በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የኤስፕሬሶ አዘገጃጀት

የኤስፕሬሶ አዘገጃጀት

የኤስፕሬሶ አዘገጃጀት

በየዓመቱ በመቶ ቢሊዮን በሚቆጠሩ ስኒዎች ለተጠቃሚዎች የሚቀርበው ቡና በዓለም ላይ እጅግ ተወዳጅ ከሆኑት መጠጦች አንዱ ሆኗል።

ቡና አፍቃሪ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች “ግሩም ቡና” የሚሉት በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀ ኤስፕሬሶን እንደሆነ ሳይንቲፊክ አሜሪካን የተሰኘው መጽሔት ይገልጻል። “ይህም የሆነው ልዩ የሆነው የኤስፕሬሶ አዘገጃጀት የቡናው ጣዕም ገንኖ እንዲወጣ ስለሚያደርገው ነው።” ኤስፕሬሶ የሚዘጋጀው በሚገባ በተፈጨ ቡና ውስጥ እንፋሎት ወይም የፈላ ውኃ በኃይለኛ ግፊት እንዲያልፍ በማድረግ ነው።

የቡና አዘገጃጀት ባለሞያ የሆነ አንድ ግለሰብ ለንቁ! መጽሔት እንደተናገረው “ሰዎች በካፊቴሪያዎች ውስጥ የሚዘጋጀውን ኤስፕሬሶ ስለሚወዱት ቤታቸውም ይህንኑ ዓይነት ቡና ማዘጋጀት ይፈልጋሉ።” በአሁኑ ጊዜ በቤት ውስጥ ኤስፕሬሶ ማዘጋጀት የሚቻልባቸው ማሽኖች ስላሉ ሰዎች ይህን ማድረግ ችለዋል። በዚህም ምክንያት በቤት ውስጥ የሚዘጋጀው ኤስፕሬሶ ፍጆታ በአንዳንድ አገሮች በፍጥነት እየጨመረ ነው።

ቡና ትወዳለህ? ከባድ የሆነውን የኤስፕሬሶ አዘገጃጀት በደንብ ማወቅ ትፈልጋለህ? ግሩም ኤስፕሬሶ ማዘጋጀት የሚቻለው እንዴት ነው? ንቁ! ቡና በመቁላት ባለሞያ ለሆኑትና በሲድኒ፣ አውስትራሊያ ለሚኖሩት ለጆንና ለአባቱ ለጄራርዶ ይህን ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር።

በትክክለኛው መጠን መቀላቀል

በጆንና በጄራርዶ ቡና መቁያ ፋብሪካ ውስጥ ከመላው ዓለም የመጣ ጥሬ ቡና በጆንያዎች ተደርጎ መደዳውን ተደርድሯል። ጆን እንዲህ ይላል፦ “በጥንቃቄ የተዘጋጀውን መመሪያ በመከተል ዓይነታቸው የተለያዩ ጥሬ ቡናዎችን እቀላቅላለሁ። እያንዳንዱ የቡና ዓይነት የራሱ የሆነ ጣዕም ስላለው የተለያዩ ቡናዎች ተደባልቀው መጨረሻ ላይ ለሚገኘው ጣዕም የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። የምትፈልገውን ዓይነት ጣዕም ለማግኘት ጊዜ ይጠይቃል። እንዲያውም ታዋቂነት ያተረፈልንን ኤስፕሬሶ ለማዘጋጀት የምንጠቀምበትን ትክክለኛውን የቡና ቅልቅል ለማግኘት ስድስት ወር ፈጅቶብኛል።” ቡና የሚቆሉ ሰዎች የአዘገጃጀት መመሪያቸው ሌላ ሰው እጅ እንዳይገባ በጣም የሚጠነቀቁ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም!

ጄራርዶ ቡናው የሚቆላበትን ሂደት የሚቆጣጠር ሲሆን ይህም የረጅም ጊዜ ሥልጠና የሚጠይቅ ሙያ ነው፤ ምክንያቱም ቡናው ሲቆላ የቡናው ፍሬዎች ኬሚካላዊ ባሕርይ በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጦ ወደ 500 ያህል የሚተንኑ ንጥረ ነገሮች ይፈጠራሉ። የቡና ፍሬዎቹ በጋዝ በሚሠራው መቁያ ውስጥ እየተገለባበጡ በሚቆሉበት ጊዜ በውስጣቸው ያለው ውኃና ካርቦን ዳይኦክሳይድ ስለሚወጣ ፍሬዎቹ የሚንጣጣ ድምፅ ያሰማሉ፤ እንዲሁም እያበጡ ይሄዳሉ። ፍሬዎቹ ማበጣቸው በውስጣቸው ያሉት ሴሎች ግድግዳ እንዲሰነጠቅ ስለሚያደርግ ግሩም መዓዛ ያላቸው ቅባቶች ከፍሬዎቹ ውስጥ ይወጣሉ። የኤስፕሬሶው መዓዛና ጣዕም የተመካው በእነዚህ ቅባቶች ላይ ነው። ዋናው ሙያ አቆላሉ ላይ ሲሆን ይህም ተገቢውን የሙቀት መጠን እንዲሁም ምን ያህል መቆላት እንዳለበት ጠንቅቆ ማወቅ ይጠይቃል።

ጄራርዶ እየተቆላ ያለው የቡና ፍሬ ጠቆር ያለ ቡናማ መልክ ሲይዝ ከመቁያው አውጥቶ ከብረት በተሠራ ቅርጫት ውስጥ ይገለብጠዋል፤ ከዚያም ቡናውን የራሱ ሙቀት እንዳያሳርረው ሲል ቀዝቃዛ አየር እንዲያገኝ በማድረግ ያናፍሰዋል። “የቡና ጣዕም በደንብ የሚወጣው ተቆልቶ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ሲቀመጥ ነው” በማለት ጆን ይናገራል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ለቡናው ጣዕም የሚሰጡት ቅባቶች በደንብ ስለሚወጡ ቡናው ለመሠራት ዝግጁ ይሆናል።

የአዘገጃጀቱ ዘዴ

ጆን “ከቡና አዘገጃጀት ዘዴዎች ሁሉ የኤስፕሬሶ አሠራር በትንሽ ቡና ግሩም ጣዕም ለማግኘት የሚያስችል ሆኖም እጅግ አስቸጋሪ ነው” ይላል። ግሩም ኤስፕሬሶ ለማዘጋጀት፣ ወሳኝ የሆኑ ሦስት ነገሮችን ማሟላት ያስፈልጋል፤ እነሱም፦ የተቆላውን ቡና መፍጨት (1)፣ ዱቄቱን በቡና መሥሪያ ማሽኑ ላይ ባለው ማጥለያ ውስጥ በደንብ ደምድሞ ማስቀመጥ (2) እንዲሁም ኤስፕሬሶውን መሥራት (3) ናቸው። ጆን “የተቆላውን ቡና በትክክል መፍጨት በጣም አስፈላጊ ነው” ይላል። “ቡናው በግርድፉ ከተፈጨ ኤስፕሬሶው ቀጭን ይሆናል። ዱቄቱ በጣም ከላመ ደግሞ ቡናው የሚመር ከመሆኑም ሌላ ያረረ ጣዕም ይኖረዋል። ዱቄቱ በግርድፉ ቢፈጭም ወይም በጣም ቢልምም ኤስፕሬሶው ከማጥለያው ሲወርድ የሚታየው ክሬማ (ኤስፕሬሶው እንደተቀዳ ከላዩ የሚታየው ወርቃማ ቀለም ያለው አረፋ) የቡናው ቅባት በደንብ መውጣት አለመውጣቱን ይጠቁማል።”

ጆን ከተቆላው ቡና የተወሰነውን ከፈጨ በኋላ ዱቄቱን በማጥለያው ውስጥ በደንብ በመጠቅጠቅ ለጥ ያለ እስኪሆን ድረስ ያስተካክለዋል። ቀጥሎ ማጥለያውን በማሽኑ ላይ ከገጠመ በኋላ ማሽኑን ሲያስነሳው ትኩስና ቡናማ ቀለም ያለው ፈሳሽ እየተንዶለዶለ ይወርዳል። ኤስፕሬሶ በመሥራት ልምድ ያካበተው ጆን ቡናው ሲወርድ በመመልከት ዱቄቱ ግርድፍ እንደሆነ ለማወቅ ጊዜ አልወሰደበትም። እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩ ኤስፕሬሶ መሥራት ብዙውን ጊዜ ተደጋጋሚ ሙከራ የማድረግ ጉዳይ ነው። እስቲ ቡናውን ደቀቅ አድረግን ፈጭተን እንደገና እንሞክረው። እንዲሁም ኤስፕሬሶው ቀስ ብሎ እንዲወርድ ዱቄቱን የበለጠ እንጠቀጥቀዋለን።”

ጆን አስፈላጊውን ማስተካከያ ካደረገ በኋላ ማሽኑን እንደገና አስነሳው። በዚህ ጊዜ ኤስፕሬሶው እንደ ማር ወለላ ከማጥለያው ውስጥ በቀስታ መውረድ ጀመረ፤ ክሬማው (አረፋው) ከላይ ተንሳፍፎ ይታያል። ምራቅ የሚያስውጠው ግሩም መዓዛ ቤቱን ሲያውደው በጆን ፊት ላይ የሚታየው ፈገግታ ኤስፕሬሶው ጥሩ ሆኖ እንደወጣ ይጠቁማል። “ቡናው መልኩ መቅጠን ሲጀምር መቅዳታችንን ማቆማችን በጣም አስፈላጊ” መሆኑን ጆን ይናገራል። ኤስፕሬሶውን ለመሥራት የሚያስፈልገው ከ30 ሴኮንዶች ያነሰ ጊዜ ነው። ጆን “ከዚህ በኋላ መቅዳታችንን ብንቀጥል የሚወጣው ቡና መራራ ጣዕም እንዲሁም ብዙ ካፌይን ያለው ይሆናል” ብሏል።

ጆን ወፍራም የሆነውንና ቶሎ የማይጠፋውን ክሬማ ሲመለከት “አሁን ግሩም ኤስፕሬሶ የሠራን ይመስለኛል” አለ። ከዚያም “ቡና መጠጣት የሚፈልግ አለ?” ብሎ ጠየቀ።

ባሕላዊውን አሠራር የሚወዱ ሰዎች በተለምዶ አጭር ጥቁር በመባል የሚታወቀውን ኤስፕሬሶ ይመርጣሉ። በሌላ አነጋገር ከትንሽ ስኳር በቀር ቡናው ውስጥ ሌላ ነገር እንዲጨመር አይፈልጉም። ሌሎች ደግሞ ካፑቺኖ፣ ላቴ ወይም ሌላ የኤስፕሬሶ ዓይነት ለመሥራት ቡናው ውስጥ ትኩስ ወተት ይጨምሩበታል። ፍሬሽ ካፕ ማጋዚን “በዛሬው ጊዜ ከሚሸጡት የኤስፕሬሶ ዓይነቶች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወተት ይጨመርባቸዋል” ይላል። *

ቡናም ሆነ ሻይ፣ የመረጣችሁትን ዓይነት ጥሩ ሆኖ የተዘጋጀ መጠጥ እየጠጣችሁ ዘና ብሎ መጫወት በሕይወት ውስጥ በቀላሉ ከሚያስደስቱ ነገሮች አንዱ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ጆን “ግሩም ጣዕም ያላቸው መጠጦች ሰዎችን ያቀራርባሉ” በማለት ይናገራል። “ምናልባትም እነዚህ መጠጦች ያላቸው ጥሩ ጎን ይኸው ሳይሆን አይቀርም!”

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.15 ቡናና ሻይ ሱስ ሊያስይዝ የሚችል ካፌይን የሚባል ንጥረ ነገር ስላላቸው አንድ ክርስቲያን እነዚህን መጠጦች ከመውሰድ መቆጠብ አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ጉዳይ የሚያሳስብህ ከሆነ በሚያዝያ 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” የሚለውን ርዕስ ማንበብ ትፈልግ ይሆናል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ቡና መግዛትና ማስቀመጥ

ስለ ቡና ግዢ የሚገልጽ አንድ መምሪያ እንደሚናገረው “የተቆላ ቡና ሳምንት፣ የተፈጨ ቡና አንድ ሰዓት ካለፈው ጣዕሙን ማጣት ይጀምራል፤ የተፈላ ቡና ደግሞ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጣዕሙ ይጠፋል።” በመሆኑም ያልተፈጨ ቡና የምትገዛ ከሆነ በጥቂቱ ገዝተህ ቀዝቃዛና ጨለማ በሆነ ሥፍራ ብታስቀምጠው የተሻለ ነው። ይሁን እንጂ ማቀዝቀዣ ውስጥ አታስቀምጠው፤ እንዲህ ካደረግህ እርጥበት ሊስብና ጣዕሙን ሊያጣ ይችላል። ምንጊዜም ቢሆን ቡናውን ወዲያው እንደተፈጨ አፍላው።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Photo 3: Images courtesy of Sunbeam Corporation, Australia