በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የባሕር በክቶርን—ብዙ ጥቅሞች ያሉት ተክል

የባሕር በክቶርን—ብዙ ጥቅሞች ያሉት ተክል

የባሕር በክቶርን—ብዙ ጥቅሞች ያሉት ተክል

በመጸው ወራት መጀመሪያ ላይ ሩሲያን የሚጎበኙ ሰዎች በገጠር አካባቢ ሲጓዙ ደማቅ ብርቱካንማ ቀለም ያላቸውና ዶቃ የሚመስሉ ትንንሽ ፍሬዎች የሞሉበትን የባሕር በክቶርን * የሚባል አነስተኛ ቁጥቋጦ ወይም ዛፍ ሊያገኙ ይችላሉ። ዓይን የሚማርክ ቀለም ያላቸው የዛፉ ፍሬዎች የሚያድጉት በዛላ ሆነው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ፍሬዎቹ እያንዳንዱን ቅርንጫፍና ቀንበጥ ይሸፍኑታል።

ፍሬዎቹ የሚበሉ ቢሆኑም በእጅህ ስትለቅማቸው ሹል የሆኑት እሾሆች እንዳይወጉህ መጠንቀቅ ያስፈልግሃል! እያንዳንዱን ፍሬ ለየብቻ መልቀም ያለብህ ሲሆን እንዳትጨፈልቃቸው መጠንቀቅ ይኖርብሃል። ለባሕር በክቶርን ይበልጥ ተስማሚ የሆነው የአየር ንብረት ቀዝቃዛ በመሆኑ ብዙውን ጊዜ ይህ ተክል ከሰሜናዊ ምዕራብ አውሮፓ አንስቶ በማዕከላዊ እስያ እስከሚገኙት የአልታኢ ተራሮች ድረስ ባሉት ተራራማ አካባቢዎች እንዲሁም በምዕራብና በሰሜናዊ ቻይና ብሎም በሰሜናዊ ሂማልያ ተራሮች ላይ ይገኛል። ለብዙ መቶ ዘመናት የዚህ ተክል ፍሬዎች እንደ ሩሲያ፣ ቲቤትና ቻይና ባሉት አካባቢዎች በጣም ተፈላጊ ሆነው ቆይተዋል።

በቲቤት ስለ መድኃኒት በሚገልጹ ጽሑፎችና በጥንቷ ግሪክ ጽሑፎች ላይ የባሕር በክቶርን ተጠቅሷል። በግሪክኛ ይህ ተክል ሂፖፌይ የሚባል ሲሆን “የሚያብረቀርቅ ፈረስ” የሚል ትርጉም አለው። በጥንቷ ግሪክ ውስጥ ለግልቢያ ውድድር የሚሆኑ ፈረሶች የሚያብረቀርቅ መልክ እንዲኖራቸው ለማድረግ ሰዎች የባሕር በክቶርንን ዛፍ ፍሬዎች ወይም ቅጠሎች ይጠቀሙበት ነበር፤ ሂፖፌይ የሚለው ስም ይህን ልማድ እንደሚያመለክት ይታመናል።

የባሕር በክቶርንን መጀመሪያ ወደ ሰሜን አሜሪካ ያመጡት በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከሩሲያ የፈለሱ ሰዎች ሲሆኑ የተለያዩ ቁጥቋጦዎችን ለንግድ በሚሆን ደረጃ ለማልማት ከሳይቤሪያ ወደ ካናዳና ዩናይትድ ስቴትስ ይዘው ሄደው ነበር። ይህ ተክል ለምግብነትና ለመድኃኒትነት ጥቅም ስለሚሰጥ በአሁኑ ጊዜ ብዙ አገሮች ያለሙታል።

የባሕር በክቶርን ፍሬዎች ቫይታሚን ሲ እና ኢ፣ ፎሊክ አሲድ፣ ከራትኖይዶች፣ ፋቲ አሲዶች እና ፍሌቮኖይዶች እንዲሁም ሌሎች ንጥረ ነገሮች አሏቸው። የባሕር በክቶርን ለካንሰር ሕክምና ጥቅም እንዳለው እንዲሁም ለልብ ሕመም የሚያጋልጡ ችግሮችን ለመቀነስ ብሎም የጨጓራና አንጀት ቁስለትን፣ የቆዳ ችግሮችንና የጉበት ሕመምን ለማከም እንደሚረዳ የሚሰነዘረው ሐሳብ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ በቅርቡ የሕክምና ጥናት ተካሂዶ ነበር። ከዚህም ሌላ ይህ ፍሬ ደስ የሚል ኮምጣጣ መጠጥ የሚሠራበት ሲሆን የተለያዩ ሕመሞች ያሉባቸው ሰዎች ብርታት እንዲያገኙ ለመርዳት ጥቅም ላይ ይውላል።

በባሕር በክቶርን ፍሬ ውስጥ የሚገኙት ትናንሽ የሆኑ ጥቁር ዘሮች ከፍተኛ ዋጋ አላቸው። በፍሬው ውስጥ ያለው አብዛኛው አልሚ ንጥረ ነገር የሚገኘው ከእነዚህ ዘሮች በሚወጣው ዘይት ውስጥ ነው። ከባሕር በክቶርን የሚወጣው ዘይት የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ከፍ ለማድረግ እንደሚረዳ አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ። በተጨማሪም ይህ ዘይት የቆዳ መጨማደድን ያስወግዳል ስለሚባል መዋቢያዎችንና ለቆዳ ተብለው የሚሠሩ ምርቶችን ለመሥራት ያገለግላል።

ሩሲያን የመጎብኘት አጋጣሚ ካገኘህ ወደ ወርቅማነት የሚወስደው ብርቱካንማ ቀለም ያላቸውን የባሕር በክቶርን ፍሬዎች ተመልክተህ ውበታቸውን ማድነቅ ትችላለህ። ሆኖም ቀደም ብለን እንደጠቀስነው ይህ ተክል ውበት ብቻ ሳይሆን ብዙ ጥቅምም አለው። በእርግጥም ይህ ፍሬ የፈጣሪያችንን ጥበብና ጥሩነት ከሚመሠክሩት በርካታ የፍጥረት ሥራዎቹ አንዱ ነው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ለዚህ ተክል ይህ ስም የተሰጠው በአውሮፓና እስያ በሚገኙ የባሕር ዳርቻዎች ላይ ስለሚበቅል ሊሆን ይችላል።