በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጊዜዬን በአግባቡ ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?

ጊዜዬን በአግባቡ ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

ጊዜዬን በአግባቡ ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?

“‘በአሥር ሰዓት እንዲመጣልህ የምትፈልግ ከሆነ ዘጠኝ ሰዓት ቅጠረው’ በማለት አንድ ሰው ስለ እኔ በቀልድ መልክ ሲናገር ሰማሁ። በጊዜ አጠቃቀሜ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብኝ የተገነዘብኩት በዚህ ወቅት ነበር።”—ሪኪ *

በቀን ውስጥ ምን ያህል ተጨማሪ ሰዓት ብታገኝ ደስ ይልሃል? ተጨማሪውን ሰዓት የምትፈልገው ምን ልታደርግበት ነው?

□ ከጓደኞችህ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ

□ ለእንቅልፍ

□ ለማጥናት

□ ስፖርት ለመሥራት

□ ሌላ

በቀን ውስጥ ተጨማሪ ሰዓት ማግኘት ቢቻል ጥሩ ይሆን ነበር፤ ይሁንና ይህ የማይታሰብ ነገር ነው! ታዲያ ምን ማድረግ ትችላለህ? በርካታ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት ማድረጋቸው በጣም አስፈላጊ ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ሰዓት ለማግኘት አስችሏቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጊዜያቸውን እንዴት እንደሚጠቀሙበት ማወቃቸው ውጥረት ቀንሶላቸዋል፤ የትምህርት ውጤታቸው እንዲሻሻል አድርጎላቸዋል፤ እንዲሁም በወላጆቻቸው ዘንድ ይበልጥ አመኔታ እንዲያተርፉ ረድቷቸዋል። ጊዜህን በአግባቡ መጠቀምህ አንተን ሊጠቅምህ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

አንደኛው ተፈታታኝ ሁኔታ፦ ፕሮግራም ማውጣት

እንቅፋት የሚሆንብህ ነገር። በፕሮግራም መመራት የሚለውን ነገር ገና ስታስበው መፈናፈኛ እንደሚያሳጣህ ሆኖ ይሰማሃል። ያሰኘህን ነገር ባሰኘህ ሰዓት ማድረግ ያስደስትሃል፤ እንዲሁም እያንዳንዱን የሕይወትህን እንቅስቃሴ ፕሮግራም እንዲቆጣጠረው አትፈልግም።

ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? ንጉሥ ሰለሞን “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 21:5) ሰለሞን ሥራ የሚበዛበት ሰው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ባል፣ የልጆች አባትና ንጉሥ ነበር፤ ይህን ሁሉ ኃላፊነት የተሸከመው ምናልባትም 20 ዓመት ሳይሞላው ሊሆን ይችላል! ከዚያ በኋላ የነበረው ሕይወቱም ይበልጥ በሥራ የተወጠረ ነበር። አንተም በተመሳሳይ፣ ጊዜ እንደሚያጥርህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና ዕድሜህ እየጨመረ ሲሄድ ሕይወትህ ይበልጥ በሥራ የተወጠረ ሊሆን እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። እንግዲያው ያ ጊዜ ሳይመጣ ከወዲሁ በፕሮግራም የምትመራ ሰው መሆንን ብትለማመድ የተሻለ ነው!

እኩዮችህ የሰጡት አስተያየት። “ከስድስት ወራት ገደማ በፊት፣ ለማከናውናቸው ነገሮች ሁሉ ፕሮግራም ማውጣት ጀመርኩ። በፕሮግራም መመራቴ ነገሮችን ማከናወን ቀላል እንዲሆንልኝ አድርጓል።”—ጆዪ

“ላደርጋቸው ያሰብኳቸውን ነገሮች በዝርዝር መጻፌ ፕሮግራሜን እንድከተል ረድቶኛል። ተጨማሪ ነገሮች ማድረግ በሚኖርብኝ ጊዜ ደግሞ እኔና እናቴ ሁሉንም ነገር በዝርዝር ከጻፍን በኋላ እንዴት ተረዳድተን ግቦቻችን ላይ መድረስ እንደምንችል እንነጋገራለን።”—ማለሪ

ምን ሊረዳህ ይችላል? እስቲ ነገሩን በዚህ መልክ ለማሰብ ሞክር፦ ከቤተሰብህ ጋር ጉዞ ለማድረግ እየተዘጋጀህ ነው እንበል። ሁሉም የቤተሰብ አባል ሻንጣውን የመኪናው ዕቃ መጫኛ ውስጥ እንዳመጣለት ይወረውራል። ሆኖም ሁኔታውን ስታይ ለሁሉም ሻንጣ የሚበቃ ቦታ ያለ አይመስልም። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ትችላለህ? ሁሉንም ሻንጣዎች ካወጣህ በኋላ ከትላልቆቹ ሻንጣዎች ጀምረህ እንደገና በየተራ ለመጫን ልትሞክር ትችላለህ። በዚህ ጊዜ ለትናንሾቹ ሻንጣዎች የሚሆን ቦታ ታገኛለህ።

በሕይወትህ የምታደርጋቸውን ነገሮች በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ጊዜህን በትናንሽ ነገሮች ካጣበብክ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ጊዜ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። መጀመሪያ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ጊዜ ስጥ፤ ከዚያም ሌሎች ነገሮችን ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ እንደተረፈህ ስታውቅ ትገረማለህ።—ፊልጵስዩስ 1:10

ልታደርጋቸው የሚገቡ ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው?

․․․․․․

አሁን የጻፍከውን ዝርዝር በድጋሚ ተመልከትና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር በማሰብ በቅደም ተከተል ቁጥር ስጣቸው። በቅድሚያ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች የምታከናውን ከሆነ ትናንሽ ነገሮችን ለማከናወን የሚያስችልህ ብዙ ጊዜ ታተርፋለህ። ይሁንና መዘንጋት የማይገባህ አንድ ነገር አለ፦ ትናንሽ ለሆኑ ነገሮች ቅድሚያ ለመስጠት ብትሞክር ተመሳሳይ ውጤት አታገኝም!

ማድረግ የምትችለው ነገር። በኪስ የሚያዝ አጀንዳ አዘጋጅ፤ ከዚያም ማከናወን ከሚኖርብህ ነገሮች ውስጥ ቅድሚያ ልትሰጣቸው የሚገቡህን በማሰብ በቅደም ተከተል ጻፋቸው። ወይም ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ ከቀረቡት አማራጮች መካከል አንዱን ለመጠቀም ትመርጥ ይሆናል።

□ የሞባይል ስልክ የቀን መቁጠሪያ

□ አነስ ያለ ማስታወሻ ደብተር

□ የኮምፒውተር የቀን መቁጠሪያ

□ ጠረጴዛ ላይ የሚቀመጥ የቀን መቁጠሪያ

ሁለተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ፦ ያወጣኸውን ፕሮግራም መከተል

እንቅፋት የሚሆንብህ ነገር። ከትምህርት ቤት እንደተመለስክ ለጥቂት ደቂቃዎች ዘና ማለትና ቴሌቪዥን መመልከት ትፈልጋለህ። ወይም ደግሞ ፕሮግራምህ ለማጥናት ሆኖ ሳለ ጓደኞችህ የስልክ መልእክት በመላክ ሲኒማ አብረሃቸው እንድትገባ ይጋብዙሃል። ፊልሙ የሚታይበት ሰዓት ሊለወጥ አይችልም፤ ጥናትህን ግን ማታ ስትመለስ ልትደርስበት ትችላለህ። ‘በዚያ ላይ ደግሞ የተሻለ የምሠራው ጊዜ እንደሌለኝ ሲሰማኝ ነው’ ብለህ ታስባለህ።

ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? አእምሮህ የበለጠ ንቁ እያለ ብታጠና በትምህርት ቤት የተሻለ ውጤት ልታመጣ ትችላለህ። ደግሞስ ያለብህ ውጥረት ሳያንስ ሌሊቱን በችኮላ ለማጥናት በመሞከር በራስህ ላይ ለምን ሌላ ውጥረት ትጨምራለህ? በማግስቱ ጠዋት ምን ሊከሰት እንደሚችል እስቲ አስብ! ከእንቅልፍህ አርፍደህ ልትነቃ እንዲሁም የበለጠ ውጥረት ሊሰማህ ይችላል፤ ከዚህም በላይ ተጣድፈህ ከቤት መውጣት ሊኖርብህና ትምህርት ቤት ዘግይተህ ልትደርስ ትችላለህ።—ምሳሌ 6:10, 11

እኩዮችህ የሰጡት አስተያየት። “ቴሌቪዥን ማየት፣ ጊታር መጫወትና ከጓደኞቼ ጋር መሆን በጣም ያስደስተኛል። እነዚህን ነገሮች ማድረግ በራሱ ስህተት ባይሆንም ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ጉዳዮች ለሌላ ጊዜ እንዳስተላልፍ ስለሚያደርጉኝ መጨረሻ ላይ ነገሮችን በጥድፊያ ለማከናወን እገደዳለሁ።”—ጁልየን

ምን ሊረዳህ ይችላል? በፕሮግራምህ ውስጥ፣ የግድ ማድረግ ያለብህን ነገር ብቻ ሳይሆን ማድረግ የሚያስደስትህን ነገር ጭምር አካትት። “በኋላ ላይ አንድ የሚያስደስተኝ ነገር ለማድረግ ፕሮግራም ካለኝ በቅድሚያ መሥራት የሚገባኝን ነገር ማከናወን ቀላል ይሆንልኛል” በማለት ጁልየን ተናግሯል።

ሌላው አማራጭ ደግሞ የሚከተለው ሊሆን ይችላል፦ ልትደርስበት የምትፈልገው አንድ ግብ አውጣ፤ ከዚያም እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉህና ዒላማህን እንዳትስት የሚረዱህ ትንንሽ ግቦች አውጣ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የአሥራ ስድስት ዓመቱ ጆዪ እንዲህ ብሏል፦ “ሙሉ ጊዜዬን ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስተማር ለማሳለፍ እፈልጋለሁ። እንዲህ ዓይነት ግብ ማውጣቴ በፕሮግራሜ መሠረት እንድንቀሳቀስ የሚረዳኝ ሲሆን ይህ ደግሞ ወደፊት ለሚኖረኝ በሥራ የተወጠረ ሕይወት ያዘጋጀኛል።”

ማድረግ የምትችለው ነገር። በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ልትደርስባቸው የምትችላቸው አንድ ወይም ሁለት ግቦች ምንድን ናቸው?

․․․․․․

በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ልትደርስበት የምትችለው ግብ ምንድን ነው? እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ከአሁን ጀምሮ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

ሦስተኛው ተፈታታኝ ሁኔታ፦ ጥንቁቅና የተደራጀህ መሆን

እንቅፋት የሚሆንብህ ነገር። ‘ጥንቁቅና የተደራጁ መሆን ጊዜን በአግባቡ ከመጠቀም ጋር ምን ግንኙነት አለው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። በዚያ ላይ ደግሞ ዝርክርክ መሆን በጣም ቀላል ነው። ክፍልህን ማሰናዳት ነገም ሊደርስ ይችላል፤ ወይም ከነጭራሹ ቢቀርስ! ክፍልህ መዝረክረኩ ምንም ስለማይመስልህ ‘ያን ያህል የሚካበድ ነገር አይደለም!’ ብለህ ታስባለህ። ይሁንና ይህ በእርግጥ ችላ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው?

ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? ሁሉንም ነገር በሥርዓት ማስቀመጥህና የተደራጀህ መሆንህ አንድ ነገር ስትፈልግ ቶሎ ለማግኘት ስለሚያስችልህ ጊዜ ይቆጥብልሃል። ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነውን የአእምሮ ሰላም እንድታገኝ ይረዳሃል።—1 ቆሮንቶስ 14:40

እኩዮችህ የሰጡት አስተያየት። “ልብሶቼ ከተዝረከረኩ የምፈልጋቸውን ነገሮች ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ይሆንብኛል።”—ማንዲ

“አንድ ጊዜ የኪስ ቦርሳዬን ለአንድ ሳምንት ያህል ማግኘት ስላልቻልኩ በጣም ተጨነቅኩ። ክፍሌን ያሰናዳሁ ዕለት ግን አገኘሁት።”—ፍራንክ

ምን ሊረዳህ ይችላል? በተቻለህ መጠን ዕቃዎችህን ወዲያውኑ በየቦታቸው ለመመለስ ጥረት አድርግ። ክፍልህ ተዝረክርኮ ለማጽዳት አስቸጋሪ እስኪሆን ከመጠበቅ ይልቅ ከሥር ከሥሩ ማሰናዳት ለማጽዳትም ሆነ ዕቃ ስትፈልግ ለማግኘት ቀላል ያደርግልሃል።

ማድረግ የምትችለው ነገር። ጥንቁቅና የተደራጀህ ለመሆን ጥረት አድርግ። ሁሉንም ነገር በሥርዓት ለማስቀመጥ ጥረት አድርግና ይህ ውጥረት ይቀንስልህ እንደሆነ ለማየት ሞክር።

በትንሹም ቢሆን ዛሬውኑ ለምን አትጀምርም? በዚህ ርዕስ ውስጥ ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል ለአንተ ይበልጥ ጠቃሚ ሆነው ያገኘኻቸው የትኞቹን ነው?

․․․․․․

እነዚህን ነጥቦች ለ․․․․․․ ሳምንት ያህል ከሞከርኳቸው በኋላ ምን ያህል እንደረዱኝ አያለሁ።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ በሚቀጥለው ቀን ነገሮችን በጥሩ ሁኔታ ለማከናወን ምን ያህል ሰዓት መተኛት ያስፈልግሃል?

▪ ፕሮግራም በማውጣት እንዲረዳህ ማንን መጠየቅ ትችላለህ?

▪ በአሁኑ ጊዜ በፕሮግራም የምትመራ ከሆነ ምን ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልግሃል?

[በገጽ 20 ,21 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከ8 እስከ 18 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በአንድ ሳምንት ውስጥ ያላቸውን ሰዓት የሚያሳልፉት በሚከተለው መንገድ ነው፦

17

ከወላጆቻቸው ጋር

30

በትምህርት ቤት

44

ቴሌቪዥን በማየት፣ የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት፣ የስልክ መልእክት በመላላክና ሙዚቃ በማዳመጥ

ጊዜዬን የሚወስድብኝ ምንድን ነው?

በእያንዳንዱ ሳምንት የተለያዩ ነገሮችን በማድረግ የምታሳልፈውን ሰዓት ጻፍና ደምረው

ቴሌቪዥን በማየት፦ ․․․․․․

የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት፦ ․․․․․․

ኮምፒውተር በመጠቀም፦ ․․․․․․

ሙዚቃ በማዳመጥ፦ ․․․․․․

ድምር፦

እምብዛም አስፈላጊ ባልሆኑ እንቅስቃሴዎች ከማሳልፈው ጊዜ ላይ ቀንሼ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ላውለው የምችለው ሰዓት፦

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጀመሪያ ቦታውን በትናንሽ ነገሮች ከሞላኸው ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ቦታ አታገኝም