በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፍቅር ጭፍን ጥላቻን ያሸንፋል

ፍቅር ጭፍን ጥላቻን ያሸንፋል

ፍቅር ጭፍን ጥላቻን ያሸንፋል

“በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ ዓይነት ሃይማኖታዊ ማኅበረሰብ ብቅ አለ፦ ይህ ማኅበረሰብ ብሔራዊ ስሜትን የሚያመልክ አንድ አገር ሳይሆን ማኅበራዊም ሆነ የዘርና የጎሳ ልዩነት የማይገድበው በፈቃደኝነት የተመሠረተ ቡድን ነው፦ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በመካከላቸው ልዩነት ሳይፈጠር አምላካቸውን ያመልካሉ።”—ኤ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቺያኒቲ፣ በፖል ጆንሰን

እውነተኛው ክርስትና በመላው የሮም ግዛት ሲሰራጭ ሰዎች አንድ አስገራሚ ነገር መመልከት ቻሉ፤ ይኸውም እውነተኛ ሰላምና አንድነት በሰፈነበት መንገድ አብሮ መኖርን የተማረ ዓለም አቀፋዊ መንፈሳዊ ቤተሰብ ነው። ይህ “ቤተሰብ” እንዲህ ዓይነት ሰላም እንዲኖረው ያስቻለው ሚስጥር እውነተኛ ፍቅር ነው፤ በአባላቱ መካከል ያለው ይህ ዓይነቱ ፍቅር ከአምላክ በተማሩት መሠረታዊ ሥርዓቶች እንጂ በስሜታዊነት ላይ የተመሠረተ አልነበረም።

እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ኢየሱስ ክርስቶስ በቃልም ሆነ በድርጊት ያስተማረ ሲሆን እሱ ራሱ የጭፍን ጥላቻ ዒላማ ነበረ። (1 ጴጥሮስ 2:21-23) ለዚህም አንደኛው ምክንያት ኢየሱስ የመጣው ከገሊላ መሆኑ ነው፤ አብዛኞቹ የገሊላ ሰዎች ገበሬዎችና ዓሣ አጥማጆች ስለነበሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ይንቋቸው ነበር። (ዮሐንስ 7:45-52) በተጨማሪም፣ ድንቅ መምህር የነበረው ኢየሱስ በተራው ሕዝብ ይወደድና ይከበር ነበር። በዚህም ምክንያት የሃይማኖት መሪዎቹ በጣም ቀኑበት፤ በመሆኑም ስለ እሱ ውሸት ከማሰራጨትም አልፈው ሊገድሉት አሴሩ!—ማርቆስ 15:9, 10፤ ዮሐንስ 9:16, 22፤ 11:45-53

ሆኖም ኢየሱስ “በክፉ ፋንታ ክፉ [አልመለሰም]።” (ሮም 12:17) ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ፈሪሳውያን (ኢየሱስን ይቃወመው የነበረው የአይሁድ ሃይማኖታዊ ወገን አባላት) በግለሰብ ደረጃ ወደ እሱ ቀርበው በቅንነት ጥያቄ ሲያቀርቡለት በደግነት መልስ ይሰጣቸው ነበር። (ዮሐንስ 3:1-21) እንዲያውም ኢየሱስ በመጠኑም ቢሆን ለእሱ ጭፍን ጥላቻ የነበረውን አንድ ፈሪሳዊ ጨምሮ ከፈሪሳውያን ጋር አብሮ ተመግቧል። ፈሪሳዊው ለኢየሱስ ጭፍን ጥላቻ እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው? በዚያ ዘመን የእንግዶችን እግር ማጠብ የተለመደ ባሕል ቢሆንም ፈሪሳዊው ግን ይህን በማድረግ ለኢየሱስ አክብሮት እንዳለው አላሳየም። ታዲያ ኢየሱስ በዚህ ተቀየመ? በፍጹም። እንዲያውም በዚያ ምሽት ስለ ርኅራኄና ይቅር ባይነት ግሩም ትምህርት ሰጥቷል።—ሉቃስ 7:36-50፤ 11:37

ኢየሱስ የተናቁትን ይወድ ነበር

በጣም ከታወቁት የኢየሱስ ምሳሌዎች አንዱ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረው ሲሆን በምሳሌው ላይ ሳምራዊው ሰው ተደብድቦና ተዘርፎ የነበረው አይሁዳዊ የሚያስፈልገውን እንክብካቤ እንዲያገኝ እንዳደረገ ተገልጿል፤ ሳምራዊው ይህን ያደረገው በራሱ ወጪ ነበር። (ሉቃስ 10:30-37) ሳምራዊው ያደረገው ነገር የላቀ ግምት የሚሰጠው ለምንድን ነው? በገሐዱ ዓለም አይሁዳውያንና ሳምራውያን እርስ በርስ ይናናቁ ስለነበር ነው። እንዲያውም “ሳምራዊ” የሚለው ስያሜ አብዛኛውን ጊዜ አይሁዳውያን ንቀትን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት አጠራር ነበር፤ ኢየሱስንም እንኳ ለመቃወም በዚህ ስያሜ ተጠቅመዋል። (ዮሐንስ 8:48) ከዚህ አንጻር፣ ኢየሱስ ለሰዎች አድሎ የሌለበት ፍቅር ስለማሳየት ለማስተማር የተጠቀመበት ይህ ምሳሌ ኃይለኛ መልእክት የያዘ ነበር።

ኢየሱስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ የሆነ ሳምራዊ ሰውን በመፈወስ የተናገረውን ነገር በተግባር በማዋል ምሳሌ ሆኗል። (ሉቃስ 17:11-19) ከዚህም በላይ ኢየሱስ አድናቂ የሆኑ ሌሎች ሳምራውያንን አስተምሯል፤ አልፎ ተርፎም ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ረጅም ጭውውት ማድረጉ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ነገር ነው። (ዮሐንስ 4:7-30, 39-42) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ወግ አጥባቂ የሆኑት የአይሁድ ረቢዎች ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ይቅርና የቅርብ ዘመዳቸውም እንኳ ብትሆን ከማንኛዋም ሴት ጋር በአደባባይ አይነጋገሩም ነበር!

ይሁንና አምላክ፣ በውስጡ ያለውን ጭፍን ጥላቻ ለማስወገድ የሚታገልን ሰው የሚመለከተው እንዴት ነው? ለዚህ ጥያቄም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጽናና መልስ ይሰጣል።

አምላክ ይታገሠናል

በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ አይሁዳውያን ያልነበሩ በርካታ ሰዎች አማኞች እየሆኑ ሲመጡ ብዙ አይሁድ ክርስቲያኖች ለረጅም ጊዜ በውስጣቸው የነበረው ጭፍን ጥላቻ መጀመሪያ ላይ ተጽዕኖ አድርጎባቸው ነበር። መከፋፈልን ሊያስከትል ይችል የነበረውን ይህን ጉዳይ በተመለከተ ይሖዋ አምላክ ምን አደረገ? የክርስቲያን ጉባኤን በትዕግሥት አስተማረው። (የሐዋርያት ሥራ 15:1-5) አምላክ ጉዳዩን በትዕግሥት መያዙም ጥሩ ፍሬ አፍርቷል፤ በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ክርስቲያኖች ‘ማኅበራዊም ሆነ የዘርና የጎሳ ልዩነት ሳይገድባቸው’ በመካከላቸው አንድነት እንዲሰፍን ማድረግ ችለው ነበር። በዚህም የተነሳ “ጉባኤዎቹ በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።”—የሐዋርያት ሥራ 16:5

ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ጭፍን ጥላቻ በውስጥህ ካለ ተስፋ አትቁረጥ፤ ከዚህ ይልቅ ‘በእምነት መለመኑን ለሚቀጥል’ ሁሉ ጥበብና የመንፈስ ጥንካሬን በልግስና በሚሰጠው አምላክ መተማመንህን ቀጥል። (ያዕቆብ 1:5, 6) በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች መጀመሪያ ላይ የተጠቀሱትን ጄኒፈርን፣ ቲሞቲን፣ ጆንን እና ኦልጋን ታስታውሳቸዋለህ? ጄኒፈር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስትገባ በመንፈሳዊ እድገት አድርጋ ስለነበር ዘሯንና ቁመናዋን በተመለከተ የሚሰነዘሩባትን ስድቦች በቸልታ ማለፍ ተምራ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አብረዋት የሚማሩት ልጆች አንዲትን ተማሪ ሲሰድቧት ጄኒፈር የተከላከለችላት ከመሆኑም ሌላ አጽናንታታለች።

ቲሞቲ የክፍሉ ልጆች የእሱን ዘር የሚያንቋሽሽ ነገር እየተናገሩ ሲያፌዙበት ስሜቱን እንዲቆጣጠር የረዳው ምን ነበር? እንዲህ ይላል፦ “በይሖዋ አምላክ ስም ላይ ነቀፌታ እንዳላመጣ እጠነቀቅ ነበር። በተጨማሪም ‘ክፉን በመልካም ማሸነፍ’ እንጂ በክፉ መሸነፍ እንደሌለብን የሚናገረውን ምክር ዘወትር አስታውስ ነበር።”—ሮም 12:21

ጆን ከሃውሳ ጎሳ በሆነው የክፍሉ ልጅ ላይ የነበረውን ጭፍን ጥላቻ አስወገደ። እንዲህ ብሏል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለሁ የሃውሳ ጎሳ አባላት ከሆኑ ተማሪዎች ጋር ጓደኝነት መሠረትኩ። ከእነዚህ ልጆች መካከል ከአንዱ ጋር የቡድን ሥራ እንድንሠራ ተመደብን፤ አብረን ስንሠራ በጣም ተግባባን። አሁን በሰዎች ዘር ወይም ጎሳ ላይ ትኩረት ሳላደርግ በግለሰብ ደረጃ ማንነታቸውን ለመመልከት እጥራለሁ።”

ኦልጋና ሚስዮናዊ ጓደኛዋ በጥላቻ የተሞሉ ተቃዋሚዎች ስደት ቢያደርሱባቸውም ፈርተው ወደኋላ አላሉም፤ ከዚህ ይልቅ በከተማዋ ከሚኖሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ውሎ አድሮ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት እንደሚቀበሉ በመተማመን በጽናት መስበካቸውን ቀጠሉ። በእርግጥም ብዙዎች መልእክታቸውን ተቀብለዋል። ኦልጋ እንዲህ ብላለች፦ “ሃምሳ ከሚያህሉ ዓመታት በኋላ አንድ ሰው ወደ እኔ መጣና የሚያምር ቦርሳ ሰጠኝ። በቦርሳው ውስጥ እንደ ጥሩነት፣ ደግነት፣ ፍቅርና ሰላም ያሉት ክርስቲያናዊ ባሕርያት የተቀረጹባቸው ትንንሽ ድንጋዮች ነበሩ። ይህ ሰው በዚያን ጊዜ ድንጋይ ከወረወሩብኝ ልጆች አንዱ እንደነበረና አሁን ግን ክርስቲያን ወንድሜ እንደሆነ ነገረኝ። ከዚያም እሱና ሚስቱ ድንጋዮችን ከያዘው ቦርሳ በተጨማሪ ብዛት ያላቸው ነጭ ጽጌረዳ አበቦችን ሰጡኝ።”

ጭፍን ጥላቻና መድሎ ፈጽሞ የማይኖሩበት ጊዜ ይመጣል!

በቅርቡ ጭፍን ጥላቻና መድሎ ይወገዳሉ። እንዴት? መጀመሪያ ነገር፣ መላዋን ምድር የሚገዛት ‘ዐይኑ እንዳየ እንደማይፈርድ’ በተግባር ያሳየው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ይሆናል። (ኢሳይያስ 11:1-5) በተጨማሪም በዚያን ጊዜ የኢየሱስ ምድራዊ ተገዢዎች በሙሉ ከእሱና ከአባቱ ከይሖዋ አምላክ ስለሚማሩ የኢየሱስን አስተሳሰብ ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባርቃሉ።—ኢሳይያስ 11:9

ከአምላክና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት አሁንም እየተሰጠ ሲሆን ይህም የአምላክን ሕዝቦች ፍጹም አዲስ በሆነው ሥርዓት ውስጥ ለሚኖራቸው ሕይወት እያዘጋጃቸው ነው። ታዲያ አንተም በነፃ ከሚካሄደው ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም ለምን ተጠቃሚ አትሆንም? * አዎን፣ አምላክ አያዳላም፤ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑ እንዲሁም የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ይፈልጋል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.18 መጽሐፍ ቅዱስን በሚመችህ ጊዜና ቦታ በነፃ ማጥናት የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ ወዳለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አለዚያም በገጽ 5 ላይ ከተጠቀሱት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ወደ አንዱ መጻፍ ትችላለህ። ወይም ደግሞ www.watchtower.org የሚለውን ድረ ገጽ በመመልከት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት ትችላለህ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በቅርቡ ጭፍን ጥላቻና መድሎ የሰው ልጆችን ማሠቃየታቸው ያበቃል

[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሕይወታችንን ልንመራባቸው የሚገቡ ከአምላክ የተሰጡ መመሪያዎች

“ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። . . . ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።” (ሮም 12:17-21) ከዚህ ጥቅስ ምን እንማራለን? ሌሎች ክፉ ነገር ሲፈጽሙብህ መልካም ምላሽ መስጠትን ተማር። ኢየሱስ ክርስቶስ “ያለ ምክንያት ጠሉኝ” በማለት ተናግሯል። ሆኖም አፀፋውን አልመለሰም።—ዮሐንስ 15:25

“አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።” (ገላትያ 5:26) ምቀኝነትና ተገቢ ያልሆነ ኩራት በመንፈሳዊ ጎጂ ሲሆኑ ብዙውን ጊዜም ወደ ቂምና ጭፍን ጥላቻ ሊያመሩ ይችላሉ።—ማርቆስ 7:20-23

“እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል።” (ማቴዎስ 7:12) ‘እኔ ምን እንዲደረግልኝ እፈልጋለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ሌሎች በየትኛውም ዕድሜ ላይ ይገኙ እንዲሁም ምንም ዓይነት የቆዳ ቀለም፣ ቋንቋ ወይም ባሕል ይኑራቸው አንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን አድርግላቸው።

“ክርስቶስ እኛን እንደተቀበለን ሁሉ . . . እናንተም አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ።” (ሮም 15:7) የተለየ አስተዳደግና ባሕል ያላቸውን ሰዎች፣ በተለይም እንደ አንተ የአምላክ አገልጋዮች የሆኑትን ቀርበህ ይበልጥ ለማወቅ ጥረት ታደርጋለህ?—2 ቆሮንቶስ 6:11

“አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል።” (መዝሙር 27:10) ሌሎች ለአንተ ያላቸው አመለካከት ምንም ይሁን፣ ለአምላክ ታማኝ እስከሆንክ ድረስ እሱ ፈጽሞ አይተውህም።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ ደግ ሳምራዊ፣ የተዘረፈውን አይሁዳዊ ረዳው