በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የካቶሊክ ወጣቶች ምሥክርነት እንዲሰጡ ተበረታቱ

የካቶሊክ ወጣቶች ምሥክርነት እንዲሰጡ ተበረታቱ

የካቶሊክ ወጣቶች ምሥክርነት እንዲሰጡ ተበረታቱ

አውስትራሊያ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ የሮም ካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች የ2008ቱን የዓለም ወጣቶች ቀን ለማክበር በሲድኒ፣ አውስትራሊያ ተሰብስበው ነበር፤ ይህንን ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ያዘጋጀችው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ናት።

ከ170 ብሔራት የተውጣጡ ጎብኚዎች ወይም ምዕመናን ባንዲራ እያውለበለቡ፣ በደስታ እየጮሁና እየዘመሩ በጎዳናዎቹ ላይ ሲዘዋወሩ ከተማዋን አድምቀዋት ነበር። ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ በቀለማት ባሸበረቁ 12 ጀልባዎች ታጅበው ሲድኒ ሃርበር ሲደርሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ወደቡ ላይ ተሰብስበው እየጠበቋቸው ነበር። በዓለም ዙሪያ 500 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ይህ ደማቅ ሥነ ሥርዓት በቴሌቪዥን በቀጥታ ሲተላለፍ ተመልክተዋል።

በከተማዋ ውስጥ የፈረስ ግልቢያ ውድድር በሚካሄድበት ቦታ ላይ በተከናወነው የመጨረሻው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት ላይ 4,000 የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣናትንና 2,000 የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞችን ጨምሮ 400,000 የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተዋል። በአውስትራሊያ በአንድ ክንውን ላይ ይህን ያህል ብዛት ያለው ሰው ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው፤ በዚህ ወቅት የተሰበሰበው ሕዝብ ብዛት በ2000 በተካሄደው የሲድኒ የኦሎምፒክ ውድድር ላይ ከተገኘው ተመልካች ብዛት እንኳ ይበልጣል።

የዓለም ወጣቶች ቀን ምንድን ነው? ይህ ቀን የሚከበረው ለምንድን ነው? በዚህ ክብረ በዓል ላይ ምን ዝግጅቶች ይቀርባሉ? ይህ ክብረ በዓል በሲድኒ ስለሚገኙት ወጣቶች እምነት ምን አሳይቷል?

‘የእምነት መሸርሸር’

የዓለም ወጣቶች ቀን፣ የካቶሊክ ወጣቶችን እምነት ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው። ምዕመናን አብዛኛውን ጊዜ ይህንን ክብረ በዓል የሚያከብሩት በአካባቢያቸው ባለው ሃገረ ስብከት ውስጥ ነው። ይሁንና በሁለት ወይም በሦስት ዓመት አንዴ አንድ ትልቅ ከተማ ይህን ክብረ በዓል የሚያስተናግድ ከመሆኑም ሌላ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊክ የሆኑ ወጣቶች ይጋበዛሉ። እስከ አሁን ድረስ በአምስት አህጉራት የሚገኙ አሥር ከተሞች ይህን ክብረ በዓል ያዘጋጁ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዝግጅቱ ላይ ተገኝተዋል።

የቤተ ክርስቲያኗ ባለሥልጣናት እንደገለጹት የዓለም ወጣቶች ቀን የተዘጋጀው የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮች ቁጥር እንዳያሽቆለቁል ለመግታትና የአማኞቹን እምነት ለማጠናከርም ጭምር ነው። በአውስትራሊያ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ጆርጅ ካርዲናል ፔል የተባሉት የካቶሊክ ቄስ እንዲህ ብለዋል፦ “ምዕመናን በካቶሊክ ሃይማኖት ሥርዓት መሠረት አለመመላለሳቸውና በተወሰነ ደረጃ እምነታቸው እየተሸረሸረ መሆኑ ከባድ ችግር ሆኖብናል። የዓለም ወጣቶች ቀን የሚከበረው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ሲባል ነው።”

ቫቲካን ያወጣችው መረጃ እንደሚጠቁመው በዓለም ዙሪያ የቀሳውስት ቁጥር እያሽቆለቆለ ነው። በቅርብ አሥርተ ዓመታት ውስጥ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ቀሳውስት ትዳር ለመመሥረት ሲሉ ቅስናቸውን ትተዋል። በአውስትራሊያ በቅስና ለማገልገል የሚሠለጥኑት ሰዎች ቁጥር ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ቀንሷል። በአውስትራሊያ በሚገኘው በትልቁ ሃገረ ስብከት ውስጥ የሚያገለግሉት ቀሳውስት አማካይ ዕድሜ በ60ዎቹ ውስጥ ሲሆን ይህም በ1977 ከነበሩት ቀሳውስት አማካይ ዕድሜ በ20 ዓመት ይበልጣል።

በአብዛኞቹ አገሮች ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ምዕመናን ቁጥርም እየቀነሰ ነው። ከአውስትራሊያ ዜጎች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት የካቶሊክ እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ቢናገሩም ከእነዚህ መካከል ወደ ቤተ ክርስቲያን አዘውትረው የሚሄዱት 14 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ካቶሊክ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ከ10 በመቶ እንደሚያንሱ ይታመናል። ከዚህም ሌላ በርካታ ካቶሊኮች የጾታ ሥነ ምግባርን፣ የወሊድ መከላከያን እንዲሁም ፍቺን በተመለከተ ቤተ ክርስቲያኗ የምትሰጠውን ትምህርት አይከተሉም። ሌሎች ደግሞ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በሚፈጸመው ቅሌት፣ ለምሳሌ ሕፃናትን በሚያስነውሩ ቀሳውስት ድርጊት ስሜታቸው ተጎድቷል።

ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ የተባለው ጋዜጣ የዓለም ወጣቶች ቀንን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “[ይህ ክብረ በዓል] ቤተ ክርስቲያንን ከውድቀት ለመታደግ የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ነው። . . . በአውስትራሊያና በሮም የሚገኙት የቤተ ክርስቲያኗ ባለሥልጣናት በወጣቶች አማካኝነት የእምነት ተሃድሶ ለማካሄድ ጥረት እያደረጉ ነው።” የቤተ ክርስቲያኗ ባለሥልጣናት የወጣቶችን እምነት ለማጠናከር የሞከሩት በምን መንገድ ነው?

ደማቅ ክብረ በዓላትና ፓርቲዎች

የ2008ቱ የዓለም ወጣቶች ቀን፣ ደማቅ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትንና የቡድን ውይይቶችን እንዲሁም ቅዱስ ቦታዎችን መጎብኘትን ያካተተ ነበር፤ ከዚህም ሌላ የቁርባን ሥነ ሥርዓትን ለማካሄድ በርካታ ሰዎች ተሰብስበው ነበር። በርካታ ምዕመናን በእነዚህ ዝግጅቶች ልባቸው የተነካ ቢሆንም አንዳንዶቹ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለየት ያለ መንፈስ ይንጸባረቅ እንደነበር አስተውለዋል። አሌክሳንድራ የተባለች አሜሪካዊት ካቶሊክ ወጣት፣ ስለ ዓለም ወጣቶች ቀን ስትናገር “ትልቅ ፓርቲ ነበር” ብላለች።

በሲድኒ ለስድስት ቀናት በቆየው በዚህ ክብረ በዓል ላይ የሙዚቃ ትርዒቶችን፣ ፊልሞችን፣ ቲያትሮችን፣ ኤግዚቢሽኖችንና በጎዳናዎች ላይ የሚታዩ ትእይንቶችን ጨምሮ 450 አዝናኝ ዝግጅቶች ቀርበው ነበር። በዝግጅቱ ላይ የቀረበው ሙዚቃ፣ ኦፔራንና የቤተ ክርስቲያን ዝማሬን እንዲሁም ሄቪ ሜታልንና ራፕን ያካተተ ነበር። በወቅቱ የቀረቡት የሮክ የሙዚቃ ትርዒቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ፈንጠዝያ የሚወዱ ወጣቶችን ቀልብ ማርከዋል።

እነዚህ ዝግጅቶች አንዳንድ ካቶሊኮችን አሳስበዋቸዋል። ፒተር ስኮት የተባሉ ቄስ ክብረ በዓሉን አስመልክተው ለአውስትራሊያው ኤቢሲ የዜና አገልግሎት የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል፦ “ክብረ በዓሉ አስደሳች ፓርቲ ከመሆን አላለፈም፤ ሳምንቱ ያለፈው ቅዱስ የሆነ ዝግጅት እምብዛም ሳይከናወንበት በፓርቲዎችና በሙዚቃ ትርዒቶች እንዲሁም በሌሎች ዓለማዊ እንቅስቃሴዎች ነበር።” እንዲያውም በ2000 ዓ.ም. ካርዲናል ራትጺንገር (የአሁኑ ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ) እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፦ “‘የሮክ’ [ሙዚቃ] ሥጋዊ ስሜት የሚገለጽበት ሲሆን ከክርስትና አምልኮ በተለየ መልኩ በሮክ የሙዚቃ ትርዒቶች ላይ ሰዎች ሙዚቃውንና አቀንቃኞቹን ያመልኳቸዋል።”—ዘ ስፒሪት ኦቭ ሊተርጂ

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ “የዓለም ወጣቶች ቀን በሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ የሚያስከትል ክብረ በዓል መሆን ችሏል?” የሚል ነው። በቅስና ያገለግሉ የነበሩት ፖል ኮሊንስ እንዲህ ብለዋል፦ “ምናልባት በጥቂቶች ሕይወት ላይ ለውጥ አምጥቶ ሊሆን ይችላል። . . . ይሁንና አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ቀድሞ አኗኗራቸው ይመለሳሉ። . . . ሥር ነቀል ለውጥ የሚመጣው በማሰላሰል፣ ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ በማውጣት እንዲሁም ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለማስወገድ ፈቃደኛ በመሆን እንጂ አስደሳች በሆኑ ክብረ በዓላት ላይ በመካፈል አይደለም።”

“ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ”

የቤተ ክርስቲያኗ ባለሥልጣናት ከላይ የተገለጸውን ሐቅ እንደተገነዘቡ ግልጽ ነው። በዚህም ምክንያት የ2008ቱ የዓለም ወጣቶች ቀን መሪ ጥቅስ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ . . . ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” የሚል ነበር። *

ምዕመናኑ “በዘመናዊው ዓለም ውስጥ ወንጌልን በተሟላ ሁኔታ ለመመሥከር የሐዋርያት ዓይነት አዲስ ቅንዓት እንዲያዳብሩ” በጳጳሳቱ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ ምዕመናኑን “አዲስ የሐዋርያት ትውልድ” እንዲሆኑ አሳስበዋቸዋል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ “ለጓደኞቻቸው፣ ለቤተሰባቸው አባላት እንዲሁም ለሚያገኟቸው ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን” እንዲናገሩ ምዕመናኑን አበረታተዋቸዋል።

እነዚህ ማበረታቻዎች፣ ቅን ልብ ያላቸውን አንዳንድ ምዕመናን ለሥራ አነሳስተዋቸዋል። ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣ ራሚዶ የተባለ የ20 ዓመት ወጣት “ምሥክርነት የመስጠቱን ሥራ በቁም ነገር እመለከተዋለሁ” በማለት ለአንድ ጋዜጠኛ ተናግሯል። በሌላ በኩል ግን ከጣሊያን የመጣችው የ18 ዓመቷ ቢያትሪቼ እንዲህ ብላለች፦ “በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች ስለ አምላክ አይናገሩም። በዚህ ዘመን ምሥክርነት መስጠት በጣም ከባድ ነገር ነው።” ከቴክሳስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የመጡ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሁለት ሴቶች “በእኛ አካባቢ ሲመሠክሩ የሚታዩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው!” ብለዋል፤ በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙ በርካታ ወጣቶችም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ።

ምሥክርነት የሚሰጡ ወጣቶች

በእርግጥም፣ ወጣትም ሆኑ አረጋዊ የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በቅንዓት በሚያከናውኑት የምሥክርነት ሥራ በስፋት ይታወቃሉ። ይህንን ሥራ የሚያከናውኑት ለምንድን ነው? በሲድኒ የሚኖረው ሶቲር የተባለ የ22 ዓመት ወጣት የይሖዋ ምሥክር እንደተናገረው ይህን የሚያደርጉት “ለአምላክ፣ ለሰዎችና ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር” ስላላቸው ነው።

የ2008 የዓለም ወጣቶች ቀን በተከበረበት ሰሞን በሲድኒ የሚኖሩ ወደ 400 የሚጠጉ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች በክብረ በዓሉ ላይ ባይካፈሉም ከሌሎች አገራት ለመጡት ካቶሊኮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለመናገር በተደረገው ልዩ ዘመቻ ተካፍለው ነበር። ትራቫስ የተባለ የ25 ዓመት ወጣት “ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ካላቸው ከእነዚህ ወጣት ካቶሊኮች ጋር መወያየቴ አስደስቶኛል” ብሏል። አክሎም “አብዛኞቹ ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች የነበሯቸው ሲሆን እኔም አጥጋቢ መልስ ልሰጣቸው በመቻሌ ተደስቻለሁ” በማለት ተናግሯል።

የ23 ዓመቷ ታርሻ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ቀለል ባለና መደበኛ ባልሆነ መንገድ አነጋግራቸው ነበር። ወደ ሲድኒ በመምጣታቸው መደሰቴን ከገለጽኩላቸው በኋላ ስለሚያምኑበት ነገር እንዲነግሩኝ ለማድረግ እሞክር ነበር።” የ20 ዓመቱ ፍሬዘር እንዲህ ብሏል፦ “አመቺ ሆኖ ሳገኘው ለጎብኚዎቹ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? * የሚለውን መጽሐፍ በስጦታ መልክ አበረክትላቸው ነበር። ያገኘኋቸው ሰዎች ሁሉ መጽሐፉን በደስታ ተቀብለውታል።”

አብዛኞቹ ጎብኚዎች የይሖዋ ምሥክር ከሆኑት ወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ተደስተዋል። ከፊጂ የመጣችው ሱዛን፣ አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ ቤሊንዳ የተባለችውን የ19 ዓመት ወጣት የይሖዋ ምሥክር ጠየቀቻት። ቤሊንዳም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚለው መጽሐፍ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠውን መልስ አብረው እንዲወያዩበት ሐሳብ አቀረበችላት። ውይይታቸውን ሲጨርሱ ሱዛን እንዲህ አለች፦ “አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የአምላክ ሥራ ሚስጥር እንደሆነ ይነግሩኛል። ዛሬ ግን ትክክለኛ መልስ አገኘሁ!” ቤሊንዳ መጽሐፉን ስትሰጣት ሱዛን “መጽሐፉን ትሰጭኛለሽ ብዬ ስላላሰብኩ የነገርሽኝን ነገሮች ሁሉ ላለመርሳት እየጣርኩ ነበር!” በማለት በደስታ ተናገረች።

የፊሊፒንስ ዜጋ የሆነች አንዲት ጎብኚ፣ በሲድኒ የሚገኝ አንድ ቦታ ላይ ፎቶግራፍ እንድታነሳት የይሖዋ ምሥክር የሆነችውን ማሪና የተባለች የ27 ዓመት ሴት ጠየቀቻት። በዚህ መንገድ ጨዋታ የጀመሩ ሲሆን ማሪና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ለሴትየዋ ሰጠቻት። ሴትየዋም “ትናንትና ማታ መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ለመረዳት እንዲረዳኝ ወደ አምላክ ጸልዬ ነበር። ይህ መጽሐፍ የጸሎቴ መልስ ሊሆን ይችላል!” አለች።

የ27 ዓመት ወጣት የይሖዋ ምሥክር የሆነው ሊቫይ፣ ከፓናማ ከመጡ እናትና ልጅ ጋር መወያየት ጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ማውራት የጀመሩ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምራቸው ነገሮች ጥሩ ውይይት አደረጉ። ሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ ወሰዱ። ቀጥሎም ሊቫይ “በጉብኝታችሁ ወቅት ካጋጠሟችሁ ነገሮች ትልቁን ቦታ የያዘው ምንድን ነው?” በማለት ጠየቃቸው። ልጅቷ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ እያሳየችው “ከአንተ ጋር መገናኘታችን” በማለት መለሰችለት።

በእርግጥም በርካታ ወጣት ካቶሊኮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለማወቅ ጉጉት ነበራቸው። አንተስ? ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ እንዲያስጠኑህ ለምን አትጠይቃቸውም? አንተን መርዳት ያስደስታቸዋል!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.19 ይህ መሪ ጥቅስ ከሐዋርያት ሥራ 1:8 ላይ የተወሰደ ነው።

^ አን.25 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ምዕመናን በካቶሊክ ሃይማኖት ሥርዓት መሠረት አለመመላለሳቸውና በተወሰነ ደረጃ እምነታቸው እየተሸረሸረ መሆኑ ከባድ ችግር ሆኖብናል።”—የሮም ካቶሊክ ቄስ የሆኑት ጆርጅ ካርዲናል ፔል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የቤተ ክርስቲያን ሞያ ኤግዚቢሽን

የ2008ቱ የዓለም ወጣቶች ቀን ሲከበር በአውስትራሊያ ከዚያ ቀደም ከተከናወኑት ሁሉ የሚበልጥ ሃይማኖታዊ ኢግዚቢሽን ተዘጋጅቶ ነበር። ከ100 የሚበልጡ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና የካቶሊክ ድርጅቶች፣ ከ50,000 የሚበልጡ ምዕመናንን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቀሳውስት ወይም መነኩሳት ሆነው እንዲያገለግሉ አሊያም ሃይማኖታዊ ሥራ እንዲያከናውኑ አበረታተዋቸዋል።

[በገጽ 24 እና 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቀለማት ያሸበረቁ ልብሶችን የለበሱ ምዕመናን በጎዳናዎቹ ላይ በሰልፍ ሲዘዋወሩ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች የሲድኒን ከተማ ለጎበኙት ምዕመናን መሥክረውላቸዋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Getty Images