በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፕሎቭዲፍ—ጥንታዊ መሠረት ያላት ዘመናዊት ከተማ

ፕሎቭዲፍ—ጥንታዊ መሠረት ያላት ዘመናዊት ከተማ

ፕሎቭዲፍ—ጥንታዊ መሠረት ያላት ዘመናዊት ከተማ

ቡልጋሪያ የሚገኘው የንቁ! ጸሐፊ እንዳዘጋጀው

ፕሎቭዲፍ፣ ከሮምና ከካርቴጅ እንዲሁም ከኮንስታንቲኖፕል በፊት የተቆረቆረች ጥንታዊት ከተማ ናት። በማዕከላዊ ደቡብ ቡልጋሪያ የምትገኘውና ሰባት ኮረብቶች ያሏት ይህች ከተማ ወደ 350,000 የሚጠጋ ሕዝብ ይኖርባታል።

በከተማዋ ጥንታዊ ጎዳናዎች ላይ ስትጓዝ፣ ፕሎቭዲፍ ቀደም ባሉት ዘመናት ክብር የተጎናጸፈች ሆኖም ያልተረጋጋች ከተማ እንደነበረች የሚጠቁሙ በርካታ ማስረጃዎችን መመልከት ትችላለህ። ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበሩት ዘመናት የኖሩትና በሌሎች ዘንድ በጣም የሚፈሩት የትሬስ ሰዎች የገነቧቸውን ግዙፍ ሕንፃዎች ጨምሮ ግሪካውያን ያቆሟቸውን ዓምዶች፣ የሮማውያንን የቲያትር ማሳያ ስፍራዎች እንዲሁም ቱርኮች የሠሯቸውን የመስጊድ ማማዎች በከተማዋ ውስጥ ማየት ይቻላል።

‘ከሁሉ ይልቅ ውብ የሆነች ከተማ’

በከተማዋ ውስጥም ሆነ በአካባቢዋ በተደረገው የአርኪኦሎጂ ጥናት የተገኙት ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት በዚህች ከተማ ሰዎች መኖር የጀመሩት ከ1000 ዓ.ዓ. በፊት ነው። የአሁኗ ፕሎቭዲፍ በምትገኝበት ቦታ ላይ የትሬስ ሰዎች የቆረቆሯት ዩሞልፒያስ የተባለች የተመሸገች ከተማ ከአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በፊት ትገኝ እንደነበር አሚአኑስ ማርሴሊኑስ የተባለው ሮማዊ የታሪክ ምሑር ጽፏል። የታላቁ እስክንድር አባት የሆነው የመቄዶንያው ዳግማዊ ፊሊፕ፣ በ342 ዓ.ዓ. ዩሞልፒያስን ድል አደረጋት። ከዚያም ፊሊፕ የከተማዋን ስም ቀይሮ ፊሊፖፖሊስ በማለት ሰየማት።

ሮማውያን በ46 ዓ.ም. ከተማዋን ሲቆጣጠሩ ትሪሞንቲየም በማለት የሰየሟት ሲሆን የትሬስ ዋና ከተማ አደረጓት። በባልካን አካባቢ የሚገኘው ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ቪያ ዲያጎናሊስ የተባለ ጎዳና ከተማዋን አቋርጦ ያልፍ ስለነበር ሮማውያን ትሪሞንቲየምን መልቀቅ አይፈልጉም ነበር። ሮማውያን በከተማዪቱ ውስጥ ስታዲየም፣ አምፊቲያትር (ከላይ የሚታየው) እና በርካታ የመታጠቢያ ቦታዎች እንዲሁም ተለይተው የሚታወቁባቸውን የተለያዩ ሕንፃዎች ገንብተዋል።

የሳሞሳታ ተወላጅ የሆነው ሉሸን፣ በሮዶፒ ተራሮች ግርጌ በሦስት ኮረብቶች መሃል ስለምትገኘው ስለዚህች ከተማ ተፈጥሯዊ ውበት ጽፏል። ( ገጽ 18 ላይ ያለውን “ሰባት ኮረብቶች ያሏት ከተማ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ከተማዋ የምትገኘው በመሪትሳ ወንዝ አቅራቢያ ሲሆን ለም የሆነው የትሬስ መስክ ከፊት ለፊቷ ተንጣሎ ይታያል። ሉሸን፣ ስለ ትሪሞንቲየም ሲጽፍ “ከሁሉ ይልቅ ታላቅና ውብ ከተማ” እንደነበረች ገልጿል።

የሮማውያንን መውደቅ ተከትሎ በመጣው የጨለማው ዘመን ተብሎ በሚጠራው ወቅት የስላቭ ሰዎች በትሪሞንቲየም ሰፍረው ነበር። በቀጣዮቹ ጥቂት መቶ ዓመታት ውስጥ በአራት የተለያዩ ጊዜያት ጦረኞች ከተማዋን ዘርፈዋታል። ከዚያም በ14ኛው መቶ ዘመን ከተማዋ በቱርኮች እጅ ስትወድቅ ፖለቲካዊ ለውጥ ተካሄደ። ቱርኮች ደግሞ ከተማዋን ፊሊቤ ብለው የጠሯት ሲሆን እስከ 1878 ድረስ በእነርሱ ቁጥጥር ሥር ቆይታለች። ዩማያ የተባለው መስጊድና ማማው እንዲሁም የጥላው ሰዓት ቱርኮች ከተማዋን ይገዙ የነበረበትን ዘመን የሚያስታውሱ ናቸው።

በ1878 ሩሲያ ቱርክን ስታሸንፍ የፊሊቤ ስም ወደ ፕሎቭዲፍ ተቀየረ። በ1892 ከተማዋ የንግድ ትርዒት ማስተናገዷ ኢኮኖሚዋ እንዲያድግ አድርጓል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፕሎቭዲፍ የቡልጋሪያ ዋና የንግድ ማዕከል ሆነች። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚዎች ለተወሰነ ጊዜ ከተማዋን ተቆጣጥረዋት የነበረ ቢሆንም በ1944 ሶቪየቶች ናዚዎችን አስወጧቸው። ከዚያም በ1989 የሶቪየት ሕብረት አገዛዝ ሲንኮታኮት ፕሎቭዲፍ ከዚህ ኃያል መንግሥት ነፃ ወጣች። ከፕሎቭዲፍ የቀድሞ ገዢዎች አንዳንዶቹ ቀና አመለካከት የነበራቸው ሊሆኑ ቢችሉም ሰብዓዊ ገዢዎች ሁሉ ሊያመልጡት የማይችሉት አለፍጽምና ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል።

በፕሎቭዲፍ ‘ምሥራቹ’ ተሰበከ

በ1938 ናብሉዳቴልና ኩላ (መጠበቂያ ግንብ) የተባለ ኮርፖሬሽን በፕሎቭዲፍ የተቋቋመ ሲሆን ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ በመንግሥት ተመዘገበ። ይህ ኮርፖሬሽን መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በማተም በቡልጋሪያ ያሰራጭ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች በኮሚኒስት አገዛዝ ተቃውሞ ቢደርስባቸውም ፍጹም የሆነ ሰማያዊ መንግሥት እንደሚመጣ የሚገልጸውን ምሥራች ለፕሎቭዲፍ ነዋሪዎች ከመስበክ ወደኋላ አላሉም። (ማቴዎስ 24:14) አንዳንድ ሰዎችም ለመልእክቱ በጎ ምላሽ መስጠት ጀመሩ። በአሁኑ ጊዜ በፕሎቭዲፍ ከይሖዋ ጎን እንደሚቆሙ ያሳዩ ከ200 የሚበልጡ ሰዎች የሚገኙ ሲሆን በሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ታቅፈዋል።

ከእነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ የቡልጋሪያ ዜጎች ናቸው። ያም ሆኖ ባለፉት ዘመናት በዚህች ከተማ የተለያዩ አገራት ዜጎች የኖሩ እንደመሆኑ መጠን በፕሎቭዲፍ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል በርካታ የሌላ አገር ዜጎችም ይገኛሉ። የሞልዶቪያ፣ የብሪታንያ፣ የአሜሪካ፣ የካናዳ፣ የጣሊያንና የፖላንድ ዜጎች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች በፕሎቭዲፍ ይኖራሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ወደፊት ፍጹም በሆነ አገዛዝ ሥር የመኖር ተስፋ እንዳለን በኅብረት ሆነው ለሰዎች ይናገራሉ። ይህ ተስፋ እውን በሚሆንበት ወቅት የፕሎቭዲፍ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች በሙሉ ደኅንነታቸው ተጠብቆ ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፤ የሚያስፈራቸው አይኖርም።”—ሚክያስ 4:4

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

“ሰባት ኮረብቶች ያሏት ከተማ”

  በዛሬው ጊዜ ፕሎቭዲፍን የሚጎበኝ ሰው ታዋቂ የሆኑትን የከተማዋን ሰባት ኮረብቶች ወይም በአገሬው አጠራር ቴፔዎች ማግኘት ያስቸግረው ይሆናል። ማርኮቮ ቴፔ የተባለው ኮረብታ ከተማዋን ለማስፋት ሲባል ከመቶ ዓመት በፊት እንዲናድ ተደርጓል። ስድስቱ ኮረብቶች ግን ለፕሎቭዲፍ ጥንታዊ ታሪክ ድምፅ አልባ ምሥክሮች ሆነው አሁንም ድረስ ይታያሉ።

ሦስቱን ኮረብቶች በቀላሉ መለየት ይቻላል፤ እነዚህም ቡናርጂክ ቴፔ፣ ጄንዴም ቴፔ እንዲሁም ሳሃት ቴፔ ናቸው። ሳሃት ቴፔ ይህ ስያሜ የተሰጠው ቱርኮች በዚህ ኮረብታ ላይ የሰዓት ማማ ስለሠሩ ነው። ሮማውያን ትሪሞንቲየም ብለው በጠሯት በፕሎቭዲፍ ውስጥ ሌሎቹ ሦስት ኮረብቶችም ይገኛሉ። እነዚህም፦ ከፍታው ከሁሉም የሚበልጠውና ትልቅ የሆነው ጃምባዝ ቴፔ፣ ታክሲም ቴፔ እንዲሁም በቱርክ ቋንቋ “መጠበቂያ ኮረብታ” የሚል ትርጉም ያለው ኔቤት ቴፔ ናቸው።

በትሪሞንቲየም ውስጥ የሚጓዝ ሰው፣ የፊሊፖፖሊስን ጥንታዊ ፍርስራሾችና ግንቦችም ሆነ አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የሮማውያን ቲያትር ቤት የሚገኙበትን የፕሎቭዲፍ ጥንታዊ አካባቢ መመልከት ይችላል። በድንጋይ ንጣፍ በተሠሩት ጠባብ ጎዳናዎች ዳርና ዳር የሚገኙት በቡልጋሪያ ብሔራዊ የተሃድሶ ዘመን የተገነቡት በጥሩ ሁኔታ ተጠብቀው የቆዩ ቤቶችም የጎብኚዎችን ትኩረት የሚስቡ ናቸው።

[ምንጭ]

© Caro/Andreas Bastian

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቡልጋሪያ

ሶፊያ

ፕሎቭዲፍ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ፦ © Wojtek Buss/age fotostock; ከታች፦ David Ewing/Insadco Photography/age fotostock