በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቀሳውስትና ምእመናን የሚል ልዩነት ሊኖር ይገባል?

ቀሳውስትና ምእመናን የሚል ልዩነት ሊኖር ይገባል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ቀሳውስትና ምእመናን የሚል ልዩነት ሊኖር ይገባል?

ፓትሪያርክ፣ ሊቀ ጳጳሳት፣ አቡን፣ ብፁዕነታቸው፣ መሪ ጌታ፣ ጳጳስ፣ አባ፣ ረቢ፣ ፓስተር፣ መምህር። እነዚህ የማዕረግ ስሞች በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ ቀሳውስትን ከምእመናኑ የሚለዩ ስሞች ናቸው። በበርካታ ሃይማኖቶች ውስጥ ቀሳውስትና ምእመናን ተብሎ መለየቱ የተለመደ ነው፤ ይሁንና ይህ ሁኔታ አምላክ ያቋቋመው ሥርዓት ነው ወይስ የሰው ወግ ነው? ደግሞስ እንዲህ ዓይነት ልዩነት መኖሩ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለው?

“በአዲስ ኪዳን ውስጥም ሆነ በጥንቶቹ ሐዋርያት ዘመን፣ ቀሳውስት ወይም ምእመናን በሚል ልዩነት አልነበረም” በማለት የሃይማኖት ፕሮፌሰር የሆኑት ክሊተስ ዌሰል ተናግረዋል። ስለ ክርስትና የሚያብራራ አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ (ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ክሪስቺያኒቲ) እንዲህ ይላል፦ “በቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች ቀሳውስት፣ የተቀረውን ሕዝብ ደግሞ ምእመናን ብሎ መለየት ቀስ በቀስ እየተለመደ መጣ፤ . . . የቤተ ክርስቲያንን ‘ተራ’ አባላት [በመንፈሳዊ እውቀት] ብቃት እንደሌላቸው አድርጎ ማየት ተጀመረ።” እንዲህ ያለው ልዩነት በሦስተኛው መቶ ዘመን ማለትም ክርስቶስ ከሞተ ሁለት መቶ ዓመታት በላይ ቆይቶ በግልጽ የሚታይ ነገር ሆነ።

ቀሳውስትና ምእመናን የሚለው ልዩነት፣ የኢየሱስ ሐዋርያትና የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ የተከተለ አለመሆኑ ይህ ሥርዓት ስህተት ነው እንድንል ያደርገናል? በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ስህተት ነው። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

“ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ”

መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ክርስቲያኖች የአምላክ አገልጋዮች እንደሆኑና ማንኛቸውም ከሌላው በላይ ወይም በታች እንዳልሆኑ ይነግረናል። (2 ቆሮንቶስ 3:5, 6) በሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉት አሌክሳንድሬ ፌቭሬ፣ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በመካከላቸው የቀሳውስት ክፍልና ምእመናን የሚል “ልዩነት እንዳይፈጠር አጥብቀው ታግለዋል” በማለት ተናግረዋል። “ልዩነት እንዳይፈጠር” መታገላቸው ኢየሱስ “እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” ሲል ለተከታዮቹ ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል።—ማቴዎስ 23:8

እርግጥ ነው፣ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንዶች የበላይ ተመልካች ሆነው አገልግለዋል፤ ይህም እረኝነትንና ማስተማርን ይጨምር ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:28) ይሁንና እነዚህ ወንዶች ደሞዝ የሚከፈላቸው ቀሳውስት አልነበሩም። አብዛኞቹ በገዛ እጃቸው እየሠሩ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩ ተራ ሰዎች ነበሩ። ከዚህም በላይ የበላይ ተመልካች ሆነው ለማገልገል ብቃቱን ያገኙት ከሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ሳይሆን የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናትና አምላክ የሚፈልግባቸውን መንፈሳዊ ባሕርያት በማዳበር ነው። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው፦ “በልማዶቹ ልከኛ የሆነ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያለው፣ ሥርዓታማ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ለማስተማር ብቃት ያለው፣ . . . ምክንያታዊ የሆነ፣ የማይጣላ፣ ገንዘብ ወዳድ ያልሆነ፣ . . . የራሱን ቤተሰብ በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳድር።”—1 ጢሞቴዎስ 3:1-7

መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን በጥብቅ መከተል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “ከተጻፉት ነገሮች አትለፍ” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 4:6) ሰዎች ይህን የአምላክ መመሪያ ለመታዘዝ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ ብዙውን ጊዜ በመንፈሳዊ ችግር ያስከትላል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው የቀሳውስትና የምእመናን ልዩነት ለዚህ እንደ ማስረጃ ሊጠቀስ ይችላል። እንዴት? የሚከተሉትን ስድስት ነጥቦች ተመልከት።

1. የቀሳውስት ክፍል መኖሩ አንድ ሰው የአምላክ አገልጋይ ለመሆን አምላክ በተለየ መንገድ ሊመርጠው ይገባል የሚል አንድምታ አለው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች አምላክን ማገልገልና ስሙን ማወደስ እንዳለባቸው ይናገራል። (ሮም 10:9, 10) በጉባኤ ውስጥ ማገልገልን በተመለከተ ደግሞ ክርስቲያን ወንዶች በአጠቃላይ እንዲህ ያለው መብት ላይ ለመድረስ እንዲጣጣሩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል፤ የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉት ይህን ሥርዓት ነው።—1 ጢሞቴዎስ 3:1

2. በቀሳውስትና በምእመናን መካከል ልዩነት መደረጉ ከማዕረግ ስሞቻቸው ማየት እንደሚቻለው ለቀሳውስቱ የተለየ ክብር እንዲሰጥ ያደርጋል። ይሁንና ኢየሱስ “ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው” ብሏል። (ሉቃስ 9:48) ትሕትና ከሚንጸባረቅበት ከዚህ ሐሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ በሃይማኖታዊ የማዕረግ ስሞች መጠራት እንደሌለባቸውም ለተከታዮቹ ነግሯቸዋል።—ማቴዎስ 23:8-12

3. ደሞዝተኛ የሆኑ ቀሳውስት በተለይ የተንደላቀቀ ኑሮ የለመዱ ከሆኑ በገንዘብ ረገድ በምእመናኑ ላይ ከባድ ሸክም ሊጭኑባቸው ይችላሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ሰብዓዊ ሥራ በመሥራት በቁሳዊ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ራሳቸው ያሟላሉ፤ በዚህም ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። *የሐዋርያት ሥራ 18:1-3፤ 20:33, 34፤ 2 ተሰሎንቄ 3:7-10

4. አንድ ቄስ ቁሳዊ ፍላጎቶቹን የሚያሟሉለት ሌሎች ከሆኑ እነዚህን ሰዎች ላለማስከፋት ሲል የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እነሱ እንደሚፈልጉት አድርጎ ለማቅረብ ሊፈተን ይችላል። እንዲህ ያለው ሁኔታ እንደሚከሰት መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ ተናግሯል። “ጤናማውን ትምህርት የማይታገሡበት ጊዜ ይመጣል፤ ከዚህ ይልቅ ከራሳቸው ፍላጎት ጋር በሚስማማ ሁኔታ ጆሯቸውን እንዲኮረኩሩላቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ይሰበስባሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 4:3

5. በቀሳውስትና በምእመናን መካከል ልዩነት መኖሩ ምእመናኑ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ማከናወን የቀሳውስቱ ኃላፊነት እንደሆነና እነሱ በሳምንታዊ የስብከት ፕሮግራም ላይ ከተገኙ በቂ እንደሆነ እንዲሰማቸው ያደርጋል። ሆኖም ሁሉም ክርስቲያኖች መንፈሳዊነታቸውን ለመገንባት ጥረት ማድረግና ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሆን አለባቸው።—ማቴዎስ 4:4፤ 5:3

6. ምእመናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ከሌላቸው ቀሳውስቱ በቀላሉ ሊያታልሏቸው እንዲያውም መጠቀሚያ ሊያደርጓቸው ይችላሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንደተከሰተ የሚያሳዩ በርካታ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። *የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30

የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በጥብቅ መከተል ስለሚፈልጉ የቀሳውስት ክፍል የላቸውም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንጋ በፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ደሞዝ የማይከፈላቸው መንፈሳዊ እረኞችና አስተማሪዎች አላቸው። ይህ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ በአቅራቢያህ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመሰብሰቢያ አዳራሽ እንድትሄድ እናበረታታሃለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.13 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ አልፎ አልፎ “በምሥራቹ አማካኝነት በሚያገኙት ነገር [ኖረዋል]።” ይህንንም ያደረጉት ሌሎች በፈቃደኝነት ተነሳስተው የሚያደርጉላቸውን መስተንግዶና የገንዘብ መዋጮ በመቀበል ነው።—1 ቆሮንቶስ 9:14

^ አን.16 ኃጢአትን ለማስተሰረይ ገንዘብ ማስከፈልን፣ የካቶሊክ ፍርድ ቤትን (ኢንኩዊዚሽን)፣ አልፎ ተርፎም የአምላክ ቃል በመንጎቻቸው እጅ እንዳይገባ ለማድረግ የፈለጉ ቀሳውስት መጽሐፍ ቅዱሶችን ማቃጠላቸውን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።—የኅዳር 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 27 ተመልከት።

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች አንዳቸው ሌላውን እንዴት መመልከት ይገባቸዋል?—ማቴዎስ 23:8

▪ ክርስቲያን ወንዶች በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆነው ለማገልገል የትኞቹን ብቃቶች ማሟላት አለባቸው?—1 ጢሞቴዎስ 3:1-7

▪ ቀሳውስትና ምእመናን የሚል ልዩነት መኖሩ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ለምንድን ነው?—1 ቆሮንቶስ 4:6

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ቀሳውስት ካላቸው አመለካከት በተለየ ኢየሱስ ራሱን ከሌሎች “እንደሚያንስ” አድርጎ ቆጥሯል