በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተበኬ—ከእንጨት የሚሠራ መዋቢያ

ተበኬ—ከእንጨት የሚሠራ መዋቢያ

ተበኬ—ከእንጨት የሚሠራ መዋቢያ

ደረቅ በሆነው የደቡባዊ ምዕራብ ማዳጋስካር ክልል ሴቶች ለቱሪስቶች የሚሸጥ ዛጎል ለመፈለግ የባሕር ዳርቻውን ያስሳሉ። ሴቶቹ ፊታቸውን ተበኬ የሚባል ነጭ ነገር ተቀብተዋል። ፊታቸው ላይ የሚቀቡት ይህ ነገር የተለያየ ጥቅም አለው፤ ኃይለኛ የሆነው የፀሐይ ጨረር ቆዳቸውን እንዳይጎዳው ለመከላከል ብቻ ሳይሆን እንደ መዋቢያም ሆኖ ያገለግላል።

ተበኬ የሚዘጋጀው ማሱንዡአኒ እና ፍሃሚ (ኤቪያቪ ተብሎም ይጠራል) ከሚባሉት ዛፎች ውስጠኛ ክፍል ነው። አዘገጃጀቱም ቀላል ነው፦ አንዲት ሴት ከቅርፊቱ ቀጥሎ ያለውን የዛፉን ክፍል በመውሰድ በጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ ከፈገፈገችው በኋላ በእንጨቱ ፍቅፋቂ ላይ ቀስ በቀስ ትንሽ ውኃ ጠብ እያደረገች ትለውሰዋለች። ከዚያም ክብ ወይም ቀጭን ጫፍ ባለው የእንጨት ቁራጭ አሊያም ፕላስቲክ ተጠቅማ ያዘጋጀችውን ውህድ እያጠቀሰች ፊቷን ታስጌጠዋለች።

አንዳንድ ሴቶች ዓይናቸው ብቻ ሲቀር ሙሉ ፊታቸውን ተበኬ ይቀባሉ። ሌሎች ደግሞ ግምባራቸውን፣ ጉንጫቸውን ወይም አገጫቸውን ብቻ መቀባት ይመርጣሉ። ተበኬ በፊት ላይ የሚገኝን እንከን ለመደበቅ ወይም ፊት ላይ ወዝ እንዳይኖር ለማድረግ አሊያም ለመዋቢያነት ሊያገለግል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ተበኬ ውስጥ ሌሎች ነገሮችንም በመደባለቅ ውህዱ የተለያየ ዓይነት ቀለምና ውፍረት እንዲኖረው ማድረግ እንዲሁም በፊት ላይ የተለያየ ቅርጽ መሥራት ይቻላል።

ለመዋቢያ የሚሆን ነገር ከእንጨት ይገኛል ብሎ ማን ያስባል? በፓሪስ እና በኒው ዮርክ ከሚገኙት የፋሽን ማዕከላት ርቃ በምትገኘው በማዳጋስካር፣ ተበኬ ያልተለመደ ሆኖም ጠቃሚ መዋቢያ ሆኖ ያገለግላል።