረጥ መብት አላቸው

ሕሙማን የመምረጥ መብት አላቸው

ጣሊያን የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

የይሖዋ ምሥክሮች ለሕክምና ደም አይወስዱም። እንዲህ ያለ አቋም የወሰዱት የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ ለማክበር ስለሚፈልጉ ነው፤ ከደም ጋር በተያያዘ አምላክ የሰጠው የመጀመሪያ ትእዛዝ “ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ” ይላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም ‘ከደም እንዲርቁ’ ግልጽ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።—ዘፍጥረት 9:4፤ የሐዋርያት ሥራ 15:29፤ ዘሌዋውያን 17:14

በጣሊያን አገር በሞንቴሬንትስዮ ከተማ የሚገኙ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ደም መለገስ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ጽሑፍ እንዲያዘጋጁ ተጠይቀው ነበር። ከተማሪዎቹ መካከል ቤኔዴታ የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር ትገኝበታለች። ይህች ወጣት ያዘጋጀችው ጽሑፍ በከፊል እንዲህ ይላል፦

“የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ስለሚከተሉ ለሕክምና ብለው ደም እንደማይወስዱ በሰፊው የታወቀ ነው፤ ይህ ሲባል ግን ሌላ ዓይነት ሕክምና እንዲደረግላቸው አይፈልጉም ማለት አይደለም። እንዲያውም የይሖዋ ምሥክሮች ለጤንነታቸው ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ። ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው ከሁሉ የተሻለውን ሕክምና ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። እምነታቸውን እስካከበሩላቸው ድረስም ከሐኪሞች ጋር ለመተባበር ፈቃደኞች ናቸው።”

ቤኔዴታ አክላም እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “እያንዳንዱ ታካሚ ይጠቅመኛል ብሎ ያሰበውን የሕክምና ዓይነት የመምረጥ፣ የመከበርና የሚወስደው ሕክምና የሚያስከትለውን ጉዳትና ያለውን ጥቅም የማወቅ መብት አለው።”

በሞንቴሬንትስዮ የሚገኘው የጣሊያን ደም ለጋሾች ማኅበር ቅርንጫፍ፣ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ከሁሉ በተሻለ መንገድ የግል ስሜታቸውን ለገለጹ ተማሪዎች ሽልማት ሰጥቷል። ሞንቴሬንትስዮ ቪቫቼ የተሰኘው መጽሔት እንደሚከተለው ሲል ዘግቧል፦ “ቤኔዴታ ባርቢ፣ ከብዙኃኑ የተለየ አመለካከት የሚንጸባረቅበት ጽሑፍ ብታቀርብም በስም ተጠቅሳ ተመስግናለች፤ የጽሑፏ ሐሳብ የጣሊያን ደም ለጋሾች ማኅበር ካለው አቋም ፈጽሞ የተለየ ቢሆንም ተማሪዋ ሚዛናዊነትና ጨዋነት በተንጸባረቀበት መንገድ እምነቷን መግለጽ ችላለች።”

የይሖዋ ምሥክሮች ደምን በተመለከተ ያላቸው አቋም “ከብዙኃኑ የተለየ” ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሐኪሞች የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ያለ አቋም መያዛቸው ያለውን ጠቀሜታ ተገንዝበዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸው ይህ አቋም፣ በቀዶ ሕክምና ወቅት የሚፈሰውን ደም ለመቀነስ የሚረዱ አዳዲስ የሕክምና ዘዴዎች በሥራ ላይ እንዲውሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህ ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮችን ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሕሙማንን ጭምር ጠቅሟል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ደምን የማይወስዱበት ዋነኛ ምክንያት በመግቢያው ላይ እንደተገለጸው የመጽሐፍ ቅዱስን ትእዛዝ ለማክበር ጥብቅ አቋም ስላላቸው ነው።

ከዚህ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ቤትህ ሲመጡ ደምን በተመለከተ የፈጣሪ አመለካከት ምን እንደሆነ ለምን አትጠይቃቸውም? “ጥልቅ አክብሮት” በሚንጸባረቅበት መንገድ በዚህ ርዕስ ላይ ሊያነጋግሩህ ፈቃደኞች ናቸው።—1 ጴጥሮስ 3:15

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትፈልጋለህ?

እውቅ የሆኑ በርካታ ባለሙያዎች የሰጡትን አስተያየት የያዘው ትራንስፊውዥን ኦልተርኔቲቭስ የተባለው ዲቪዲ በደም ምትክ የሚሰጡ ሕክምናዎችን አስመልክቶ ከሕክምና፣ ከሕግና ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ መመሪያዎችን ያብራራል። ይህን ዲቪዲ ከይሖዋ ምሥክሮች ማግኘት ትችላለህ።