በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዓለም ጦርነት እንዲከሰት ያደረጉ ከባድ ስህተቶች

የዓለም ጦርነት እንዲከሰት ያደረጉ ከባድ ስህተቶች

የዓለም ጦርነት እንዲከሰት ያደረጉ ከባድ ስህተቶች

ሦስተኛ የዓለም ጦርነት ድንገት ይጀምር ይሆን? የአገር መሪዎችና ወታደራዊ አማካሪዎቻቸው ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ ባለማስላት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለጥፋት ይዳርጉ ይሆን?

አናውቅም፤ በታሪክ ውስጥ ተመሳሳይ ነገር ተከስቶ እንደነበር ግን እናውቃለን። የዛሬ መቶ ዓመት አካባቢ የአውሮፓ መሪዎች ሊደርስ የሚችለውን ሰቆቃ ሳይገነዘቡ ሕዝቦቻቸው ወደ አንድ ታላቅ ጦርነት እንዲገቡ አድርገው ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ ጦርነት አንደኛው የዓለም ጦርነት ተብሎ ተጠርቷል። ከ1916 እስከ 1922 የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዴቪድ ሎይድ ጆርጅ “በጦርነት ታመስን” በማለት ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። እስቲ ይህን ዘግናኝ እልቂት ካስከተሉት ዋና ዋና ክስተቶች መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

ታሪክ ጸሐፊው ጆን ቴይለር “የትኛውም የአገር መሪ መጠነ ሰፊ ጦርነት የማካሄድ ፍላጎት አልነበረውም፤ ይሁን እንጂ ሁሉም መሪዎች ሌሎችን ማስፈራራትና ማሸነፍ ይፈልጉ ነበር” በማለት ጽፈዋል። የሩሲያው ዛር ለሰላም ሲባል ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንዳለበት ቢሰማውም ለሚከሰተው አሰቃቂ እልቂት ተጠያቂ መሆን ግን አልፈለገም ነበር። ይሁንና ሰኔ 28, 1914 ከረፋዱ 5:15 ላይ የተተኮሱ ሁለት ጥይቶች ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆኑ በማድረግ የዓለም ታሪክ እንዲለወጥ አደረጉ።

ዓለምን የለወጡ ሁለት ጥይቶች

እስከ 1914 ባለው ጊዜ ውስጥ በአውሮፓ መንግሥታት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው ኃይለኛ ፉክክር አገሮቹ በሁለት ተቃራኒ ጎራ እንዲሰለፉ አድርጓቸው ነበር፤ አንደኛው ጎራ ኦስትሪዮ-ሃንጋሪን፣ ጣሊያንን እና ጀርመንን ያቀፈው ባለ ሦስት ጥምር መንግሥት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይና ሩሲያ የሚገኙበት ጎራ ነው። ከዚህም በላይ እነዚህ አገሮች የባልካን አገሮችን ጨምሮ ከሌሎች በርካታ አገሮች ጋር ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ነበራቸው።

በወቅቱ የባልካን አገሮች፣ በኃያላን መንግሥታት ይደርስባቸው የነበረው ጭቆና አማሯቸው ስለነበር ነፃነት ለማግኘት በድብቅ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካዊ ቡድኖች በአካባቢው እንደ አሸን ፈልተው ነበር። የኦስትሪያው አርክዱክ ፍራንሲስ ፈርዲናንድ ሰኔ 28 የቦስኒያን * ዋና ከተማ ሳረዬቮን በሚጎበኝበት ጊዜ እሱን ለመግደል ያሴረው የወጣቶች ቡድን ለነፃነት ከሚታገሉት ቡድኖች መካከል አንዱ ነበር። በስፍራው የነበረው የፖሊስ ኃይል አነስተኛ መሆኑ ወጣቶቹ ያሰቡትን እንዲፈጽሙ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸው ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ወጣቶች ግድያውን ለመፈጸም የሚያስችል በቂ ሥልጠና አላገኙም ነበር። አንደኛው ወጣት አንድ ትንሽ ቦምብ ቢወረውርም ዒላማውን መምታት ሳይችል ቀረ፤ ሌሎቹም ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። ከሴራው ጠንሳሾች አንዱ የነበረው ጋቭሪሎ ፕሪንሲፕም ቢሆን አርክዱኩን ለመግደል የተሳካለት በአጋጣሚ ነበር። የተሳካለት እንዴት ነው?

ፕሪንሲፕ፣ የተወረወረው ቦምብ መኪና ውስጥ በነበረው አርክዱክ ላይ ምንም ጉዳት እንዳላደረሰ ባየ ጊዜ መኪናው ላይ ለመድረስ ቢሞክርም አልተሳካለትም ነበር። በሁኔታው ተስፋ የቆረጠው ይህ ወጣት መንገዱን ተሻግሮ ወደ አንድ ምግብ ቤት ገባ። ይህ በዚህ እንዳለ በተቃጣበት የግድያ ሙከራ የተናደደው ልዑል ጉብኝቱን ለማቋረጥ ወሰነ። ይሁን እንጂ ሾፌሩ አርክዱኩ የጉብኝቱን እቅድ መለወጡን አላወቀም ነበር፤ ይህን በተረዳ ጊዜ ግን ወደኋላ ለመመለስ ተገደደ። ልክ በዚያች ቅጽበት ፕሪንሲፕ ከምግብ ቤቱ ሲወጣ ሦስት ሜትር በማይሞላ ርቀት ላይ አርክዱክ ፈርዲናንድን ከፊት ለፊቱ በክፍት መኪናው ውስጥ ተቀምጦ አየው። በዚህ ጊዜ ወደ መኪናው ቀረብ ብሎ በሁለት ጥይት አርክዱኩንና ሚስቱን ገደላቸው። * በብሔራዊ ስሜት ተነሳስቶ ይህን ግድያ የፈጸመው ሰርቢያዊው ፕሪንሲፕ ድርጊቱ ስለሚያስከትለው አስከፊ ሰቆቃ ያወቀው ነገር አልነበረም። ሆኖም ያንን ግድያ ተከትለው ለመጡት አሰቃቂ እልቂቶች ተወቃሹ እሱ ብቻ አይደለም።

ጦርነት ሊፈነዳ ተቃርቦ ነበር

ከ1914 በፊት አብዛኞቹ አውሮፓውያን ለጦርነት የተዛባ አመለካከት ነበራቸው። እነዚህ ሰዎች ክርስቲያኖች እንደሆኑ ቢናገሩም ጦርነትን ጠቃሚ፣ የሚደነቅና ክብር ያለው ነገር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር። እንዲያውም አንዳንድ የአገር መሪዎች ጦርነት ብሔራዊ አንድነትን እንደሚያጠናክርና የሕዝቡን ወኔ እንደሚጨምር ያምኑ ነበር! ከዚህም በላይ አንዳንድ ጄኔራሎች በፍጥነትና በማያዳግም መንገድ በጦርነት ድል መቀዳጀት እንደሚቻል ለመሪዎቻቸው አስረግጠው ይነግሯቸው ነበር። አንድ ጀርመናዊ የጦር አዛዥ “ፈረንሳይን በሁለት ሳምንት ውስጥ ድል እናደርጋለን” በማለት በጉራ ተናግሮ ነበር። ያኔ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምሽግ ውስጥ ዓመታት ያሳልፋሉ ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም።

ከዚህም በላይ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ዓመታት ውስጥ “አውሮፓ በከፍተኛ የብሔራዊ ስሜት ማዕበል ተጥለቅልቃ ነበር” በማለት ኮኦፐሬሽን አንደር አናርኪ የተሰኘው መጽሐፍ ተናግሯል። መጽሐፉ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ጋዜጦችና መጽሔቶች ብሎም ፖለቲከኞች፣ ሰዎች እንደዚህ ባለው ከልክ ያለፈ የብሔርተኝነት ስሜት እንዲዋጡና ለራሳቸው ክብር ከፍተኛ ቦታ እንዲሰጡ ያበረታቱ ነበር።”

የሃይማኖት መሪዎች ይህን መጥፎ አስተሳሰብ ለመግታት እምብዛም ጥረት አላደረጉም። ታሪክ ጸሐፊው ፖል ጆንሰን እንደተናገሩት “በአንዱ ወገን ፕሮቴስታንቷ ጀርመን፣ ካቶሊኳ ኦስትሪያ፣ ኦርቶዶክሷ ቡልጋሪያና ሙስሊሟ ቱርክ ተሰልፈው ነበር። በሌላው ወገን ደግሞ ፕሮቴስታንቷ ብሪታኒያ፣ ካቶሊኮቹ ፈረንሳይና ጣሊያን እንዲሁም ኦርቶዶክሷ ሩሲያ ነበሩ።” አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “[አብዛኞቹ ቀሳውስት] ክርስትናን የሚመለከቱት ከአገር ፍቅር ጋር እኩል አድርገው ነበር። ከሁሉም የክርስትና ሃይማኖቶች የተውጣጡ ወታደሮች በአዳኛቸው [በክርስቶስ] ስም አንዳቸው ሌላውን እንዲገድሉ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር።” ካህናትና ሴት መነኮሳት እንኳን ሳይቀሩ ሰዎች ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ ሲያበረታቱ የነበሩ ሲሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ካህናት በውጊያ ላይ ሳሉ ሞተዋል።

ከባድ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ለመከላከል ስምምነት ያደረጉት የአውሮፓ አገሮች ለጦርነቱ መጀመር አስተዋጽኦ ሳያበረክቱ አልቀሩም። በምን መንገድ? ኮኦፐሬሽን አንደር አናርኪ እንደሚከተለው ብሏል፦ “የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ደህንነት በጥብቅ የተመካው እርስ በርሳቸው ባላቸው ትስስር ላይ ነበር። እያንዳንዱ ኃያል መንግሥት የራሱ ደህንነት የተመካው በሌሎች አጋሮቹ ላይ እንደሆነ ይሰማው ስለነበር አጋሮቹ ራሳቸው ጠብ ጭረው ጦርነት ውስጥ ቢገቡም እንኳ እነሱን ደግፎ መዋጋት እንዳለበት ይሰማው ነበር።”

ለጦርነቱ መቀስቀስ መንስኤ የሆነው ሌላው ምክንያት ደግሞ የጀርመን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መምሪያ ኃላፊ በነበረው በጀኔራል አልፍሬት ፎን ሽሊፌን ስም የተሰየመው የሽሊፌን የጦርነት እቅድ ነው። አስቀድሞ ፈጣን ጥቃት የመሰንዘር ጽንሰ ሐሳብን በውስጡ ያካተተው ይህ የጦርነት እቅድ፣ ‘ጀርመን ፈረንሳይንና ሩሲያን መዋጋት ይኖርባታል’ በሚለው ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ የተነደፈ ነበር። በመሆኑም ጀርመን፣ ሩሲያ ገና ለጦርነት እስክትዘጋጅ ድረስ በፈረንሳይ ላይ ፈጣን ድል ለመቀዳጀትና ከዚያ በኋላ ሩሲያን ለማጥቃት አቅዳ ነበር። ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደተናገረው “[የሽሊፌን] እቅድ በተግባር ላይ መዋል ሲጀምር አገሮቹ ወታደራዊ ኅብረት መፍጠራቸው በአውሮፓ አጠቃላይ የሆነ ጦርነት እንደሚነሳ አመላካች ሆነ።”

ሰቆቃው ጀመረ

የሰርቢያ መንግሥት በአርክዱኩ ግድያ እጁ እንዳለበት የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ባይገኝም ኦስትሪያ የስላቮችን ዓመፅ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ወስና ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ጆን ሮበርትስ ኦስትሪያ “ለሰርቢያ ትምህርት ለመስጠት” ጓግታ እንደነበር ተናግረዋል።

በሰርቢያ ዋና ከተማ ይኖሩ የነበሩት የሩሲያ አምባሳደር ኒኮላስ ሃርትዊግ ውጥረቱን ለማርገብ በማሰብ ሁለቱን አገራት ለማስታረቅ ሞክረው ነበር። ይሁን እንጂ ከኦስትሪያ ልዑካን ጋር በስብሰባ ላይ ሳሉ በድንገተኛ የልብ ሕመም ሞቱ። በመጨረሻም ሐምሌ 23 ላይ ኦስትሪያ፣ ሰርቢያ እንድታደርግ የምትጠብቅባትን ነገሮች ዝርዝር የያዘ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ላከችላት። ሰርቢያ ከሚጠበቁባት ነገሮች መካከል የማትስማማበት ነገር ስለነበራት ኦስትሪያ ወዲያውኑ ከሰርቢያ ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋረጠች። በዚያ ወሳኝ ወቅት ላይ ማንኛውም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ።

ያም ሆኖ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ለማድረግ የተወሰኑ ጥረቶች ተደርገው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ዩናይትድ ኪንግደም ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ እንዲካሄድ ሐሳብ ያቀረበች ሲሆን የጀርመኑ ካይዘር ደግሞ የሩሲያው ዛር ጦርነት እንዳይጀምር ማሳሰቢያ ሰጥቶት ነበር። ይሁን እንጂ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ሆኑ። ዚ ኢንተርፕራይዝ ኦቭ ዎር የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው “የአገር መሪዎች፣ የጦር አዛዦችና መላ ሕዝቦቻቸው እየተፈጸመ ያለው መጠነ ሰፊ ክስተት ሊገምቱት ከሚችሉት በላይ ሆኖባቸው ነበር።”

የኦስትሪያው ንጉሠ ነገሥት የጀርመንን ድጋፍ እንደሚያገኝ በመተማመን ሐምሌ 28 ቀን በሰርቢያ ላይ ጦርነት አወጀ። ሩሲያ ደግሞ ለሰርቢያ በማገዝ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ እግረኛ ሠራዊቶችን ወደ ኦስትሪያ ድንበር እንደምትልክ በማወጅ ኦስትሪያን ለማስፈራራት ሞከረች። ሩሲያ እንዲህ ማድረጓ ድንበሯ ለጀርመን ጥቃት የተጋለጠ እንዲሆን ስለሚያደርገው የዛሩ መንግሥት እያቅማማም ቢሆን መላው ሠራዊት እንዲከተት አዋጅ አወጣ።

የሩሲያው ዛር ጀርመንን የመውረር እቅድ እንደሌለው በመግለጽ የጀርመኑን ካይዘር ለማረጋጋት ሞክሮ ነበር። ይሁን እንጂ ሩሲያ የጦር ሠራዊቷን ማስከተቷ ጀርመን የጦር እቅዷን ተግባራዊ ለማድረግ በፍጥነት እንድትንቀሳቀስ አደረገ፤ ጀርመን ሐምሌ 31 ላይ የሽሊፌንን የጦር እቅድ በሥራ ላይ ማዋል የጀመረች ሲሆን ነሐሴ 1 በሩሲያ ላይ፣ ከሁለት ቀን በኋላ ደግሞ በፈረንሳይ ላይ ጦርነት አወጀች። ጀርመን የነደፈችው የጦር እቅድ በቤልጂየም በኩል ማለፍን ይጠይቃል፤ ይህን የተገነዘበችው ብሪታንያ ጀርመን ገለልተኛ የሆነችውን ቤልጂየምን የምትነካ ከሆነ ጦርነት እንደምታውጅባት በመግለጽ አስጠነቀቀቻት። የጀርመን ሠራዊት ነሐሴ 4 ላይ የቤልጂየምን ድንበር አቋርጦ ገባ። በዚህ ጊዜ ጦርነት መጀመሩ አይቀሬ ሆነ።

“የዘመናችን ትልቁ ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራ”

ታሪክ ጸሐፊው ኖርመን ዴቪስ እንደጻፉት “ብሪታንያ ጦርነት ማወጇ የዘመናችን ትልቁ ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራ እንዲከሰት ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አበርክቷል።” በዚያው ወቅት ታሪክ ጸሐፊ የነበሩት ኤድሞንድ ቴይለር እንደጻፉት ከሆነ ደግሞ ኦስትሪያ ሐምሌ 28 ጦርነት ካወጀች በኋላ “የተፈጠረው ትርምስ [ጦርነት] እንዲጀመርም ሆነ እየተባባሰ እንዲሄድ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በተለያዩ ቦታዎች ላይ በጣም ብዙ የሆኑ ነገሮች በፍጥነት ይከሰቱ ነበር። . . . አስተዋይ የሆኑና የተረጋጋ አእምሮ ያላቸው ሰዎች እየተነገራቸው ያለው መረጃ ሊዋጥላቸው አልቻለም ነበር።”

በተፈጠረው አደገኛ “ትርምስ” ከ13 ሚሊዮን የሚበልጡ ወታደሮችና ሰላማዊ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሠልጥነዋል የሚባሉ ሰዎች ኃይለኛ፣ ጅምላ ጨራሽና አዲስ የተፈለሰፉ መሣሪያዎችን ታጥቀው ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን እርስ በርሳቸው መተላለቃቸው ሰዎች ስለወደፊቱ ጊዜም ሆነ ስለ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ የነበራቸው ብሩሕ አመለካከት እንዲጨልም አድርጓል። ከዚያ በኋላ ዓለም ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ በፍጹም ሊመለስ አይችልም።—“የዓለም ጦርነት—የዘመናችን ምልክት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ቦስኒያ በአሁኑ ጊዜ የቦስኒያ ሄርዘጎቪና ግዛት ናት።

^ አን.8 ፕሪንሲፕ የአርክዱኩን ሚስት የገደላት በስህተት ነበር። እሱ ለመግደል ያሰበው በመኪናው ውስጥ ከእነዚህ ባልና ሚስት ጋር የነበረውን የቦስኒያ አገረ ገዢ ጄኔራል ፖቲዮሬክን ነበር፤ ይሁን እንጂ ዒላማውን እንዲስት ያደረገ አንድ ነገር አጋጥሞታል።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የዓለም ጦርነት—የዘመናችን ምልክት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጦርነት የዚህን ክፉ ዓለም የመጨረሻ ቀኖች ለይቶ የሚያሳውቀው ምልክት አንዱ ገጽታ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3, 7፤ ራእይ 6:4) ይህ ምልክት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን ማግኘቱ የአምላክ መንግሥት ምድርን ሙሉ በሙሉ ወደሚቆጣጠርበት ጊዜ በፍጥነት እየቀረብን መሆኑን የሚጠቁም ነው።—ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10

ከዚህም በላይ የአምላክ መንግሥት፣ በዓለም ላይ በሚከሰቱ ነገሮች ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉትን የማይታዩ ኃይላት ይኸውም በሰይጣን ዲያብሎስ የሚመሩትን ክፉ መናፍስት ያስወግዳል። አንደኛ ዮሐንስ 5:19 “መላው ዓለም ግን በክፉው ኃይል ሥር ነው” በማለት ይናገራል። የሰይጣን ክፉ ተጽዕኖ አንደኛው የዓለም ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት የሆኑትን አሰቃቂ ክስተቶች ጨምሮ በሰው ልጅ ላይ ለደረሱት አብዛኞቹ ወዮታዎች አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ምንም ጥርጥር የለውም።—ራእይ 12:9-12 *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.30 ስለ መጨረሻዎቹ ቀኖችና ስለ ክፉ መናፍስት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተሰኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መጽሐፍ ተመልከት።

[ምንጭ]

U.S. National Archives photo

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አርክዱክ ፈርዲናንድ ሲገደል

[ምንጭ]

© Mary Evans Picture Library