ወጣቶች እርዳታ ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?
ወጣቶች እርዳታ ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?
ያለንበት ዓለም ሁሉም ነገር የተመቻቸበት ቢሆን ኖሮ ሁሉም ወላጆች ለልጆቻቸው ያላሰለሰ ፍቅራዊ መመሪያና ሥልጠና መስጠት ይችሉ ነበር። ከልጆቻቸው ጋር ያወሩ፣ መጽሐፍ ያነቡላቸው፣ አብረዋቸው ይበሉ እንዲሁም ስሜታቸውን ይረዱላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ወላጆች ፍጹም አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል” ብሎ በትክክል ይናገራል።—ሮም 3:23
ወጣት ከሆንክ የቤተሰብ ሕይወትህ ጥሩ እንዳልሆነ ይሰማህ ይሆናል፤ እንዳልከውም ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ጭንቀትህን ለመቀነስና ደስታህን ለመጨመር ልታደርገው የምትችለው ብዙ ነገር አለ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ ሊረዳህ የሚችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ልብ በል።
የመፍትሔ ሐሳብ 1
ለብቻህ ከመሆን ይልቅ ጓደኞች አፍራ
“ወዳጅነትን የማይፈልግ ሰው የራሱን ፍላጎት ብቻ ይከተላል፤ ቅን የሆነውን ፍርድ ሁሉ ይቃወማል።” (ምሳሌ 18:1) አንዳንድ ወጣቶች ከሰዎች ጋር ሲሆኑ ነፃነት ስለማይሰማቸው ቴሌቪዥን መመልከት ወይም የቪዲዮ ጨዋታዎችን መጫወት ይቀላቸዋል። ሌሎች ደግሞ እጅግ ዓይናፋሮች ስለሆኑ ራሳቸውን ከሰው ያገላሉ። ኤልዛቤት “አብሯት የኖረ ዓይናፋርነት” እንደነበረባት ትናገራለች። “የእኔ ዓይናፋርነት ከኃይለኛ ፍርሃት ጋር ይመሳሰላል። ሰዎችን መቅረብና ከእነሱ ጋር ማውራት በጣም ይከብደኛል” ትላለች።
ኤልዛቤት የዓይናፋርነትን ችግር መቋቋም የቻለችው እንዴት ነው? ኤልዛቤት የይሖዋ ምሥክር ናት፤ በመሆኑም ለአምላክ የምታቀርበው አምልኮ ክፍል በሆኑት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትራ ትገኛለች። እንዲህ ትላለች፦ “ዓይናፋር ብሆንም በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ አንድ ሰው የማነጋገር ግብ አወጣሁ። ይህን ሳላደርግ ከቀረሁ ተስፋ ላለመቁረጥ ጥረት አደርጋለሁ። ከዚህ ይልቅ ማከናወን በቻልኳቸው ነገሮች ላይ አተኩራለሁ። ሌሎችን ቀርቤ ማወቅ በእርግጥ እንደጠቀመኝ ተረድቻለሁ።”
ይበልጥ ልታውቃቸው የምትፈልጋቸውን ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ስም በማስታወሻህ ላይ ለምን አትመዘግብም? ከዚያም በቀጣዩ ሳምንት ወይም ሳምንታት ስለ እያንዳንዳቸው ከአሁን በፊት ያላወቅሃቸውን አዳዲስ ነገሮች ለማወቅ ግብ አውጣ። ቀጥለህ ደግሞ ለእያንዳንዳቸው በሚቀጥለው ወር ምን ጥሩ ነገር ልታደርግላቸው እንደምትችል ጻፍ፤ ያሰብከውንም ፈጽመው።—የሐዋርያት ሥራ 20:35
ችግሮችና ሰዎች አይድረሱብኝ የምትል ከሆነ ውሎ አድሮ ስለ ራስህ ከሚገባው በላይ ማሰብ ትጀምራለህ። በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ራሳችሁ ጉዳይ ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ጉዳይም ትኩረት ስጡ” በማለት ይመክረናል። (ፊልጵስዩስ 2:4) ከቤተሰብህ አባላትና በአካባቢህ ካሉ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት ይህንን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ካዋልህ ስለ ችግሮችህ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖርህና በተሻለ መንገድ መፍትሔ ልታገኝላቸው ትችላለህ።
የመፍትሔ ሐሳብ 2
ከጾታ ብልግና ሽሽ
“ከዝሙት ሽሹ። አንድ ሰው የሚፈጽመው ሌላ ኃጢአት ሁሉ ከአካሉ ውጪ ነው፤ ዝሙት የመፈጸም ልማድ ያለው ግን በራሱ አካል ላይ ኃጢአት እየሠራ ነው።” (1 ቆሮንቶስ 6:18) የጾታ ብልግና መፈጸም በሌሎች ወጣቶች ዘንድ በጣም የተለመደ ድርጊት በሆነበት በዚህ ዘመን አንተ በሌሎች ተጽዕኖ ተሸንፈህ በዚህ ተግባር ከመካፈል መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው?
በመጀመሪያ፣ ፈተና ሳያጋጥምህ ወይም ግፊት ሳይደረግብህ በፊት ይህን ጉዳይ በጥንቃቄ ልታስብበት ይገባል። ጥበብ የተሞላበት አንድ ምሳሌ “አስተዋይ . . . ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) በደቡብ አፍሪካ የምትኖረው ምባሊ የተባለች ወጣት እንደሚከተለው ብላለች፦ “በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለሁ አንድ የክፍሌ ልጅ የፍቅር ጓደኛው እንድሆን በተደጋጋሚ ይጠይቀኝ ነበር። ይህ ወጣት በጣም ቆንጆ ከመሆኑም ሌላ የፋሽን ሞዴልና የትምህርት ቤቱ የእግር ኳስ ተጫዋች ስለነበረ በክፍሌ ውስጥ የነበሩ ልጃገረዶች ከእሱ ጋር የፍቅር ጓደኝነት እንድመሠርት ገፋፉኝ። ልጁ ማራኪ እንደሆነ ቢሰማኝም የሥነ ምግባር አቋሜን ላለማበላሸት አስቀድሜ ወስኜ ነበር። እኩዮቼ በአጋጣሚ ካገኙት ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸም ያን ያህል ስህተት እንዳልሆነ ይሰማቸው ነበር። እኔ ግን ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለይቼ ስለማውቅ ይህ ዓይነቱ ፈተና ገና ሳያጋጥመኝ ምን ማድረግ እንደሚኖርብኝ አስቀድሜ ወስኜ ነበር።”
ሁለተኛ፣ አምላክ ላወጣቸው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ታማኝ እንድትሆን የእሱን እርዳታ ለማግኘት ጸልይ። በእንግሊዝ የምትኖር ማጊ የተባለች ወጣት እንደሚከተለው ብላለች፦ “ጸሎት፣ የጾታ ብልግና እንድፈጽም የሚደረግብኝን ግፊት ለመቋቋም የሚያስፈልገውን ጥንካሬ እንዳገኝ ይረዳኛል። ይህን ሁኔታ በራሴ መቋቋም እችላለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። በተጨማሪም ስለ ጉዳዩ ከወላጆቼ ጋር የምነጋገር ሲሆን አንዳንድ ጊዜም ከሌሎች የጎለመሱ ጓደኞቼ ጋር እወያይበታለሁ።
የመፍትሔ ሐሳብ 3
የወላጆችህን ስሜት ተረዳላቸው
“ሁላችሁም አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይኑራችሁ፣ የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፣ የወንድማማች መዋደድ ይኑራችሁ፣ ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ።” (1 ጴጥሮስ 3:8) ወላጆችህ ተለያይተው መኖራቸው ወይም መፋታታቸው እንዲሁም ሁለቱም ሙሉ ቀን ሥራ የሚውሉ መሆናቸው በአንተ ቁጥጥር ሥር አይደለም። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁኔታዎች ከወላጆችህ ጋር ያለህን ግንኙነት እንዲያበላሹት መፍቀድና አለመፍቀድ በተወሰነ መጠንም ቢሆን በቁጥጥርህ ሥር ነው። ጭንቀትህን መቀነስና ደስታህን መጨመር የምትችልበት አንዱ መንገድ ለወላጆችህ ማዘንና እየገጠሟቸው ያሉትን ችግሮች ለመረዳት መሞከር ነው።
አምበር የተባለች አንዲት ወጣት ይህን ምክር ተግባራዊ አድርጋለች። ከእናቷ ጋር ያላት ግንኙነት አንዳንድ ጊዜ በውጥረት፣ ባለመግባባትና በብስጭት የተሞላ እንደሚሆን ተናግራለች። ያም ሆኖ እንዲህ ትላለች፦ “እናቴ በሕይወቷ ውስጥ ብዙ ችግር አሳልፋለች። እኛን አራት ልጆቿን ብቻዋን አሳድጋለች። ምንጊዜም አንገታችንን የምናስገባበት መጠለያ፣ የምንመገበው ምግብና የምንለብሰው ልብስ እንዳናጣ ትጥር ነበር። ጥንካሬዋን ከልብ የማደንቅ ሲሆን እኔም ችግር ሲደርስብኝ ተመሳሳይ ቆራጥነት እንደማሳይ ተስፋ አደርጋለሁ።”
ራስህን በወላጆችህ ቦታ ለማድረግና ስሜታቸውን ለመረዳት መሞከርህ ስላሉብህ ችግሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርህ ሊረዳህ ይችላል። እንዲህ ማድረግህ የወላጆችህን ጥሩ ባሕርያት እንድትገነዘብና ምሳሌያቸውን እንድትከተልም ሊረዳህ ይችላል።
የአስተማማኝ ምክር ምንጭ
ከላይ የቀረቡት የመፍትሔ ሐሳቦች የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለሚገኘው ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው ጥበብ ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። ስለዚህ መጽሐፍ ይበልጥ እየተማርክ ስትሄድ የሚሰጠው ምክር ምን ያህል አስተማማኝ እንደሆነ ትገነዘባለህ። *
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ መማር የምትችልበት አንዱ መንገድ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በመሰብሰብና መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ነው። በአስቸጋሪ ጊዜ የሚደግፉህና የመጽሐፍ ቅዱስን ጥበብ ያዘለ ምክር በሕይወትህ ተግባራዊ እንድታደርግ የሚረዱህ እውነተኛ ጓደኞች ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል ታገኛለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት መኖር ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። ይሁን እንጂ ይህን የሕይወት ጎዳና ከመረጥህ ዘላቂ ጥቅም ታገኛለህ።—ኢሳይያስ 48:17, 18
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.21 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀው ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 የተባለው ግሩም መጽሐፍ ወጣቶች የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች መቋቋም እንዲችሉ የሚረዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ምክሮችን ይዟል። ተመሳሳይ መረጃ www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ ይገኛል።
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ከወላጆቻቸው የሚፈልጉት ምንድን ነው?
አብሮ ጊዜ ማሳለፍ፦ ይሖዋ አምላክ በእስራኤል ለነበሩ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ዘወትር ይኸውም ‘በቤታቸው ሲቀመጡም ሆነ በመንገድ ሲሄዱ’ ማውራት እንዳለባቸው ነግሯቸው ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7) ይህን ለማድረግ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ ለልጆች ጊዜ መስጠት እንደሚገባው ተሰምቶት ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ሰዎች ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው ትንንሽ ልጆችን ወደ እሱ ባመጡ ጊዜ’ ኢየሱስ ምን አደረገ? ጥቅሱ “ልጆቹንም አቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ይባርካቸው ጀመር” ይላል። (ማርቆስ 10:13, 16) ይህ ለወላጆች እንዴት ያለ ጥሩ ምሳሌ ነው!
ሐቀኝነት የተሞላበት ግልጽ ውይይት ማድረግ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “ምክር ሲጓደል ዕቅድ ይፋለሳል” ይላል። (ምሳሌ 15:22) ልጆቻችሁ ትንንሾች በነበሩበት ወቅት ከእነሱ ጋር ልብ ለልብ መጨዋወት አስፈላጊ ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሲሆኑ ማለትም ወጣቶች በቤት የሚያሳልፉት ጊዜ እየቀነሰና ከትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ እየጨመረ በሚሄድበት ወቅት ደግሞ ከእነሱ ጋር ልብ ለልብ መጨዋወት ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ልጆችና ወላጆች የልባቸውን አውጥተው የማያወሩ ማለትም ሐቀኝነት የተሞላበትና ግልጽ የሆነ ውይይት የማያደርጉ ከሆነ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ለቤተሰቦቻቸው እንግዳ ሊሆኑ ይችላሉ።
ተገቢ የሆነ ተግሣጽ፦ ተግሣጽ በዋነኝነት የሚያመለክተው እርማትና ሥልጠና መስጠትን ሲሆን ቅጣትንም ሊጨምር ይችላል። ምሳሌ 15:5 “ተላላ የአባቱን ምክር ይንቃል፤ መታረምን የሚቀበል ግን አስተዋይነቱን ያሳያል” በማለት ይናገራል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኝ ወጣት እርማት ካልተሰጠው ‘መታረምን ሊቀበል’ አይችልም። እርግጥ ነው፣ ወላጆች በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆቻቸው ተግሣጽ ሲሰጡ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልጋቸዋል። በጣም ጥብቅ ከመሆን መቆጠብ አለባቸው፤ አለበለዚያ ልጃቸውን ሊያበሳጩትና ምናልባትም በራስ የመተማመን ስሜቱን ሊያጠፉበት ይችላሉ። (ቆላስይስ 3:21) ሆኖም ወላጆች ልጆቻቸውን ስድ መልቀቅና ለልጆቻቸው አስፈላጊውን ሥልጠና ሳይሰጡ መቅረት የለባቸው። ልጆችን ስድ መልቀቅ ጎጂ ውጤት ሊኖረው ይችላል። *
[የግርጌ ማስታወሻ]