በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በጣም አሳሳቢ አደጋ [በጆርጂያ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ] ተጋርጦብናል . . . አምላክ ከእኛ ጋር ነው፤ ድንግል ማርያምም እየጠበቀችን ነው። ይሁን እንጂ አንድ ጉዳይ እጅግ እያሳሰበን ነው፤ ሩሲያውያን ኦርቶዶክሶች የጆርጂያን ኦርቶዶክሶች በቦምብ እየደበደቡ ነው።”—የጆርጂያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ የሆኑት ዳግማዊ ኢላይ

“እንደፀነሱ ሲሰማቸው እርግዝናውን ወዲያውኑ የሚያስወግድ መድኃኒት ለማግኘት ሐኪም የሚያማክሩ ሴቶች ቁጥር ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በሦስት እጥፍ የጨመረ ሲሆን ሽያጩም ከ2004 ወዲህ ከ200 በመቶ በላይ ጨምሯል። . . . የምክር አገልግሎት ጠያቂዎች የስልክ ጥሪ የሚበዛው ሰኞ ሰኞ ነው። ብዙዎቹ ምክር ጠያቂዎች ደግሞ በጉርምስና ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው።”—ክላሪን፣ አርጀንቲና

በአሜሪካ ከ13 እስከ 17 ዓመት መካከል ባለው ዕድሜ ክልል የሚገኙ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች “[በ2008] ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባሉት ወራት [እያንዳንዳቸው] በየወሩ በአማካይ 1,742 የመልእክት ልውውጦችን አድርገዋል።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“ወደ 12 በመቶ የሚጠጋው የዓለም ሕዝብ በአእምሮ ሕመም ይጠቃል።”—የዓለም የአእምሮ ጤና ፌዴሬሽን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“ከአምስት አውሮፓውያን ትልልቅ ሰዎች መካከል አንዱ በዕድሜው ውስጥ በሆነ ወቅት ላይ [የማሪዋና ምንጭ የሆነውን ካናቢስ የሚባል ዕፅ] ወስዶ እንደነበር ይገመታል።”—በአውሮፓ ውስጥ የሚገኘው የዕፅና የዕፅ ሱሰኝነት መቆጣጠሪያ ማዕከል፣ ፖርቱጋል

በቁፋሮ የተገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞች

ኢየሩሳሌም ውስጥ በጥንቷ የዳዊት ከተማ ሲቆፍሩ የነበሩ አርኪኦሎጂስቶች “የጳስኮር ልጅ ጎዶልያስ” የሚል ስም የያዘ 2,600 ዓመት ዕድሜ ያለው የሸክላ ማኅተም አገኙ። በ2005 በዚሁ አካባቢ በቁፋሮ የተገኘው የሁክሃል የሚለው ስም “የሰሌምያ ልጅ ዩካል [የየሁካል (የየሁክሃል) አጭር አጠራር]” ተብሎ በኤርምያስ 38:1 ላይ ተጠቅሶ እንደሚገኘው ሁሉ ጎዶልያስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚሁ ጥቅስ ላይ ይገኛል። ሁለቱም ሰዎች በንጉሥ ሰዴቅያስ ዘመን የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት ነበሩ። ዘ ጀሩሳሌም ፖስት እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “በእስራኤል የመሬት ቁፋሮ ታሪክ፣ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ የተገለጹ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ስሞችን የያዙ ሁለት የሸክላ ማኅተሞች በአንድ ቦታ ሲገኙ ይህ የመጀመሪያው ነው።”

ቴክኖሎጂ ወንጀልን ለመከላከል እየዋለ ነው

የኒው ዮርክ ፖሊስ ዲፓርትመንት ዜጎች የሚያደርጓቸውን አብዛኞቹን ጥሪዎች የሚቀበለው በስልክ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴክኖሎጂው መስክ የተገኘው እድገት በስልክ የጽሑፍ መልእክት በመላክ ከፖሊስ ጋር መገናኘት አስችሏል። “በአሁኑ ጊዜ ዜጎች ወንጀል ሲፈጸም ሲያዩ ሁኔታውን በሞባይል ስልካቸው ቀርጸው ምስሉን ለፖሊስ እንዲልኩ ማበረታቻ እየተሰጠ ነው” በማለት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። ጋዜጣው በማከል እንደተናገረው “ወንጀሎችን የሚከታተለው ማዕከል ፎቶዎቹን በአካባቢው ቅኝት ለሚያደርጉ የፖሊስ መኪናዎች በሙሉ እንዲልክ የሚያስችሉ” አንዳንድ እርምጃዎችም እየተወሰዱ ነው።

ማግፓይ የሚባሉ ወፎች ራሳቸውን መለየት ይችላሉ

“እንደ ሰዎች ሁሉ በመስታወት ውስጥ የራሳቸውን መልክ የመለየት ችሎታ ያላቸው ቺምፓንዚዎች፣ ዶልፊኖችና ዝሆኖች ብቻ እንደሆኑ ተደርጎ ይታሰብ ነበር” በማለት የሮይተር ዘገባ ይናገራል። አሁን ግን ዩሬዥያን ማግፓይ የተባሉት ወፎች መልካቸውን በመስታወት አይተው መለየት የሚችሉ ሕያዋን ፍጥረታት በሚገኙበት “ቡድን” ውስጥ ሊፈረጁ እንደሚችሉ ተረጋግጧል። ተመራማሪዎች ማግፓይ የተባለው ወፍ በመስታወት ብቻ ሊያየው በሚችለው የሰውነቱ ክፍል ላይ ቀለም አደረጉ። “ወፎቹ በገላቸው ላይ ያለውን ቀለም ለማስወገድ አዘውትረው መጣራቸው በመስታወቱ ውስጥ የተመለከቱት የሌላ እንስሳን ሳይሆን የራሳቸውን መልክ እንደሆነ እንደሚያውቁ ያረጋግጣል” በማለት ሪፖርቱ ተናግሯል።