በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ሕይወት የሚጀምረው መቼ ነው?

የሰው ሕይወት የሚጀምረው መቼ ነው?

የሰው ሕይወት የሚጀምረው መቼ ነው?

“ወላጅ እናቴ የሳላይን ውርጃ ለመፈጸም ስትወስን ዕድሜዋ 17 ዓመት ሲሆን የ7 ወር ከ15 ቀን ነፍሰ ጡር ነበረች” በማለት ጊያና የተባለች ሴት ተናግራለች። * አክላም “ያስወረደችው እኔን ነበር። እኔ ግን ከሞት ተረፍኩ” ብላለች።

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ከውርጃ ጋር በተያያዘ ባቋቋመው ኮሚቴ ፊት በ1996 ይህን የምሥክርነት ቃል የሰጠችው የ19 ዓመቷ ጊያና ነበረች። ጊያና ለሰባት ወር ተኩል በእናቷ ማህፀን ውስጥ በነበረችበት ወቅት ሁሉም የሰውነቷ ክፍሎች ተሠርተው እንደነበር ግልጽ ነው። ከእናቷ ማህፀን ከወጣች በኋላም እንደ አንድ ሰው መኖር ስለቀጠለች ከማህፀን ከመውጣቷ በፊትም ሰው ነበረች በሚለው ሐሳብ ሳትስማማ አትቀርም።

ይሁን እንጂ ጊያና የአምስት ሳምንት ፅንስ ሳለች ማለትም አንድ ሴንቲ ሜትር የሚያክል መጠን በሚኖራት ጊዜ ላይ ሰው ነበረች? እውነት ነው፣ በዚህ ጊዜ ላይ የሰውነት ክፍሎቿ ሙሉ በሙሉ አልተሠሩም፤ ይሁን እንጂ አንጎሏን ጨምሮ የነርቭ ሥርዓቷ መሠረት የተጣለው በዚህ ጊዜ ነው። በዚህ ዕድሜዋ ወደ ደም ሥሮቿ ደም የሚረጭ በደቂቃ 80 ጊዜ የሚመታ ልብ ነበራት። ስለዚህ ጊያና በሰባት ወር ተኩል ከማሕፀን ስትወጣ ሰው ከነበረች በአምስት ሳምንቷ ያን ያህል ትልቅ ባትሆንም እንኳ ሰው ነበረች ብሎ መደምደም ምክንያታዊ አይሆንም?

ተአምር የሆነው የፅንስ አጀማመር

የአንድ ሽል የአካል ክፍሎች በሙሉ እድገታቸው የሚጀምረው ፅንሱ በሚፈጠርበት ጊዜ ማለትም በእናቲቱ ማሕፀን ውስጥ የሚገኘው እንቁላል ከአባትየው አብራክ ከሚወጣው ዘር ጋር ከተዋሃደበት ጊዜ ጀምሮ ነው። በቴክኖሎጂ መስክ የተገኙት አዳዲስ እድገቶች፣ የሳይንስ ሊቃውንት በዳበረ በአንድ ሴል እንቁላል ውስጥ የሚካሄዱትን አስገራሚ ለውጦች እንዲመለከቱ አስችለዋቸዋል። ከእናትየውና ከአባትየው ዲ ኤን ኤ (ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ) የተዋቀሩት ሞለኪዩሎች ተዋሕደው ከዚያ በፊት ኖሮ የማያውቅ ሰብዓዊ ሕይወት ይፈጥራሉ።

የተሟሉ የአካል ክፍሎች ያሉትን ሽል የመገንባቱ ተአምራዊ ሂደት የሚጀምረው ከዚህ ነጠላ ሴል ነው። ይህ “የግንባታ” ፕሮጀክት የሚካሄድበት መንገድ የሚወሰነው የዲ ኤን ኤ ክፍል በሆኑት በራሳችን ጂኖች ነው። እነዚህ ጂኖች ስለ እኛ ሁሉንም ነገር ይቆጣጠራሉ ለማለት ይቻላል። ቁመታችንን፣ የፊታችንን ገጽታ፣ የዓይናችንንና የፀጉራችንን ቀለም እንዲሁም በሺህ የሚቆጠሩ ሌሎች ባሕርያትን ይወስናሉ።

ከዚያ በኋላ ያ የመጀመሪያው ሴል እየተከፋፈለ ሲሄድ የጂኖቹ “ንድፍ” በእያንዳንዱ አዲስ ሴል ውስጥ ይቀረጻል። የሚገርመው ነገር፣ እያንዳንዱ አዲስ ሴል በውስጡ ወደሚፈለገው ዓይነት ሴል እንዲከፈል የሚነግረው ፕሮግራም አለው። የሚፈለገው ሴል የልብ፣ የአንጎል፣ የአጥንት፣ የቆዳ ወይም ብርሃን የሚያስተላልፈው የዓይን ሴል ሊሆን ይችላል። አዲስ ሰብዓዊ አካል እንዲዋቀር በሚያደርገው የመጀመሪያ ሴል ውስጥ የተሞላው የመጀመሪያው ፕሮግራም ብዙውን ጊዜ “ተአምር” ተብሎ መጠራቱ ምንም አያስገርምም።

እውቅ ሞለኪውላር ባዮሎጂስት የሆኑት ዶክተር ዴቪድ ፉ-ቺ ማርክ እንደተናገሩት “አንድ ሰው ገና አንድ ሴል በነበረበት ደረጃ ላይ፣ በመላ ሕይወቱ የሚያደርገው የእድገት ሂደት ምን እንደሚመስል የሚገልጽ የተሟላ መረጃ በውስጡ ነበረው።” እኚሁ የሳይንስ ሊቅ “እያንዳንዱ ሰው ገና ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ከሌሎች ሰዎች ፈጽሞ የተለየ ራሱን የቻለ ሰው እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

በማህፀን ውስጥ ያለ ሰው ነው?

በማህፀን ውስጥ ያለ ልጅ ገና ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ የእናቲቱ አካል ክፍል ሳይሆን ራሱን የቻለ ሰው ነው። የእናቱ ሰውነት ፅንሱን የሚመለከተው እንደ ባዕድ አካል አድርጎ ነው። ፅንሱ በእናቱ ማሕፀን ውስጥ “የተከለለ ዓለም” ባይፈጠርለት ኖሮ ሰውነቷ ፅንሱን ለማስወጣት አፋጣኝ እርምጃ ይወስድ ነበር። በእናቱ ውስጥ የራሱን ቤት የሠራው ይህ አዲስ ሰብዓዊ ፍጡር ከሌላው ፍጹም የተለየ የራሱ ዲ ኤን ኤ ያለው ሰው ነው።

አንዳንድ ሰዎች፣ እንግዳ የሆኑ ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ በማህፀን ውስጥ ያለ ፅንስ ብዙ ጊዜ እንደሚጨነግፍ በመግለጽ ‘ታዲያ ሐኪሞች ፅንስን ቢያስወርዱ ምን አለበት?’ ብለው ይከራከራሉ። ሆኖም ድንገተኛ በሆነ ሞትና ሆን ብሎ ሰው በመግደል መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። በአንድ የደቡብ አሜሪካ አገር ውስጥ ከ1,000 ሕፃናት መካከል 71 የሚሆኑት በተወለዱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይሞታሉ። ብዙ ልጆች ዕድሜያቸው አንድ ዓመት ከመሙላቱ በፊት ስለሚሞቱ ብቻ አንድን ልጅ አንድ ዓመት ሳይሞላው መግደል ተቀባይነት ይኖረዋል? እንደማይኖረው ግልጽ ነው!

መጽሐፍ ቅዱስ በማሕፀን ውስጥ ያለውን ፅንስ ሕይወት ያለው ሰብዓዊ ፍጡር አድርጎ የሚገልጸው መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል። መዝሙራዊው ዳዊት አምላክን አስመልክቶ “ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ በመጽሐፍህ ተመዘገቡ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 139:16) ዳዊት “ያልተበጀ አካል” በማለት በደፈናው ከመናገር ይልቅ “ገና ያልተበጀውን አካሌን” ማለቱ ሕይወቱ የጀመረው ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ይኸውም ገና ሲፀነስ መሆኑን ያሳያል። በተጨማሪም ዳዊት ገና በተፀነሰበት ቅጽበት እያንዳንዱ የአካሉ ክፍል እንዴት እንደሚያድግ የሚያሳይ ንድፍ ወይም ‘የተመዘገበ’ ዝርዝር መመሪያ እንደነበረው በአምላክ መንፈስ ተመርቶ ጽፏል።

ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንዲት ሴት የምትፀንሰው “ተራ ሥጋ” ነው ብሎ እንደማይናገር ልብ በል። ከዚህ ይልቅ “ወንድ ልጅ ተፀነሰ” በማለት ይናገራል። (ኢዮብ 3:3) ይህ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ልጅ ገና ከተፀነሰበት ጊዜ ጀምሮ ልክ እንደ አንድ ሰው እንደሚቆጥረው ያመለክታል። አዎን፣ የሰው ሕይወት የሚጀምረው ከተፀነሰበት ቅጽበት ጀምሮ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 የሳላይን ውርጃ የሚካሄደው በእናቲቱ ማህፀን ውስጥ መርዛማ ጨው በመርፌ አማካኝነት በመጨመር ነው፤ ከዚያም ሽሉ መርዙን ይውጠውና አብዛኛውን ጊዜ በሁለት ሰዓት ውስጥ ይሞታል። ከ24 ሰዓት ገደማ በኋላ እናትየው ምጥ ይይዛትና የሞተ አሊያም ከተወለደ በኋላ የሚሞት ልጅ ትወልዳለች።

[በገጽ 6 እና 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

አምስት ሳምንት የሆነው ፅንስ ተራ ሥጋ ሳይሆን በውስጡ አንድ ትልቅ ሰው የሚኖሩትን የአካል ክፍሎች መዋቅር የያዘ ነው

(ትክክለኛ መጠኑ)