ለመንፈስ ጭንቀት ምን ዓይነት ሕክምና ማግኘት ይቻላል?
ለብዙ ዓመታት በመንፈስ ጭንቀት የተሠቃየችው ሩት እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ባደረግነው ጥረት የሕክምና እርዳታ አገኘሁ፤ የአኗኗር ለውጥ አደረኩ፤ እንዲሁም ከአቅሜ በላይ ባልሆኑ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች የመካፈል ልማድ አዳበርኩ። አሁን ውጤታማ ሕክምና ያገኘን ይመስላል፤ ምክንያቱም ጤንነቴ እየተሻሻለ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ብዙም የማይረዱኝ ወቅት አለ፤ በዚህ ጊዜ ባለቤቴና ጓደኞቼ ያለመታከት የሚያሳዩኝ ፍቅር ተስፋ እንዳልቆርጥ ይረዳኛል።”
የሩት ተሞክሮ እንደሚያመለክተው በከባድ የመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃዩ ሰዎች መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉ የሕክምና ዓይነቶችን ማግኘት ጨምሮ ማንኛውም ድጋፍ ሊደረግላቸው ያስፈልጋል። የመንፈስ ጭንቀት ችላ ከተባለ ውጤቱ አደገኛ ይሆናል፤ ምክንያቱም የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ሕክምና ካላገኙ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ‘በሽተኞች ሐኪም ያስፈልጋቸዋል’ ብሎ መናገሩ የሕክምና ሙያ ያላቸው ሰዎች አስፈላጊውን እርዳታ ሊሰጡ እንደሚችሉ ይጠቁማል። (ማርቆስ 2:17) ይህ ሁኔታ ሐኪሞች የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸውን የብዙ ሰዎች ሥቃይ ሊያስታግሱ እንደሚችሉ ያሳያል። *
አንዳንድ ጠቃሚ አማራጮች
የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸውን ሰዎች ሊረዱ የሚችሉ በርካታ ሕክምናዎች አሉ። እነዚህ ሕክምናዎች እንደ ሕመሙ ዓይነትና ክብደት ይለያያሉ። (በገጽ 5 ላይ የሚገኘውን “ምን ዓይነት የመንፈስ ጭንቀት ነው?” የሚለውን ) ብዙ ሰዎች ማንኛውንም ሐኪም ማማከራቸው ሊረዳቸው ይችላል፤ ይሁን እንጂ አንዳንዶች በመስኩ የሠለጠነ ሐኪም እርዳታ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ሐኪሙ ጭንቀት የሚያስታግሱ መድኃኒቶችን ሊያዝዝ ወይም ሌላ ዓይነት የሕክምና እርዳታ እንዲከታተሉ ሐሳብ ሊያቀርብ ይችላል። አንዳንድ ሰዎች፣ ከዕፅዋት የሚዘጋጁ መድኃኒቶችን በመውሰድ፣ አመጋገባቸውን በማስተካከል ወይም ቁጥጥር የሚደረግበት የአካል እንቅስቃሴ ፕሮግራም በመከታተል ጥሩ ውጤት አግኝተዋል።
ሊያጋጥሙ የሚችሉ የተለመዱ ነገሮች
1. በጥሩ ዓላማ የተነሳሱ ጓደኞች እምብዛም ወይም ምንም ዓይነት የሕክምና እውቀት ሳይኖራቸው የትኛውን የሕክምና ዘዴ ብትከታተል ወይም ብትተው እንደሚሻል ሊነግሩህ ይሞክሩ ይሆናል። እንዲሁም ከዕፅዋት የሚዘጋጁ መድኃኒቶችን ወይም በሐኪም የሚታዘዙ መድኃኒቶችን እንድትወስድ ወይም እንዳትወስድ አሊያም ምንም ነገር መውሰድ እንደሌለብህ ጠንከር ያለ አስተያየት ይሰነዝሩ ይሆናል።
የሚከተለውን አስብበት፦ ማንኛውንም ምክር ከመቀበልህ በፊት አስተማማኝ ከሆነ ምንጭ የመጣ መሆን አለመሆኑን አረጋግጥ። በኋላም ሁኔታውን አገናዝበህ መወሰን ያለብህ አንተ እንደሆንክ አትዘንጋ።
2. ተስፋ መቁረጥ አንድ ሕመምተኛ መድኃኒቱ ምንም ለውጥ እንዳላመጣለት ወይም አንዳንድ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳስከተለበት ተሰምቶት እየወሰደው ያለውን ሕክምና እንዲያቋርጥ ሊያደርገው ይችላል።
የሚከተለውን አስብበት፦ “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል፤ በብዙ አማካሪዎች ግን ይሳካል።” (ምሳሌ 15:22) ማንኛውም የሕክምና ዓይነት ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው በሐኪሙና በሕመምተኛው መካከል ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት ሲኖር ነው። በመሆኑም የሚያሳስብህን ነገር ወይም የሕመሙን ምልክቶች ለሐኪምህ በግልጽ ንገረው፤ እንዲሁም የሕክምናውን ዓይነት መለወጥ ያስፈልግህ እንደሆነ አሊያም ለውጥ ለማየት የተወሰነ ጊዜ መጠበቅ ይኖርብህ እንደሆነ ጠይቀው።
3. ከመጠን በላይ በራስ መተማመን አንድ ሕመምተኛ እንደተሻለው ተሰምቶት ሕክምናውን በጥቂት ሳምንታት
ውስጥ በድንገት እንዲያቆም ሊያደርገው ይችላል። ሕክምናውን ከመጀመሩ በፊት በምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንደነበረ ሊረሳ ይችላል።የሚከተለውን አስብበት፦ ሐኪም ሳያማክሩ አንድን ሕክምና በድንገት ማቋረጥ ሕመሙን ሊያባብስ እንዲሁም ሕይወትን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መማሪያ መጽሐፍ ባይሆንም የመጽሐፉ ምንጭ ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። የሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት የአምላክ ቃል በመንፈስ ጭንቀት ለሚሠቃዩ ሰዎችም ሆነ ለተንከባካቢዎቻቸው የሚሆን ምን ማጽናኛና መመሪያ እንደያዘ ያብራራል።
^ አን.3 ንቁ! ይህ ሕክምና ይሻላል የሚል ሐሳብ አይሰጥም። እያንዳንዱ ግለሰብ የግል ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ያሉትን አማራጮች በጥንቃቄ መመዘን ይኖርበታል።