በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወላጅ ሞት ያስከተለብኝን ሐዘን እንዴት መቋቋም እችላለሁ?

የወላጅ ሞት ያስከተለብኝን ሐዘን እንዴት መቋቋም እችላለሁ?

የወጣቶች ጥያቄ

የወላጅ ሞት ያስከተለብኝን ሐዘን እንዴት መቋቋም እችላለሁ?

“እማማ ስትሞት ግራ ገብቶኝ እንዲሁም የከንቱነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። የቤታችን ምሰሶ እሷ ነበረች።”—ካረን *

ላጅን በሞት የማጣትን ያህል በጣም ሊጎዳህ የሚችል ነገር የለም ማለት ይቻላል። በዚህ ጊዜ፣ የደረሰብህን ጥልቅ ሐዘን መቋቋም ብቻ ሳይሆን የወደፊት ሕይወትህ ካሰብከው ፍጹም የተለየ ሊሆን ስለሚችል ይህንንም መጋፈጥ ይኖርብሃል።

ምናልባትም የምትወዳት እናትህ ወይም የምትወደው አባትህ መንጃ ፈቃድ ስታወጣ ወይም ስትመረቅ አሊያም በሠርግህ ቀን ተገኝተው የደስታህ ተካፋይ እንደሚሆኑ ተስፋ አድርገህ ይሆናል። አሁን ግን ይህ ተስፋህ እንደ ጉም በኗል፤ ይህም እንድታዝንና ተስፋ እንድትቆርጥ አልፎ ተርፎም እንድትበሳጭ ሊያደርግህ ይችላል። ታዲያ በእናትህ ወይም በአባትህ ሞት ምክንያት ከደረሰብህ ጥልቅ ሐዘን ለመጽናናት ምን ሊረዳህ ይችላል?

‘እንዲህ የሚሰማኝ የጤና ነው?’

የእናትህ ወይም የአባትህ መሞት እውነት መሆኑን ስታስበው ከዚያ በፊት አጋጥሞህ የማያውቅ የተለያየ ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ይሆናል። የ13 ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ በልብ በሽታ የሞተበት ብራየን ሲናገር “የአባቴን ሞት በሰማንበት ምሽት ተቃቅፈን ከማልቀስ በስተቀር ምንም ማድረግ አልቻልንም” ብሏል። አባቷ በካንሰር ሲሞት የአሥር ዓመት ልጅ የነበረችው ናተሊ ደግሞ “ግራ ገብቶኝ፣ ደንዝዤ እንዲሁም በድን ሆኜ ነበር” በማለት ተናግራለች።

የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚፈጥረው ስሜት ከሰው ሰው ይለያል። መጽሐፍ ቅዱስ “ማንም ሰው” የራሱ የሆነ ‘የሚሰማው ጭንቀትና ሕመም’ እንዳለው ይናገራል። (2 ዜና መዋዕል 6:29) ይህን በአእምሮህ ይዘህ የእናትህ ወይም የአባትህ ሞት የፈጠረብህን ስሜት ለማሰብ ሞክር። ቀጥሎ በተሰጠው ክፍት ቦታ ላይ (1) ለመጀመሪያ ጊዜ የእናትህን ወይም የአባትህን መሞት ስታውቅ ምን እንደተሰማህና (2) አሁን ምን እንደሚሰማህ ግለጽ። *

(1) ․․․․․

(2) ․․․․․

ስሜትህ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እንደተረጋጋ ከመልሶችህ አስተውለህ ሊሆን ይችላል። ይህ የሚጠበቅ ነገር ነው። ይሁንና እናትህን ወይም አባትህን ረስተሃል ማለት አይደለም። በተቃራኒው ደግሞ ስሜትህ ከበፊቱ ምንም እንዳልተለወጠ ወይም ሐዘንህ ከመጀመሪያው ጊዜ የበለጠ እንደከበደብህ አስተውለህ ይሆናል። ምናልባትም ሐዘንህ ድንገት መጥቶ እንደሚመለስ ማዕበል ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ስሜት የሚሰማህ እናትህን ወይም አባትህን በሞት ካጣህ ከዓመታት በኋላ ቢሆንም እንኳ ይህም የሚጠበቅ ነገር ነው። በአሁኑ ጊዜ የሚሰማህ ስሜት ምንም ይሁን ምን፣ ከሐዘንህ ለመጽናናት የምትችለው እንዴት ነው?

ከሐዘንህ ለመጽናናት የሚረዱ መንገዶች

ማልቀስ ካሰኘህ አልቅስ! ማልቀስ የሐዘንን ስሜት ለማስታገስ ይረዳል። ይሁንና የ19 ዓመት ልጅ ሳለች እናቷ የሞተችባት አሊሺየ እንደተሰማት ዓይነት ስሜት ሊሰማህ ይችላል። አሊሺየ እንዲህ ብላለች፦ “በጣም ካለቀስኩ ሰዎች እምነት እንደሌለኝ አድርገው ይመለከቱኛል የሚል ስሜት አደረብኝ።” ይሁን እንጂ እስቲ አስበው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት የነበረው ፍጹም ሰው ነበር። የሚወደው ጓደኛው አልዓዛር በሞተበት ወቅት ግን ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:35) ስለዚህ ማልቀስ ካሰኘህ እንባህን ለመቆጣጠር አትሞክር። ማልቀስህ እምነት እንደሌለህ የሚያሳይ አይደለም! አሊሺየ “በመጨረሻ ግን አለቀስኩ፤ በየቀኑ ለረጅም ሰዓት አለቅስ ነበር” በማለት ተናግራለች። *

የሚሰማህን የጥፋተኝነት ስሜት ለማሸነፍ ሞክር። እናቷ በሞተችበት ወቅት የ13 ዓመት ልጅ የነበረችው ኬረን እንዲህ ብላለች፦ “ማታ ማታ እማማን ‘ደህና እደሪ’ ብዬ የመሳም ልማድ ነበረኝ። ሆኖም እንዲህ ሳላደርግ የቀረሁበት አንድ ምሽት ነበር። በማግስቱም እማማ ሞተች። ምክንያታዊ እንዳልሆንኩ ቢገባኝም ያን ምሽት እናቴን ባለማየቴ እንዲሁም በማግስቱ የተከናወኑትን ነገሮች ሳስብ ጥፋተኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል። አባባ ለሥራ ከከተማ ሲወጣ እማማን አየት እንድናደርጋት ለእኔና ለእህቴ ነግሮን ነበር። ይሁንና ማታ ላይ አምሽተን ተኛን። መኝታ ክፍሏ ስሄድ እማማ መተንፈስ አቁማ ነበር። አባባ ከቤት ሲወጣ ደህና ስለነበረች በጣም አዘንኩ!”

ልክ እንደ ኬረን አንተም ሳታደርግ የቀረኸውን ነገር ስታስብ በመጠኑም ቢሆን የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ “እንዲህ ባደርግ ኖሮ” እያልክ ራስህን ልታስጨንቅ ትችላለህ። ለምሳሌ፣ ‘አባባ ሐኪም ቤት እንዲሄድ ጨቅጭቄው በሆነ ኖሮ’ ወይም ‘እማማን ቀደም ብዬ አይቻት በሆነ ኖሮ’ እያልክ በማሰብ የምትጨነቅ ከሆነ የሚከተለውን አስታውስ፦ በተለየ መንገድ ልታደርጋቸው የምትችላቸውን ነገሮች በማሰብ መቆጨት ያለ ነገር ነው። ምን እንደሚከሰት ብታውቅ ኖሮ ነገሮችን በተለየ መንገድ ታደርግ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ይሁንና ምን እንደሚከሰት አስቀድመህ አላወቅህም። በመሆኑም የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማህ አይገባም። አባትህ ወይም እናትህ የሞቱት በአንተ ጥፋት አይደለም! *

ስሜትህን ለሌሎች ግለጽ። ምሳሌ 12:25 ‘መልካም ቃል ሰውን ደስ ያሰኛል’ ይላል። ስሜትህን አምቀህ መያዝ ከሐዘንህ መጽናናት አስቸጋሪ እንዲሆንብህ ሊያደርግ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ስሜትህን ለምታምነው ሰው መግለጽህ በጣም ባዘንክበት ጊዜ የሚያስፈልግህን የሚያጽናና “መልካም ቃል” እንድታገኝ አጋጣሚውን ይከፍትልሃል። እንግዲያው ከዚህ ቀጥሎ ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል ቢያንስ አንዱን ተግባራዊ ለማድረግ ለምን አትሞክርም?

የሚሰማህን ነገር በሕይወት ላለው ወላጅህ ንገረው። ይህ ወቅት በሕይወት ላለው ወላጅህ በጣም ከባድ እንደሚሆን የታወቀ ቢሆንም በዚህ ጊዜም እንኳ የሚያስፈልግህን እርዳታ ለመስጠት እንደሚፈልግ ጥርጥር የለውም። ስለሆነም የሚሰማህን ነገር ንገረው። እንዲህ ማድረግህ ሐዘንህን በተወሰነ መጠን የሚያቀልልህ ከመሆኑም ሌላ ሁለታችሁን ያቀራርባችኋል።

ለመነጋገር ቀላል እንዲሆንልህ እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በሞት ስለተለየህ አባትህ ወይም እናትህ ማወቅ የምትፈልገውን ሁለት ወይም ሦስት ነገሮች ጻፍና በሕይወት ያለው ወላጅህ ከእነዚህ መካከል ስለ አንዱ እንዲነግርህ ጠይቀው። *

․․․․․

ስሜትህን ለቅርብ ጓደኞችህ ንገራቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ወዳጅ “ለክፉ ቀን ይወለዳል” ይላል። (ምሳሌ 17:17) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አሊሺየ እንዲህ ብላለች፦ “ፈጽሞ ካልጠበቃችሁት ሰው እርዳታ ልታገኙ ትችላላችሁ። ስለዚህ ስለሚሰማችሁ ነገር ለማውራት አትፍሩ።” እርግጥ ነው፣ መጀመሪያ ላይ ከጓደኛህ ጋር ለመወያየት ስትሞክር በምን መንገድ ሐሳባችሁን ብትገልጹ እንደሚሻል እያሰባችሁ ስለምትጨነቁ ግራ ልትጋቡ ትችላላችሁ። ይሁንና የሚሰማህን ሐዘን በተመለከተ ከሌላ ሰው ጋር ማውራትህ በጊዜ ሂደት ይጠቅምሃል። ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ በልብ በሽታ የሞተበት ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “ስሜቴን አምቄ ለመያዝ ሞከርኩ። ይሁን እንጂ የውስጤን አውጥቼ ብናገረው ኖሮ ይሻለኝ ነበር። እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ ከሐዘኔ በተሻለ ሁኔታ ለመጽናናት እችል ነበር።”

የሚሰማህን ለአምላክ ንገረው። በጸሎት አማካኝነት ለይሖዋ አምላክ ‘ልብህን ካፈሰስክ’ በኋላ እፎይታ እንደሚሰማህ ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 62:8) ጸሎትን እንደ አንድ የውጥረት ማስታገሻ ዘዴ ብቻ አድርገህ ማየት የለብህም። በጸሎት የምታነጋግረው ‘በመከራችን ሁሉ ማጽናኛ የሚሰጠንን የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

አምላክ የሚያጽናናበት አንዱ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነውን] ኃይል” በመስጠት ሐዘንህ ያስከተለብህን ሥቃይ እንድትቋቋም ይረዳሃል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) በተጨማሪም አምላክ “ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ” አማካኝነት ያጽናናናል። (ሮም 15:4) በመሆኑም አምላክ መንፈሱን እንዲሰጥህ በጸሎት ጠይቀው፤ እንዲሁም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ማበረታቻ አንብብ። (2 ተሰሎንቄ 2:16, 17) እንዲያውም ለአንተ የሚያጽናኑ ሆነው ያገኘሃቸውን ጥቅሶች ደጋግመህ እንድታያቸው ጽፈህ ቅርብ ቦታ ልታስቀምጣቸው ትችላለህ። *

ሐዘንህን ሙሉ በሙሉ የምትረሳበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?

ከሐዘንህ ለመጽናናት ጊዜ ያስፈልግሃል። በ16 ዓመቷ እናቷ የሞተችባት ብሪያን እንዲህ ብላለች፦ “ከሐዘንህ በአንድ ጀምበር ልትጽናና አትችልም። አንዳንዴ እንቅልፍ እስኪወስደኝ ድረስ አነባለሁ። በሌላ ጊዜ ደግሞ በደረሰብኝ ሐዘን ላይ ሳይሆን ይሖዋ በሰጠው ተስፋ ላይ ትኩረት ለማድረግ እሞክራለሁ፤ ከእናቴ ጋር በገነት ስለማሳልፈው አስደሳች ጊዜ አስባለሁ።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ብሪያን በተናገረችለት ገነት ውስጥ “ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” በማለት ዋስትና ይሰጠናል። (ራእይ 21:3, 4) ይህን በመሰሉት ተስፋዎች ላይ ማሰላሰል ወላጅህን በሞት ማጣትህ ካስከተለብህ ሐዘን እንድትጽናና አንተንም ሊረዳህ ይችላል።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.8 ለእነዚህ ጥያቄዎች አሁን መልስ መስጠት ከከበደህ ወደፊት ለመመለስ ልትሞክር ትችላለህ።

^ አን.13 ማዘንህን ለማሳየት የግድ ማልቀስ እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። ሰዎች ሐዘናቸውን የሚገልጹበት መንገድ ይለያያል። ማልቀስ ካሰኘህ ግን ይህ ወቅት ‘ለማልቀስ ጊዜው’ እንደሆነ አስታውስ።—መክብብ 3:4

^ አን.15 እንዲህ ያለ የጥፋተኝነት ስሜት ለረጅም ጊዜ የሚያስጨንቅህ ከሆነ በሕይወት ላለው ወላጅህ ወይም ለሌላ አዋቂ ሰው ስሜትህን አካፍል። በጊዜ ሂደት የበለጠ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ታዳብራለህ።

^ አን.18 ያደግከው በነጠላ ወላጅ ከነበረ ወይም በሕይወት ያለው ወላጅህ በሆነ ምክንያት አብሮህ የማይኖር ከሆነ ከሌላ ከጎለመሰ ሰው ጋር መነጋገር ትችላለህ።

^ አን.22 የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዳንዶችን አጽናንተዋቸዋል፦ መዝሙር 34:18፤ 102:17፤ 147:3፤ ኢሳይያስ 25:8፤ ዮሐንስ 5:28, 29

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

በዚህ ርዕስ ውስጥ ከተጠቀሱት ሐሳቦች የትኞቹን ተግባራዊ ለማድረግ አስበሃል?

ቀጥሎ ባለው ክፍት ቦታ ላይ ሐዘን ሲበረታብህ ሊያጽናኑህ የሚችሉ ጥቂት ጥቅሶችን ጻፍ።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ማልቀስህ ችግር የለውም . . . እነሱም አልቅሰዋል!

አብርሃም—ዘፍጥረት 23:2

ዮሴፍ—ዘፍጥረት 50:1

ዳዊት—2 ሳሙኤል 1:11, 12፤ 18:33

የአልዓዛር እህት ማርያም—ዮሐንስ 11:32, 33

ኢየሱስ—ዮሐንስ 11:35

መግደላዊት ማርያም—ዮሐንስ 20:11

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የሚሰማህን ነገር በማስታወሻ ላይ ጻፍ

በሞት ስላጣኸው አባትህ ወይም እናትህ የሚሰማህን ነገር መጻፍ ሐዘንህን እንድትቋቋም በእጅጉ ሊረዳህ ይችላል። ልትጽፈው የምትችለው ብዙ ነገር አለ። ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል።

ስለ አባትህ ወይም እናትህ የምታስታውሳቸውን አንዳንድ አስደሳች ትዝታዎች ጻፍ።

አባትህ ወይም እናትህ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ብትነግራቸው ደስ ይልህ እንደነበረ የሚሰማህን ነገር ጻፍ።

በደረሰባችሁ ሐዘን ምክንያት የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማው ታናሽ ወንድም ወይም እህት እንዳለህ አድርገህ አስብ። ከዚያም ወንድምህን ወይም እህትህን ለማጽናናት ምን ማለት እንደምትችል አስብና በጽሑፍ አስፍረው። ይህን ማድረግህ አንተ ራስህ የሚሰማህን የጥፋተኝነት ስሜት ለመቋቋም ሊረዳህ ይችላል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የትዳር ጓደኛውን በሞት ላጣው ወላጅ የተሰጠ ምክር

የትዳር ጓደኛን በሞት ማጣት መሪር ሐዘን ያስከትላል። ይሁንና ይህ አሳዛኝ ሁኔታ የደረሰብህ በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጅህ የአንተን እርዳታ በሚፈልግበት ወቅት ላይ መሆኑን አትዘንጋ። ታዲያ የራስህን ስሜት ችላ ሳትል ልጅህ ሐዘኑን እንዲቋቋም ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው? *

ስሜትህን አፍነህ ለመያዝ አትሞክር። ልጅህ በሕይወቱ ውስጥ የተማራቸውን አብዛኞቹን ጠቃሚ ትምህርቶች ያገኘው አንተን በመመልከት ነው። ሐዘኑን እንዴት መቋቋም እንደሚችል የሚማረውም በዚሁ መንገድ ነው። በመሆኑም ለልጅህ ስትል ጠንካራ መሆን እንዳለብህ በማሰብ ሐዘንህን ለመደበቅ አትሞክር። ስሜትህን ለመደበቅ የምትሞክር ከሆነ ልጅህም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርግ እያስተማርከው ነው። ከዚህ በተቃራኒ ሐዘንህን የምትገልጽ ከሆነ ልጅህ ስሜቱን አፍኖ ከመያዝ ይልቅ ማውጣቱ የተሻለ መሆኑን፣ እንዲሁም ማዘኑ አንዳንድ ጊዜም መበሳጨቱ የሚጠበቅ ነገር እንደሆነ ይገነዘባል።

ልጅህ ሐሳቡን እንዲገልጽ አበረታታው። ልጅህ እንደተጫንከው ሆኖ ሳይሰማው የልቡን አውጥቶ እንዲያወራ አበረታታው። ለማውራት ፈቃደኛ ካልሆነ ደግሞ በዚህ ርዕስ ላይ ለመወያየት ልትሞክሩ ትችላላችሁ። በተጨማሪም በሞት ስለተለየህ የትዳር ጓደኛህ አንዳንድ አስደሳች ትዝታዎችን እያነሳህ አውራለት። እንዲሁም የደረሰብህን ሐዘን መቋቋም ምን ያህል ከባድ ሊሆንብህ እንደሚችል በግልጽ ንገረው። ስሜትህን አውጥተህ ስትገልጽ መስማቱ እሱም እንዲህ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲማር ይረዳዋል።

አንተ ራስህ እርዳታ እንደሚያስፈልግህ አትዘንጋ። በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ለልጅህ ያልተቋረጠ ድጋፍ መስጠት እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ አንተም የምትወዳት የትዳር ጓደኛህ ሞት በጣም እንደጎዳህ አስታውስ። በመሆኑም ለተወሰነ ጊዜ ስሜታዊና አካላዊ ጥንካሬ ላይኖርህ እንዲሁም አእምሮህ ሊደክም ይችላል። (ምሳሌ 24:10) ስለሆነም ሌላ የቤተሰብህ አባል ወይም የጎለመሱ ጓደኞችህ እንዲረዱህ መጠየቅ ሊያስፈልግህ ይችላል። እርዳታ መጠየቅ የበሳልነት ምልክት ነው። ምሳሌ 11:2 “በትሑት ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች” ይላል።

ከሁሉ የተሻለ እርዳታ ማግኘት የምትችለው ከይሖዋ አምላክ ነው። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ‘እኔ ይሖዋ አምላክህ “አትፍራ፤ እረዳሃለሁ” ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና’ በማለት ቃል ገብቶላቸዋል።—ኢሳይያስ 41:13

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.53 ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል እርዳታ ስለሚያሻው ልጅ ስንናገር በተባዕታይ ጾታ ተጠቅመናል። ይሁንና የቀረበው መሠረታዊ ሥርዓት ለሁለቱም ጾታዎች ይሠራል።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐዘን ድንገት መጥቶ እንደሚመለስ ማዕበል ሊሆን ይችላል