በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሙታንን ልትፈራ ይገባሃል?

ሙታንን ልትፈራ ይገባሃል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሙታንን ልትፈራ ይገባሃል?

በናይጄሪያ የሚገኙት የአናግ ጎሳ አባላት፣ አንድ ሰው ሲሞት ተገቢ የሆነ ውዳሴና አክብሮት ተሰጥቶት ካልተቀበረ ነፍሱ በቤተሰቡ አባላት ላይ ችግር ሊያስከትል ሌላው ቀርቶ ሊገድላቸው እንደሚችል ያምናሉ። አንዳንድ ቻይናውያንም ሙታንን ሲቀብሩ ባሕላዊውን ሥርዓት ካልተከተሉ የሞቱት ሰዎች ነፍስ በሕይወት ባሉ ሰዎች ላይ ጥቃት ሊያደርስ አልፎ ተርፎም ሊገድላቸው እንደሚችል ያምናሉ።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የተለያዩ ባሕሎች ያሏቸው ሰዎች፣ አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ ወይም መንፈሱ ከሥጋው ተለይቶ እንደሚወጣ ያምናሉ። በተጨማሪም በርካታ ሰዎች ከሥጋው ተለይቶ የወጣው ነፍስ ወይም መንፈስ በቤተሰቡ አባላት አሊያም በጓደኞቹ ሕይወት ውስጥ ጣልቃ ይገባል የሚል እምነት አላቸው።

ይሁን እንጂ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ በሕይወት መኖሩን የሚቀጥል ነገር አለ? እንዲሁም ይህ “ነገር” በሕይወት ባሉ ሰዎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል?

ሙታን የሚያውቁት ነገር አለ?

መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን “ምንም አያውቁም” ይላል። ከዚህም በተጨማሪ ሙታን “ጠፍተዋል” በማለት ይናገራል። (መክብብ 9:5፤ ኢሳይያስ 26:14 የ1954 ትርጉም) የአምላክ ቃል የመጀመሪያውን ሰው አዳምን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር ዐፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ሆነ።”ዘፍጥረት 2:7

አዳም፣ ነፍስ ማለትም ሕይወት ያለው ሰው ሆኖ እንደተፈጠረ ልብ በል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዳም ከሥጋው ተለይቶ መኖር የሚችል ነፍስ እንደተሰጠው አይናገርም። በመሆኑም አዳም ኃጢአት ሲሠራ ሞተ። በሌላ አባባል ‘የሞተ ነፍስ’ ሆነ። (ዘኍልቍ 6:6 NW) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” በማለት ይናገራል። (ሕዝቅኤል 18:4) ሁላችንም ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ኃጢአትን ወይም አለፍጽምናን ወርሰናል። በመሆኑም ስንሞት ነፍስ ሞተ ማለት ነው።—ሮም 5:12

መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ሲናገር ሚስጥራዊ የሆኑ ቃላትን ከመጠቀም ይልቅ በቀላሉ ልንረዳው በምንችለው መንገድ ሐሳቡን ያስቀምጠዋል፤ ለምሳሌ መዝሙራዊው “የሞት እንቅልፍ እንዳልተኛ” በማለት እንደተናገረ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። (መዝሙር 13:3) በአንድ ወቅት ኢየሱስ አንዲት የ12 ዓመት ልጅ እንደሞተች ሲነገረው “ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” ብሎ ነበር። ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ “ልጅቷ እንደሞተች ያውቁ ስለነበር በማፌዝ ይስቁበት ጀመር።” ይሁንና ኢየሱስ ልጅቷን ከሞት እንቅልፍ እንዳስነሳት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ሉቃስ 8:51-54

አልዓዛር በሞተበት ወቅትም ኢየሱስ ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል። ኢየሱስ፣ አልዓዛርን “ከእንቅልፍ ልቀሰቅሰው ወደዚያ እሄዳለሁ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸው ነበር። ደቀ መዛሙርቱ፣ ምን ማለቱ እንደሆነ ስላልገባቸው ‘ኢየሱስ በግልጽ “አልዓዛር ሞቷል” አላቸው።’ ሐዋርያው ጳውሎስም “በሞት አንቀላፍተው ስላሉት” የተናገረ ሲሆን አምላክ በወሰነው ጊዜ ወደ ሕይወት እንደሚመልሳቸውም ገልጿል።—ዮሐንስ 11:11-14፤ 1 ተሰሎንቄ 4:13-15

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ መኖሩን እንደሚቀጥል የሚገልጽ አንድም ጥቅስ የለም። በመሆኑም ሙታንን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ታዲያ ሰው ከሞተ በኋላ ከሥጋው ተለይቶ መኖሩን የሚቀጥል ነገር እንዳለ የሚገልጸው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው እምነት ምንጩ ምንድን ነው? ሙታን በሕይወት ባሉ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ለሚለው ፍርሃት መንስኤው ምንድን ነው?

ማታለያ

የሐሰት ሃይማኖቶች፣ ሰዎች ሲሞቱ በሕይወት የሚቀጥል ነገር እንዳለ ያስተምራሉ። ሰዎች የማይሞት ነፍስ አላቸው የሚለው ትምህርት ከሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ በዓለም ዙሪያ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ገዥዎች፣ ለምሳሌ የጥንቷ ግብጽ ፈርዖኖች ሲሞቱ ከሞት በኋላ በሚኖራቸው ሕይወት የሚያገለግላቸው ሰው እንዲኖር ሲባል ባሪያዎቻቸው ይገደሉ ነበር።

ብዙዎች፣ ጥቃት የሚያደርሱባቸው የሙታን ነፍሶች ወይም መንፈሶች እንደሆኑ ተነግሯቸዋል። እነዚህ ሰዎች ይህን ጥቃት የሚያደርሱባቸው በእነሱ ያልተደሰቱ የሞቱ ዘመዶቻቸው ወይም የሌሎች ሰዎች ነፍሶች እንደሆነ ያምናሉ። ይሁንና ቅዱሳን መጻሕፍት በግልጽ እንደሚያሳዩት ይህ እውነት አይደለም። በሰዎች ላይ እንዲህ ያለ ጥቃት የሚያደርሱት አጋንንት ተብለው የሚጠሩ የማይታዩ መንፈሳዊ ኃይሎች ናቸው፤ አጋንንት ሰዎችን ማሠቃየትና ማስፈራራት ያስደስታቸዋል።—ሉቃስ 9:37-43፤ ኤፌሶን 6:11, 12

መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን “የውሸት አባት” እንደሆነና “የብርሃን መልአክ ለመምሰል ዘወትር ራሱን [እንደሚለዋውጥ]” ይናገራል። እሱም ሆነ አጋንንቱ ‘መላውን ዓለም እያሳሳቱ’ ነው። (ዮሐንስ 8:44፤ 2 ቆሮንቶስ 11:14፤ ራእይ 12:9) ሰው ሲሞት ነፍሱ በሕይወት እንደሚቀጥልና በሕይወት ያሉ ሰዎችን መጉዳት እንደሚችል የሚገልጸውን ውሸት የሚያስፋፋው ሰይጣን ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ሰዎች ግን እንዲህ ባለው ውሸት አይታለሉም። ሰይጣን፣ ሙታን በሕይወት ካሉ ሰዎች ጋር መነጋገር እንደሚችሉ በመግለጽ ሰዎችን ለማታለል እንደሚሞክር ያውቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም።” (መክብብ 9:5) በእርግጥም፣ የአምላክ ቃል ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እውነቱን እንድናውቅ በማድረግ ከውሸት ነፃ ያወጣናል።—ዮሐንስ 8:32

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ሙታን የሚያውቁት ነገር አለ?—መክብብ 9:5፤ ኢሳይያስ 26:14

▪ ሰው ከሞተ በኋላ ከሥጋው ተለይቶ መኖሩን የሚቀጥል ነገር እንዳለ የሚገልጸውን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውን እምነት ያመነጨው ማን ነው?—ዘፍጥረት 3:4, 5

▪ ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ እውነቱን ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?—ዮሐንስ 8:32፤ 17:17

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሰዎችን በማሠቃየት የሚደሰቱት ክፉ መንፈሳዊ ፍጡራን እንጂ የሞቱ ሰዎች አይደሉም