በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኙ ልጃገረዶች ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ዕድሜያቸው 20 ዓመት ከመሙላቱ በፊት ያረግዛሉ።”—ሴንተርስ ፎር ዲዚዝ ኮንትሮል ኤንድ ፕሪቬንሽን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በዩናይትድ ስቴትስ “በቤት ውስጥ የሚፈጸም የኃይል ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን” በሚመለከት በ420 ወንዶች ላይ የተደረገ ጥናት “ከ10 ወንዶች ውስጥ ሦስቱ እንደተደበደቡ ወይም በሌላ መንገድ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው” አመልክቷል።—አሜሪካን ጆርናል ኦቭ ፕሪቬንቲቭ ሜዲስን

ብዙ ቋንቋዎችን መማር ይችላሉ?

ብዙ ወላጆች ትንንሽ ልጆቻቸው ሁለተኛ ቋንቋ እንዲማሩ ማድረግ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመናገር ችሎታቸውን ይቀንሰዋል ብለው ይፈራሉ። ሆኖም በቶሮንቶ፣ ካናዳ የነርቭ ጥናት ሊቅ በሆኑት ሎራ አን ፐቲቶ የሚመራው የምርምር ቡድን ሐቁ የዚህ ተቃራኒ እንደሆነ ገልጿል። “ስትወለዱ ጀምሮ የሚኖራችሁ የነርቭ ሕብረ ሕዋስ . . . ቋንቋ ለመማር ዝግጁ ከመሆኑም ሌላ . . . ብዙ ቋንቋዎችን የመማር ችሎታም አለው” በማለት ፐቲቶ ይናገራሉ። በትምህርት ቤት፣ ሁለት ቋንቋ የሚናገሩ ልጆች አንድ ቋንቋ ብቻ ከሚናገሩ ልጆች በአብዛኛው የተሻሉ ናቸው። ይሁን እንጂ ቶሮንቶ ስታር እንደሚናገረው “ወላጆች ልጆቻቸው ሁለት ቋንቋ መናገር መቻላቸው የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች በሙሉ እንዲያገኙ ከፈለጉ ልጆችን ሁለተኛ ቋንቋ በማስተማር ረገድ እነሱ ራሳቸው ቀዳሚ መሆን አለባቸው።”

የብልግና ምሥሎች ልጆችን ይረብሿቸዋል

ልጆች ገና በለጋ ዕድሜያቸው በኢንተርኔት የሚሠራጩ ጎጂ የሆኑ የብልግና ምሥሎችንና ዓመፅ የሞላባቸውን ቪዲዮዎች ያያሉ። የጀርመን የቋንቋ አመጣጥ ተመራማሪዎች ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት ሃይንትስ ፔተር ማይዲንዠ እንደሚሉት ከሆነ 12 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወንዶች ልጆች ብዙውን ጊዜ ዘግናኝ ዓመፅና ወራዳ የብልግና ምሥሎች የሚታዩባቸውን ድረ ገጾች እንዴትና የት ማግኘት እንደሚቻል ያውቃሉ። ምንም እንኳ ልጆች ፊታቸው ሲታይ የሚያዩት ነገር ያስጨነቃቸው ወይም የረበሻቸው ባይመስልም እንደዚህ ያሉትን ነገሮች በሚያዩበት ጊዜ አብዛኞቹ ውስጣቸው የሚረበሽ ከመሆኑም ሌላ በጣም ይዘገንናቸዋል። ወላጆች ልጆቻቸው ምን እንደሚያስቡና በኮምፒውተራቸው ምን እንደሚመለከቱ ለማወቅ ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉ ማይዲንዠ አበረታተዋል።

ለፍቺ ወቅት መዘጋጀት

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ አውስትራሊያውያን የትዳር ጓደኛቸው ሊከተለው ስለሚገባው የአኗኗር መንገድ ከጋብቻ በፊት የስምምነት ውል እንዲፈርም እንደሚጠብቁበት የሲድኒው ሰንዴይ ቴሌግራፍ ዘግቧል። ከጋብቻ በፊት የሚፈረሙ ስምምነቶች ባልና ሚስቱ ቢፋቱ ንብረታቸውን እንዴት እንደሚካፈሉ በዝርዝር የሚገልጹ ውሎች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ግን እንዲህ ያሉት በርካታ ስምምነቶች እያንዳንዱ የትዳር ጓደኛ ትዳሩ ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ መከተል ያለበትን የአኗኗር ዘይቤ ይዘረዝራሉ። በአንቀጾቹ ላይ ምግብ የሚያበስለው፣ የሚያጸዳው ወይም መኪና የሚነዳው፣ ውሻውን የሚያንሸራሽረውና ቆሻሻ የሚደፋው ማን እንደሆነ፣ እንደ ውሻና ድመት ያሉ እንስሳትን ማሳደግ ይቻል እንደሆነ እንዲሁም እያንዳንዱ የትዳር ጓደኛ ክብደቱ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ሊገለጽ ይችላል። ክሪስቲን ጄፍሬስ የተባሉ ጠበቃ፣ ሰዎች “ትዳራቸው ለዘላለም እንደሚቆይ ያላቸው እምነት ዝቅተኛ እንደሆነ” ገልጸዋል።

ፍቅር ለማሳየት የሚታገሉ ወላጆች

“ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ወላጆች ለትንንሽ ልጆቻቸው የተፈጥሮ ፍቅር ማሳየት ስላልቻሉ ልጆቻቸውን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚገልጽ መመሪያ አስፈልጓቸዋል” በማለት ኒውስዊክ ፖልስካ የተሰኘ የፖላንድ መጽሔት ዘግቧል። ወላጆች ልጆቻቸውን እንደ ማቀፍ፣ አብረዋቸው እንደ መጫወትና ለልጆቻቸው እንደ መዘመር የመሳሰሉትን መሠረታዊ ነገሮች መማር አስፈልጓቸዋል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ደግሞ ልጆች ተገቢውን እድገት እንዲያደርጉ በጣም አስፈላጊ ናቸው። ይሁን እንጂ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት “በፖላንድ ቤተሰቦች ውስጥ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ጊዜ ከሚያሳልፉባቸው በጣም የተለመዱ ነገሮች ውስጥ ቴሌቪዥን መመልከትና ገበያ መውጣት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ።” በዝርዝሩ ውስጥ ከልጆች ጋር አብሮ መጫወት በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።