በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሪክሾ ፈላጊ!

ሪክሾ ፈላጊ!

ሪክሾ ፈላጊ!

የባንግላዴሽን ዋና ከተማ ዳካን የሚጎበኝ አንድ ሰው ወዲያውኑ አንድ የተለየ ነገር ይመለከታል። በሚርመሰመሰው ሕዝብ መካከል ብዙ ቁጥር ያላቸው ሪክሾዎች ይታያሉ! ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሪክሾዎች፣ ሰዎችንና ሸቀጦችን ጭነው በጎዳናዎችና በጠባብ መተላለፊያ መንገዶች ላይ ይነጉዳሉ።

ሪክሾ አሁንም ድረስ በዳካ ብዙዎች የሚጠቀሙበት የመጓጓዣ ዘዴ ነው። በመዝገብ የሰፈሩት ሪክሾዎች ቁጥር 80,000 ገደማ ሆኖ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች በየዕለቱ በመንገድ ላይ የሚታዩት ሪክሾዎች ቁጥር ግን ከዚህ በእጅጉ እንደሚበልጥ ይሰማቸዋል። እንዲያውም ዳካ፣ ‘የዓለም ሪክሾዎች ዋና ከተማ’ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷታል።

የቀድሞዎቹ ሪክሾዎች

የተንቀሳቃሽ ወንበሮች የቀድሞ ሞዴሎች ጥቅም ላይ የዋሉት በፈረንሳዩ ንጉሥ ሉዊ 14ኛ የግዛት ዘመን (1638-1715) ቢሆንም የመጀመሪያውን በሰው የሚጎተት ሪክሾ የፈለሰፈው በ1870ዎቹ በጃፓን ይኖር የነበረ ጆናታን ጋብል የተባለ አንድ አሜሪካዊ ሚስዮናዊ እንደሆነ ይገመታል። ይህን አዲስ ዓይነት መጓጓዣ የሠራው አቅመ ደካማ ለነበረችው ሚስቱ እንደሆነ ይነገራል፤ ይህ መጓጓዣ በጃፓንኛ ቋንቋ ጂንሪክሻ ተብሎ የተጠራ ሲሆን ቃሉ በሰው የሚጎተት ተሽከርካሪ ማለት ነው። በመጨረሻ ይህ ቃል በእንግሊዝኛ “ሪክሾ” ተባለ። ከጊዜ በኋላ በመላው እስያ የተለያዩ የሪክሾ ዓይነቶች እየተበራከቱ የመጡ ሲሆን ለመሳፈሪያ የሚከፈለው ዋጋም ውድ አልነበረም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) የሚያከናውኑትን ሥራ በቅንዓት ይመራ የነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል (ከታች) በ1912 ጃፓንን በጎበኘበት ወቅት እሱም ሆነ ከእሱ ጋር የመጡት ልዑካን በአገሪቱ ውስጥ ለመዘዋወር የተጠቀሙት በሪክሾ ነበር።

ሦስት ጎማ ያላቸው ሪክሾዎች በዳካ መታየት የጀመሩት በ1930ዎቹ መገባደጃ አካባቢ ነበር። ከተሽከርካሪው አካል ጋር የተያያዙ ሁለት እንጨቶችን በመጎተት ሰው ከሚነዳው ሪክሾ በተለየ እነዚህኞቹ ሪክሾዎች ሦስት ጎማ ያለው ትልቅ ብስክሌት ይመስላሉ። የሪክሾው ነጂ የብስክሌቱን ፊተኛ ፔዳል በእግሩ እየመታ ይነዳል። በዚህ መንገድ ተሽከርካሪ በበዛበትና በሰው በተጨናነቀ መንገድ ላይ ተሳፋሪዎቹን ወይም ጭነቱን በቀላሉ ራቅ ወዳለ ቦታ ማድረስ ይችላል።

ያጌጡ ሪክሾዎች

በዳካ የሚገኙ ሪክሾዎች ሙሉ በሙሉ በሥዕል የተሸፈኑ ናቸው ማለት ይቻላል። ሪክሾዎችን የማስዋብ ባሕል የመጣው ከየት ነው? ሪክሾዎች በዳካ ብቅ ባሉበት ጊዜ፣ ተሳፋሪዎችን እንዲሁም ዕቃዎችን ከሚያጓጉዙት ቶምቶም የሚባሉ በፈረስ የሚጎተቱ ጋሪዎች ጋር ገበያ መሻማት ነበረባቸው። የሪክሾ ባለቤቶች፣ ሰዎች አዲሱን መጓጓዣ እንዲጠቀሙ ለመማረክ ሳይሆን አይቀርም ሪክሾዎቻቸውን ማሳመር ጀመሩ። በሪክሾዎቹ ላይ የሚታዩት የቀለም ቅቦችና ማስታወቂያዎች የኋላ ኋላ ወደ ልዩ ኪነ ጥበብ ተለወጡ።

ሪክሾ ላይ የሚታየው ኪነ ጥበብ በጣም አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ በተሽከርካሪ ላይ ያለ ኪነ ጥበብ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። እንዲያውም የባንግላዴሽ የኪነ ጥበብ ሐያሲ የሆኑት ሳይድ ማንዙሩል ኢዝላም፣ በዳካ ያሉትን ሪክሾዎች “ተንቀሳቃሽ የሥዕል ኤግዚቢሽን” በማለት ገልጸዋቸዋል። የተሽከርካሪው ክፍል አንድም ሳይቀር በተለያዩ ንድፎች፣ ሥዕሎችና ቀለማት ያሸበረቀ ነው። በሪክሾው ጎንና ጎን ወይም ሸራው ላይ ዘርፍ ይደረግበታል፤ እንዲሁም ብልጭልጭ ነገሮችና የሚያብረቀርቁ ዶቃዎች ይንጠለጠሉበታል።

ሠዓሊዎቹ የየራሳቸው አሠራርና የሚወዱት ርዕስ አላቸው። አንዳንዶቹ ሥዕሎች፣ ከሕንድና ከባንግላዴሽ የድሮና የአሁን ፊልሞች ላይ የተወሰዱ ስለሆኑ ማስታወቂያዎች ይመስላሉ። ሌሎች ሥዕሎች ደግሞ የገጠሩን ሕይወትና መልክዓ ምድሩን የሚያስታውሱ፣ አንዳንድ ጊዜም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የሚያንጸባርቁ ሊሆኑ ይችላሉ። እንስሳትን፣ ወፎችን፣ አደንንና ለምለሙን ገጠራማ አካባቢ በሥዕል መግለጽም የተለመደ ነው።

በ1950ዎቹ የነበሩት የሪክሾ ሠዓሊዎች በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ። በዛሬው ጊዜ በዚህ ልዩ የኪነ ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ ባለሙያዎች አሉ። ሪክሾዎቹ የሚገጣጠሙት ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች ተብሎ በተዘጋጀ መገጣጠሚያ ቦታ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የሪክሾው የተለያዩ ክፍሎች የሚሠሩት ለሌላ አገልግሎት ውለው ከነበሩ ቁሳቁሶች ነው። ለምሳሌ ያህል ሠዓሊው የምግብ ዘይት ይዞ ከነበረ ቆርቆሮ ወይም ከሌላ የተጣለ ዕቃ ላይ ቆርጦ ይወስድና በዘይት ቀለም በጣም የሚያምር ሥዕል ይስልበታል። በሪክሾ ላይ የሚታየው የሥዕል ሥራ የባንግላዴሽ ባሕላዊ ኪነ ጥበብ ነው። የራሱ የሆነ የሚማርክ ውበት አለው።

የሪክሾ ነጂ

ሪክሾ የሚነዳ ሰው ሕይወት በጣም አድካሚ መሆኑን መረዳት ከባድ አይደለም። እስቲ አስበው፣ ሰዎችንም ይሁን ዕቃዎችን ወይም ማንኛውንም ዓይነት ከባድ ጭነት ይዘህ ቀኑን ሙሉ ሪክሾ እየነዳህ ብታሳልፍ ምን ያህል አድካሚ ሊሆን ይችላል? ተሳፋሪዎቹ የቤት እመቤቶች፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴዎች ወይም ዕቃ የተሸከሙ ገበያተኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ በአንድ ሪክሾ ላይ ሁለት፣ ሦስት፣ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ተጣበው ይቀመጣሉ። አንድ ነጋዴ ሊሸጥ ወደ ገበያ የሚወስዳቸውን እንደ ሩዝ፣ ድንች፣ ሽንኩርት፣ ወይም ቅመማ ቅመም ያሉ ነገሮችን ለማጓጓዝም በሪክሾ ሊጠቀም ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ተሳፋሪው ባስጫነው ዕቃ ላይ ተቀምጦ ይጓዛል። ዳር ቆሞ ለሚመለከት ሰው ሪክሾ ነጂው እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ጭነት እየጎተተ መሄድ የሚችል አይመስልም። ሆኖም ትሑት የሆነው የሪክሾ ነጂ በንዳዱ ፀሐይ ወይም በክረምቱ ዝናብ ምንም ሳያጉረመርም ተግቶ ይሠራል።

አብዛኞቹ የሪክሾ ነጂዎች የመጡት በድህነት ከተጠቁ የገጠር አካባቢዎች ነው፤ በእነዚህ አካባቢዎች በግብርና ሥራ የሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር በቂ አይደለም። ብዙዎቹ ጥሩ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ለማግኘት ስለሚቸገሩ ቤተሰቦቻቸውን ጥለው የሪክሾ ነጂ ለመሆን ወደ ከተሞች ይሄዳሉ። በዚያም ጉልበታቸውንና ኃይላቸውን ሁሉ ተጠቅመው በየቀኑ ጥቂት ገንዘብ ያገኛሉ።

ልዩ የመጓጓዣ ዘዴ

የመሬቱ አቀማመጥ ሜዳማ በሆነባት እንዲሁም ሌላ ዓይነት መጓጓዣ ለመጠቀም የማይመቹ ጠባብ መተላለፊያዎችና መንገዶች በሚበዙባት በዳካ፣ ሪክሾዎች አሁንም ሰፊ አገልግሎት ይሰጣሉ። ብዙ ሰዎች፣ ብክለት የማያስከትለው ይህ የመጓጓዣ ዘዴ ጠቃሚ እንደሆነ ብቻ ሳይሆን አስደሳች እንደሆነ ጭምር ይናገራሉ።

በአብዛኞቹ የእስያ ከተሞች ሪክሾዎች እንደቀድሞው በብዛት አይገኙም። በእነዚህ ከተሞች ውስጥ ብዙ ሕዝብ በሚጭኑ መጓጓዣዎች የመጠቀም ፍላጎት መጨመሩና የአኗኗር ዘይቤው እየተለወጠ መሄዱ ሪክሾ ዘመን ያለፈበት የመጓጓዣ ዘዴ እንዲሆን አድርጎታል። ብዙ ሰዎች ሪክሾዎችን ዘመን እንዳለፈባቸው አድርገው ቢመለከቷቸውም የተሻሻለ ንድፍ እንዲኖራቸው በማድረግ እነዚህ ተሽከርካሪዎች እንዳይጠፉ ጥረት እየተደረገ ነው።

ዳካ ውስጥ ስትዘዋወር ከብዙ ዓይነት የሕዝብ መጓጓዣዎች መካከል ማለትም ከአውቶቡስ፣ ከታክሲ፣ ከሞተር ብስክሌት፣ በሞተር ከሚሠራ ሪክሾና በቀለማት ካሸበረቀ የብስክሌት ሪክሾ መካከል አንዱን ልትመርጥ ትችላለህ። ይሁን እንጂ በሕዝብ በተጨናነቁት የዳካ ጎዳናዎች ላይ በብስክሌት ሪክሾ የምታደርገውን ረጋ ያለ ጉዞ ፈጽሞ አትረሳውም!

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ባለ ሙሉ ገጽ ሥዕል]