በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከድምፅ አልባ አገልግሎት ወደ ቅዱስ አገልግሎት

ከድምፅ አልባ አገልግሎት ወደ ቅዱስ አገልግሎት

ከድምፅ አልባ አገልግሎት ወደ ቅዱስ አገልግሎት

አንድሩ ሆግ እንደተናገረው

የባሕር ሰርጓጅ መርከባችን አዛዥ “የኑክሌር አረሮቻችንን ለማስወንጨፍ ከተገደድን ተልእኳችን ይከሽፋል” በማለት ተናገረ። ይህን ሲናገር የኑክሌር ጦርነት ማካሄድ ተገቢ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ሞቅ ያለ ውይይት ተነሳ። ለመሆኑ በባሕር ሰርጓጅ መርከብ (በአብዛኛው ሥራችንን የምናከናውነው በጥንቃቄና በስውር በመሆኑ ድምፅ አልባው አገልግሎት ተብሎም ይጠራል) ላይ ማገልገል የጀመርኩት እንዴት ነው?

የተወለድኩት በ1944 ዩናይትድ ስቴትስ፣ ፔንሲልቬንያ ግዛት በምትገኘው ፊላደልፊያ ውስጥ ነው። በጦር ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉት አባቴ፣ አያቴና አጎቴ የውትድርና አገልግሎት ሰዎች ከፍ አድርገው ሊመለከቷቸው ከሚገቡ ሥራዎች ሁሉ የሚበልጥ እንደሆነ ይሰማቸው ነበር፤ በመሆኑም ከልጅነቴ ጀምሮ ይህ አመለካከት እንዲኖረኝ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረውብኛል። ልጅ ሳለሁ በአቅራቢያችን ያለውን የባሕር ኃይል ግቢ በመዘዋወር የጎበኘሁ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ያየሁት ያን ጊዜ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በባሕር ሰርጓጅ መርከብ ላይ ማገልገል ግቤ ሆነ። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጨረሻው ዓመት ላይ ሳለሁ በዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ኃይል አካዳሚ ተቀባይነት አገኘሁ። ከአራት ዓመት በኋላ ሰኔ 1966 ተመረቅሁ።

ከኑክሌር ምሕንድስናና ከባሕር ሰርጓጅ መርከቦች አሠራር ጋር በተያያዘ ሥልጠና ለማግኘት ኔቭል ኑክሌር ፕሮፐልሽን ፕሮግራም ተካፈልኩ። ከዚያም ሚያዝያ 1967 ውዷን ባለቤቴን ሜሪ ሊ ካርተርን አገባሁ። መጋቢት 1968 ዩኤስኤስ ጃክ በተባለው የመጀመሪያዬ በሆነው ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ላይ ስመደብ የልጅነት ሕልሜ በመጨረሻ እውን ሆነ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ሜሪ ሊ፣ አሊሰን የተባለችውን የመጀመሪያ ልጃችንን ወለደች።

በመግቢያዬ ላይ የጠቀስኩትን ሐሳብ የተናገረው ካፒቴን ይሠራበት በነበረው ዩኤስኤስ አንድሩ ጃክሰን በሚባል መርከብ ላይ መሐንዲስ መኮንን ሆኜ በ1971 ተሾምኩ። ፖላሪስ የሚባል ሚሳይል በጫነው በዚህ ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ላይ ሳለን የሁሉም ባሕር ሰርጓጅ መርከበኞች ስጋት የሆነው የእሳት አደጋ በድንገት ተነሳ። ጊዜው እኩለ ሌሊት ትንሽ አለፍ ብሎ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር በመዝናናት ላይ ነበርን። በመጀመሪያ ‘ድም’ የሚል ድምፅ ተሰማን፤ ከዚያም አደጋ መድረሱን የሚያሳውቀው ደወል የጮኸ ከመሆኑም በላይ “በማሽን ክፍል ቁጥር አንድ ውስጥ እሳት ተነስቷል!” የሚል የማስጠንቀቂያ መልእክት በድምፅ ማጉያ ተሰማ።

በሁሉም የማሽንና የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ላይ ማለት ይቻላል ኃላፊው እኔ ስለነበርኩ የደረሰውን ጉዳት ለማጣራት ወደ መርከቡ የኋለኛ ክፍል ፈጥኜ ሄድኩ። በመርከቡ ውስጥ የምንተነፍሰው አየር እንዲኖር ከሚረዱት የኦክስጂን ማመንጫዎች በአንዱ ላይ እሳት ተነስቶ ነበር። እኔና ሌሎች ሦስት ሰዎች በፍጥነት የአየር መተንፈሻ ጭምብል ካጠለቅን በኋላ ተቀጣጣይ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ ከአካባቢው አስወገድን። ደግነቱ ከመካከላችን ጉዳት የደረሰበት ማንም አልነበረም። አደጋው ቢከሰትም እንኳ ሥራችንን መቀጠል ችለናል፤ ይህ ደግሞ ቡድኑ ጥሩ ሥልጠና ያገኘ መሆኑን የሚያሳይ ነበር።

ሰላም ፈጣሪ ስለሆነ ሰው ለማንበብ መረጥሁ

ሥራው የሚያስከትልብንን ውጥረት ለመቋቋም እንዲረዳን በየሳምንቱ ለጥቂት ሰዓታት አእምሯችንን ዘና በሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች እንድናሳልፍ እንበረታታ ነበር። በመሆኑም በእረፍቴ ወቅት አብዛኛውን ጊዜዬን የማሳልፈው በውትድርናው ዓለም ታዋቂ ስለሆኑ ሰዎች የሕይወት ታሪክ በማንበብ ነበር። በሆነ ወቅት ግን በሰዎች መካከል ሰላም እንዲኖር በማድረግ ረገድ ታዋቂ ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማንበብ ወሰንሁ። ከባሕር ኃይል አካዳሚ ስመረቅ የተሰጠኝን መጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ወንጌሎችን ማንበብ ጀመርኩ። ይሁን እንጂ በማነብበት ጊዜ ለጥያቄዎቼ መልስ ከማግኘት ይልቅ ተጨማሪ ጥያቄዎች ተፈጠሩብኝ። በመሆኑም እርዳታ እንደሚያስፈልገኝ ተሰማኝ።

አሰሳ የማድረግ ሥራችንን ልንጨርስ ስንቃረብ አዛዣችን መኮንኖቹን በመርከቡ የመዝናኛ ሳሎን ሰብስቦ እንዲህ የሚል ማስታወቂያ ተናገረ፦ “ክቡራን መኮንኖች፣ መሐንዲሳችን ከአሁን ጀምሮ በዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ኃይል ውስጥ ከፍተኛ በሆነው ሥራ ላይ እንዲያገለግል ተመድቧል። ለባሕር ኃይሉ በዓይነቱ አዲስ በሆነው አጥቂ ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ላይ መሐንዲስ መኮንን ሆኖ ያገለግላል።” ይህን ስሰማ ክው ብዬ ቀረሁ!

እኔም በተነገረኝ መሠረት ቤተሰቤን ይዤ ወደ አዲሱ ምድቤ ማለትም ዩኤስኤስ ሎስ አንጀለስ የተባለችው ሰርጓጅ መርከብ እየተሠራች ወደነበረበት በቨርጂኒያ ወደሚገኘው ኒውፖርት ኒውስ ወደተባለው የወደብ ከተማ ሄድኩ። የተሰጠኝ ኃላፊነት የመርከቡ የተለያዩ ክፍሎች በሚገባ መሥራታቸውን የመፈተሹን ሥራ በበላይነት መቆጣጠር እንዲሁም ቴክኒካዊ መመሪያዎችንና የሥልጠና ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት የሚጨምር ነበር። ሥራው እጅግ ውስብስብ ቢሆንም የሚያረካ ነበር። በዚህ መሃል ሜሪ ሊ፣ ድሩ የተባለውን ወንድ ልጃችንን ወለደች። አሁን የሁለት ልጆች አባት ስሆን እንደገና ስለ አምላክ አሰብኩ። ‘አምላክ ስለ ጦርነት ምን ይሰማዋል? ስንሞት ምን እንሆናለን? ገሃነመ እሳት አለ?’ በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል ጀመርኩ።

በመጨረሻ ለጥያቄዎቼ መልስ አገኘሁ!

በዚህ ወቅት ባለቤቴ ከሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ውይይት ጀምራ ነበር። አንድ ቀን መርከብ ከሚሠራበት ቦታ ሆኜ ቤት ስልክ ስደውል ሜሪ ሊ “ሁለት ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ሴቶች’ ቤት መጥተዋል” አለችኝ።

“ከየትኛው ቤተ ክርስቲያን ነው የመጡት?” በማለት ጠየቅኳት።

እሷም “የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው” አለችኝ።

ስለ የይሖዋ ምሥክሮች የማውቀው ነገር አልነበረም፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እፈልግ ነበር። በመሆኑም “አንድ ቀን ማታ እንዲመጡ ንገሪያቸው” አልኳት። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አንደኛዋ ሴት ከባለቤቷ ጋር ተመልሳ መጣች፤ እኔና ባለቤቴ መጽሐፍ ቅዱስን ከእነሱ ጋር ማጥናት ጀመርን።

በመጨረሻም ለዓመታት ግራ ሲያጋቡኝ ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ጀመርኩ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ በንጽጽር እንደገለጸው ሙታን ከባድ እንቅልፍ የወሰዳቸው ያህል ‘ምንም እንደማያውቁ’ ተማርኩ። (መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 11:11-14) ስለዚህ ሙታን በገነትም ሆነ በመቃጠያ ሥፍራ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ በሞት “አንቀላፍተው” ትንሣኤ እየጠበቁ ናቸው።

በተጨማሪም እኔና ሜሪ ሊ በአካባቢያችን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን። በአዳራሹ ውስጥ ያየናቸው የይሖዋ ምሥክሮች የተለያየ ባሕል፣ የትምህርት ደረጃና ጎሣ ያላቸው ቢሆንም ሁሉም አምላክን በሰላምና በአንድነት ሲያገለግሉ ተመለከትን። እኔና ባለቤቴ “መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም የሰዎችን ሕይወት ያሻሽላል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስን።—መዝሙር 19:7-10

ውሳኔ ማድረግ ነበረብኝ

በ1973 በአረቦችና በእስራኤላውያን መካከል ጦርነት ሲነሳ የዩኤስ አትላንቲክ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ወደ አካባቢው ተሰማርተው ነበር። በዚህ ወቅት ነገሮች በቀላሉ ሊባባሱ ይችሉ እንደነበር አሰብኩ፤ በመሆኑም እውነተኛና ዘላቂ ሰላም የሚያመጣው የሰዎች ፖለቲካ ሳይሆን የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ተገነዘብኩ። እርግጥ ነው፣ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በምድር ላይ ይሁን” እያልኩ አዘውትሬ እጸልይ ነበር። (ማቴዎስ 6:9, 10) አሁን ግን የአምላክ መንግሥት በሰማይ የሚገኝ መስተዳድር እንደሆነና በቅርቡ ክፋትንና ክፉ አድራጊዎችን ከምድር ላይ በማጥፋት መላዋን ምድር እንደሚገዛ ተረዳሁ።—ዳንኤል 2:44፤ 7:13, 14

በተለይ በ2 ቆሮንቶስ 10:3, 4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ያስጨንቀኝ ነበር። ይህ ጥቅስ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ማሳሰቢያ ሲሰጥ እንዲህ ይላል፦ “በሥጋ የምንኖር ቢሆንም የምንዋጋው በሥጋዊ መንገድ አይደለም። ምክንያቱም የምንዋጋባቸው የጦር መሣሪያዎቻችን ሥጋዊ አይደሉም፤ ይሁን እንጂ ምሽግን ለመደርመስ የሚያስችል መለኮታዊ ኃይል ያላቸው ናቸው።” እነዚህ ‘መሣሪያዎች’ መንፈሳዊ እንደሆኑና ከእነሱም መካከል ‘የመንፈስ ሰይፍ’ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገኝበት ተማርኩ።—ኤፌሶን 6:17

በመሆኑም ምርጫ ማድረግ ነበረብኝ። ታዲያ ተፈታታኝ ሆኖም አስደሳች በሆነው ሥራዬ ልቀጥል? ወይስ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ተስማምቼ ልኑር? በጉዳዩ ላይ በሚገባ በጸሎት ካሰብኩበት በኋላ ሰላምን የማምጣት ልባዊ ፍላጎት ካለኝ ይህንን ማድረግ ያለብኝ በአምላክ መንገድ ሊሆን ይገባል የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኩ።

የመጨረሻውን ከፍተኛ ባለሥልጣን ማገልገል

እኔና ሜሪ ሊ የወደፊት ሕይወታችንን አስመልክቶ ከጸለይንና ከተወያየን በኋላ የመጨረሻ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆነውን ይሖዋ አምላክን ለማገልገል ቆረጥን። ሁለታችንም በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ወሰንን፤ በመሆኑም ከባሕር ኃይሉ መሰናበት እንደምፈልግ የሚገልጽ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ አስገባሁ። ከዚያም ቨርጂኒያ ወደምትገኘው ኖርፈክ እንድዛወርና እዚያ ሆኜ የሥራ መልቀቂያዬን እንድጠባበቅ ተደረኩ። አብዛኞቹ የሥራ ባልደረቦቼ በውሳኔዬ ግራ የተጋቡ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ተቃወሙኝ። ይሁን እንጂ ሌሎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስለተመሠረተው አቋሜ ለማወቅ ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳዩ ሲሆን ያደረኩትንም ውሳኔ አክብረዋል።

የሥራ መልቀቂያዬን በ1974 ተቀበልኩ። በዚያው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች “መለኮታዊ ዓላማ” በሚል ጭብጥ በሀምፕተን፣ ቨርጂኒያ ባደረጉት ትልቅ ስብሰባ ላይ እኔና ባለቤቴ ሕይወታችንን ለይሖዋ መወሰናችንን ለማሳየት በውኃ ተጠመቅን። (ማቴዎስ 28:19, 20) አዲስ ሕይወት ጀመርን።

አዳዲስ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጥ

እኔና ሜሪ ሊ ያለን ገንዘብ ለጥቂት ወራት ብቻ የሚያቆየን የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሁለት ልጆችን ይዘን ምንም የገቢ ምንጭ ሳይኖረን ሕይወታችንን መምራት ተፈታታኝ ሆኖብን ነበር። የሥራ ማመልከቻዬን ወደተለያዩ ድርጅቶች ካስገባሁ በኋላ ጉዳዩን ለይሖዋ ተውኩት። ብዙም ሳይቆይ በአንድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ውስጥ ተቀጠርኩ። ክፍያው ባሕር ኃይል ሳለሁ ከማገኘው በግማሽ ያህል የሚያንስ ቢሆንም ይህን ሥራ በማግኘቴ ቤተሰባችን ባለበት አካባቢ መቆየት ችሏል።

እኔና ባለቤቴ በመንፈሳዊ እድገት እያደረግን ስንሄድ ይሖዋን የበለጠ ለማገልገል ፈለግን። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ የአንድ ቤተሰብ አባላት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ ማዕከላዊ ቨርጂኒያ ተዛውረው ነበር፤ እነዚህን ቤተሰቦች እናውቃቸው ስለነበር ሄደን እንድንጠይቃቸው ጋበዙን። ቤተሰቡን የጠየቅነው አንዴ ቢሆንም በዚያ ያየነው ነገር እኛም ወደ አካባቢው ለመሄድ እቅድ እንድናወጣ አነሳሳን። የምሠራበት ድርጅት ወደዚያ አካባቢ እንዲያዘዋውረኝ ማመልከቻ አስገባሁ፤ ደስ የሚለው ማመልከቻዬ ተቀባይነት አገኘ። እንዲያውም የሥራ እድገት አገኘሁ! በተጨማሪም ድርጅቱ የጉዞ ወጪያችንን እንደሚሸፍንልን ነገረን። ‘በእርግጥም አምላክ ፈቃዱን ለማድረግ ለሚጥሩ ሰዎች ያስባል’ ተባባልን።—ማቴዎስ 6:33

ቤተሰባችን በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ቀላል አኗኗር ይመራ ስለነበር እኔና ሜሪ ሊ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ገብተን ማገልገል ችለናል። በተጨማሪም ሁለቱን ጥሩ ልጆቻችንን በምናሳድግበት ወቅት ከእነሱ ጋር ሰፋ ያለ ጊዜ እንድናሳልፍ አስችሎናል። አሊሰንና ድሩ “በእውነት መመላለሳቸውን” ስለቀጠሉ በእርግጥም እንዲህ ማድረጋችን ወሰን የሌለው ደስታ አምጥቶልናል።—3 ዮሐንስ 4፤ ምሳሌ 23:24

አዎ፣ ከገንዘብ፣ ከቤት፣ ከጤና እንዲሁም ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ የተጨነቅንባቸው ወቅቶች ነበሩ። ይሁን እንጂ ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን አልተለየንም። “ድምፅ አልባውን አገልግሎት” ትቼ በመውጣቴ በፍጹም አልተቆጨሁም! እኔና ሜሪ ሊ ሕይወታችንን መለስ ብለን ስናስበው ይሖዋን ማገልገል የሰው ልጆች ሊያከናውኗቸው ከሚገቡ ሥራዎች ሁሉ እጅግ የላቀና የሚክስ ስለመሆኑ ምንም ጥያቄ እንደሌለው በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን።—መክብብ 12:13

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የመጨረሻውን ከፍተኛ ባለሥልጣን ለማገልገል ቆረጥን

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዩኤስኤስ “ሎስ አንጀለስ” የምትባለው ባሕር ሰርጓጅ መርከብ

[ምንጭ]

U.S. Navy photo

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ከሜሪ ሊ ጋር