በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሳካላቸው ቤተሰቦች—ክፍል አንድ

የተሳካላቸው ቤተሰቦች—ክፍል አንድ

የተሳካላቸው ቤተሰቦች—ክፍል አንድ

ልዩ እትም በሆነው በዚህ ንቁ! መጽሔት ላይ እስካሁን እንደተመለከትነው የተሳካላቸው ቤተሰቦችም ችግር የሚያጋጥማቸው ጊዜ አለ። የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ በመሆኑ ቤተሰቦች ከችግር ሙሉ በሙሉ ነፃ አለመሆናቸው የሚያስገርም አይደለም። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) መልኩ ይለያይ እንጂ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ ችግር መከሰቱ አይቀርም።

አንድ ቤተሰብ ተሳክቶለታል የሚባለው ሁሉም ነገር ስለተመቻቸለት አለመሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። በተቃራኒው ኢየሱስ “በመንፈሳዊ ድሆች መሆናቸውን የሚያውቁ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3) የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በመከተል መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉ ቤተሰቦች፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም እንኳ ለተሳካ የቤተሰብ ሕይወት ቁልፍ የሆነውን ነገር አግኝተዋል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

አካል ጉዳተኛ የሆነን ልጅ መንከባከብ። መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውን ጨምሮ የቤተሰብ አባላትን መንከባከብ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ኃላፊነት እንደሆነ ይገልጻል። እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 5:8

በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ ቪክቶር የሚባል አንድ አባት እሱና ባለቤቱ አካል ጉዳተኛ የሆነ ልጃቸውን ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት እንዴት እንደተንከባከቡት የሚገልጽ ታሪክ በገጽ 15 ላይ ይገኛል።

ጉዲፈቻ ልጅ ሆኖ ማደግ። አንድ ሰው በወላጆቹ የተተወ ቢሆንም እንኳ ለራሱ ጥሩ ግምት እንዲኖረው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ሊረዱት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው በእርግጥም ይሖዋ አምላክ አባት ለሌለው “ረዳቱ” ይሆናል።—መዝሙር 10:14

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ኬንያታ የተባለች ወጣት ወላጆቿን የማታውቅ መሆኗ ያስከተለባትን ስሜታዊ ጉዳት እንዴት እንደተቋቋመች የሚገልጽ ታሪክ በገጽ 16 ላይ ይገኛል።

የወላጅ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም። እናትን ወይም አባትን በሞት ማጣት በቀላሉ የማይሽር የስሜት ጠባሳ ሊያስከትል ይችላል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ በጣም ይረዳል። መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ይሖዋ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:3

በአውስትራሊያ የምትኖርን አንጄላ የተባለች ወጣት ከአምላክ ጋር ያላት ዝምድና ሐዘኗን ለመቋቋም እንዴት እንደረዳት የሚገልጽ ታሪክ በገጽ 17 ላይ ይገኛል።

ሁሉም ቤተሰቦች ሊቋቋሙት የሚገባ አንድ ዓይነት ችግር ይኖራቸዋል። በሚቀጥሉት ገጾች ላይ ያሉት ታሪኮች በግልጽ እንደሚያሳዩት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ የሚያውሉ ሁሉ ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ችግሮች በተሳካ ሁኔታ ለመቋቋም የሚረዳቸውን ወሳኝ ቁልፍ አግኝተዋል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አካል ጉዳተኛ የሆነን ልጅ መንከባከብ

ደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ቪክቶር ሜይንስ እንደተናገረው

“አንድሩ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ልብሱን የምናለብሰው፣ የምናጥበው፣ አንዳንዴም ምግቡን የምናጎርሰው እኛ ነን። አሁን 44 ዓመቱ ነው።”

አንድሩ አንድ ዓመት ከሆነው በኋላም እንኳ በእግሩ መሄድ ሳይችል ሲቀር አንድ ችግር እንዳለበት ጠረጠርን። ከዚያም በዚያው ጊዜ አካባቢ አንድ ቀን አንዘፍዝፎት ወደቀ። አንድሩን በፍጥነት ወደ ሆስፒታል የወሰድነው ሲሆን የሚጥል በሽታ እንደያዘውም አወቅን። ይሁንና አንድሩ የነበረበት ችግር ይህ ብቻ አልነበረም። ተጨማሪ ምርመራዎች ሲደረጉ የአንድሩ ችግር ከአእምሮው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ታወቀ።

ከብዙ የሕክምና ሙከራ በኋላ ይህን የሚጥል በሽታ በቁጥጥር ሥር ማዋል ቻልን። ለተወሰነ ጊዜ ያህል አራት ዓይነት መድኃኒቶችን በቀን ሦስት ጊዜ መውሰድ ነበረበት። እርግጥ ነው፣ በአእምሮው ላይ ያለው ጉዳት በመድኃኒት ሊሻሻል የሚችል አልነበረም። አንድሩ አሁን 44 ዓመቱ ቢሆንም እንኳ የአእምሮ ችሎታው የአምስት ወይም የስድስት ዓመት ልጅ ያህል ነው።

ሐኪሞች አንድሩን ልዩ እንክብካቤ ወደሚሰጥበት ተቋም እንድናስገባው መክረውን ነበር፤ እኛ ግን ይህን ላለማድረግ ወሰንን። አንድሩን ለመንከባከብ የምንችልበት ሁኔታ ላይ ስለነበርን ተፈታታኝ ሊሆንብን እንደሚችል ብንረዳም በቤት ውስጥ ልንንከባከበው ወሰንን።

በመሆኑም መላው ቤተሰብ እሱን በመንከባከቡ ሥራ እንዲተባበር አደረግን። ከአንድሩ ሌላ ሁለት ሴቶች ልጆችና አንድ ወንድ ልጅ የነበሩን ሲሆን አብረውን በኖሩበት ጊዜ ሁሉ ብዙ ረድተውናል፤ ለዚህም በጣም አመሰግናቸዋለሁ! በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ከጉባኤያችን አባላት ግሩም ድጋፍ እናገኝ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ምግብ አዘጋጅተው ያመጡልን ነበር፤ እንዲሁም እኛ በአገልግሎት ስንካፈል ወይም ሌሎች ጉዳዮች ሲያጋጥሙን አንድሩን ይንከባከቡልን ነበር።

‘“ታምሜአለሁ” የሚል ሰው የማይኖርበት’ ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጸውን በኢሳይያስ 33:24 ላይ የሚገኘውን ተስፋ ምንጊዜም እናስታውሳለን። አምላክ አዲስ ዓለም ለማምጣትና በሽታን በሙሉ ለማጥፋት ያለውን ዓላማ እንደሚፈጽም ሙሉ እምነት አለን። (2 ጴጥሮስ 3:13) ስለዚህ አንድሩ የተሟላ ጤንነት የሚያገኝበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። እስከዚያው ድረስ ግን በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንግሥት ካስቀደምን የሚያስፈልጉን ነገሮች በሙሉ እንደሚሟሉልን ኢየሱስ በተናገረው ቃል ላይ እምነት አለን። (ማቴዎስ 6:33) እነዚህ የኢየሱስ ቃላት በእኛ ሕይወት ሲፈጸሙ ተመልክተናል። ምንም ነገር አጥተን አናውቅም።

እርግጥ ነው፣ ሁሉም ቤተሰቦች የታመመውን የቤተሰባቸውን አባል በቤት ውስጥ መንከባከብ እንደማይችሉ የታወቀ ነው። እንዲህ እያደረጉ ላሉ ሁሉ ግን በቅድሚያ የምሰጠው ምክር አዘውትረው ልባዊ ጸሎት እንዲያቀርቡ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ሁለተኛ፣ ልጃችሁን በሚገባ ተንከባከቡት እንዲሁም ፍቅር አሳዩት፤ ደግሞም ይሖዋ አምላክን መውደድን ለመማር ያለውን ችሎታ አቅልላችሁ አትመልከቱ። (ኤፌሶን 6:4) ሦስተኛ፣ የታመመውን የቤተሰብ አባል በመንከባከቡ ሥራ መላው ቤተሰብ እንዲካፈል አድርጉ፤ እርዳታ እንዲያበረክቱ ፍቀዱላቸው። አራተኛ፣ ልጃችሁ ከሁሉ የበለጠ ፍቅር ማግኘት የሚችለው በቤታችሁ መሆኑን አስታውሱ። እርግጥ ነው፣ የአንድ ቤተሰብ ሁኔታ ከሌላው ይለያል። በእኛ በኩል ግን አንድሩን በቤታችን በመንከባከባችን ፈጽሞ ተቆጭተን አናውቅም። አንድሩ ለእኔ እጅግ የሚወደድ ልጅ፣ እንዲሁም እጅግ የሚወደድ ትልቅ ሰው ነው።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ጉዲፈቻ ልጅ ሆኖ ማደግ

ዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ኬንያታ የንግ እንደተናገረችው

“የእንጀራ ልጅ ከሆናችሁ ከአንደኛው ወላጃችሁ ጋር በደም ትገናኛላችሁ። እኔ ግን ጉዲፈቻ ልጅ ስለሆንኩ ከአንዳቸውም ጋር የደም ትስስር የለኝም። ማንን እንደምመስል እንኳ አላውቅም።”

አባቴ ማን እንደሆነ የማውቀው ነገር የለም፤ እናቴንም ቢሆን አይቻት አላውቅም። እኔን አርግዛ እያለች የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ ትጠጣ እንዲሁም አደንዛዥ ዕፆች ትወስድ ነበር። እንደተወለድኩ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች የሚያሳድግ ድርጅት ወሰደኝ፤ ሁለት ዓመት ገደማ እስኪሆነኝ ድረስ እንዲህ በመሰሉ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ የቆየሁ ሲሆን ከዚያም አንድ ባልና ሚስት በጉዲፈቻ ወሰዱኝ።

አሳዳጊ አባቴ እኔን ለማሳደግ የወሰነው ገና ፎቶግራፌን እንዳየ መሆኑን ነግሮኛል። አዲሷን እናቴንም ቢሆን ወዲያውኑ ወደድኳት። እናቴ እንደሆነችና ከእሷ ጋር ቤት መሄድ እንደምፈልግ ነገርኳት።

የሆነ ሆኖ ገና በልጅነት አእምሮዬ አንድ ጥፋት ባጠፋ ወደ ሕፃናት ማሳደጊያው እላካለሁ ብዬ እፈራ እንደነበር ትዝ ይለኛል። እንደ ሌሎች ልጆች መነጫነጭ ሌላው ቀርቶ መታመምም እንኳ እንደማልችል ይሰማኝ ነበር። ጉንፋን እንኳ እንዳይዘኝ እጠነቀቅ ነበር! ወላጆቼ ግን እንደሚወዱኝና እንደማይተዉኝ በተደጋጋሚ በመንገር ሊያረጋጉኝ ጥረት ያደርጉ ነበር።

ካደግኩ በኋላም እንኳ አንዳንድ ጊዜ፣ ‘በወላጅ አባትና እናት ያደጉ ልጆችን ያህል ቦታ የለኝም’ የሚል ስሜት ያስጨንቀኛል። ይህንን ስሜት እንደምንም ብዬ ሳሸንፍ ደግሞ “ሊያሳድጉሽ ፈቃደኛ የሆኑ ግሩም ወላጆች በማግኘትሽ በጣም አመስጋኝ መሆን አለብሽ!” የሚለኝ ሰው ያጋጥመኛል። ለዚህ አመስጋኝ ነኝ፤ ይሁንና እንዲህ ያለው አስተያየት አንድ ችግር እንዳለብኝና አሳዳጊ ወላጆቼ እኔን ለመውደድ ልዩ ጥረት ማድረግ እንደጠየቀባቸው እንዲሰማኝ ያደርጋል።

‘ወላጅ አባቴ ማን እንደሆነ መቼም ቢሆን አላውቅ ይሆናል’ የሚለውን ሐሳብ መቀበል በጣም ይከብደኛል። አንዳንድ ጊዜ፣ ወላጅ እናቴ እኔን ለማሳደግ ስትል ሕይወቷን ያላስተካከለችው ያን ያህል ሊደከምልኝ እንደሚገባ አድርጋ ስላልቆጠረችኝ እንደሆነ ስለሚሰማኝ ይከፋኛል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ታሳዝነኛለች። ከእሷ ጋ የመገናኘት አጋጣሚ ባገኝም እኔ በጥሩ ሁኔታ እንዳደግኩና ስለተወችኝ ማዘን እንደሌለባት እነግራት ነበር እያልኩ ብዙ ጊዜ አስባለሁ።

አሳዳጊ ወላጆቼ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ ከእነሱ ካገኘኋቸው ግሩም ስጦታዎች አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ነው። በመዝሙር 27:10 ላይ የሚገኙት ‘አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ ይሖዋ ይቀበለኛል’ የሚሉት ቃላት ሁልጊዜ ያጽናኑኛል። ይህ ጥቅስ በእኔ ሕይወት ሲፈጸም ተመልክቻለሁ። ደግሞም ጉዲፈቻ ልጅ ሆኖ ማደግ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት። ለምሳሌ ያህል፣ ምናልባትም እኔ ወላጅ እናቴንና አባቴን ስለማላውቃቸው ሊሆን ይችላል፣ ስለ ሰዎች አስተዳደግና ታሪካቸውን ማወቅ ያስደስተኛል። ሰው እወዳለሁ፤ ይህ ደግሞ ለክርስቲያናዊው አገልግሎት በጣም ጠቃሚ ነው። የይሖዋ ምሥክር መሆኔና ለሌሎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መናገሬ ለራሴ አክብሮት እንዲኖረኝና ሕይወቴ ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርጎልኛል። በምጨነቅበት ጊዜ ወጥቼ ሌሎችን እረዳለሁ። ሰዎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ከእነሱ ጋር እንደሚያቀራርበኝ ተገንዝቤያለሁ። እያንዳንዱ ሰው የራሱ ታሪክ አለው።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የወላጅ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም

“አባቴ ሲሞት አውላላ ሜዳ ላይ ብቻዬን እንደቀረሁ ሆኖ ተሰማኝ። ሁሉን ነገር የሚያውቀውንና በሕይወቴ ውስጥ የሚገጥመኝን ማንኛውንም ችግር ሊፈታልኝ የሚችለውን ሰው አጣሁ።”

አውስትራሊያ የምትኖረው አንጄላ ረትገርዝ እንደተናገረችው

አባቴን በሞት የተነጠቅኩት ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለሁ ነበር። ከመሞቱ ከስድስት ወራት በፊት ቀዶ ሕክምና ተደርጎለት ነበር፤ ገና በማገገሚያ ክፍል ውስጥ እንዳለ ሐኪሙ ‘ከዚህ በላይ ምንም ልናደርግለት አንችልም’ አለን። እናቴ ተጨማሪ ነገር እንዲነግሯት ጎተጎተቻቸው፤ ወንድሜ ራሱን ስቶ ወደቀ፤ እኔ ደግሞ ሁሉ ነገር ተዘበራረቀብኝ። ከስድስት ወራት በኋላ አባቴ ሞተ።

ከዚያ በኋላ የተለያየ ዓይነት ስሜት ይሰማኝ ጀመር። በአንድ በኩል ጓደኞቼ እየተሰማኝ ያለውን ነገር እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ፤ ሆኖም እንደ ምስኪን መቆጠር ደግሞ አልፈለግኩም። ስለዚህ ጓደኞቼ ስሜቴን እንዳያውቁብኝ ለማድረግ እጥር ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ከእነሱ ጋር መሳቅ መጫወቴ ‘ከሐዘኗ ተጽናንታለች’ ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል ብዬ አስብ ነበር፤ እኔ ግን ከሐዘኔ ፈጽሞ አልተጽናናሁም። አሁን መለስ ብዬ ሳስበው ጓደኞቼን በጣም ግራ አጋብቻቸው እንደነበር ይሰማኛል!

አባቴ በመሞቱ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል? አዎ፣ ይሰማኛል! ‘አባቴን እቅፍ አድርጌ እንደምወደው ደጋግሜ ብነግረው ኖሮ ወይም አብሬው ብዙ ጊዜ ባሳልፍ ኖሮ እንዴት ጥሩ ነበር’ እያልኩ አስባለሁ። ‘እሱ እንዲህ እንዲሰማኝ አይፈልግም’ ብዬ ለራሴ ደጋግሜ ብነግረውም እንኳ ይህ ስሜት ሊለቀኝ አልቻለም።

የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የማነብበው የትንሣኤ ተስፋ በእጅጉ አጽናንቶኛል። (ዮሐንስ 5:28, 29) አባቴ ወደ ሩቅ አገር እንደሄደና መቼ እንደሆነ ባይታወቅም አንድ ቀን ወደ ቤቱ እንደሚመለስ አድርጌ ለማሰብ እሞክራለሁ። የሚገርመው ነገር አባቴ እንደሞተ አካባቢ ሰዎች “አባትሽ በትንሣኤ ተመልሶ ይመጣል” ሲሉኝ አያጽናናኝም ነበር። ‘እኔ አባቴን የምፈልገው አሁን ነው!’ የሚል ስሜት ነበረኝ። ወደ ሩቅ አገር ስለመሄድ የሚናገረው ምሳሌ ግን አጽናንቶኛል። ይህ ምሳሌ በትንሣኤ ከመመለስ ጋር የሚመሳሰል ከመሆኑም ሌላ አሁን እሱን በማጣቴ የሚሰማኝን ሐዘን እንድቋቋም ረድቶኛል።

የእምነት አጋሮቼም ይህ ነው የማይባል ድጋፍ አድርገውልኛል። በተለይ አንድ ወንድም የነገረኝን አልረሳውም፤ ስለ አባቴ ሞት ማንሳት እንደሚከብደው ሆኖም ስለ እኔም ሆነ ስለ ቤተሰቤ ሁልጊዜ እንደሚያስብ ገለጸልኝ። ይህን አስተያየት መላልሼ አስበው ነበር። ይህም ወንድሞችና እህቶች ባይናገሩትም እንኳ ስለ እኔና ስለ ቤተሰቤ እንደሚያስቡ እንድገነዘብ ስላደረገኝ በእነዚያ አስጨናቂ ጊዜያት ሐዘኔን እንድቋቋም ረድቶኛል። ሌሎች እንደሚያስቡን ማወቄ ትልቅ ነገር ነበር!

አባቴ ከሞተ ከአራት ወራት በኋላ እናቴ ይበልጥ በአገልግሎት መካፈል ጀመረች፤ ከዚህም ከፍተኛ ደስታ ማግኘት እንደቻለች ተመለከትኩ። ስለዚህ እኔም አብሬያት በአገልግሎት መካፈል ጀመርኩ። በጣም የሚገርመው ነገር ሌሎችን መርዳት የራስን ሐዘን ለመቋቋም በእጅጉ ይረዳል። አገልግሎት በይሖዋ ቃልና በተስፋዎቹ ላይ ያለኝን እምነት ያጠነከረልኝ ከመሆኑም በላይ አሁንም እንኳ በሐዘኔ ላይ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ በሆኑ ሌሎች ነገሮችም ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል።