በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በንቀት መታየት

በንቀት መታየት

በንቀት መታየት

“ስፔን ውስጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በገባሁበት በመጀመሪያው ዓመት ቁመቴ በክፍሌ ውስጥ ከነበሩት ልጆች በጣም ያጥር ስለነበር ልጆቹ ያፌዙብኝ ነበር። በየቀኑ ማለት ይቻላል ወደ ቤት የምመለሰው እያለቀስኩ ነበር።”—ጄኒፈር፣ የፊሊፒንስ ስደተኞች ልጅ

“ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ተቀይሬ ስሄድ ነጭ የቆዳ ቀለም ያላቸው ተማሪዎች በሚያዋርዱ ስሞች ይጠሩኝ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ከእነሱ ጋር እንድጣላ ለማድረግ እንደሆነ ባውቅም እንደምንም ብዬ ስሜቴን እቆጣጠረው ነበር። በውስጤ ግን በጣም እጎዳ የነበረ ከመሆኑም በላይ ተፈላጊ እንዳልሆንኩ ይሰማኝ ነበር።”—ቲሞቲ፣ ትውልደ አፍሪካ አሜሪካዊ

“የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ ኢግቦና ሃውሳ በሚባሉት በናይጄሪያ የሚኖሩ ሕዝቦች መካከል ግጭት ተፈጠረ። ጥላቻው በእኔም ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር፤ በክፍሌ ውስጥ ያለው የሃውሳ ጎሳ አባል የሆነ ልጅ ጓደኛዬ ቢሆንም እንኳ አሾፍበት ነበር።”—ጆን፣ የኢግቦ ጎሳ አባል

“እኔና የሚስዮናዊነት አገልግሎት ጓደኛዬ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሰዎች እያካፈልን ሳለ የአካባቢው ቄስ ያነሳሳቸው አንዳንድ ልጆች እየተከተሉ ድንጋይ ይወረውሩብን ጀመር። ቄሱ ከተማውን ለቀን እንድንሄድ ፈልጎ ነበር።”—ኦልጋ

ጭፍን ጥላቻ ላይ የተመሠረተ መድሎ ደርሶብህ ያውቃል? እንዲህ ያለው ክብርን ዝቅ የሚያደርግ ሁኔታ የደረሰብህ በቆዳ ቀለምህ፣ በሃይማኖትህ፣ በኑሮ ደረጃህ፣ በጾታህ ወይም በዕድሜህ ምክንያት ሊሆን ይችላል። በጭፍን ጥላቻ የተነሳ በደል የሚደርስባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሕይወታቸው ተመሳሳይ ነገር ይደርስብናል በሚል ስጋት የተሞላ ነው። ሰዎች በተሰበሰቡበት አካባቢ ሲያልፉ፣ ወደ ሱቅ ሲገቡ፣ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ሲቀየሩ ወይም ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች ሲገኙ በጭንቀት ሊዋጡ ይችላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የጭፍን ጥላቻና መድሎ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሥራ ለማግኘት ሊቸገሩ ወይም ጥሩ ሕክምና ላያገኙ እንዲሁም ጥራት ያለው ትምህርት እንዳይከታተሉ ሊደረጉና ሌሎች የሚያገኟቸውን ማኅበራዊና ሕጋዊ መብቶች ሊነፈጉ ይችላሉ። ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች የሚደረገውን መድሎ የሚደግፉት ከሆነ ደግሞ እንደ ዘር ማጥፋት የመሳሰሉትን የክፋት ድርጊቶች ወደ መፈጸም ሊመራ ይችላል። በጥንት ዘመን የዘር ማጥፋት ሙከራ ተደርጎ እንደነበረ የሚያሳይ ምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በአስቴር መጽሐፍ ላይ ይገኛል። ቂምና ጭፍን ጥላቻ ወደ ምን እንደመራ ተመልከት።—አስቴር 3:5, 6

መድሎን የሚቃወሙ ሕጎች ባሉባቸው አገሮች ውስጥም እንኳ ጠባብነትንና አለመቻቻልን ማስወገድ ሊያስቸግር ይችላል። የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር እንዲህ ብለዋል፦ “ዓለም አቀፋዊው የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ከወጣ ከስድስት አሥርተ ዓመታት በኋላም እንኳ . . . እኩልነት እንዲኖርና መድሎ እንዲወገድ ለማድረግ የወጡት ደንቦች ዛሬም ቢሆን በዓለም ዙሪያ ተፈጻሚነት አላገኙም።” ይህ በጣም የሚያሳዝን ነው፤ ምክንያቱም በዛሬው ጊዜ የሕዝብ ፍልሰትና የስደተኞች መጉረፍ በብዙ አገሮች ውስጥ የተለያየ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ተቀላቅለው እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

ታዲያ መድሎ የሌለበት ኅብረተሰብ እንዲያው ሕልም ብቻ ነው? ወይስ ጭፍን ጥላቻና መድሎ ሊወገድ ይችላል? የሚቀጥሉት ርዕሶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።