በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በአሁኑ ጊዜ ከሚከሰቱት አሥር አደጋዎች መካከል ዘጠኙ ከአየር ጠባይ ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ባለፉት ሃያ ዓመታት በየዓመቱ የተመዘገቡት አደጋዎች ቁጥር ከ200 ተነስቶ ከ400 በላይ በመሆን በእጥፍ አድጓል።”—ጆን ሆልምስ፣ የተባበሩት መንግሥታት የእርዳታና ፈጥኖ ደራሽ ቢሮ ዋና ጸሐፊ

ለአገሬው ተወላጆች ሰብዓዊ መብታቸውን ማሳወቅ

የተባበሩት መንግሥታት፣ የአገሬው ተወላጆችን ሰብዓዊ መብት አስመልክቶ በ2007 ያጸደቀው አዋጅ በአሁኑ ጊዜ በሜክሲኮ በስፋት በሚነገሩት ማየ እና ናዋትል በተባሉ ሁለት ቋንቋዎች ተተርጉሟል። ኤል ዩኒቨርሳል የተሰኘው ጋዜጣ “[በሜክሲኮ] የሚኖሩ ቢያንስ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች መብታቸውን አያውቁም” በማለት ዘግቧል። “በመሆኑም ብዙውን ጊዜ በደል እየተፈጸመባቸው ስለመሆኑ የሚያውቁት ነገር የለም።” በሁለቱ ቋንቋዎች የተተረጎመው አዋጅ እነዚህ ሕዝቦች መሠረታዊ የሆኑትን ሰብዓዊ መብቶቻቸውን የሚያስከብሩበት መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል ተብሎ ይታመናል።

ድንግልናን መሸጥ

ኒውስዊክ ፖልስካ የተሰኘው መጽሔት እንደዘገበው አንዳንድ ፖላንዳዊ ወጣቶች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸው የማኅበራዊ ኑሮ ጠበብቶችን አስደንግጧቸዋል። በዢሎና ጉራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ምሑር የሆኑት ያፄክ ኩዥንፓ “ወጣቶች ‘ሁሉም ነገር የሚሸጥ ነው’ የሚል ቀላል መልእክት ከሁሉም አቅጣጫ ይደርሳቸዋል” በማለት ተናግረዋል። እንዲያውም ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ወጣቶች በኢንተርኔት ላይ ድንግልናቸውን ለጨረታ እስከ ማቅረብ ደርሰዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ወጣቶች እንዲህ ዓይነቱን ምርጫ ማድረጋቸው ውሎ አድሮ ከባድ ዋጋ ያስከፍላቸዋል። “እንዲህ ያለው ውሳኔ በአንዲት ወጣት የወደፊት ሕይወት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከመሆኑም ሌላ ጋብቻ በምትመሠርትበት ጊዜ ከትዳር ጓደኛዋ ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ ችግር ያጋጥማታል” በማለት ኩዥንፓ ተናግረዋል።

በአንድ ወቅት አማዞን ውስጥ ከተማ ነበር

ሰው ረግጦት አያውቅም ተብሎ ይታመን የነበረው በደቡባዊ አማዞኒያ የሚገኘው ሰፊ ደን በአንድ ወቅት “በትላልቅ ግንቦች በተከበበ” ከተማ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች ሳይሰፍሩበት አይቀርም። ወደዚህ ድምዳሜ የደረሱት በማቶ ግሮሶ፣ ብራዚል ውስጥ የሚሠሩት ስለ ሰው ዘር አመጣጥ የሚያጠኑ ምሑራን ናቸው። እነዚህ ምሑራን “የቅርብ ትስስር የነበራቸው ነዋሪዎች የሚኖሩባቸውና የግንብ አጥሮች ያሏቸው ከተሞችንና ትንንሽ መንደሮችን” በዚህ አካባቢ አግኝተዋል፤ ከተሞቹ 30,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ተቆርቁረው እንደነበር የሚገመት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ በደን ተሸፍነዋል። ከከተሞቹ ውስጥ አንዳንዶቹ 60 ሄክታር የሚያህል የቆዳ ስፋት አላቸው። ስለ ሰው ዘር አመጣጥ የሚያጠኑት እነዚህ ምሑራን የሚሠሩበት የፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት ከተሞቹ እንደተቆረቆሩ የሚታሰበው “ከ1250 እስከ 1650 ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን አብዛኞቹን ነዋሪዎች ለህልፈተ ሕይወት የዳረጉት አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎችና እነሱ ይዘዋቸው የመጡት በሽታዎች ሳይሆኑ አይቀሩም።”

ተክሎች ከቀዶ ሕክምና ቶሎ ለማገገም ይረዳሉ

ተፈጥሮን መመልከት ውጥረት እንደሚቀንስ፣ ጥሩ ስሜት እንደሚፈጥርና የታመሙ ሰዎችን ሥቃይ እንደሚያስታግስ ከረዥም ጊዜ በፊት ጀምሮ ይታመን ነበር። በቅርብ የተደረገ አንድ ጥናት የዚህን እውነተኝነት አረጋግጧል። ሳይንስ ዴይሊ እንደገለጸው “ሕሙማን በሆስፒታል ውስጥ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ እንዲተኙ በተደረጉባቸው በአንዳንዶቹ ክፍሎች ውስጥ ተክል ያለ ሲሆን በሌሎቹ ውስጥ ደግሞ ምንም ተክል አልነበረም።” ተክል ባለበት ክፍል ውስጥ የተኙት ሕሙማን ተክል በሌለበት ክፍል ውስጥ ከተኙት ሰዎች በተሻለ ሥቃዩ ቀንሶላቸዋል፣ ያስፈለጋቸው የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት አነስተኛ ነበር፣ የልብ ምታቸውና የደም ግፊታቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል እንዲሁም በተኙበት ክፍል ደስተኞች ናቸው። ተክሎች ባሉበት ክፍል ከተኙት ውስጥ 93 በመቶ የሚሆኑት ክፍላቸውን “እጅግ ተስማሚ” ያደረጉት ተክሎቹ እንደሆኑ ተናግረዋል።