ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ “በአሁኑ ወቅት በሩሲያ ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ቶን የሚመዝን መርዛማ ቆሻሻ ይገኛል፤ ይህንን ለማስወገድ የሚያስችል ውጤታማ የሆነ መንገድ ደግሞ የለም።”—ሪአ ኖቮስቲ፣ ሩሲያ
▪ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የባሕር ላይ ዘራፊዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል። ለምሳሌ በ2007 “263 የባሕር ላይ ዘረፋዎችና የዝርፊያ ሙከራዎች ተፈጽመዋል።”—ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዩናይትድ ስቴትስ
በእርግዝና ወቅት የአልኮል መጠጥ መጠጣት
ጀርመን ውስጥ በየዓመቱ ከሚወለዱት ሕፃናት መካከል 10,000 ገደማ የሚሆኑት ከአልኮል መጠጥ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎች እንደሚኖሩባቸው ዙዶይቼ ፃይቱንግ ዘግቧል። ከእነዚህ ልጆች መካከል 4,000 ገደማ የሚሆኑት ከባድና ዘላቂ የሆነ የአካል ጉዳት ይደርስባቸዋል። የመድኃኒት ቁጥጥር ቢሮ ኮሚሽነር የሆኑት ዛቢኔ ቤትሲንግ እንዲህ በማለት አስጠንቅቀዋል፦ “በእርግዝና ወቅት ‘ይህን ያህል መጠን ያለው የአልኮል መጠጥ መጠጣት ምንም ችግር የለውም’ ብሎ መናገር አይቻልም። [ነፍሰ ጡር የሆነች አንዲት ሴት] አንድ ብርጭቆ የአልኮል መጠጥ አልፎ አልፎ መጠጣቷ እንኳ በልጁ ላይ አእምሯዊና አካላዊ ጉዳት ሊያደርስበት ወይም የባሕርይ ችግር ሊያስከትልበት እንደሚችል በመግለጽ ሐኪሞች፣ አዋላጅ ነርሶችና ነፍሰ ጡር ሴቶች ይህንን በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሰፉ ማድረግ አለብን።”
አትክልት መንከባከብ ለጤንነትህ ጥሩ ነው
“ተመራማሪዎች የምታሳልፈው ጊዜ ይብዛም ይነስም የምትመገባቸውን ምግቦች ራስህ ማብቀልህ ከሚታሰበው በላይ ለጤንነትህ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ደርሰውበታል” በማለት ሳይኮሎጂ ቱደይ ዘግቧል። አንድ ጥናት እንዳሳየው ከሆነ “በአፈር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ የማይክሮባክቴሪያ ዓይነቶች” በአፍ አሊያም በአፍንጫ በኩል ወደ ሰዎች ሰውነት በሚገቡበት ጊዜ “የሰዎቹ በሽታን የመከላከል አቅም በእጅጉ ከፍ ይላል።” በመሆኑም መጽሔቱ እንዲህ ብሏል፦ “በአፈር ላይ የሚበቅሉትን ምርጥ ፍራፍሬዎችና አትክልቶች መመገብ ለሰው ልጆች ጤንነት አስፈላጊ የሆነውን ያህል በአፈር ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮች መመገብም ጠቃሚ መሆኑ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ ይመስላል።”
ያለማቋረጥ በመብረር የተመዘገበ ሪኮርድ
በዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም (USGS) ውስጥ የሚገኙ የሳይንስ ሊቃውንት “በየብስ ላይ ከሚኖሩ ወፎች መካከል ያለማቋረጥ ረጅም ርቀት በመብረር ረገድ የተመዘገበውን ሪኮርድ” በተመለከተ ሪፖርት አውጥተዋል። ባር-ቴይልድ ጎድዊት የተባሉ በርካታ ወፎች በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ፓስፊክ ውቅያኖስን አቋርጠው ሲፈልሱ በሳተላይት ክትትል ተደርጎባቸው ነበር። ከእነሱም መካከል አንዲት ወፍ ከአላስካ ተነስታ እስከ ኒው ዚላንድ ይኸውም 11,650 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ርቀት ለስምንት ቀናት ያህል ያለማቋረጥ መብረር ችላለች። ወፏ ኒው ዚላንድ ስትደርስ “700 ግራም ከሚመዝነው የሰውነቷ ክብደት ውስጥ ግማሽ ያህሉን ተጠቅማበት ነበር” ሲል ዘ ዊክ መጽሔት ዘግቧል። ጎድዊት የተባሉት እነዚህ ወፎች ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱ ከኒው ዚላንድ ወደ ቻይና ከዚያም ወደ አላስካ የሚበሩ ሲሆን የደርሶ መልስ ጉዟቸው በአጠቃላይ 29,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ይሸፍናል። የዩናይትድ ስቴትስ የጂኦሎጂ ጥናት ተቋም እንዳለው ከሆነ “በየዓመቱ የሚያደርጉት ጉዞ በአማካይ 29,000 ኪሎ ሜትር ከሆነ አንድ ጎድዊት በሕይወት ዘመኑ 463,000 ኪሎ ሜትር ይበራል ማለት ነው።”
የቁልቋል ሌቦችን መያዝ
በአሪዞና፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ሰግዋሮ ብሔራዊ ፓርክ፣ አካባቢው ተለይቶ የሚታወቅባቸው አንዳንድ የቁልቋል ዝርያዎች በሌቦች እየተሰረቀበት ነው። የአሪዞና ግብርና ቢሮ የልዩ ምርመራ ዲፓርትመንት ባልደረባ የሆኑት ጂም ማጊነስ “ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ሰግዋሮ የሚባለው የቁልቋል ዝርያ በደጃፉ ላይ እንዲኖር ይፈልጋል” ብለዋል። በመሆኑም ቁልቋል የጫነ መኪና በበረሃው ውስጥ ሲጓዝ መመልከት የተለመደ ነው። ሌቦች በተለይ የሚያተኩሩት ከአንድ እስከ ሁለት ሜትር ርዝመት ባለው ቁልቋል ላይ ሲሆን ይህም አንድ ሺህ የአሜሪካ ዶላር ወይም ከዚያ በላይ ሊያወጣ ይችላል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ስርቆቱን ለመከላከል በቁልቋሎቹ ውስጥ ትንንሽ የሆኑ የኮምፒውተር ቺፖችን ለመቅበር አቅደዋል። ከዚያም በእጅ የሚያዙ ጠቋሚ መሣሪያዎችን በመጠቀም በችግኝ መሸጫ ቦታዎች ላይ የሚገኙ አሊያም ግቢን በማስዋብ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሰዎች የሚተክሏቸው ቁልቋሎች ከፓርኩ የተሰረቁ መሆን አለመሆናቸውን ማወቅ ይቻላል።