በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዘመናዊ የግብርና ዘዴ ዓለምን የለወጠው እንዴት ነው?

ዘመናዊ የግብርና ዘዴ ዓለምን የለወጠው እንዴት ነው?

ዘመናዊ የግብርና ዘዴ ዓለምን የለወጠው እንዴት ነው?

ምግብ የምታገኘው እንዴት ነው? ከገበያ ገዝተህ ነው ወይስ ራስህ አምርተህ? አብዛኛው የሰው ዘር ለቀለቡ የሚሆነውን ነገር ራሱ ያመርት የነበረበት ጊዜ ብዙም ሩቅ አይደለም። በአሁኑ ወቅት ግን በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አንዳንድ አገሮች ውስጥ በግብርና ሥራ ላይ የተሰማራው ከ50 ሰዎች 1 ሰው ብቻ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ ሊመጣ የቻለው እንዴት ነው?

ውጤታማ የግብርና ዘዴዎችን ለማግኘት ሲባል የተደረጉት ለውጦች መጀመሪያ ላይ አዝጋሚ የነበሩ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ፈጣን የሆነ መሻሻል ይታይ ጀመር። በዚህ ረገድ የተወሰደው እያንዳንዱ እርምጃ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ቤተሰቦች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተለ ሲሆን ይህ ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው። በግብርና መስክ የተደረገው መሻሻል በሰዎች ሕይወት ላይ ምን ለውጥ እንዳስከተለ መመልከትህ ዓለም በዛሬው ጊዜ ያለውን መልክ እንዴት እንደያዘ ይበልጥ ለመረዳት ያስችልሃል።

አብዮት ጀመረ

በአውሮፓ ውስጥ ሰዎች ለቀለባቸው የሚሆን ምርት ከማምረት አልፈው ግብርናን በስፋት ለማካሄድ እንዲችሉ ከረዷቸው ከፍተኛ ለውጦች አንዱ በ12ኛው መቶ ዘመን የተጀመረው በፈረስ የማረስ ዘዴ ነው። በፈረሱ ደረት ዙሪያ ቀበቶ በማጥለቅና ፈረሱ ከዚህ ጋር የተያያዘውን ማረሻ እንዲጎትተው በማድረግ የሚታረስበት ዘዴ ፈረሱ አንገቱ ሳይታነቅ ለመሥራት ያስችለዋል። ይህ አሠራር ቀደም ሲል ይሠራበት ከነበረው በበሬ የማረስ ዘዴ ይልቅ የተሻለ ነበር፤ ምክንያቱም ፈረሶቹ ከበሬዎች ይልቅ ማረሻውን በኃይልና በፍጥነት መጎተት እንዲሁም ለረጅም ሰዓታት ማረስ ይችላሉ። ገበሬዎች በፈረስ ማረስ ሲጀምሩ ምርታቸውን መጨመር ቻሉ። በዚህ ዘዴ አማካኝነት ቀደም ሲል ለማረስ አስቸጋሪ የነበረውን መሬት የብረት ማረሻ ተጠቅመው ማረስ ቻሉ። ቀደም ባሉት ዘመናት ከተደረጉት መሻሻሎች ሌላው ደግሞ እንደ ባቄላ፣ አተርና አልፋልፋ የመሳሰሉ ሰብሎችን በማብቀል የአፈሩ ለምነት እንዲጨምር የማድረግ ዘዴ ነው፤ እነዚህ ሰብሎች አፈሩ በናይትሮጂን የበለጸገ እንዲሆን ያደርጋሉ። በንጥረ ነገሮች የበለጸገ አፈር ብዙ ምርት ይሰጥ ጀመር።

በግብርናው መስክ የተደረጉት እነዚህ እድገቶች አንዳንድ ገበሬዎች ከራሳቸው አልፈው ለገበያ የሚያቀርቡት እህል ለማምረት አስችለዋቸዋል። ሰዎች ቀለባቸውን ከገበያ መሸመት መቻላቸው በንግድ ሙያ ላይ እንዲሰማሩ እንዲሁም ፋብሪካዎች እንዲከፍቱ ምክንያት ሆኗል፤ ይህ ደግሞ ከተሞች እንዲስፋፉ አስተዋጽኦ አድርጓል። ባለጸጋ ከሆኑት ከእነዚህ ባለ ፋብሪካዎች፣ ነጋዴዎችና ገበሬዎች አንዳንዶቹ የመጀመሪያዎቹን የግብርና ማሽኖች ፈለሰፉ።

በ1700 ገደማ ጄትሮ ቱል የሚባል እንግሊዛዊ ገበሬ፣ ትልምን ተከትሎ ዘር የሚዘራ በፈረስ የሚጎተት መሣሪያ ፈለሰፈ፤ ይህ መሣሪያ ዘር እንዲባክን የሚያደርገውን በእጅ የመዝራት ልማድ የሚተካ ነበር። በ1831 ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖር ሳይረስ ማኮርሚክ የሚባል ሰው በፈረስ የሚጎተት ማጨጃ ማሽን የፈለሰፈ ሲሆን በዚህ ማሽን ማጨድ በእጅ ከማጨድ ጋር ሲነጻጸር በአምስት እጥፍ ይፈጥናል። በተጨማሪም በዚያው ጊዜ አካባቢ ነጋዴዎች በደቡብ አሜሪካ ከሚገኘው የአንዲያን የባሕር ዳርቻ ወደ አውሮፓ ማዳበሪያዎች ማምጣት ጀመሩ። በማሽኖችና በማዳበሪያ መጠቀም የእርሻ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አደረገ። ይሁንና ይህ በሰዎች ሕይወት ላይ ምን ለውጥ አስከተለ?

በግብርና መስክ የተደረገው እድገት ለከተሞች በርካሽ ዋጋ የተትረፈረፈ ምግብ እንዲቀርብ አጋጣሚ በመክፈቱ የኢንዱስትሪው አብዮት እንዲካሄድ አስችሏል። ይህ አብዮት በመጀመሪያ የተካሄደው ከ1750 እስከ 1850 ባለው ጊዜ ውስጥ በብሪታንያ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በከሰል ማዕድን ማውጫዎች፣ በብረት ማቅለጫዎች፣ መርከብ በሚሠራባቸው ወይም በሚጠገንባቸው ቦታዎችና በልብስ ፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው ለመሥራት ሲሉ ኢንዱስትሪ ወደተቋቋመባቸው ከተሞች ለመሄድ ተገደዱ። እነዚህ ሰዎች ከዚህ የተሻለ አማራጭ አልነበራቸውም። አዳዲስ የግብርና ዘዴዎችን ለመጠቀም አቅም ያልነበራቸው አነስተኛ ገበሬዎች ምርታቸውን ሸጠው የሚያገኙት ገንዘብ ጥቂት በመሆኑ ኪራያቸውን መክፈል አቃታቸው። በመሆኑም እርሻቸውን ትተው በመሄድ በሽታ በቀላሉ በሚዛመትባቸውና በሕዝብ በተጨናነቁ ጎስቋላ ከተሞች ውስጥ ለመኖር ይገደዱ ነበር። ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው በእርሻ ሥራ ላይ መሠማራታቸው ቀርቶ ወንዶች ከቤታቸው ርቀው መሥራታቸው የግድ ሆነ። ልጆችም እንኳ ሳይቀሩ በፋብሪካዎች ውስጥ ለረጅም ሰዓታት ይሠሩ ጀመር። ብዙም ሳይቆይ በሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ለውጦች መከሰት ጀመሩ።

ሳይንሳዊ የግብርና ዘዴ ተጨማሪ ለውጦችን አመጣ

በ1850 አንዳንድ አገሮች በጣም ስለበለጸጉ የእርሻ ምርምር ለማካሄድ የሚያስችል የገንዘብ አቅም ነበራቸው። በግብርናው መስክ የሚደረገው ሳይንሳዊ ጥናት በዘመናችንም ለውጥ ማምጣቱን ቀጥሏል። ለምሳሌ ያህል፣ ተክሎችን የሚያራቡ ሰዎች የተክሎችን ዘር በማጥናት ከፍተኛ የሆነ ምርት የሚሰጡ ወይም በሽታን የሚቋቋሙ ተክሎችን ማግኘት ቻሉ። በተጨማሪም ተመራማሪዎች ለተለያዩ ሰብሎችና የአፈር ዓይነቶች የሚያስፈልጉትን የናይትሬትና የፎስፌት ውሕዶች ትክክለኛ መጠን በምርምር አገኙ። የተዘራው ዘር አድጎ ቡቃያ በሚሆንበት ጊዜ አረም ስለሚበዛ የእርሻ ሠራተኞች ማሳውን በመጎልጎል ተጠምደው ይውሉ ነበር። ይሁን እንጂ የሳይንስ ሊቃውንት የአረሞችን ዕድገት የሚቆጣጠሩ ዘመናዊ የአረም ማጥፊያዎችን በማግኘታቸው አረም በማረም ሥራ ላይ የተሰማሩ በርካታ የእርሻ ሠራተኞች ሥራቸውን አጥተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ነፍሳት፣ ትሎችና የአዝርዕት ተባዮች ገበሬዎችን ለዘመናት መከራ ሲያሳዩአቸው ኖረዋል። በአሁኑ ጊዜ ግን ገበሬዎች ማንኛውንም ተባይ ለማጥፋት የሚያስችሏቸው ብዙ ዓይነት ኬሚካሎች አሉ። *

የከብት አርቢ ገበሬዎች ሕይወትም ቢሆን ተለውጧል። ወተት ለማለብና ከብቶችን ለመመገብ የሚያስችሉ ማሽኖች በመፈልሰፋቸው አንድ ከብት አርቢ በእነዚህ መሣሪያዎች በመታገዝ ከረዳቱ ጋር ሆኖ እስከ 200 የሚደርሱ ላሞችን መንከባከብ ይችላል። በተጨማሪም ገበሬዎች፣ ጥጆችንና አሣማዎችን ሜዳ ላይ ከማሰማራት ይልቅ በመጠለያ ውስጥ አድርገው ሙቀታቸውንና ቀለባቸውን እየተቆጣጠሩ በማሳደግ ከድሮው በተሻለ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማደለብ ይችላሉ።

ሳይንሳዊው የግብርና ዘዴ ብዙ አስደናቂ ውጤቶች አስገኝቷል። አንዳንድ ገበሬዎች የኢንዱስትሪው ዘመን ከመጀመሩ በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ምርታቸውን በእያንዳንዱ ሠራተኛ በመቶ አልፎ ተርፎም በሺህ እጥፍ ማሳደግ ችለዋል። ይሁንና እነዚህ ሁሉ እድገቶች በሰዎች ሕይወት ላይ ምን ለውጥ አስከትለዋል?

የገበሬው ሕይወት ተለወጠ

ማሽኖች፣ በብዙ ቦታዎች የገበሬው ሕይወት እንዲለወጥ አድርገዋል። በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ገበሬዎችና ተቀጥረው የሚሠሩ የእርሻ ሠራተኞች ዘመናዊ መሣሪያዎችን ለመጠቀምና ለመጠገን ሥልጠና ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። እንዲሁም በደቦ መዝራት፣ ማረምና ሰብል መሰብሰብ እየቀረ በመምጣቱ ገበሬዎች ሥራቸውን የሚያከናውኑት ብቻቸውን ሆኗል።

በብዙ አገሮች የተወሰኑ የእህል ዓይነቶችን ወይም አንድ ዓይነት እህል በገፍ የሚያመርቱ በከፍተኛ ደረጃ የተማሩና ነጋዴም ጭምር የሆኑ ገበሬዎች ብቅ እያሉ ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ገበሬዎች መሬት ለመግዛት፣ ለግንባታና ለማሽኖች ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ንዋይ ያፈሳሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ገበሬዎች አሁንም ቢሆን ሥራቸውን ለማካሄድ የሌሎችን እገዛ መፈለጋቸው አልቀረም። ትላልቅ የምግብ ዝግጅት ኩባንያዎችና ብዙ ቅርንጫፎች ያሏቸው የገበያ ማዕከሎች ገበሬዎቹ የሚያቀርቡትን ምርት ዋጋ ከመተመን አልፈው የምርቱን ዓይነት፣ መጠንና ቀለም ሳይቀር ይወስናሉ። በግብርና ምህንድስና መስክ የተሰማሩ ባለሞያዎች፣ ገበሬዎቹ እህላቸውን ስለሚያመርቱበት መንገድ ንድፍ የሚያወጡላቸው ሲሆን የግብርና ግብኣቶችን የሚያቀርቡ ኩባንያዎች ደግሞ ለገበሬዎቹ የእርሻ መሬት ተስማሚ የሆኑ ማዳበሪያዎችን፣ ፀረ ተባይ መድኃኒቶችንና የተዳቀሉ ዘሮችን ያቀርቡላቸዋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ገበሬዎች የሚከተሉት የግብርና ዘዴ በአያቶቻቸው ዘመን ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እመርታ አሳይቷል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ገበሬዎች ችግሮች አሉባቸው፤ እንዲሁም አንዳንድ ሰዎች አንዳንድ የግብርና ዘዴዎች ሊያስከትሉ የሚችሉት ጉዳት ያሳስባቸዋል።

ገበሬዎች አሁንም ከችግር አልተላቀቁም

በበለጸጉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ገበሬዎች በግብርና መስክ ከተሰማሩ ትላልቅ ኩባንያዎች ጋር መወዳደር ስለማይችሉ ከእርሻቸው ላይ እየተባረሩ ነው። አንዳንዶቹ ገበሬዎች የሚወዱትን የግብርና ሥራ ሳይለቁ መቆየት የቻሉት የተለያዩ የመዝናኛ አገልግሎቶችን በመስጠት ነው፤ ከእነዚህም መካከል ለአገር ጎብኚዎች ማረፊያ ቦታ ማዘጋጀት ወይም ለሽርሽር የሚሆኑ ድንኳኖች የሚተከሉባቸውን ቦታዎችና ለጎልፍ መጫወቻ የሚሆኑ ሜዳዎችን ማዘጋጀት እንዲሁም ባሕላዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን ማምረት ይገኙባቸዋል። ሌሎች ደግሞ ለየት ያሉ ምርቶችን በማቅረብ ማለትም ለምግብነት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በተፈጥሯዊ መንገድ በማልማት እንዲሁም አበቦችን በማምረት፣ ሰጎኖችንና አልፓካ የሚባሉትን እንስሶች በማርባት ሥራ ላይ ተሠማርተዋል።

ከጠቅላላው ሕዝብ ውስጥ 80 በመቶ ያህሉ በግብርና በሚተዳደርባቸው ድሃ አገሮች ውስጥ ቀለባቸውን ራሳቸው እያመረቱ የሚኖሩ ገበሬዎችም ቢሆኑ ከፍተኛ ለውጦች እየመጡባቸው ነው። ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን በመከተል በትላልቅ የእርሻ ቦታዎች ላይ የሚያመርቱ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች ምርጥ የሆነውን አብዛኛውን መሬት ይገዙት ይሆናል፤ ከዚያም ያመረቱትን እህል ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች ወስደው ይሸጡታል። በዚህም የተነሳ ቀለባቸውን ራሳቸው እያመረቱ የሚኖሩት አብዛኞቹ ገበሬዎች ቤተሰባቸውን ለመመገብ ሲሉ በተወሰኑ ማሽኖች በመጠቀም (እሱንም ካገኙ ነው) ለምነት በሌለው ወይም የበሬ ግንባር በሚያህል መሬት ላይ ለማረስ ይገደዳሉ።

በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች የሚታየው ከገጠሮች ወደ ከተሞች የሚደረግ ከፍተኛ የሕዝብ ፍልሰት በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የጀመረው ለውጥ ውጤት ነው። ሰዎች በግብርና መተዳደራቸው እየቀረ ወደ ከተማ መሄዳቸው አሁንም ቢሆን አንዳንዶችን ሲጠቅም ሌሎችን ለከፍተኛ ችግር እየዳረጋቸው ይገኛል። በዚህ የተነሳ ችግር ላይ ለወደቁት ሕዝቦች በመራራት ውጤታማ የሆነ እርዳታ ያቀረቡ መንግሥታት ቢኖሩ እንኳ በጣም ጥቂት ናቸው። በእርግጥም ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚረዳቸው የአምላክ መንግሥት መምጣቱ ለሰው ልጆች በጣም ያስፈልጋቸዋል!—ኢሳይያስ 9:6

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.10 ንቁ! ሰዎች አንድ የተወሰነ የግብርና ዘዴን እንዲከተሉ አያበረታታም።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ሁለት ዓይነት ገበሬዎች

ዩሴቢዮ የሚኖረው በአንዲስ ተራሮች ላይ ሲሆን ሰብል የሚያመርት ከመሆኑም ሌላ 14 የቀንድ ከብቶች አሉት። ዩሴቢዮ እንዲህ ይላል፦ “እያንዳንዱ ከብት የራሱ ስም አለው። ግብርና እወዳለሁ። የምንጠቀምባቸውን አትክልቶች በሙሉ የምናመርተው ራሳችን ነን። እኔና ባለቤቴ፣ መሬቱ በሚታረስበትና እህል በሚሰበሰብበት ወቅት ጎረቤቶቻችንን እንረዳቸዋለን፤ እነሱም በተራቸው እኛን ይረዱናል። ማንኛችንም ብንሆን ማሽን የለንም። የምናርሰው በበሬዎች ሲሆን መሬቱ ተዳፋት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ በዶማ እንቆፍረዋለን።

“በአንድ ወቅት በሽታ ገብቶ አብዛኞቹን ከብቶቻችንን ገደለብን። ከዚያ በኋላ ስለ ከብት ሕክምና የአጭር ጊዜ ሥልጠና ወሰድኩ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ አንድም ከብት በበሽታ አልሞተብንም፤ እንዲሁም የጎረቤቶቻችን ከብቶች ሲታመሙ መርዳት ችያለሁ። በመንደራችን ባለው ገበያ ላይ አይብ እንሸጣለን፤ ይሁን እንጂ ከዚያ የምናገኘው ገቢ በጣም ጥቂት ነው። ያም ሆኖ ለስድስት ልጆቻችን የሚሆን ቀለብ አጥተን አናውቅም።”

ሪቻርድ የሚኖረው በካናዳ ሲሆን ከ500 ሄክታር የሚበልጥ መሬት ያርሳል። በዘር መዝሪያና በአጨዳ ወራት ከሚረዳው ሰው በስተቀር የሚሠራው ብቻውን ነው።

“አሁን አሁን በግብርና ሙያ ላይ የተሰማራ ሰው ከሰውነቱ ይበልጥ የሚዝለው አእምሮው ነው” በማለት ሪቻርድ ይናገራል። “ትራክተሬም ሆነ ማጨጃ መኪናዬ አየር ማቀዝቀዣ ያለው ክፍል አላቸው፤ እንዲሁም ክፍሉ ዙሪያው የተሸፈነ በመሆኑ አቧራም ሆነ ነፍሳት አያስቸግሩኝም። ዘጠኝ ሜትር ስፋት ያላቸው ማሽኖች ስላሉኝ በአንድ ቀን ውስጥ 65 ሄክታር መሬት መዝራት ወይም ማጨድ እችላለሁ። ይሁን እንጂ እነዚህ ማሽኖች ከሌሉ ምንም መሥራት የማልችል መሆኑ ውጥረት አምጥቶብኛል። አልፎ አልፎ ማሽኖቹን በአዲስ ለመተካት መበደር ይኖርብኛል። ዝናብ፣ ውርጭ፣ የገበያ ዋጋ እንዲሁም የወለድ መጠን የተበደርኩትን ገንዘብ መክፈል በመቻሌ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሲሆን እነዚህ ነገሮች ደግሞ ከእኔ ቁጥጥር ውጭ ናቸው። ግብርና የሚያስከትለው ውጥረት እዚህ የሚኖሩ ብዙ ገበሬዎች በትዳራቸው ውስጥ ችግሮች እንዲያጋጥሟቸው ከማድረግም አልፎ አንዳንዶቹን የራሳቸውን ሕይወት እስከ ማጥፋት አድርሷቸዋል።”

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1831 የተፈለሰፈው የማኮርሚክ ማጨጃ መሣሪያ ገበሬዎች እህላቸውን ከበፊቱ አምስት እጥፍ በሆነ ፍጥነት ማጨድ እንዲችሉ ረድቷቸዋል

[ምንጭ]

Wisconsin Historical Society, WHi-24854