በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቦሊቪያው “የጠፋ ዓለም”

የቦሊቪያው “የጠፋ ዓለም”

የቦሊቪያው “የጠፋ ዓለም”

የብሪታንያ ሮያል ጂኦግራፊ ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ ደቡብ አሜሪካ ያላትን ከፍተኛ መጠን ያለው እምቅ ሀብት በተመለከተ በ1906 ከኮሎኔል ፐርሲ ሃረሰን ፎሴት ጋር ተወያዩ። ፕሬዚዳንቱ አንድ ካርታ ወደ ፎሴት ጠጋ አድርገው “ይህን አካባቢ ተመልከት! እምብዛም የማይታወቅ በመሆኑ በካርታው ላይ ምንም ዓይነት መግለጫ አታገኝበትም” አሉት። ከዚያም ለኮሎኔሉ ይህን አካባቢ የማሰስ ሥራ ሰጡት። እሱም ሥራውን በፈቃደኝነት ተቀበለ።

ፎሴት በዕለታዊ ማስታወሻው ላይ በአሁኑ ጊዜ በቦሊቪያ ግዛት ስለሚገኘውና ዋንቻካ ተብሎ ስለሚጠራው ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ ፕላቶ የጻፈ ከመሆኑም ሌላ አካባቢውን “የጠፋ ዓለም” በማለት ጠርቶታል። * አንዳንድ ሰዎች፣ ሰር አርተር ኮናን ዶይል የተባለው ዝነኛ እንግሊዛዊ ደራሲ እስከ ዘመናችን የኖሩ “ዝንጀሮ መሰል ሰዎች” እና አስፈሪ የሆኑ ዳይኖሰሮች ስለሚኖሩበት የፈጠራ ዓለም የሚተርከውን ዘ ሎስት ወርልድ (የጠፋው ዓለም) የተባለ ረጅም ልብ ወለድ ለመጻፍ የተነሳሳው የፎሴትን ማስታወሻዎችና ፎቶግራፎች ከተመለከተ በኋላ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይህ ድንግል የአማዞን አካባቢ በአሁኑ ጊዜ የቦሊቪያን ኖኤል ኬምፕፍ ሜርካዶ ብሔራዊ ፓርክ ያጠቃልላል፤ እጅግ ውብ የሆነው ይህ ፓርክ በ2000 ዓ.ም. በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል። *

ከብራዚል ጋር የሚዋሰነውና በሰሜን ምሥራቅ ቦሊቪያ የሚገኘው ይህ ፓርክ 15,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ያህል ስፋት አለው። ፓርኩ አምስት ሥነ ምህዳሮችን አካትቶ ይዟል፤ እነሱም ክረምት ከበጋ የማይደርቁ ደኖች ያሉበት ተራራማ አካባቢ፣ በመጸው ወራት ቅጠላቸው የሚረግፍ ደኖች ያሉበት አካባቢ፣ ደረቅ ሳር ያለበት ተራራማ አካባቢ፣ እርጥብ ሳር ያለበት ረግረጋማ አካባቢና በደን የተሸፈነ ረግረጋማ አካባቢ ናቸው። ዋንቻካ ፕላቶ ብቻ እንኳ 5,180 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በዙሪያው ካለው ሜዳማ አካባቢ 550 ሜትር ያህል ከፍ ብሎ ይታያል። ወደ 150 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ርዝመት ያለው ዋንቻካ ከፓርኩ ምሥራቃዊ ዳርቻ ትይዩ እንደ ጀርባ አጥንት ተጋድሞ ይታያል። ተራራማውን አካባቢና በዙሪያው ያሉትን ዝቅተኛ ቦታዎች የሚያጠጡት በርካታ ወንዞች 20 የሚያክሉ ፏፏቴዎችን ፈጥረዋል፤ ከእነዚህ መካከል ሳልቶ ሱሳና፣ አርኮ ኢሪስ፣ ፌዴሪኮ አልፌልድ፣ ኬሜላስ እና ኤል ኤንካንቶ የተሰኙት ፏፏቴዎች ይገኙበታል።

ጉብኝታችንን ጀመርን

ገለልተኛ በሆነ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ምክንያት ተጠብቆ የኖረው ይህ ፓርክ ተፈጥሮን የማየት ፍቅር ያላቸው ቱሪስቶችን የመሳብ ኃይል አለው። አብዛኞቹ ቱሪስቶች ወደዚህ የሚመጡት ከማዕከላዊ ቦሊቪያ በአውሮፕላን ተጉዘው ነው። እኛ ግን 700 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን መንገድ በመኪና ለመጓዝ መረጥን፤ ይህ ደግሞ የቦሊቪያን ገጠራማ አካባቢ በቅርበት ለማየት አስችሎናል። አንድ ቦታ ስንደርስ የተለያየ ቀለም ያላቸው ቅጠላ ቅጠሎች የሚመስሉ ነገሮች አንድ ላይ እጅብ ብለው ከርቀት ተመለከትን። ለካስ “ቅጠሎቹ” ቢራቢሮዎች ነበሩ። የሚያሳዝነው የተመለከትናቸው እኛ ብቻ አልነበርንም፤ አንድ የተራበ የእንሽላሊት ሠራዊትም ተመልክቷቸው ኖሮ በፍጥነት ተቀራመታቸው።

ወደ ብሔራዊ ፓርኩ ስንደርስ በፓራግዋ ወንዝ አጠገብ በምትገኘው ላ ፍሎሪዳ በምትባል አንዲት መንደር ጊዶ ከተባለ አስጎብኚያችን ጋር ተገናኘን። ጊዶ እኛንም ሆነ መኪናችንን በጀልባ ጭኖ ወንዙን ካሻገረን በኋላ በመኪናችን ጥቂት ተጉዘን ሎስ ፍየሮስ ወደተባለ ካምፕ ደረስን። መንገድ ላይ ሳለን አንድ ቀበሮ እንዲሁም የማታ ወፍ የምትባል መቀስ የመሰለ ጅራት ያላት የምታምር ወፍ ሽው ብላ ስታልፍ አየን።

ሌሊቱን በእንቅልፍ ካሳለፍን በኋላ ከጎጇችን በላይ በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ላይ የሠፈሩ ማካው የሚባሉ ሰማያዊና ቢጫ ቀለም ያላቸው አራት የሚያማምሩ በቀቀኖች ሲጮኹ ከእንቅልፋችን ቀሰቀሱን። በቀቀኖቹ “ወደ ቤታችን እንኳን በደህና መጣችሁ!” የሚሉ ይመስል ነበር። ቀኑን እንዲህ ባለ አስደሳች ሁኔታ መጀመራችን ብዙ አስደሳች ነገር እንደሚጠብቀን እንድንተማመን አደረገን።

ሕያዋን ፍጥረታት የሚርመሰመሱበት ስፍራ

በኖኤል ኬምፕፍ ሜርካዶ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ከ600 የሚበልጡ የአእዋፍ ዝርያዎች፣ 139 ዓይነት አጥቢ እንስሳት (በመላው ሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት ዝርያዎች ይበልጣል)፣ 74 ዓይነት ተሳቢ እንስሳት እንዲሁም ወደ 3,000 የሚጠጉ የቢራቢሮ ዝርያዎች ይገኛሉ። ከዚህም በላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የነፍሳት ዝርያዎች አሉ። ከአእዋፋቱ መካከል ከ20 የሚበልጡ የበቀቀን ዝርያዎች እንዲሁም ሃርፒ ንስር፣ ዋትሲን እና ባለባርኔጣው ማነኪን የሚባሉት አእዋፍ ይገኙበታል። ኒክ አቸሰን የተባለ አንድ የአእዋፍ አስጎብኚና የአካባቢ ጥበቃ ኤክስፐርት፣ “ቀላ ያለ ክንፍ እንዳለው እንደ ድንክ ታይራንት እና እንደ አመዴ ወፍ ያሉ ብርቅዬ አእዋፍ ለማየት ብዙ ጎብኚዎች ከመላው ዓለም ይመጣሉ” በማለት ነገረን።

በፓርኩ ውስጥ ከሚኖሩት በርካታ አጥቢ እንስሳት መካከል ግዙፉ ምስጥ በል፣ ባለ ጎፈር ተኩላ፣ ጃጓር፣ ፔካሪ፣ ታፒርና የፓምፓው ድኩላ ይገኙበታል። በፓርኩ ዙሪያ የሚገኙትና ፓርኩን የሚያጠጡት በርካታ ወንዞችም በሕያዋን ፍጥረታት የተሞሉ ናቸው። ከእነዚህ ፍጥረታት መካከል 62 የሚያክሉ በውሃና በየብስ መኖር የሚችሉ እንስሳት ዝርያዎች፣ 254 የሚያክሉ የዓሣ ዝርያዎች እንዲሁም ኬመን የሚባሉ የአዞ ዝርያዎች፣ ግዙፍ የወንዝ ኦተሮች፣ ካፐባረ የተባሉ ትልልቅ የአይጠ መጎጥ ዝርያዎችና ሐምራዊ ቀለም ያላቸው የሚያማምሩ ዶልፊኖች ይገኙበታል። በእርግጥም ይህ ፓርክ ተፈጥሮን ለሚያፈቅር ሰው ገነት ነው ማለት ይቻላል!

በአማዞንያ በርካታ የነብር ዝርያዎች ስላሉ ብዙ ጎብኚዎች ይፈራሉ፤ እኛም ስጋት ገብቶን ነበር። የሎስ ፍየሮስ ካምፕ አስተዳዳሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርኩ ውስጥ ባደረበት ወቅት ያጋጠመውን ሁኔታ እንደሚከተለው ሲል አጫወተን፦ “እኩለ ሌሊት ላይ አንድ የሚያየኝ ነገር እንዳለ ስለተሰማኝ በጣም ከበደኝና ከእንቅልፌ ነቃሁ። በመስኮት በኩል ወደ ውጭ ስመለከት አንድ ጃጓር አፍጥጦ ሲያየኝ ተመለከትኩ፤ በመካከላችን ያለው የሽቦ ወንፊት ብቻ ነበር! በጣም ከመፍራቴ የተነሳ ባኞ ቤት ገብቼ በሩን ቆለፍኩና እስኪነጋ ድረስ እዚያ ቆየሁ።” ይህን ስንሰማ ደግሞ ፍርሃታችን ጨመረ።

ይሁን እንጂ አስተዳዳሪው በመቀጠል እንዲህ አለን፦ “ትንሽ ቆይቶ እንስቷ ጃጓር ብዙውን ጊዜ ሌሊት ላይ አካባቢውን እየተዘዋወረች እንደምታይ ሆኖም እንደማትተናኮል አወቅኩ። እንዲያውም በሞቃት ወራት ጃጓሮች ወደ ካምፑ ገብተው ቀዝቀዝ በሚለው የጎጆዎቹ በረንዳ ላይ ይተኛሉ። አንድ አዲስ ሰው እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥመው ምን ያህል እንደሚደነግጥ መገመት ትችላላችሁ! ቀደም ሲል፣ በተለይ በማታ በምናስጎበኝበት ጊዜ ጠመንጃ እንይዝ ነበር። አሁን ግን ምንም ነገር አንይዝም። ይህ የሆነው የእንስሳቱ ባሕርይ ስለተለወጠ አይደለም። የተለወጠው የእኛ አመለካከት ነው።” ያም ቢሆን ግን አስተዳዳሪው ማንኛውንም የዱር እንስሳ በአክብሮት መያዝ እንዳለብን አስጠነቀቀን።

በጫካው ውስጥ ወደ ኤል ኤንካንቶ ፏፏቴ ያደረግነው ጉዞ

በፓርኩ ውስጥ የሚገኙት በርካታ ፏፏቴዎች የጎብኚዎችን ቀልብ ይስባሉ። ከአስጎብኚያችን ከጊዶ ጋር ሆነን ከዋንቻካ ፕላቶ ላይ 80 ሜትር ያህል ቁልቁል ወደሚወረወረው ወደ ኤል ኤንካንቶ ፏፏቴ ጉዞ የጀመርነው ማለዳ ላይ ነበር። ፏፏቴው አጠገብ ለመድረስ ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ 6 ኪሎ ሜትር ያህል የተጓዝን ሲሆን በምናልፋቸው ቦታዎች ሁሉ ስፓይደር (ሸረሪት) እና ሆውለር (ጩኸታም) የሚባሉ የጦጣ ዝርያዎች በዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ሆነው ሰላምታ ይሰጡን ነበር። ሁለቱም የጦጣ ዝርያዎች የሚገባቸውን ስያሜ አግኝተዋል፤ ስፓይደር የሚባለው ጦጣ ልክ እንደ ሸረሪት ቶሎ ዓይን ውስጥ የሚገቡት ረጃጅም የሆኑት እጆቹና እግሮቹ ሲሆኑ ሆውለር የሚባለው ጦጣ ደግሞ እስከ 3 ኪሎ ሜትር ድረስ ሊሰማ የሚችል ድምፅ አለው! አንገቷ ላይ ቀይ ጣል ያደረገባት የቱርክ ዶሮ የምትመስል ፓይፒንግ ግዋን የተባለች ወፍ ቁርሷን ፍለጋ ከፊታችን ሽው ብላ አለፈች። ጊዶ አጠገባችን በሚገኘው ጅረት ዳርቻ የተለያዩ የእግር ኮቴዎች አሳየን። ይህ ሰው ጥሩ ልምድ ያካበተ አስጎብኚ በመሆኑ ዱካዎቹ የሁለት የተለያዩ የድኩላ ዝርያዎች፣ የታፒር፣ የጃጓርና የኩጋር እንደሆኑ አወቀ። በዚህ ጊዜ፣ ብዙ ፍጥረታት ከተሸሸጉበት ሆነው እንደሚያዩንና አካባቢው ቀንም ሆነ ሌሊት የተለያዩ ሕያዋን ፍጥረታት የሚርመሰመሱበት ስፍራ እንደሆነ ተሰማን።

የተለያየ ሥነ ምህዳር ያለው ይህ ፓርክ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎች ስላሉበት በትዝብት የሚመለከቱን ፍጥረታት የሚሸሸጉበት ቅጠል አያጡም። እንዲያውም ከ100 የሚበልጡ የኦርኪድ ዝርያዎችን እንዲሁም በርካታ የዛፍ፣ የፈርን፣ የብሮሚሊያድና የሐረግ ዝርያዎችን ጨምሮ በፓርኩ ውስጥ 4,000 የሚያክሉ የዕፅዋት ዝርያዎች እንደሚኖሩ ይገመታል። በመንገዳችን ዳርና ዳር ያገኘናቸውን ፍራፍሬዎች እያጣጣምን፣ አስደሳች የሆኑትን ኅብረ ቀለማት እያደነቅን፣ የአበቦቹን መዓዛ በአፍንጫችን እየማግን ጉዟችንን ቀጠልን። ከቀመስናቸው ፍራፍሬዎች መካከል ዛፍ ላይ የሚበቅለው የማንጋባ ፍሬና ሐረግ ላይ የሚያድገው ፓሽን የተባለ ፍሬ ይገኙበታል።

በመጨረሻ አንድ ጅረት እንደተሻገርን ፏፏቴው የሚፈጥረውን ድምፅ ከሩቅ መስማት ጀመርን። አንድ እርምጃ በተራመድን ቁጥር የፏፏቴው ድምፅ ይጨምራል። በድንገት አንድ ገላጣ ቦታ ላይ ስንደርስ ግርማ ሞገስ ያለው የኤል ኤንካንቶ ፏፏቴ ከፊታችን ድቅን አለ፤ ታችኛው የፏፏቴው ክፍል ጢስ ይመስላል። ከፏፏቴው ሥር ባለው ጥርት ያለ ውሃ ዙሪያ የሚገኙት ቋጥኞች በብሮሚሊያድ እና በፈርኖች አጊጠዋል። ጊዶ “በሞቃታማ ወራት ጦጣዎች ቀዝቀዝ እንዲላቸው ወደዚህ ይመጣሉ” በማለት ነገረን። እኛም የእነሱን ምሳሌ ተከትለን ይህን ውብ አካባቢ እያደነቅንና እየተምዘገዘገ የሚወርደው ፏፏቴ የሚያሰማውን ደስ የሚል ድምፅ እያዳመጥን ራሳችንን ቀዝቀዝ አደረግን።

የአካባቢ ጥበቃ—ኖኤል ኬምፕፍ ሜርካዶ ያቆየው ቅርስ

የአካባቢ ጥበቃ ኤክስፐርት የነበረው ኖኤል ኬምፕፍ ሜርካዶ የሞተው በ1986 ነበር። ይሁን እንጂ በቦሊቪያ ውስጥ የሚገኘውን ይህን አካባቢ ጠብቆ ለማቆየት ጀምሮት የነበረው ጥረት አሁን ድረስ ቀጥሏል። በ1996 የቦሊቪያና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታት በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚለቀቀው በካይ ጋዝ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ብሎም ዘላቂነት ያለው ልማት ለማካሄድ 880,000 ሄክታር ስፋት ያለውን ደን ጠብቀው ለማቆየት ስምምነት አድርገው ነበር። በቀጣዩ ዓመት የቦሊቪያ መንግሥትና ሦስት የኃይል ማመንጫ ተቋማት ኖኤል ኬምፕፍ የአየር ንብረት መቆጣጠሪያ ፕሮጀክትን ጀምሩ፤ ይህ ፕሮጀክት ሲጀመር 880,000 ሄክታር ስፋት ባለው ደን ውስጥ ይካሄድ የነበረው ሕጋዊ የዛፍ ቆረጣም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ ተደረጉ። ይህ ቦታ የብሔራዊ ፓርኩ ክፍል እንዲሆን ሲደረግ የፓርኩ ስፋት በእጥፍ ሊጨምር ችሏል።

ዕጹብ ድንቅ የሆነውን ይህን አካባቢ መጎብኘታችን ለፈጣሪም ሆነ እሱ በፕላኔቷ ምድራችን ላይ ያኖራቸው ሕያዋን ፍጥረታት ላላቸው ውበትና ብዛት ያለንን አድናቆት በእጅጉ ጨምሮልናል። መዝሙር 104:24 “[ይሖዋ] ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው! ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤ ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች” ይላል። የሰው እጅ ባላበላሸው በዚህ ‘የጠፋ ዓለም’ ውስጥ በተጓዝንበት ወቅት ውበቱን ወደ ውስጣችን ከማስገባት ውጪ ምንም ዓይነት ጉዳት ላለማድረስ ቀስ ብለን መርገጥ እንዳለብን ተሰምቶን ነበር፤ እንዲሁም በካሜራችን ከቀረጽነው ፎቶግራፍና በልባችን ውስጥ ከቀረው ትዝታ በቀር ምንም ነገር ላለመውሰድ እንጠነቀቅ ነበር።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 ግንቦት 1925 ፎሴት ስለጉዞው ለባለቤቱ ደብዳቤ ጽፎላት ነበር። ይህ የመጨረሻው ደብዳቤ ሲሆን በዚያው ጠፍቶ የቀረበት ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ አይታወቅም።

^ አን.3 በ1979 የተቋቋመው ይህ ፓርክ በመጀመሪያ ዋንቻካ ብሔራዊ ፓርክ ተብሎ ይጠራ ነበር። ለዚህ ፓርክ በ1988 አዲስ ስም ተሰጥቶታል፤ ይህ የሆነው በአካባቢው ሲዘዋወር ድንገት ሕገወጥ የኮኬይን መቀመሚያ ላቦራቶሪ በማግኘቱ ምክንያት በዕፅ አዘዋዋሪዎች ለተገደለው ኬምፕፍ ሜርካዶ ለተባለ ቦሊቪያዊ ባዮሎጂስት መታሰቢያ እንዲሆን ታስቦ ነው።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የወይን ጠጅና ቀይ ቀለም ያለው ኦርኪድ

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ የሚገኘው አልፌልድ ፏፏቴ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማካው የሚባሉት በቀቀኖች

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤል ኤንካንቶ ፏፏቴ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከአየር ላይ የተነሳ ፎቶግራፍ፦ ® 2004 Hermes Justiniano/BoliviaNature.com

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ኦርኪድ፣ አልፌልድ ፏፏቴና ማካው፦ ® 2004 Hermes Justiniano/BoliviaNature.com