በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ቀኝ እጅ አጥብቆ መያዝ

የአምላክን ቀኝ እጅ አጥብቆ መያዝ

የአምላክን ቀኝ እጅ አጥብቆ መያዝ

በሜክሲኮ የሚኖረው ሄስርኤል ሲወለድ ጀምሮ ከንጄኒታል ለሜላር ኢክቲዮሲስ የሚባል አልፎ አልፎ የሚከሰት የቆዳ በሽታ ነበረበት። ይህ በሽታ በአብዛኛው የሰውነቱ ክፍል ላይ የሚገኘው ቆዳ እየተቀረፈፈ እንዲነሳና እንዲደድር ያደርጋል። “ይህም የሚያስጠላ መልክ እንዲኖረኝ አድርጓል፤ ነገር ግን በሽታው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፍ አይደለም” በማለት ሄስርኤል ይናገራል።

ሄስርኤል ከሕፃንነቱ ጀምሮ በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ ሕክምና ተደርጎለታል። ሁለት ዓመት ሲሆነው በቆዳው ላይ ያለው ቁስል እንዳያመረቅዝ ለመከላከል ሲባል ከጀርሞች በጸዳ ክፍል ውስጥ ለብቻው እንዲቆይ ተደርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ምንም ቢደረግ የቆዳ ችግሩ መሻሻል አላሳየም። በሚደርስበት መገለል የተነሳ ስሜቱ ስለሚጎዳ ይህንን መቋቋም እንዲችል የሥነ ልቦና ባለሞያዎች እርዳታ ያደርጉለት ነበር።

የሄስርኤል በሽታ ተላላፊ እንደሆነ የሚያስቡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ይርቁታል። በተለይም ከሌሎች ልጆች ጋር መጫወት በሚፈልግበት በሕፃንነቱ ጊዜ እነሱ ስለሚሸሹት ይህ የሚያሳድርበትን ስሜት መቋቋም በጣም ይከብደው ነበር። ሄስርኤል ሁኔታውን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦ “ልጆቹ ያላግጡብኝ እንዲሁም ‘የደረቀ ሬሳ፣’ ‘ከሌላ ዓለም የመጣ ሰው’ እንደሚሉ ባሉ ስሜት የሚያቆስሉ ስሞች ይጠሩኝ ነበር።”

በሌላ በኩል ደግሞ በሽታው ማንም ሰው በግልጽ ሊያየው የሚችል መሆኑ ሄስርኤል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው ተስፋው ለሌሎች መናገር እንዲችል አጋጣሚ ከፍቶለታል። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ‘እንዲህ የሆንከው እሳት አቃጥሎህ ነው?’ ይሉታል። ሄስርኤል ይህ አለመሆኑን ሲነግራቸው መልኩን ያበላሸው ምን እንደሆነ ይጠይቁታል። እሱም የቆዳ በሽታ እንዳለበትና በሽታው በአሁኑ ጊዜ መድኃኒት እንዳልተገኘለት ይነግራቸዋል።

ከዚያም እንዲህ ይላቸዋል፦ “ይሖዋ አምላክ ሕጉን የሚታዘዙ ሰዎች ከሕመምና ከሥቃይ በጸዳ አዲስ ዓለም ላይ እንደሚኖሩ ቃል ስለገባ ከሁሉ የላቀ ተስፋ አለኝ።” (ራእይ 21:3, 4) ሄስርኤል ስለ ችግሩ በዚህ መልኩ የሚወያይ መሆኑ ከሰዎች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ያስቻለው ሲሆን ከእነሱም መካከል ብዙዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸው ከፍተኛ ደስታ አግኝቷል።

“በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ በመወለዴ በጣም አመስጋኝ ነኝ” ይላል ሄስርኤል፤ “ደግሞም የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ የቅርብ ወዳጆች ማግኘት ችያለሁ። ከእነሱ መካከል አንዳቸውም በመልኬ ምክንያት አያገልሉኝም። የተጠመቅሁት በ17 ዓመቴ ሲሆን ከዚያ ወዲህ ባሉት 14 ዓመታት ፈጣሪያችንን ለማገልገል የሚያስችሉኝ ብዙ መብቶች አግኝቻለሁ።”

ሄስርኤል በኢሳይያስ 41:10, 13 ላይ የሚገኘውን ይሖዋ የተናገረውን የሚከተለውን የሚያበረታታ ሐሳብ ምንጊዜም ያስታውሳል፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ . . . በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ። እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁና።”

ሄስርኤል የይሖዋን ቀኝ እጅ አጥብቆ መያዙ ስለ መልኩ ብዙ እንዳይጨነቅና ከዚህ በሽታ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ተቋቁሞ መኖር እንዲችል ረድቶታል። እሱም እንደ ሌሎቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአምላክ አገልጋዮች የአምላክን ታላላቅ ተስፋዎች ፍጻሜ ይጠባበቃል።