የምትፈልገው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ!
የምትፈልገው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ!
▪ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት፣ ኮርሲካ በተባለች የሜድትራኒያን ደሴት ላይ በምትገኘው በአያቾ ከተማ ወደ አንድ የመኖሪያ ሕንፃ ሲገቡ ወለሉ ላይ 400 ዩሮ የያዘ አንድ ፖስታ ወድቆ አገኙ፤ ፖስታው አድራሻም ሆነ ስም አልነበረውም። የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት እነዚህ ባልና ሚስት ከዚያ በኋላ ምን እንዳደረጉ ሚስትየዋ እንዲህ በማለት ትናገራለች፦ “ፖስታው የጠፋበት ግለሰብ በስልክ ቁጥራችን ሊደውልልን እንደሚችል የሚገልጽ ማስታወሻ እንግዳ መቀበያው ክፍል ውስጥ በሚገኘው የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ለጠፍን።”
በነጋታው ምሽት ላይ አንዲት ሴት ደወለችላቸው። ገንዘቡ የጠፋባት እሷ መሆኗን የሚያረጋግጥ ነገር ከነገረቻቸው በኋላ ከባልና ሚስቱ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ያዘች። ገንዘቧን ሊመልስላት የሚችል ግለሰብ መኖሩ በጣም ስላስደነቃት ወደ ቀጠሮው ቦታ የመጣችው እቅፍ አበባ ይዛ ነበር። በጠፋባት ፖስታ ውስጥ ደሞዟን አስቀምጣ የነበረ ሲሆን በማግሥቱ ለአንድ ወር ለእረፍት ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበረች።
ሴትየዋ ባልና ሚስቱ ላደረጉላት ደግነት በድጋሚ ምስጋናዋን ለመግለጽ ለእረፍት ከሄደችበት ቦታ ካርድ ላከችላቸው። ከእረፍት ስትመለስ እነዚህ ባልና ሚስት ወደ ቤቷ በመሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰብ ሕይወትም ሆነ በየዕለቱ ለምናሳየው ምግባር ያለውን ጠቀሜታ ነገሯት፤ ሴትየዋም እንዲህ ስላለው ርዕሰ ጉዳይ መነጋገር አስደስቷት ነበር።
ባልና ሚስቱ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተጠቅመው “የቤተሰብህን ሕይወት አስደሳች ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?” ከሚለው ምዕራፍ ላይ ጥቂት ሐሳቦችን አንስተው አወያዩአት። ሴትየዋ በጣም ከመደሰቷ የተነሳ “የሚገርም ነው፤ የምፈልገው ነገር ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አለ!” በማለት በአድናቆት ተናገረች። ከዚያም በነፃ መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለው መጽሐፍ፣ ስለ ቤተሰብ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ስለ አምላክና ስለ ኢየሱስ እውነቱ ምን እንደሆነ የሚገልጽ ማብራሪያ ይዟል። እንዲሁም ሙታን የት እንዳሉ፣ አምላክ በሰው ልጆች ላይ መከራና ሥቃይ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ያብራራል፤ በተጨማሪም ሰዎችን የሚያሳስቧቸው ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን ይዟል። ይህን መጽሐፍ ማግኘት የሚፈልጉ ከሆነ ከታች ያለውን ቅጽ ሞልተው በቅጹ ላይ ወዳለው አድራሻ ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከሚገኙት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መላክ ይችላሉ።
❑ እዚህ ላይ የሚታየውን መጽሐፍ ላኩልኝ።
በየትኛው ቋንቋ እንደሚፈልጉ ይግለጹ።
❑ መጽሐፍ ቅዱስን መማር ስለምፈልግ እባካችሁ አነጋግሩኝ።