በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሁለት የተከፈለ ቤት—መፋታት በወጣቶች ላይ የሚያስከትለው ችግር

ለሁለት የተከፈለ ቤት—መፋታት በወጣቶች ላይ የሚያስከትለው ችግር

ለሁለት የተከፈለ ቤት—መፋታት በወጣቶች ላይ የሚያስከትለው ችግር

ለሙያዎቹ ምን ምክር መስጠት እንዳለባቸው የሚያውቁ ይመስላቸው ነበር። በትዳራቸው ውስጥ ችግር ለገጠማቸው ሰዎች ምክር ሲሰጡ እንደሚከተለው ይሉ ነበር፦ ‘እናንተ ማተኮር ያለባችሁ በራሳችሁ ደስታ ላይ ነው፤ ስለ ልጆቹ አትጨነቁ። ለእነሱ አይከብዳቸውም። ዘወትር ከሚጨቃጨቁ ወላጆች ጋር ከመኖር ይልቅ መፋታት የሚያስከትለውን ችግር መቋቋም ይቀላቸዋል!’

ሆኖም በአንድ ወቅት መፋታትን እንደተሻለ አማራጭ አድርገው ይመለከቱ የነበሩ አማካሪዎች ተሳስተው እንደነበረ ገብቷቸዋል። አሁን ‘መፋታት ጦርነት ነው’ ማለት ጀምረዋል። ‘በጦርነት ደግሞ ጉዳት ሳይደርስበት የሚቀር ወገን የለም፤ ልጆችም ቢሆኑ ከጉዳት አያመልጡም’ ይላሉ።

ፍቺ በእርግጥ እንደሚወራው ቀላል ነገር ነው?

በቴሌቪዥን በሚተላለፍ ኮሜዲ ፊልም ላይ አዝናኝ ሆኖ ይቀርብ ይሆናል። ምኑ? ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ታሪኩ ባልና ሚስት እንደተፋቱ ይናገራል። ከዚያም ሚስት ልጆቹን እንድታሳድግ ፍርድ ቤት በየነላት፤ በኋላም ሚስቱ የሞተችበትና ልጆች ያሉት ሰው ታገባለች። ሳምንት አልፎ ሳምንት ሲተካ ይህ ቤተሰብ ተደራራቢ ችግር ያጋጥመዋል፤ ይሁንና ተመልካቾችን በሚያስቅ ቀልድ እያዋዛ የሚቀርበው ፊልም፣ ችግሮቹ በሙሉ በ30 ደቂቃ ውስጥ መፍትሔ ሲያገኙ ያሳያል።

ከላይ የተገለጸው ታሪክ አዝናኝ የሆነ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ይወጣው ይሆናል። እውነተኛ ፍቺ ግን እንደ ቴሌቪዥኑ ፕሮግራም የሚያስቅ አይደለም። ፍቺ ጣጣው ብዙ ነው። ጋሪ ኒውማን የተባሉ ሰው ኢሞሽናል ኢንፊደሊቲ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “መፋታት ሙግት ውስጥ ያስገባል” በማለት ጽፈዋል። “[ፍቺ] አንዱ ሌላውን የሚከስበት ሂደት ነው። ለመፋታት ስትወስኑ በልጃችሁ ላይ ያላችሁን ሥልጣን አሳልፋችሁ እየሰጣችሁ ነው ማለት ነው። በተጨማሪም በገንዘባችሁና ምናልባትም በመኖሪያ ቦታችሁ ላይ ያላችሁን መብት ተነጠቃችሁ ማለት ነው። ሙግታችሁ በፍርድ ቤት መፍትሔ ያገኝ ይሆናል፤ ሆኖም ችግሩ በዚህ መንገድ ላይፈታም ይችላል። በመጨረሻም ልጃችሁን መቼ መቼ ማየት እንደምትችሉ እንዲሁም ከደመወዛችሁ ላይ ምን ያህል እንደሚቆረጥ የሚወስንላችሁ ልጃችሁንም ሆነ ቤተሰባችሁን የማያውቅ ዳኛ ሊሆን ይችላል። ይህ ዳኛ ደግሞ የሚያስበው እናንተ እንደምታስቡት አይደለም።”

ብዙውን ጊዜ ፍቺ፣ አንዱን ችግር በሌላ ችግር የሚለውጥ ድርጊት ነው። በእርግጥም መኖሪያችሁንና ገቢያችሁን ጨምሮ በርካታ ነገሮች የሚለወጡ ሲሆን ይህ ለውጥ በአብዛኛው ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ አያደርግ ይሆናል። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ መፋታት በልጆች ላይ የሚያስከትለው ችግርም አለ።

ፍቺና በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች

በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆችን የወላጆቻቸው መፋታት በጣም ሊጎዳቸው ይችላል። አንዳንድ ሰዎች በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ፍቺ የሚያስከትለውን ችግር በመቋቋም ረገድ የተሻለ አቅም እንዳላቸው ይናገራሉ። ለዚህም ወጣቶች ከትንንሽ ልጆች ይልቅ በዕድሜ የበሰሉና በቅርቡ ራሳቸውን ችለው ለመኖር እየተዘጋጁ ያሉ መሆናቸውን እንደ ምክንያት ይጠቅሳሉ። ይሁን እንጂ ፍቺ በወጣቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በእነዚሁ ምክንያቶች የተነሳ ፍቺ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን በየትኛውም ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆች በበለጠ እንደሚጎዳቸው ተገንዝበዋል። * እስቲ የሚከተለውን ተመልከት፦

በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ወደ ጎልማሳነት በሚሸጋገሩበት ዕድሜ ላይ በመሆናቸው ምናልባትም ልጆች ከነበሩበት ጊዜ ይበልጥ በራስ ያለመተማመን ስሜት ያጠቃቸዋል። ወጣት ልጆቻችሁ የበለጠ ነፃነት የሚፈልጉ መስለው መታየታቸው አያታልላችሁ፤ እንዲያውም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የተረጋጋ ቤተሰብ ሊሰጥ የሚችለው ጥበቃና መመሪያ የሚያስፈልጋቸው በዚህ ዕድሜያቸው ላይ ነው።

ወጣቶች በማስተዋል ወዳጅነት ስለመመሥረት እየተማሩ ባሉበት በዚህ ዕድሜ ላይ ወላጆቻቸው መፋታታቸው እንደ መተማመን፣ ታማኝነትና ፍቅር ያሉት ውድ ባሕርያት ያላቸውን ዋጋማነት እንዲጠራጠሩ ያደርጋቸዋል። አዋቂዎች ሲሆኑም ከናካቴው የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት የማይፈልጉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

በሁሉም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ማዘናቸውን የሚያሳዩበት መንገድ መፈለጋቸው የተለመደ ቢሆንም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ይህን የሚያደርጉት በዓመፅ እንደ መካፈል፣ የአልኮል መጠጥ ያለ ልክ እንደ መጠጣትና አደንዛዥ ዕፆችን እንደ መጠቀም ባሉ አደገኛ መንገዶች ነው።

ይህ ሲባል ግን ወላጆቻቸው የተፋቱባቸው ወጣቶች አበቃላቸው ማለት አይደለም። በተለይ ከሁለቱም ወላጆቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት ካላቸው ሊሳካላቸው ይችላል። * ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንደሚናገሩት ፍቺ ሁልጊዜም ‘ለልጆች የተሻለ ይሆናል’ አሊያም ‘በትዳር ጓደኞች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ይቋጫል’ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። እንዲያውም አንዳንዶች፣ መግባባት ካቃታቸው የትዳር ጓደኛቸው ጋር ከመፋታታቸው በፊት ከገጠማቸው ጭቅጭቅ ይልቅ ከተፋቱ በኋላ ገንዘብን ወይም ልጆችን የማሳደግ መብትን በመሳሰሉ በቀላሉ የሚያበሳጩ ጉዳዮች የበለጠ መሟገት እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝበዋል። እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች፣ ፍቺ በቤተሰብ ውስጥ ለሚነሱ ችግሮች መቋጫ ከማበጀት ይልቅ ወደ አደባባይ ያወጣቸዋል።

ሦስተኛ አማራጭ

የትዳር ሕይወትህ በጣም አስቸጋሪ ሆኖብህ ለመፋታት አስበህ ቢሆንስ? ይህ ርዕስ፣ ጉዳዩን መላልሰህ እንድታስብበት የሚያደርጉህ አሳማኝ ምክንያቶች አቅርቦልሃል። ፍቺ በትዳር ውስጥ ለሚያጋጥሙ ችግሮች በሙሉ መፍትሔ አይሆንም።

ይህ ሲባል ግን ትዳርህ ምንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንብህ መፍትሔው እንዲያው ችሎ መኖር ነው ማለት አይደለም። ሌላ አማራጭ አለ፤ ትዳርህ ውስጥ ችግር ከገጠመህ ሁኔታው እንዲሻሻል ለማድረግ ለምን አትጥርም? ያሉብህ ችግሮች ምንም መፍትሔ እንደማይገኝላቸው አድርገህ በማሰብ ይህን ሐሳብ ከአእምሮህ ለማውጣት አትቸኩል። ራስህን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ጠይቅ፦

‘መጀመሪያ ላይ የማረኩኝ የትዳር ጓደኛዬ ባሕርያት የትኞቹ ነበሩ? አሁንስ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እነዚያ ባሕርያት የሏትም?’—ምሳሌ 31:10, 29

‘ከመጋባታችን በፊት የነበሩኝን ስሜቶች መልሼ ማቀጣጠል እችላለሁ?’—ማሕልየ መሓልይ 2:2፤ 4:7

‘የትዳር ጓደኛዬ ምንም ታድርግ ምን፣ በዚህ መጽሔት ላይ ከገጽ 3 እስከ 9 የሚገኙትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ በበኩሌ ምን ላደርግ እችላለሁ?’—ሮም 12:18

‘ለትዳር ጓደኛዬ (በቃልም ይሁን በደብዳቤ) ግንኙነታችን እንዲሻሻል እንደምፈልግ መግለጽ እችላለሁ?’—ኢዮብ 10:1

‘ትዳራችንን ለማሻሻል የሚረዱንን ምክንያታዊ የሆኑ ግቦች በማውጣት ረገድ ሊረዳን ከሚችል የጎለመሰ ወዳጃችን ጋር መወያየት እንችላለን?’—ምሳሌ 27:17

መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት አንድ ሰው የትዳር ጓደኛ በሚመርጥበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በትዳር ሕይወቱ ችግሮች በሚያጋጥሙት ጊዜም ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። በዚህ መጽሔት በገጽ 9 ላይ እንደተገለጸው የተሳካላቸው ቤተሰቦችም እንኳ ችግር ያጋጥማቸዋል፤ ልዩነቱ ያለው ችግሩን በሚፈቱበት መንገድ ላይ ነው።

ይህን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በመኪና ረጅም ጉዞ ለማድረግ መንገድ ጀምረሃል እንበል። በጉዞህ ላይ መጥፎ የአየር ጠባይን፣ የትራፊክ መጨናነቅንና የመንገድ መዘጋትን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች ማጋጠማቸው የማይቀር ነው። አንዳንድ ጊዜም መንገድ ስተህ ልትጠፋ ትችላለህ። ታዲያ ምን ታደርጋለህ? ጉዞህን አቋርጠህ ወደኋላ ትመለሳለህ? ወይስ የገጠመህን መሰናክል የምትፈታበት መንገድ ፈልገህ ጉዞህን ትቀጥላለህ? በተመሳሳይም በሠርጋችሁ ዕለት ረጅም ጉዞ ጀምራችኋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ “[ያገቡ ሰዎች] በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል” ስለሚል በዚህ ጉዞ ላይም ችግሮች መከሰታቸው አይቀርም። (1 ቆሮንቶስ 7:28) ስለዚህ ጥያቄው ችግሮች ይነሳሉ ወይስ አይነሱም የሚል ሳይሆን ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ እናንተ የምትፈቷቸው እንዴት ነው? የሚል ነው። የገጠሟችሁን መሰናክሎች አስወግዳችሁ ጉዟችሁን መቀጠል የምትችሉበትን መንገድ ማግኘት ትችላላችሁ? ትዳራችሁ እንዳበቃለት ቢሰማችሁ እንኳ እርዳታ ለማግኘት ትጥራላችሁ?—ያዕቆብ 5:14

አምላክ የመሠረተው ተቋም

ጋብቻን ያቋቋመው አምላክ ስለሆነ ዝግጅቱን አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። (ዘፍጥረት 2:24) ችግሮቻችሁ ልትወጧቸው የማትችሏቸው መስለው ሲታዩአችሁ በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ሐሳቦች አስታውሱ።

1. በአንድ ወቅት ለትዳር ጓደኛችሁ የነበራችሁን የፍቅር ስሜት መልሳችሁ ለማቀጣጠል ጣሩ።—ማሕልየ መሓልይ 8:6

2. ትዳራችሁን ለማሻሻል በበኩላችሁ ምን ማድረግ እንደምትችሉ አስቡና ተግባራዊ አድርጉት።—ያዕቆብ 1:22

3. ትዳራችሁ እንዲሻሻል አስፈላጊ ናቸው የምትሏቸውን ነገሮች በቃል ወይም በደብዳቤ ለትዳር ጓደኛችሁ በግልጽ ሆኖም በአክብሮት ንገሩ።—ኢዮብ 7:11

4. የሌሎችን እርዳታ እሹ። ትዳራችሁን ለማዳን ለብቻችሁ መፍጨርጨር የለባችሁም!

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 ይህ ርዕስ የሚያተኩረው በጉርምስና ዕድሜ ላይ በሚገኙ ወጣቶች ላይ ቢሆንም ፍቺ ትንንሽ ልጆችንም ይጎዳቸዋል። ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚከተሉትን የንቁ! መጽሔት እትሞች ተመልከት፦ ታኅሣሥ 8, 1997 ከገጽ 3-4, 5-8, 9-12 (እንግሊዝኛ) እና ሚያዝያ 22, 1991 ከገጽ 3-5, 6-11 (እንግሊዝኛ)።

^ አን.13 እርግጥ ነው፣ አንድ ወላጅ ቤተሰቡን ጥሎ ከሄደ ወይም ግልጽ በሆነ ሌላ መንገድ ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑ ከታየ አልፎ ተርፎም በቤተሰቡ ደኅንነት ላይ ሥጋት የሚፈጥር ከሆነ እንዲህ ካለው ወላጅ ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት አዳጋች ነው።—1 ጢሞቴዎስ 5:8

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

‘ያሁኑስ ይሰምርልኛል’

ለሁለተኛ ጊዜ ያገቡ ሰዎች ጋብቻቸው የሰመረ የመሆኑ አጋጣሚ ከመጀመሪያ ትዳራቸው ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ እንደሆነና ለሦስተኛ ጊዜ ትዳር ከመሠረቱ ደግሞ ሁኔታው ከዚህም የባሰ እንደሚሆን ጥናቶች ያመለክታሉ። ጋሪ ኒውማን ኢሞሽናል ኢንፊደሊቲ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ይህ የሆነበትን አንዱን ምክንያት እንደሚከተለው በማለት ገልጸዋል፦ “በመጀመሪያው ትዳርህ ውስጥ ችግር ካጋጠመህ ችግሩ ጥሩ የትዳር ጓደኛ አለመምረጥህ ሳይሆን አንተ ራስህ ነህ። ሚስትህን ያገባሃት ስላፈቀርካት ነው። ከእሷ ጋር በመኖር ክፉና ደጉን አሳልፈሃል።” ኒውማን “የትዳር ጓደኛህን አሰናብተህ ከችግሩ ጋር ከመቀመጥ ይልቅ ችግሩን ሸኝተህ ከትዳር ጓደኛህ ጋር መቀመጥ ይሻላል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ትዳራችሁ በፍቺ ከፈረሰስ?

መጽሐፍ ቅዱስ ከአቅም በላይ የሆኑ ሁኔታዎች ወደ ፍቺ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ይገልጻል። * ይህ በቤተሰባችሁ ላይ ደርሶ ከሆነ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ ሁኔታውን እንዲቋቋሙት ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?

ለልጃችሁ የተፈጸመውን ነገር ንገሩት። ከተቻለ ይህን ማድረግ የሚኖርባቸው ሁለቱም ወላጆች ናቸው። አንድ ላይ ሆናችሁ፣ ለመፋታት ያደረጋችሁት ውሳኔ ያለቀለት መሆኑን ለልጃችሁ አሳውቁት። ለመፋታታችሁ ምክንያቱ ልጃችሁ እንዳልሆነና ሁለታችሁም እንደምትወዱት አረጋግጡለት።

ውጊያውን አቁሙ—ጦርነቱ አብቅቷል። አንዳንድ ወላጆች ፍቺው ከተፈጸመ ከረጅም ጊዜ በኋላም እንኳ ይጣላሉ። አንድ ምሑር እንደገለጹት እነዚህ ሰዎች “በሕግ ቢፋቱም በስሜት የተሳሰሩ፣ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያቃታቸው ተፋላሚዎች ናቸው።” አባትና እናት ሁልጊዜ በረባ ባልረባው መነታረካቸው ልጆች የወላጆቻቸውን ትኩረት እንዳያገኙ እንቅፋት ይሆንባቸዋል፤ እንዲሁም ልጆቹ የፈለጉትን ለማግኘት ሲሉ አንዱን ወላጅ ከሌላው ጋር እንዲያጣሉ ሊያበረታታቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወጣት ልጅ እናቱን “አባዬ እኮ የፈልግሁትን ያህል ውጭ አምሽቼ እንድገባ ይፈቅድልኛል። አንቺስ የማትፈቅጂልኝ ለምንድን ነው?” ሊላት ይችላል። እናቲቱም ልጇ እሷን ከድቶ “ወደ ጠላት ሠፈር” እንዳይሄድ አቋሟን ልታላላ ትችላለች።

ልጃችሁ ሐሳቡን እንዲገልጽ ፍቀዱለት። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ‘ወላጆቼ እርስ በርስ መዋደዳቸውን ካቆሙ አንድ ቀን እኔንም መውደዳቸውን ሊተዉ ይችላሉ’ ወይም ‘ወላጆቼ ሕግ ከጣሱ እኔስ መጣስ የማልችለው ለምንድን ነው?’ እያሉ ሊያስቡ ይችላሉ። የልጃችሁን ስጋት ለመቀነስና ያለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ለማስተካከል እንድትችሉ ሐሳቡን ለመግለጽ የሚያስችለው ሰፊ አጋጣሚ እንዲያገኝ አድርጉ። ይሁን እንጂ ልትጠነቀቁበት የሚገባ አንድ ነገር አለ፦ ልጃችሁ የእናንተን ሚና እንዲጫወትና ስሜታዊ ድጋፍ እንዲሰጣችሁ መፈለግ የለባችሁም። እያነጋገራችሁ ያላችሁት ልጃችሁን እንጂ ምስጢረኛችሁን አይደለም።

ልጃችሁ ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው አበረታቱት። እናንተ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ብትፋቱም ይህ ሰው ለልጃችሁ አሁንም ወላጅ ነው። የቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁን በመጥፎ ማንሳት ጉዳት አለው። ቲንስ ኢን ተርሞይል—ኤ ፓዝ ቱ ቼንጅ ፎር ፓረንትስ፣ አዶለሰንትስ፣ ኤንድ ዜር ፋሚሊስ የተሰኘው መጽሐፍ “ወላጆች በፍቺው ጦር ሜዳ ላይ ልጃቸውን እንደ ጦር መሣሪያ ከተጠቀሙበት የዘሩትን እንደሚያጭዱ መርሳት የለባቸውም” ይላል።

ራሳችሁን ጠብቁ። አንዳንድ ጊዜ ያላችሁበት ሁኔታ በጣም ሊደቁሳችሁ ይችላል። ቢሆንም ተስፋ አትቁረጡ። ጤናማ የሆነ ዕለታዊ እንቅስቃሴ ማድረጋችሁን ቀጥሉ። ክርስቲያን ከሆናችሁ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላችሁን ቀጥሉ። እንዲህ ማድረግ እናንተም ሆናችሁ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጃችሁ ሚዛናችሁን እንድትጠብቁ ይረዳችኋል።—መዝሙር 18:2፤ ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዕብራውያን 10:24, 25

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.38 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ለፍቺ በቂ ምክንያት የሚሆነው ከጋብቻ ውጭ የጾታ ግንኙነት ከተፈጸመ ብቻ ነው። (ማቴዎስ 19:9) አንደኛው የትዳር ጓደኛ ምንዝር ፈጽሞ ታማኝነት ካጎደለ፣ መፋታት የተሻለው አማራጭ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን የሚወስነው በደል የተፈጸመበት የትዳር ጓደኛ እንጂ የቤተሰብ አባላት ወይም ሌሎች አይደሉም።—ገላትያ 6:5

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሠርጋችሁ ዕለት የገባችሁትን ቃል ኪዳን ለማክበር ጣሩ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልጃችሁ የሚያድገው ሁለታችሁም ጋር ከሆነ ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው አበረታቱት