በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምን ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል?

ምን ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል?

ምን ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል?

‘በአሁኑ ጊዜ ያሉ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች ቀደም ባሉት ዘመናት ከነበሩት ይበልጥ ከባድ ናቸው?’ ተብለህ ብትጠየቅ ምን መልስ ትሰጣለህ? መልስህ ‘አይደሉም’ የሚል ከሆነ በዛሬው ጊዜ ያሉት ወጣቶች በየትኛውም ዘመን ከነበሩት ወጣቶች ይበልጥ ደስተኞች እንደሆኑ ሊሰማህ ይችላል።

በብዙ አገሮች ከዚህ ቀደም የወጣቶችን ጤንነት ያቃውሱ እንዲሁም ሕይወታቸውን ይቀጥፉ የነበሩትን በሽታዎች በሕክምና መቆጣጠር ተችሏል። በአሁኑ ጊዜ በቴክኖሎጂው መስክ የተደረገው እድገት የቀድሞው ትውልድ አስቦት እንኳ የማያውቀው ዓይነት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያና መጫወቻ ለማምረት አስችሏል። በኢኮኖሚው መስክ የተደረገው እድገትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦችን ከድህነት አላቋቸዋል። በእርግጥም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወላጆች፣ እነሱ ያላገኙትን የኑሮ ደረጃና የትምህርት አጋጣሚ ልጆቻቸው እንዲያገኙ ለማድረግ ጠንክረው ይሠራሉ።

በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች በብዙ አቅጣጫዎች የተሻለ አጋጣሚ እንዳላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ በዚያው መጠን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ለዚህ አንዱ ምክንያት በዛሬው ጊዜ የሰው ዘር የሚኖረው መጽሐፍ ቅዱስ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ብሎ በሚጠራው ዘመን ላይ መሆኑ ነው። (ማቴዎስ 24:3) ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በዚህ ዘመን ከፍተኛ ማኅበራዊ አለመረጋጋት እንደሚኖር በትክክል ተንብዮአል። (ማቴዎስ 24:7, 8) መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ዘመን ‘የመጨረሻዎቹ ቀኖች’ በማለት የሚጠራው ሲሆን “ለመቋቋም የሚያስቸግር” ማኅበራዊ ሁኔታ በሁሉም ስፍራ እንደሚኖርም ገልጿል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በዛሬው ጊዜ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች እያጋጠሟቸው ካሉት ለመቋቋም የሚያስቸግሩ ሁኔታዎች ውስጥ አንዳንዶቹን እንመልከት።

ፈተና 1

ለብቻ የመሆን አዝማሚያ እየጨመረ መሄዱ

ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና መጽሔቶች ወጣቶች ሁልጊዜ ከአብሮ አደግ ጓደኞቻቸው ጋር እንደማይለያዩና ትምህርት ጨርሰው ትልልቅ ሰዎች ከሆኑም በኋላ ጓደኝነታቸው እንደሚቀጥል አድርገው ያሳያሉ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ብዙ ወጣቶች ግን እውነታው ከዚህ የተለየ ነው።

በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ውጤት የገመገሙት ባርባራ ሽናይደርና ዴቪድ ስቲቨንሰን የተባሉት ተመራማሪዎች “ረዘም ላለ ጊዜ ከአንድ የቅርብ ጓደኛ ወይም ከተወሰኑ ጓደኞች ጋር ግንኙነታቸው ሳይቋረጥ የቀጠሉት ተማሪዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በጣም ጥቂቶች እንደሆኑ” ደርሰውበታል። ብዙ ወጣቶች “ከሰዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንደማይመሠርቱ እንዲሁም ችግራቸውን ለማወያየት ወይም ሐሳባቸውን ለማካፈል የሚቀሏቸው የቅርብ ጓደኞቻቸው በጣም ጥቂት እንደሆኑ” ሽናይደርና ስቲቨንሰን ይናገራሉ።

ጓደኞች ያሏቸው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችም ቢሆኑ ከጓደኞቻቸው ጋር የሚያሳልፉት ብዙ ጊዜ የላቸውም። በዚህ መስክ በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ሰፊ ጥናት እንዳመለከተው በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙት አብዛኞቹ ወጣቶች ከጓደኞቻቸው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው በመጨዋወት የሚያሳልፉት 10 በመቶ የሚሆነውን ጊዜያቸውን ሲሆን ከእንቅልፍ ሰዓት ውጪ ካላቸው ጊዜ እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን የሚያሳልፉት ብቻቸውን ነው፤ ይህም ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር ከሚያሳልፉት ጊዜ ይበልጣል። ብቻቸውን ይበላሉ፣ ብቻቸውን ይጓዛሉ፣ ብቻቸውን ይዝናናሉ።

የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች በብዛት መገኘት ደግሞ ለብቻ የመሆን ዝንባሌ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ታይም መጽሔት በ2006 እንደዘገበው በአሜሪካ ከ8 ዓመት እስከ 18 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ወጣቶች በየቀኑ በአማካይ ለስድስት ሰዓት ተኩል ያህል ዓይናቸው ቴሌቪዥን ላይ ተተክሎ ወይም ጆሯቸው ላይ ማዳመጫ ሰክተው እንዲሁም እጆቻቸው የቪዲዮ ጨዋታዎችን በመጫወት ተጠምደው ያሳልፋሉ። *

እርግጥ ነው፣ ሙዚቃ በማዳመጥ ወይም በጨዋታ በርካታ ሰዓታትን በማሳለፍ ረገድ ይህ ትውልድ የመጀመሪያው አይደለም። (ማቴዎስ 11:16, 17) ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ወጣቶች ከቤተሰባቸው ጋር ከመጨዋወት ይልቅ በጣም ብዙ ሰዓታት የሚያሳልፉት ከኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ጋር መሆኑ ጉዳት ሊያስከትልባቸው ይችላል። ተመራማሪዎቹ ሽናይደርና ስቲቨንሰን እንደገለጹት “ወጣቶች፣ ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ እንደሆነ፣ ደስታ እንደሚርቃቸው፣ በሚሠሩት ነገር ብዙም እንደማይደሰቱና ብቻቸውን ሲሆኑ ንቁ እንደማይሆኑ ይናገራሉ።”

ፈተና 2

የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ጫና የሚደረግባቸው መሆኑ

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሌላው ቀርቶ ከዚያ በታች ባለው ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች እንኳ የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ከፍተኛ ጫና ይደረግባቸዋል። በአውስትራሊያ የሚኖር ናታን የተባለ ወጣት “በትምህርት ቤት የማውቃቸው አብዛኞቹ ልጆች የጾታ ግንኙነት መፈጸም የጀመሩት ከ12 እስከ 15 ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ ነው” ብሏል። በሜክሲኮ የምትኖር ቪንቤይ የተባለች አንዲት ወጣት ደግሞ ምንም ዓይነት ስሜታዊ ቅርርብ ሳይኖር የጾታ ግንኙነት መፈጸም በትምህርት ቤቷ ባሉ ወጣቶች ዘንድ በጣም የተለመደ ነገር እንደነበረ ትናገራለች። “የጾታ ግንኙነት የማይፈጽሙ ወጣቶች እንደ ልዩ ፍጥረት ይታያሉ” ብላለች። በብራዚል የምትኖረው አና የተባለች የ15 ዓመት ወጣት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “በአጋጣሚ በተገናኙ ሰዎች መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነት በዕድሜ እኩዮቼ ዘንድ በጣም የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኔን አንድ ጊዜ መግለጽ ብቻ አይበቃም። የሚቀርብላችሁን ጥያቄ እንደማትቀበሉ በተደጋጋሚ መናገር ይኖርባችኋል።”

በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ተመራማሪዎች በ12 እና በ19 ዓመት መካከል ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙና የተለያየ አስተዳደግ ባላቸው አንድ ሺህ ወጣቶች ላይ ጥናት አካሂደው ነበር። ተመራማሪዎቹም ከእነዚህ ወጣቶች መካከል ወደ 50 በመቶ የሚጠጉት በሆነ መልኩ አዘውትረው የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ መሆኑን ደርሰውበታል። የጾታ ግንኙነት ከሚፈጽሙት ወጣቶች መካከል ከ20 በመቶ የሚበልጡት ዕድሜያቸው ገና 12 ዓመት ነበር! የጥናቱ መሪ የሆኑት ዶክተር ዲላን ግሪፊት “ቤተሰብ፣ ቤተ ክርስቲያንና ሌሎች ተቋማት ያደርጉት የነበረው ቁጥጥር መቅረቱ በወጣቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል” ሲሉ ተናግረዋል።

የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወጣቶች በእርግጥ “ጉዳት” ደርሶባቸዋል? ሬክተር፣ ኖይዝና ጆንሰን የተባሉት ተመራማሪዎች በ2003 በታተመ አንድ ዘገባ ላይ እንደገለጹት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በሚፈጸም የጾታ ግንኙነት እንዲሁም በመንፈስ ጭንቀትና ራስን ለማጥፋት በመሞከር መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አለ። እነዚህ ተመራማሪዎች በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኙ 6,500 ወጣቶች ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ከመረመሩ በኋላ “የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ልጃገረዶች የጾታ ግንኙነት ከማይፈጽሙት ይልቅ በመንፈስ ጭንቀት የመጠቃት አጋጣሚያቸው በሦስት እጥፍ እንደሚበልጥ” ደርሰውበታል። እንዲሁም “የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ወንዶች ልጆች የጾታ ግንኙነት ካልፈጸሙት ጋር ሲወዳደሩ በመንፈስ ጭንቀት የመያዝ አጋጣሚያቸው በእጥፍ ይበልጣል።”

ፈተና 3

የቤተሰብ መፈራረስ

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ወጣቶች በቤተሰብ ሕይወታቸው ረገድ ፈጣን ለውጥ እያጋጠማቸው ከመሆኑም ሌላ የሥነ ምግባር እሴቶች ሲቀየሩ ተመልክተዋል። ዚ አምቢሸስ ጀነሬሽን—አሜሪካስ ቲንኤጀርስ፣ ሞቲቬትድ ባት ዳይሬክሽንለስ የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶችን ሕይወት በቀጥታ የሚነኩ ጉልህ የሆኑ በርካታ ሥነ ሕዝባዊ ለውጦች ተከስተዋል። የአብዛኛው የአሜሪካ ቤተሰብ አባላት ቁጥር እየቀነሰ በመሄዱ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች የሚኖሯቸው ወንድሞችና እህቶች ቁጥር ቀንሷል። ፍቺ እየጨመረ በመምጣቱ ብዛት ያላቸው ልጆች ከፊሉን የልጅነት ሕይወታቸውን የሚያሳልፉት ከአንደኛው ወላጃቸው ጋር ነው። እንዲሁም ከአሥራ ስምንት ዓመት ዕድሜ በታች የሆኑ ልጆች ያሏቸው በርካታ እናቶች ሥራ ስለሚውሉ በቤት ውስጥ ከልጆቹ ጋር የሚቆይ ትልቅ ሰው ላይኖር ይችላል።”

ልጆች የሚኖሩት ከአንድ ወላጅ ጋርም ይሁን ከሁለቱም ወላጆቻቸው ጋር፣ ብዙዎቹ ወላጆቻቸውን በጣም በሚፈልጓቸው ወቅት ከእነሱ እንደራቁ ይሰማቸዋል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ በሚገኙ 7,000 ወጣቶች ላይ ለዓመታት የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው አብዛኞቹ ወጣቶች ወላጆቻቸው አፍቃሪና ተግባቢ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ያም ሆኖ “ችግር ሲገጥማቸው [ከወላጆቻቸው] ልዩ ትኩረትና እርዳታ እንደሚያገኙ የተናገሩት አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ብቻ ናቸው።” ጥናቱ አክሎ እንዳመለከተው “በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ብዙዎቹ ወጣቶች አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ጣልቃ በመግባት አይረዷቸውም።”

በጃፓን በቁሳዊ ነገሮች ስኬታማ ለመሆን በሚደረገው ጥረት የተነሳ በአንድ ወቅት የነበረው ጠንካራ የቤተሰብ ትስስር እየተሸረሸረ ሄዷል። የኅብረተሰብ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ዩኮ ካዋኒሺ የተባሉ ሴት እንዲህ ብለዋል፦ “በዛሬው ጊዜ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች ያሏቸው አብዛኞቹ ወላጆች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የነበረው ልጆች በብዛት የተወለዱበት ትውልድ ያፈራቸው ናቸው፤ እነዚህ ወላጆች ያደጉት አዲስ ሥነ ምግባራዊ እሴቶች ባሉት ማለትም ለኢኮኖሚያዊ ስኬትና ለቁሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ በሚሰጥ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው።” ታዲያ እንዲህ ያሉት ወላጆች ለልጆቻቸው ምን ዓይነት የሥነ ምግባር እሴቶችን ያስተላልፋሉ? ካዋኒሺ እንዲህ ብለዋል፦ “በዛሬው ጊዜ ያሉት ብዙዎቹ ወላጆች በዋነኛነት የሚያሳስባቸው ልጆቻቸው በትምህርት ስኬታማ መሆናቸው ነው። ልጆቻቸው ትምህርታቸውን እስካጠኑ ድረስ በቤት ውስጥ ሌሎች ነገሮች በሙሉ የሚሰጣቸው ሁለተኛ ደረጃ ነው፤ አለዚያም እስከ ጭራሹ ትኩረት ላይሰጣቸው ይችላል።”

በቁሳዊ ነገሮች ስኬታማ በመሆንና በትምህርት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ሚዛናዊ ያልሆነ ትኩረት መደረጉ በወጣቶች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? በጃፓን የመገናኛ ብዙኃን ኪሬሩ ስለሚባል ሁኔታ ብዙ ጊዜ ሲጠቅሱ ይሰማል፤ ይህ ቃል የሚሠራበት ወጣቶች በደንብ እንዲሠሩ በሚደረግባቸው ጫና የተነሳ በድንገት በቁጣ የሚገነፍሉበትን ሁኔታ ለመግለጽ ነው። ካዋኒሺ “ልጆች ከቁጥጥር ውጭ በመሆን የቂልነት ሥራ የሚሠሩት ቤተሰባቸው የእነሱን ምግባር የመቆጣጠር ሥልጣን እንዳለው ስለማይገነዘቡ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

ብሩሕ ተስፋ እንዲኖረን የሚያደርግ ምክንያት

በእርግጥም የምንኖረው ‘ለመቋቋም በሚያስቸግር’ ዘመን ውስጥ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ዘመን የሚኖሩ ሰዎች እየጨመረ የሚሄድ መከራ እንደሚደርስባቸው የሚገልጽ ትንቢት በመናገር ብቻ አያበቃም።

መጽሐፍ ቅዱስ ወጣቶች ሕይወታቸውን እንዴት ማሻሻል እንደሚችሉ የሚገልጹ ጠቃሚ ምክሮች ይሰጣል። የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው ይሖዋ አምላክ፣ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች መቋቋም ስለሚችሉበት መንገድ ለማስተማር ልባዊ ፍላጎት አለው። (ምሳሌ 2:1-6) ጥሩ ሕይወት እንዲኖራቸው ይፈልጋል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ “ብስለት ለሌላቸው አስተዋይነትን፣ በዕድሜ ለጋ ለሆኑት ዕውቀትንና ልባምነትን [ይሰጣል]።” (ምሳሌ 1:4) የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ወጣቶችን ሊረዱ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 በጃፓን፣ ወጣቶች ከሌሎች ተገልለው በክፍላቸው ውስጥ ብቻቸውን ማሳለፋቸው በጣም የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ እንዲህ ያሉት ወጣቶች ሂኪኮሞሪ የሚል ስም ተሰጥቷቸዋል። አንዳንድ ሰዎች በጃፓን ውስጥ ከ500,000 እስከ 1,000,000 የሚደርሱ ሂኪኮሞሪዎች እንደሚገኙ ይገምታሉ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ ጥናት እንደሚያሳየው የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ልጃገረዶች የጾታ ግንኙነት ከማይፈጽሙት ይልቅ በመንፈስ ጭንቀት የመጠቃት አጋጣሚያቸው በሦስት እጥፍ ይበልጣል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ጎጂ ባሕርያት

የብሪታንያ መንግሥት በ2006 ያወጣው ዘገባ እንደገለጸው ከ11 እስከ 15 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ኮኬይን የሚባለውን አደገኛ ዕፅ የሚጠቀሙ ወጣቶች ቁጥር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ጨምሯል። ወደ 65,000 የሚጠጉ ወጣቶች ይህን ዕፅ ወስደው እንደሚያውቁ ተናግረዋል። በሆላንድ ከ16 እስከ 24 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙት ወጣቶች መካከል ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት በተወሰነ መጠን የአልኮል መጠጥ ሱሰኞች እንደሆኑ ወይም ከአልኮል መጠጥ ጋር የተያያዘ ሕመም እንዳለባቸው ይነገራል።

ሌሎች ብዙ ወጣቶች ደግሞ የውስጥ ጭንቀታቸውን የሚገልጹት አካላቸውን በቀጥታ በሚጎዳ መንገድ ነው። እነዚህ ወጣቶች የራሳቸውን ሰውነት ይቆርጣሉ፣ ይነክሳሉ ወይም ያቃጥላሉ። ሌን ኦስቲን እና ጁሊ ኮርተም የተባሉ ተመራማሪዎች እንደገለጹት “ሦስት ሚሊዮን አሜሪካውያን በራሳቸው ሰውነት ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ እንዲሁም በአሥራዎቹ ዕድሜ ከሚገኙ 200 ወጣቶች ውስጥ አንዱ በራሱ ሰውነት ላይ ጉዳት የማድረስ ሥር የሰደደ ችግር እንዳለበት ይገመታል።”

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙ ወጣቶች የልባቸውን ሊያዋዩአቸው የሚችሉ የቅርብ ጓደኞች የሏቸውም