በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

1ኛው ቁልፍ፦ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ማስቀደም

1ኛው ቁልፍ፦ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ማስቀደም

1ኛው ቁልፍ፦ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ማስቀደም

‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ እወቁ።’—ፊልጵስዩስ 1:10

ምን ማለት ነው? የተሳካ የቤተሰብ ሕይወት ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ እያንዳንዱ የትዳር ጓደኛ ከራሱ፣ ከንብረቱ፣ ከሥራው፣ ከጓደኞቹና ሌላው ቀርቶ ከዘመዶቹም እንኳ በፊት የትዳር ጓደኛውን ፍላጎት ያስቀድማል። የተሳካ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት፣ አንዳቸው ከሌላው ጋር እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። ሁለቱም ለቤተሰቡ ጥቅም ሲሉ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ናቸው።—ፊልጵስዩስ 2:4

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰብ ትልቅ ቦታ ይሰጣል። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን የማያቀርብ ሰው “እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ሆኖም አንድ ሰው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች በጊዜ ሂደት ሊለወጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በቤተሰብ ሕይወት ዙሪያ ምክር የሚሰጡ አንድ ሰው፣ እሳቸው ባዘጋጁት አንድ ስብሰባ ላይ የተገኙ ብዙ ሰዎች ከቤተሰባቸው ይልቅ ለሥራቸው የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጡ ተገንዝበዋል። እኚህ ሰው እንደተናገሩት ሰዎቹ ወደዚህ ስብሰባ የመጡት በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት የሚያስችላቸውን “አቋራጭ መንገድ” ለመማር አስበው ይመስላል። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? አንድ ሰው ለቤተሰቡ ቅድሚያ እንደሚሰጥ በተግባር ማሳየት የመናገሩን ያህል ቀላል አይሆንለትም።

ይህን ለማድረግ ሞክር፦ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ቅድሚያ የምትሰጣቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ገምግም።

የትዳር ጓደኛዬ ወይም ልጄ ከእኔ ጋር ማውራት ሲፈልጉ በተቻለ መጠን ባፋጣኝ ትኩረት እሰጣቸዋለሁ?

ስለምሠራቸው ነገሮች ለሌሎች ሳወራ ብዙውን ጊዜ የምናገረው ከቤተሰቤ ጋር ስለማደርጋቸው ነገሮች ነው?

በሥራ ቦታም ሆነ በሌላ ሥፍራ ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጠኝ ከቤተሰቤ ጋር የማሳልፈውን ጊዜ የሚሻማብኝ ከሆነ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኔን እገልጻለሁ?

ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች ‘አዎ’ ብለህ ከመለስክ ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባህን ነገር እንዳስቀደምክ ሊሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛህና ልጆችህ በዚህ ረገድ ምን ይሰማቸዋል? እኛ ስለተሰማን ብቻ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን አስቀድመናል ማለት አይቻልም። ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት በሚቀጥሉት ገጾች ላይ በምናነሳቸው ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦች ረገድም ይሠራል።

ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ለቤተሰብህ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ማሳየት የምትችልባቸውን አንድ ወይም ሁለት መንገዶች አስብ። (ለምሳሌ ያህል፦ ከትዳር ጓደኛህና ከልጆችህ ጋር ብዙ ጊዜ እንዳታሳልፍ እንቅፋት የሚሆኑብህን ነገሮች እንዴት መቀነስ እንደምትችል አስብ።)

ይህን ቁርጥ ውሳኔህን ለቤተሰብህ አባላት ለምን አትነግራቸውም? አንዱ የቤተሰብ አባል ለመለወጥ ፈቃደኛ ከሆነ ሌሎቹም እንደዚያው ለማድረግ መነሳሳታቸው አይቀርም።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከምንም በላይ ለትዳር ጓደኛውና ለልጆቹ ቅድሚያ የሚሰጥ ወላጅ የቤተሰብ ሕይወቱ የተሳካ ይሆንለታል