በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አደጋ በማያስከትል መንገድ ማሽከርከር የምትችለው እንዴት ነው?

አደጋ በማያስከትል መንገድ ማሽከርከር የምትችለው እንዴት ነው?

አደጋ በማያስከትል መንገድ ማሽከርከር የምትችለው እንዴት ነው?

መኪና ማሽከርከር፣ በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ መሠረታዊ ነገር ተደርጎ ቢታይም ይህ ነው የማይባል ኪሣራ እያስከተለ ነው። በመላው ዓለም በየዓመቱ ከ1,200,000 የሚበልጡ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ይገመታል! በመሆኑም አደጋ በማያስከትል መንገድ ማሽከርከር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ማወቃችን ጠቃሚ አይሆንም? እስቲ ልንወስዳቸው የምንችላቸውን አንዳንድ ተግባራዊ እርምጃዎች እንመልከት።

ራስህን ፈትሽ

አውስትራሊያን ጆርናል ኦቭ ሶሻል ኢሹስ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ዘገባ እንደገለጸው አንድ አሽከርካሪ በሕይወት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ሊወስዳቸው ከሚችላቸው በጣም አስፈላጊ እርምጃዎች አንዱ በሚያሽከረክርበት ጊዜ የሚያሳየውን ባሕርይ ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ነው። ስለዚህ አንድ አሽከርካሪ መኪና ለመንዳት ከመነሳቱ በፊት ‘ለማሽከርከር በሚያስችለኝ ተገቢ ሁኔታና ስሜት ላይ እገኛለሁ?’ ብሎ ራሱን መጠየቁ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማው ይሆናል። ድካም የአንድ ሰው አእምሮ እንዲፈዝና ፈጣን ምላሽ እንዳይሰጥ ሊያደርግ ይችላል። የፊሊፒንስ የየብስ መጓጓዣ ቢሮ እንደተናገረው ከሆነ እንደ ንዴት፣ ጭንቀት፣ እና ከመጠን በላይ እንደ መደሰት ያሉ ስሜቶች በአንድ ሰው የመኪና ማሽከርከር ልማድ ላይ ችግር ሊያስከትሉ እንዲሁም አሽከርካሪው ጥበብ የጎደለው እርምጃ እንዲወስድ ሊያደርጉት አልፎ ተርፎም በግልፍተኝነት ከሌሎች ጋር እስከ መጋጨት ሊያደርሱት ይችላሉ።

የአንድ ሰው አካላዊ ሁኔታም ከግምት መግባት አለበት፤ ምክንያቱም አንዳንድ የሕመም ዓይነቶችና በሰውነት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች አንድ ሰው አደጋ በማያስከትል ሁኔታ እንዳያሽከረክር እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። የአልኮል መጠጥ በአንድ ሰው የማሽከርከር ችሎታ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል ለሌሎች ሕይወት አክብሮት ያለው አሽከርካሪ የአልኮል መጠጥ ከወሰደ ለመንዳት አይዳፈርም። አንዳንድ መድኃኒቶችም በአሽከርካሪው የማመዛዘን ችሎታ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። አንድ አሽከርካሪ በእንደነዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ካለ ጉዞውን መሰረዙ ወይም ሌላ ሰው እንዲያሽከረክርለት ማድረጉ አስተዋይነት ሊሆን ይችላል።

ችሎታህን ፈትሽ

በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ የተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ እንደመሆኑ መጠን አዲስና ልምድ የሌላቸው አሽከርካሪዎች ቁጥርም እያደገ ነው። በመሆኑም ማንኛውም አሽከርካሪ አደጋን ለማስወገድ ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ሁለት ነገሮች መመልከታችን ጠቃሚ ነው።

ተጠንቅቀህ አሽከርክር! በንቃት አሽከርክር፤ ከፊት ለፊትህና ከበስተ ኋላህ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች ይኖሩ እንደሆነ በትኩረት ተከታተል፤ እንዲሁም የአሽከርካሪዎችን ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ጨምሮ የሌሎች መኪኖች እንቅስቃሴ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀድመህ ለመገመት ሞክር። አብዛኞቹ ግጭቶች በጣም ተቀራርቦ በማሽከርከር የሚከሰቱ በመሆናቸው ብልህ የሆነ አሽከርካሪ በእሱና በሌሎች መኪኖች መካከል ሊኖር የሚገባውን ተገቢ ርቀት ጠብቆ ያሽከረክራል።

ከእይታህ ውጭ የሆኑ ነገሮችን ለማስተዋልና ትኩረትህን የሚሰርቁ ነገሮችን ላለማድረግ ጣር። በመኪናህ መስታወቶች ላይ ብቻ ከመተማመን ይልቅ አንገትህን አዙረህ በዙሪያህ ያሉትን ነገሮች ቃኝ። በምታሽከረክርበት ጊዜ ትኩረት የሚሰርቁ ነገሮችን ላለማድረግ ተጠንቀቅ። ስልክ እንደ ማውራት ወይም ሌሎች የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎችን እንደ መነካካት ያሉ ነገሮች ትኩረት የሚሰርቁ በመሆናቸው መኪና እያሽከረከርክ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ደርበህ አትሥራ።

ሞተር ብስክሌት የምታሽከረክር ከሆነ፦ አንዳንድ ባለሥልጣናት እንደገለጹት የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪ በአደጋ ምክንያት የመሞቱ አጋጣሚ የመኪና አሽከርካሪ ከሚያጋጥመው ጋር ሲወዳደር በእያንዳንዱ ኪሎ ሜትር በ37 እጅ ይበልጣል። ታዲያ ራስህን ከአደጋ ለመጠበቅ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ? ከላይ የተገለጹት ሁለት እርምጃዎች ለሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎችም ይሠራሉ። በተጨማሪም በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የሞተር ብስክሌት ደህንነት ተቋም የሚከተሉትን ምክሮች ለግሷል፦ “ከሌሎች እይታ እንዳትሰወር ጥረት አድርግ።” ሌሎች ሊያዩህ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መሆን አለመሆንህን አረጋግጥ። በምታሽከረክርበት ጊዜ ሁሉ የፊት መብራትህን አብራው። ሌሎች አሽከርካሪዎች ሊያዩህ በማይችሉበት ቦታ ላይ እንዳትሆን ጥንቃቄ አድርግ። “የአደጋ መከላከያ ልብሶችን ልበስ።” የራስ ቁር አድርግ፤ እንዲሁም የሚያንጸባርቅ ቀለም ያለውና ከአደጋ መከላከል የሚችል ወፍራም ልብስ ልበስ። “ስታሽከረክር የተለየ ጥንቃቄ አድርግ።” ሌሎች ላያዩህ እንደሚችሉ በማሰብ ተጠንቅቀህ ንዳ።

ተሽከርካሪህን ፈትሽ

አንድ አሽከርካሪ፣ ያለበት ሁኔታ ለአደጋ የማያጋልጥ መሆኑን በንቃት መፈተሽ እንዳለበት ሁሉ የተሽከርካሪው ደህንነትም የተጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ፍሬኖቹ እና ከፍሬኖቹ ጋር የተያያዙ የመኪናው ክፍሎች በሙሉ በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆን አለባቸው። ጎማዎቹ በደረቅም ሆነ በሚያዳልጥ መንገድ ላይ በቀላሉ የሚንሸራተቱ እንዳይሆኑ ጥርሳቸው ያልተበላ መሆን ይኖርበታል። በቂ ነፋስ ያለው ጎማ አሽከርካሪው መኪናውን ለመቆጣጠርና ፍሬን ለመያዝ ቀላል እንዲሆንለት ያደርጋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኛዎቹ ተሽከርካሪዎች የጥንቃቄ ቀበቶዎች አሏቸው። ቀበቶዎቹን ካልተጠቀምክባቸው መኖራቸው በራሱ ምንም ፋይዳ የለውም።

በምታሽከረክርበት ጊዜ የመንገዱንና የአየሩን ሁኔታ ጨምሮ ሰዓቱን ግምት ውስጥ አስገባ። መንገዱ የሚያዳልጥ ከሆነ በተለይ ደግሞ በበረዶ ከተሸፈነ መኪናህን በቀላሉ ማቆም እንዲሁም መሪውን እንደ ልብ መቆጣጠር አስቸጋሪ እንዲሆንብህ ሊያደርግ ይችላል። ማታ ላይ በምትነዳበት ጊዜ የፊት መብራቶቹ በጥሩ ሁኔታ የሚሠሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ብሎም ፍጥነትህን መቀነስ ይኖርብሃል። ሕይወት ከአምላክ የተገኘ ስጦታ እንደመሆኑ መጠን አደጋ በማያስከትል መንገድ ማሽከርከር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ መማርን ጨምሮ ሕይወታችንን ከአደጋ ለመጠበቅ የቻልነውን ሁሉ ማድረጋችን የተገባ ነው።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በቁጠባ ማሽከርከር

ወጥ በሆነ ፍጥነት አሽከርክር፦ ሳያስፈልግ አሁንም አሁንም ማርሽ መቀያየርና ቶሎ ቶሎ ፍሬን መያዝ ነዳጅ ያባክናል።

መኪናው በሚኒሞ እንዲሠራ አታድርግ፦ በጥቅሉ ሲታይ በዛሬው ጊዜ የሚመረቱ መኪኖች ከመነዳታቸው በፊት መሞቅ አያስፈልጋቸውም። መኪናው ከግማሽ ደቂቃ በላይ ቆሞ የሚቆይ ከሆነ ሞተሩን አጥፋው።

ጎማው ሁልጊዜ በቂ ነፋስ እንዲኖረው አድርግ፦ ጎማዎቹ በበቂ መጠን ነፋስ ከተሞሉ በቀላሉ መሽከርከር ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ የነዳጅ ፍጆታን በእጅጉ ይቀንሳል።

ስታሽከረክር በጣም አትፍጠን፦ በከፍተኛ ፍጥነት ማሽከርከር ለአደጋ ሊዳርግ ብሎም ተጨማሪ ነዳጅ ሊበላ ይችላል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

❏ በንቃት አሽከርክር

❏ የጥንቃቄ ቀበቶህን እሰር

❏ መኪና እየነዳህ ሌላ ነገር ደርበህ አትሥራ

❏ ትኩረት የሚከፋፍሉ ነገሮችን አታድርግ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

❏ ከእይታህ ውጭ የሆኑ ነገሮችን ለማስተዋል ጣር

❏ ፍሬኖቹ በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን አረጋግጥ

❏ ጎማው በቂ ነፋስ እንዲኖረው አድርግ

❏ የጎማዎቹ ጥርስ የተበላ አለመሆኑን አረጋግጥ

❏ በአንተና በሌሎች መኪኖች መካከል በቂ ርቀት እንዲኖር አድርግ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

❏ “የአደጋ መከላከያ ልብሶችን ልበስ”

❏ “ከሌሎች እይታ እንዳትሰወር ጥረት አድርግ”

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

❏ የፊት መብራቶቹ በሚገባ መሥራታቸውን አረጋግጥ