በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼን ይበልጥ ላውቃቸው የምችለው እንዴት ነው?

ወላጆቼን ይበልጥ ላውቃቸው የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

ወላጆቼን ይበልጥ ላውቃቸው የምችለው እንዴት ነው?

ጄሲካና ወላጆቿ ከወዳጆቻቸው ጋር እራት እየበሉ ነው። በዚህ መሃል ከወዳጆቻቸው አንዷ የጄሲካን እናት “በቀደም ዕለት ማንን እንዳገኘሁ ብነግርሽ አታምኚም! ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሽ ጓደኛሽ የነበረውን ሪቻርድን አገኘሁት” አለቻት።

ጄሲካ በድንጋጤ ሹካዋን ጠረጴዛው ላይ ጣለችው። ከዚህ በፊት ስለ ሪቻርድ ፈጽሞ ሰምታ አታውቅም!

“እንዴ እማዬ! ከአባዬ በፊት ጓደኛ ነበረሽ ማለት ነው? ይህን አላውቅም ነበር!”

አንተም እንደ ጄሲካ ስለ ወላጆችህ የሆነ ነገር ሰምተህ ተገርመህ ታውቃለህ? ከሆነ ‘ሌላስ ስለ ወላጆቼ የማላውቀው ምን ነገር ይኖር ይሆን?’ ብለህ አስበህ ይሆናል።

ስለ ወላጆችህ የማታውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ የሚችሉት ለምንድን ነው? ስለ እነሱ የበለጠ ማወቅህ ምን ጥቅም ሊያስገኝልህ ይችላል? ደግሞስ ስለ እነሱ እንዴት ማወቅ ትችላለህ?

ማወቅ የምትችለው ብዙ ነገር አለ

ስለ ወላጆችህ የማታውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ የሚችሉት ለምንድን ነው? አንዳንድ ጊዜ ምክንያቱ ተራርቆ መኖር ሊሆን ይችላል። አሁን የ22 ዓመት ወጣት የሆነው ጄኮብ * እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆቼ የተፋቱት የስምንት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነው። ከዚያ በኋላ አባቴን የማገኘው በዓመት ውስጥ ጥቂት ጊዜ ብቻ ነበር። ስለ እሱ ማወቅ የምፈልገው ብዙ ነገር አለ።”

ከወላጆችህ ጋር ለዓመታት አብረህ የኖርክ ቢሆንም እንኳ ስለ ራሳቸው ሁሉንም ነገር አልነገሩህ ይሆናል። ለምን? ወላጆችም እንደ ማንኛውም ሰው ቀደም ሲል የሠሯቸውን ስህተቶች ሲያስቡ ሊያፍሩ ይችላሉ። (ሮም 3:23) በተጨማሪም የሠሯቸውን ስህተቶች ከተናገሩ ለእነሱ ያለህ አክብሮት ይቀንሳል ወይም የበለጠ ነፃነት ለማግኘት ትደፋፈራለህ ብለው ይሰጉ ይሆናል።

ይሁንና በአብዛኛው ወላጆችህ ስለ ራሳቸው ያልነገሩህ ነገር ሊኖር የቻለው ርዕሰ ጉዳዩ ስላልተነሳ ብቻ ሊሆን ይችላል። ካመረን የተባለ አንድ ወጣት “ከወላጆችህ ጋር ለዓመታት ከኖርክ በኋላም እንኳ ስለ እነሱ ገና ብዙ ያላወቅከው ነገር መኖሩ የሚገርም ነው!” ብሏል። እንግዲያው ስለ ወላጆችህ የበለጠ ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም? ስለ ወላጆችህ በማወቅ ልታገኛቸው የምትችላቸውን አራት ጥቅሞች ተመልከት።

1ኛው ጥቅም፦ ወላጆችህ ስለ እነሱ ለማወቅ መፈለግህ በራሱ ሊያስደስታቸው ይችላል። ወላጆችህ ስለ እነሱ ሕይወት ለማወቅ መፈለግህ እንደሚያስደስታቸው አያጠራጥርም። ደግሞስ ማን ያውቃል፣ ይህ ሁኔታ ራሳቸውን በአንተ ቦታ በማስቀመጥ አንተንም ሆነ ስሜትህን የበለጠ እንዲረዱ ያደርጋቸው ይሆናል!—ማቴዎስ 7:12

2ኛው ጥቅም፦ ወላጆችህ ነገሮችን የሚያዩበትን መንገድ የበለጠ ትረዳለህ። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆችህ ቀደም ሲል ዝቅተኛ ኑሮ ነበራቸው? ይህን ማወቅህ አሁን ገንዘብ ቆጣቢ መሆናቸው አስፈላጊነቱ ለአንተ ባይታይህም እንኳ እንዲህ ዓይነት ሰዎች የሆኑበትን ምክንያት እንድታውቅ ይረዳሃል።

ስለ ወላጆችህ አስተሳሰብ እንዲህ ዓይነት ማስተዋል ማግኘትህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ኮዲ የተባለ ወጣት “የወላጆቼን አስተሳሰብ ማወቄ አንድ ነገር ከመናገሬ በፊት፣ የምናገራቸው ቃላት በእነሱ ላይ ምን ስሜት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ እንዳስብ አስችሎኛል” ብሏል።—ምሳሌ 15:23

3ኛው ጥቅም፦ ስለ ራስህ ሕይወት ሳትሸማቀቅ መናገር ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። የ18 ዓመቷ ብሪጂት “ስለወደድኩት አንድ ልጅ ለአባቴ መናገር አስፈርቶኝ ነበር” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ይሁን እንጂ ስሜቴን አውጥቼ ስነግረው እሱ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍቅር ሲይዘው ስለነበረው ሁኔታና ያ ስሜት ምን ያህል ደስ የሚል እንደነበር ነገረኝ። እንዲያውም ከሴት ጓደኛው ጋር የተለያዩበትን ቀንና በዚያን ወቅት ምን ያህል አዝኖ እንደነበረ አጫወተኝ። ይህ ደግሞ ስለ ራሴ ሁኔታ ተጨማሪ ነገር እንድነግረው አበረታታኝ።”

4ኛው ጥቅም፦ ትምህርት ልታገኝበት ትችላለህ። የወላጆችህ የሕይወት ተሞክሮ አንተ ራስህ የገጠሙህን የሚያስጨንቁና ተፈታታኝ የሆኑ ሁኔታዎች ለመቋቋም ሊረዳህ ይችላል። “ወላጆቼ የተለያየ አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ያሉትን ትልቅ ቤተሰብ ማስተዳደር የቻሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ እፈልጋለሁ” በማለት የ16 ዓመቱ ጆሹዋ ተናግሯል። “ከእነሱ የማገኘው ጠቃሚ ትምህርት መኖር አለበት።” መጽሐፍ ቅዱስም “ጥበብ ያለው በአረጋውያን ዘንድ አይደለምን? ማስተዋልስ ረጅም ዕድሜ ባላቸው ዘንድ አይገኝምን?” የሚል ጥያቄ ያቀርባል።—ኢዮብ 12:12

ስለ ወላጆችህ ለማወቅ እርምጃ ውሰድ

ስለ ወላጆችህ ይበልጥ ማወቅ ከፈለግክ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበውልሃል።

ትክክለኛውን ጊዜና ቦታ ምረጥ። ጊዜና ቦታው የግድ አስቀድሞ የታሰበበት መሆን አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ ዘና ብላችሁ የምትጨዋወቱበትን አጋጣሚ ልትጠቀምበት ትችላለህ። ምናልባት ከወላጆችህ ጋር ኳስ ልትጫወቱ፣ አንድ ሥራ አብራችሁ ልትሠሩ፣ ወይም በእግራችሁ ልትንሸራሸሩ ወይም በመኪና ራቅ ወዳለ ቦታ ልትጓዙ ትችሉ ይሆናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኮዲ “ከወላጆቼ ጋር ረጅም መንገድ በተጓዝንበት ጊዜ በደንብ መጨዋወት ችለን ነበር” ብሏል። “እርግጥ ነው፣ በጆሮ ማዳመጫ ሙዚቃ ማዳመጥ ወይም መተኛት ቀላል ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ጭውውት መጀመር ምንጊዜም ቢሆን የሚክስ እንደሆነ መገንዘብ ችያለሁ!”

ጥያቄዎች ጠይቅ። መገንዘብ ያለብህ አንድ ነገር አለ፦ ትክክለኛውን ጊዜና ቦታ ብትመርጥም እንኳ እናትህ ለመጀመሪያ ጊዜ ስላፈቀረችው ሰው አንስታ ላትነግርህ ትችላለች፤ አባትህም ቢሆን የቤተሰቡን መኪና እንዳጋጨ ላይነግርህ ይችላል። ይሁን እንጂ ወላጆችህ ከጠየቅሃቸው እንዲህ ስላሉት ነገሮችም ሊነግሩህ ይችላሉ!—ምን ጥያቄዎችን መጠየቅ እንደምትችል ሐሳብ ለማግኘት  ገጽ 12 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

ግትር አትሁን። ብዙውን ጊዜ ለአንድ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ ወደ ሌላ ታሪክ ወይም ርዕስ ሊመራ ይችላል። በዚህ ጊዜ ጭውውቱን መጀመሪያ ወደተነሳው ርዕስ ለመመለስ ልትፈተን ትችላለህ፤ ይሁን እንጂ እንዲህ አታድርግ! ግብህ እንዲሁ መረጃ መሰብሰብ ብቻ እንዳልሆነ አስታውስ። ከዚህ ይልቅ ፍላጎትህ ከወላጆችህ ጋር የበለጠ መቀራረብ ነው፤ ይህን ለማድረግ የሚያስችልህ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ደግሞ እነሱ በሚያስደስታቸው ርዕስ ዙሪያ ማውራት ነው።—ፊልጵስዩስ 2:4

አስተዋይ ሁን። “የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል።” (ምሳሌ 20:5) በተለይ ወላጆችህ መናገር የማይፈልጉትን ነገር እንዲነግሩህ በምትፈልግበት ጊዜ አስተዋይ መሆን ይኖርብሃል። ለምሳሌ ያህል፣ አባትህ በአንተ ዕድሜ ሳለ የፈጸመው የሚያሳፍር ስህተት ምን እንደነበረና እንደገና ዕድሉን ቢያገኝ ሁኔታውን እንዴት በተለየ መንገድ ሊይዘው እንደሚችል ለማወቅ ትጓጓ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉ ርዕሶችን ከማንሳትህ በፊት “ስለዚህ ነገር ብጠይቅህ ቅር ይልሃል?” ብለህ ብትጠይቅ ጥሩ ነው።

ዘዴኛ ሁን። ወላጆችህ ስለ ራሳቸው ሲነግሩህ ‘ለመስማት የፈጠንክ ለመናገር የዘገየህ ሁን።’ (ያዕቆብ 1:19) ወላጆችህ ያካፈሉህ ነገር ያልጠበቅከው ነገር ቢሆንም አታፊዝባቸው ወይም አትዝለፋቸው። “እንዴ! እኔ አላምንም!” ወይም “በእኔ ላይ ጥብቅ የሆንከው ለዚህ ነዋ!” እንደሚሉት ያሉ አስተያየቶችን የምትሰነዝር ከሆነ አባትህ ወይም እናትህ ተጨማሪ ነገር ሊነግሩህ አይፈልጉም። ወላጆችህ የነገሩህን ለሌሎች ሰዎች መናገርህም ወላጆችህ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆኑልህ አያበረታታቸውም።

አሁንም ጊዜ አለህ!

ከላይ የቀረቡት ሐሳቦች ከወላጆችህ ጋር አብረህ በምትኖርበት ጊዜ ከእነሱ ጋር ይበልጥ እንድትተዋወቅ ሊረዱህ ይችላሉ። ይሁን እንጂ አሁን ራስህን ችለህ የምትኖር ከሆነስ? እነዚሁ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከወላጆችህ ጋር የነበረህን ዝምድና እንድታጠናክር ወይም ከዚህ በፊት ጨርሶ ከማታውቀው ወላጅህ ጋር እንድትቀራረብ ሊረዱህ ይችላሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጄኮብ የተገነዘበው ይህንን ነው። ጄኮብ አሁን የሚኖረው ብቻውን ቢሆንም “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አባቴን ይበልጥ እያወቅኩት ነው፤ ይህ ደግሞ በጣም አስደስቶኛል” ብሏል።

ስለዚህ የምትኖረው ከወላጆችህ ጋርም ይሁን ራስህን ችለህ፣ ስለ ወላጆችህ ለማወቅ አሁንም ጊዜ አለህ። በዚህ ርዕስ ውስጥ የቀረቡትን ሐሳቦች ተጠቅመህ ወላጆችህን ይበልጥ ለማወቅ ለምን አትሞክርም?

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.9 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

በዚህ ርዕስ ከተጠቀሱት ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ወላጆችህን መጠየቅ የምትፈልገው የትኞቹን ነው?

ስለ ወላጆችህ ይበልጥ ማወቅህ ራስህን ይበልጥ ለማወቅ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

 ወላጆችህን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ጠይቃቸው፦

ጋብቻ፦ አንተና እማዬ የተዋወቃችሁት እንዴት ነበር? መጀመሪያ እንድትዋደዱ ያደረጋችሁ ምን ነበር? ከተጋባችሁ በኋላ የኖራችሁትስ የት ነበር?

የልጅነት ሕይወት፦ የተወለድከው የት ነው? ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ትስማማ ነበር? ወላጆችህ ጥብቅ ይሆኑብህ ነበር? ወይስ ልል ነበሩ?

ትምህርት፦ በጣም የምትወደው ትምህርት ምን ነበር? የማትወደውስ ትምህርት የትኛው ነበር? ከሁሉ አስበልጠህ የምትወደው አስተማሪ ነበረህ? እንድትወደው ያደረገህ ነገር ምንድን ነው?

ሥራ፦ የመጀመሪያ ሥራህ ምን ነበር? ትወደው ነበር? ሌላ ዓይነት ሥራ ምረጥ ብትባል ምርጫህ ምን ይሆን ነበር?

የሚያስደስታቸው ነገር፦ በዓለም ላይ ያሉ ቦታዎችን የመጎብኘት አጋጣሚ ብታገኝ የት ብትሄድ ደስ ይልሃል? ምን ችሎታ ቢኖርህ ደስ ይልህ ነበር?

መንፈሳዊ ታሪክ፦ ያደግከው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነው? ካልሆነ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት እንዲያድርብህ ያደረገው ነገር ምንድን ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ሕይወትህን ለማስማማት ከባድ የሆነብህ ነገር ምንድን ነው?

ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነገር፦ ለጥሩ ጓደኝነት በጣም አስፈላጊ የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው ትላለህ? ለደስተኛ ሕይወትስ? ለተሳካ ትዳርስ? በጣም ጥሩ ነው የምትለው ምን ምክር ተሰጥቶሃል?

እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ከላይ ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ ጥቂቶቹን ምረጥና ወላጆችህ ምን መልስ ሊሰጡ እንደሚችሉ ገምት። ከዚያም እነሱን ጠይቃቸውና የሚሰጡህን መልስ አንተ ይነግሩኛል ብለህ ከገመትከው ጋር አወዳድር።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የተሰጠ ማሳሰቢያ

ከባለቤትሽ፣ ከሴት ልጅሽና ከወዳጆቻችሁ ጋር እራት እየበላችሁ ነው እንበል። በጭውውቱ መሃል ጓደኛሽ፣ ከባለቤትሽ ጋር ከመተዋወቃችሁ በፊት ጓደኛሽ ስለነበረ አንድ ሰው አነሳች። ከዚህ በፊት ይህን ታሪክ ለሴት ልጅሽ አልነገርሻትም። አሁን ልጅሽ ተጨማሪ ነገር ለማወቅ ፈልጋለች። ታዲያ ምን ታደርጊያለሽ?

አብዛኛውን ጊዜ የተሻለው ነገር ለልጅሽ ጥያቄ መልስ ለመስጠት መሞከር ነው። ልጅሽ ጥያቄ ጠይቃ የምትሰጫትን መልስ ስታዳምጥ የልባችሁን ለማውራት የሚያስችል አጋጣሚ ይከፈታል፤ ይህ ደግሞ አብዛኞቹ ወላጆች የሚፈልጉት ነገር ነው።

ታዲያ ለወንድ ልጅሽ ወይም ለሴት ልጅሽ ስለ ቀድሞ ሕይወትሽ መናገር የሚኖርብሽ ምን ያህል ነው? በአብዛኛው የሚያሳፍርሽን ነገር ከመናገር መቆጠብን ትመርጪ ይሆናል። ሆኖም ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ፣ የፈጸምሻቸውን አንዳንድ ስህተቶችና አስቸጋሪ የሆኑብሽን ነገሮች ለልጆችሽ ብትነግሪያቸው ሊጠቅማቸው ይችላል። እንዴት?

አንድ ምሳሌ ተመልከቺ። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው። . . . እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ!” ብሎ ስለራሱ ተናግሯል። (ሮም 7:21-24) ይሖዋ አምላክ እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገቡና እስከ ዛሬ ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደረገው ለእኛ ጥቅም ሲል ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) በእርግጥም ደግሞ ጥቅም እናገኝበታለን፤ ምክንያቱም ሁላችንም ጳውሎስ በግልጽ የተናገረውን ሐሳብ እንጋራለን።

በተመሳሳይም ልጆችሽ አንቺ ስላደረግሻቸው ጥሩ ምርጫዎች ብቻ ሳይሆን ስለሠራሻቸው ስህተቶችም ጭምር መስማታቸው ስሜትሽን እንዲረዱልሽና ይበልጥ እንዲቀርቡሽ ሊረዳቸው ይችላል። እርግጥ ነው፣ አንቺ ያደግሽበት ዘመን ከአሁኑ የተለየ ነው። ይሁን እንጂ ዘመኑ ቢለወጥም የሰው ተፈጥሮም ሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች አልተለወጡም። (መዝሙር 119:144) ስላጋጠሙሽ ተፈታታኝ ሁኔታዎችና እነዚህን እንዴት እንደተወጣሻቸው በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆችሽ ጋር መወያየትሽ እነሱም የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲያሸንፉ ሊረዳቸው ይችላል። ካመረን የተባለው ወጣት “አንተን የሚያጋጥሙህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በወላጆችህ ላይ ደርሰው እንደነበር ስታውቅ ወላጆችህም እንዳንተው እንደሆኑ እንድትገነዘብ ያደርግሃል” ሲል ተናግሯል። አክሎም “ሌላ ችግር ሲያጋጥምህ ‘ወላጆቼም ይህንን ችግር አሳልፈው ይሆን?’ ብለህ ታስባለህ” ብሏል።

ይሁንና የነገርሻቸው ታሪክ ሁሉ ምክር በመስጠት መደምደም አለበት ማለት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልግሻል። እውነት ነው፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆችሽ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ ወይም እነሱም ተመሳሳይ ስህተት ቢፈጽሙ ምንም ማለት እንዳልሆነ አድርገው ያስባሉ ብለሽ ትሰጊ ይሆናል። ይሁን እንጂ ልጆችሽ ከውይይቱ እንዲያገኙ የፈለግሽውን ትምህርት ግልጽ ለማድረግ (“እናንተ ፈጽሞ እንዲህ ማድረግ የሌለባችሁ ለዚህ ነው”) ብለሽ ከማጠቃለል ይልቅ አንቺ ምን እንደሚሰማሽ ብቻ በአጭሩ ተናገሪ። (“ያኔ እንዲህ ዓይነት ነገር ባላደርግ ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር፤ ምክንያቱም . . .”) ልጆችሽ ምክር እየተሰጣቸው እንደሆነ ሳይሰማቸው ከአንቺ ተሞክሮ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ።—ኤፌሶን 6:4

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“አንድ ጊዜ ለእናቴ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ከምሆን ይልቅ ትምህርት ቤት አብረውኝ ከሚማሩ ልጆች ጋር ስሆን እንደሚቀልለኝ ሳልደብቅ ነገርኳት። በቀጣዩ ቀን እናቴ የጻፈችውን ደብዳቤ ጠረጴዛዬ ላይ አገኘሁ። በደብዳቤው ላይ እሷም ከክርስቲያኖች መካከል ጓደኛ የሚሆናት ሰው እንዳጣች ይሰማት እንደነበረ ነገረችኝ። ከዚያም አብሯቸው ሆኖ የሚያበረታታቸው ሰው ሳይኖር አምላክን ስላገለገሉ ግለሰቦች የሚተርኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን እንዳስታውስ አደረገችኝ። በተጨማሪም የሚያንጹ ጓደኞች ለማፍራት ስላደረግሁት ጥረትም አመሰገነችኝ። ይህ ችግር የገጠመኝ እኔ ብቻ አለመሆኔን ሳውቅ ገረመኝ። እናቴም እንደኔው ዓይነት ችግር ገጥሟት ነበር፤ ይህን በማወቄ በጣም ደስ ስላለኝ አለቀስኩ። እናቴ በነገረችኝ ነገር በጣም ተበረታታሁ፤ እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ጥንካሬ አገኘሁ።”—የ17 ዓመቷ ጁንኮ፣ ጃፓን

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወላጆችህን የድሮ ፎቶግራፎችን ወይም ሌሎች ዕቃዎቻቸውን እንዲያሳዩህ ጠይቃቸው። እነዚህ ነገሮች ብዙውን ጊዜ ሞቅ ያለ ጭውውት ለመጀመር ይረዳሉ