ወላጆች ልጆቻችሁን አሠልጥኑ
ወላጆች ልጆቻችሁን አሠልጥኑ
“ቀደም ሲል የሚያሳስበን [ልጆች] ለረጅም ሰዓት ቴሌቪዥን መመልከታቸው ብቻ ነበር። አሁን ግን የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ ኮምፒውተሮችና ሞባይል ስልኮች መጥተዋል። እነዚህ ነገሮች በትንንሽ ልጆች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሲሆን ሱስ ያለበት ሰው የሚኖረው ዓይነት ባሕርይ እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። . . . አእምሯቸው በጣም ብዙ የሚያነቃቁ ነገሮችን መስማትና ማየት ስለለመደ ልጆቹ እነዚህን ነገሮችን ካላገኙ ምን እንደሚሠሩ ግራ ይገባቸዋል።”—ማሊ ማን የተባሉ የሕክምና ዶክተር
በመገናኛ ቴክኖሎጂ መስክ ለተደረገው እድገትና ለኢንተርኔት አገልግሎት ምስጋና ይግባውና በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ሰዎች ጋር መገናኘት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቀላል እየሆነ መጥቷል። ብዙ ወጣቶች በእጅ የሚያዝ የሙዚቃና የፊልም ማጫወቻ ወይም ሞባይል ስልክ ሳይዙ ከቤት መውጣት አይሆንላቸውም። እነዚህና ሌሎች መሣሪያዎች ይበልጥ ቀልጣፋና ብዙ ነገር ማከናወን የሚችሉ እንዲሁም በዝቅተኛ ዋጋ የሚገኙ በሆኑ መጠን በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የመገናኛ ቴክኖሎጂ ጎርፍ ይበልጥ እየጨመረ የሚሄድ ይመስላል፤ ይህ ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸውን መቆጣጠር፣ ማሠልጠንና እርማት መስጠት ይበልጥ ተፈታታኝ እንዲሆንባቸው አድርጓል።
ወላጆች ሁለት አስፈላጊ ነገሮችን በማድረግ እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት ይችላሉ። አንደኛ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በምሳሌ 22:15 ላይ የሚገኘውን “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቅለታል” የሚለውን አባባል እውነተኝነት መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ሁለተኛ፣ ቴክኖሎጂ በልጆች ላይ በጎ አሊያም መጥፎ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል እንዳለው በመረዳት በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድርባቸው ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል።
ከሕፃንነታቸው ጀምሩ!
በብዙ ቤቶች ውስጥ ልጆች ከቴክኖሎጂ ጋር የሚተዋወቁት በቴሌቪዥን ነው። እንዲያውም ቴሌቪዥን ብዙውን ጊዜ ለልጆች እንደ ሞግዚት ሆኖ ያገለግላል። ሆኖም አንዳንድ የአእምሮ ጤንነት ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ልጆች ገና በሕፃንነታቸው ከልክ በላይ ቴሌቪዥን መመልከታቸው አካላዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ፍላጎት እንዳይኖራቸው እንዲሁም በገሐዱ ዓለምና በቴሌቪዥን በሚያዩት መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ እንዲከብዳቸው ሊያደርግ ይችላል፤ እንዲሁም ስሜታዊ ችግር ሊያስከትልባቸውና የኋላ ኋላም በክፍል ውስጥ በሚማሩበት ጊዜ ሐሳባቸውን መሰብሰብ እንዲያስቸግራቸው ሊያደርግ ይችላል። እንዲያውም ዶክተር ማሊ ማን እንደሚሉት ከሆነ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸውን አንዳንድ ልጆች በተመለከተ የሕክምና ባለሙያዎች “ትኩረት የመሰብሰብ ችግር (አቴንሽን ዴፊሲት ዲስኦርደር) ወይም ትኩረት የመሰብሰብና ያለመረጋጋት ችግር (አቴንሽን ዴፊሲት ሃይፐርአክቲቪቲ ዲስኦርደር) አሊያም ባይፖላር ዲስኦርደር የሚባለው የአእምሮ ሕመም አለባቸው ወደሚል የተሳሳተ መደምደሚያ ሊደርሱ ይችላሉ።” በመሆኑም አንዳንድ ባለሙያዎች ዕድሜያቸው ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ቴሌቪዥን ማየት እንደሌለባቸው ይመክራሉ።
“አንድ ሕፃን ከተወለደ በኋላ ባሉት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከሚከናወኑት ነገሮች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ከወላጆቹ ጋር ጥብቅ ትስስር መፍጠሩ ነው” በማለት አሜሪካን አካዳሚ ኦቭ ፒዲያትሪክስ የተባለው ተቋም ቃል አቀባይ የሆኑት ዶክተር ኬኔዝ ጊንዝበርግ ይናገራሉ። እንዲህ ያለ ጥብቅ ትስስር የሚፈጠረው ደግሞ ወላጆች ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር ሲያወሩና ሲጫወቱ እንዲሁም ሲያነቡላቸው ነው። ደግሞም ብዙ ወላጆች እንደሚያውቁት ልጆች ዘወትር ሲነበብላቸው ለንባብ ፍቅር የሚያዳብሩ ሲሆን ይህም በጣም ጠቃሚ ነገር ነው።
በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ልጆች ስለ ኮምፒውተሮችና ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ስላላቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማወቅ ጠቃሚ ብሎም አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል አሌ የማይባል ነገር ነው። ይሁን እንጂ ልጆቻችሁ በኮምፒውተሮች፣ በኮምፒውተር ጨዋታዎች፣ በኢንተርኔትና በመሳሰሉት ነገሮች ከልክ በላይ እንደተጠመዱ ከተመለከታችሁ ሌሎች ነገሮችንም እንዲወዱ መርዳት የጥበብ እርምጃ ሊሆን ይችላል። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ከላይ ከተገለጹት ነገሮች የተለየ ሆኖም ጠቃሚና ትኩረታቸውን የሚስብ እንዲሁም አስደሳች የሆነ ማንኛውንም ነገር ለምሳሌ አንድ ዓይነት የእጅ ሙያ እንዲማሩ ወይም የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት እንዲለምዱ ማድረግ ይቻላል።
ልጆቻችሁ ሊሳተፉበት የሚችሉ ጊዜ ማሳለፊያ በጥንቃቄ ከመረጣችሁ ልጆቹ አስደሳች መዝናኛ የሚኖራቸው ከመሆኑም በላይ ሌላ ጥቅም ያገኛሉ። እንዲህ ማድረጋችሁ ቴክኖሎጂ ለሁሉም ችግሮች መፍትሔ በማያስገኝበት በዚህ ዓለም ላይ ልጆቻችሁ በሕይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ የሚያስችሏቸውን እንደ ትዕግሥት፣ ጽናትና ራስን መግዛት ያሉትን ባሕርያት እንዲሁም የፈጠራ ችሎታ እንዲያዳብሩ ሊረዳቸው ይችላል።
ልጆች ‘ጥበብና አርቆ ማስተዋል’ ያስፈልጋቸዋል
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትልልቅ ሰዎችም ሆኑ ልጆች “የማሰብ ችሎታ” ወይም አርቆ የማስተዋል ችሎታ እንዲያዳብሩ ያበረታታል። ሮም 12:1፤ ምሳሌ 1:8, 9፤ 3:21 የ1980 ትርጉም) እነዚህን ባሕርያት ማዳበራችን ትክክል የሆነውን ከስህተቱ እንድንለይ ብቻ ሳይሆን ጥበብ የሆነውንና ያልሆነውን አካሄድ ለመለየት ያስችለናል። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ የኮምፒውተር ጨዋታ በመጫወት ወይም ቴሌቪዥን በመመልከት ብዙ ሰዓት ማሳለፍ የተከለከለ ነገር አይደለም፤ ነገር ግን እንዲህ ማድረጉ ጥበብ ነው? ዘመናዊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መግዛት ስህተት አይደለም፤ ይሁንና ይህስ ቢሆን ጥበብ ነው? ታዲያ በቴክኖሎጂ ረገድ ልጆቻችሁ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው?
(▪ አደጋዎቹን አስረዷቸው። በቴክኖሎጂና በኢንተርኔት ረገድ ልጆች ለመማር ፈጣኖች ሊሆኑ ይችላሉ፤ ሆኖም ጥበብና ተሞክሮ ስለሚጎድላቸው የሞኝነት እርምጃ ይወስዳሉ። ስለዚህ ሊርቋቸው የሚገቡትን አደገኛ ሁኔታዎችና እንዴት ሊርቋቸው እንደሚችሉ ግለጹላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ማህበራዊ ግንኙነት የሚመሠረትባቸውን ድረ ገጾች እንውሰድ። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነቶቹ ድረ ገጾች ልጆች ማንነታቸውን እንዲገልጹና ከሌሎች ወጣቶች ጋር እንዲገናኙ ያስችሏቸዋል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ድረ ገጾች የፆታ ጥቃት መፈጸም ለሚፈልጉ ግለሰቦችና መጥፎ ዓላማ ላላቸው ሌሎች ሰዎች ልጆችን ማግኘት እንደሚቻልበት “የገበያ አዳራሽ” ናቸው። * (1 ቆሮንቶስ 15:33) በመሆኑም አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው በእነዚህ ድረ ገጾች ላይ የግል መረጃዎቻቸውን በሙሉ እንዳያሰፍሩ ይመክሯቸዋል። *
እርግጥ ነው፣ ልጆች ከዕድሜያቸው ጋር የሚመጣጠን ነፃነት ሊሰጣቸው ይገባል። ይሁን እንጂ ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን አምላክ ልጆቻችሁን የማሠልጠንና የመቆጣጠር ሥልጣንም ሆነ ኃላፊነት ሰጥቷችኋል። (ምሳሌ 22:6፤ ኤፌሶን 6:4) ልጆቻችሁ ለእነሱ በመጨነቅ የምታደርጉትን ነገር እንደ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ሳይሆን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገው እንደሚመለከቱት ተስፋ እናደርጋለን።
“ይሁን እንጂ ልጆቼ የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች እንዴት እንደሚሠሩ ካላወቅሁ እንዴት ልረዳቸው እችላለሁ?” ትሉ ይሆናል። ቢያንስ መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች ለምን አትማሩም? ሜልባ የተባሉ በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አረጋዊት ለመጀመሪያ ጊዜ በኮምፒውተር የተጠቀሙት 80 ዓመት ካለፋቸው በኋላ ነበር። ሜልባ እንዲህ ብለዋል፦ “ለመጀመሪያ ጊዜ በኮምፒውተር ለመጠቀም የሞከርኩ ዕለት በመስኮት አውጥቼ ልወረውረው ቃጥቶኝ ነበር። ሆኖም ለሁለት ወራት ያህል ከተጠቀምኩበት በኋላ እንዴት እንደሚሠራ የገባኝ ሲሆን አሁን ኢ-ሜይል መላላክና ሌሎች ነገሮችንም ማከናወን ችያለሁ።”
▪ ልጃችሁ በቴክኖሎጂ ውጤቶች የሚጠቀምበትን ጊዜ ገደብ አብጁለት። ልጃችሁ ብቻውን ሆኖ ቴሌቪዥን በመመልከት፣ ድረ ገጾችን በመቃኘት ወይም የኮምፒውተር ጨዋታ በመጫወት ረጅም ሰዓት የሚያሳልፍ ከሆነ በቤት ውስጥ በእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የማትጠቀሙበት ጊዜና ቦታ እንዲኖር ለምን አታደርጉም? ይህም ልጃችሁ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጠቃሚነት እንዲማር ይረዳው ይሆናል። ይህም ሲባል ከቤተሰባቸውና ከጓደኞቻቸው ጋር የሚያሳልፉት፣ የቤት ሥራ የሚሠሩበት፣ የሚመገቡበት፣ አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን የሚያከናውኑበት ጊዜ አለ ማለት ነው። (መክብብ 3:1) ለቤተሰባችሁ ምክንያታዊ የሆኑ ደንቦች ማውጣትና እነዚህ ደንቦች ሁልጊዜ ተግባራዊ እንዲሆኑ መጣር የቤተሰብ ሕይወታችሁ ሥርዓታማ እንዲሆን የሚያደርግ ሲሆን ልጆችም ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እንዲሁም ተግባቢና ለሌሎች አሳቢ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።
በእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች የመጨረሻ ክፍል ላይ አዋቂዎችም ሆንን ልጆች ሁላችንም ቴክኖሎጂን ለሌሎች አሳቢነት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ እንድንጠቀምበት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ስንገዛ ገንዘባችንን አላግባብ እንዳናባክን የሚረዱንን አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.12 ወላጆች በጥቅምት 2008 ንቁ! ላይ የወጣውን “ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ልጆች—ወላጆች ማወቅ የሚገባቸው ነገር” የሚለውን ርዕስ ቢያነቡ ይጠቀማሉ። በመጋቢትና በታኅሣሥ 2007 እንዲሁም በጥር 2008 የንቁ! እትሞች ላይ ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን፣ የቪድዮ ጨዋታዎችን እንዲሁም ኢንተርኔትን አስመልክቶ ጠቃሚ ርዕሶች ወጥተዋል።
^ አን.12 በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ወጣቶች በሞባይል ስልኮች ተጠቅመው ለፆታ ብልግና የሚያነሳሱ ፎቶግራፎች በመነሳት ለጓደኞቻቸው ይልካሉ። እንዲህ ዓይነት ምስሎችን የሚልከው ወጣት ዓላማው ምንም ይሁን ምን አብዛኛውን ጊዜ ፎቶግራፎቹን ብዙ ሰው የሚያያቸው በመሆኑ ድርጊቱ አሳፋሪ ከመሆኑም ሌላ ሞኝነት ነው።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልጆች፣ አእምሯቸው እንዲሰፋና ትዕግሥትንና ጽናትን እንዲያዳብሩ በሚረዷቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መካፈል ይኖርባቸዋል