በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቴክኖሎጂ ፍንዳታ

የቴክኖሎጂ ፍንዳታ

የቴክኖሎጂ ፍንዳታ

በአልባኒያ አንድ አረጋዊ ሰው በአህያ ላይ ተቀምጠው እየሄዱ በሞባይል ስልክ ሲያወሩ ማየት የተለመደ ነው። በሕንድ አንድ ለማኝ ልመናውን አቋርጦ ስልክ ለመደወል ወይም ጥሪ ለመቀበል ሞባይሉን ሊያነሳ ይችላል። አዎን፣ የሞባይልም ሆነ የኮምፒውተር እንዲሁም የቴሌቪዥን ቴክኖሎጂ ሀብታም ድሃ ሳይል በመላው ዓለም የተዳረሰ ከመሆኑም ሌላ ለብዙዎች የሕይወታቸው ክፍል ሆኗል።

የቴክኖሎጂ መስፋፋት ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው በሞባይል ስልኮች እንደ አሸን መፍላት ሲሆን አብዛኞቹ ሞባይል ስልኮች ደግሞ እንዲሁ ስልክ ብቻ አይደሉም። በጣም ዘመናዊ የሆኑት ሞባይል ስልኮች የኢንተርኔት አገልግሎት ለማግኘት፣ የኢ-ሜይልና አጫጭር የጽሑፍ መልእክቶችን ለመላክና ለመቀበል፣ ቴሌቪዥን ለመመልከት፣ ሙዚቃ ለማዳመጥና ፎቶግራፍ ለማንሳት የሚያስችሉ ከመሆኑም ሌላ ግሎባል ፖዚሽኒንግ ሲስተም (GPS) የሚባል አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ ሊኖራቸው ይችላል! እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያሉት ስልኮች ለመደዋወልም ያገለግላሉ።

ዋሽንግተን ፖስት በሚባለው ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ እንደገለጸው፣ እንደ ኮምፒውተር ብዙ ነገሮችን ማከናወን የሚችል አንድ ዘመናዊ ሞባይል ስልክ “መረጃ የማስተናገድ አቅሙ በ1965 የሰሜን አሜሪካ አየር ኃይል [የሚጠቀምበት መሣሪያ] ከነበረው አቅም ይበልጣል።” ጋዜጣው አክሎ እንደገለጸው “በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ ካሉት ሁለት ሰዎች መካከል አንዱ ሞባይል ስልክ ያለው ሲሆን” ቢያንስ ቢያንስ 30 የሚያህሉ አገሮች ከሕዝቦቻቸው ቁጥር የሚበልጥ ሞባይል ስልክ አላቸው። በእርግጥም “በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በዓለም ዙሪያ እጅግ ፈጣን የሆነ የቴክኖሎጂ መስፋፋት” እየተመለከትን እንደሆነ ጋዜጣው ተናግሯል።

በመላው ዓለም ከሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች መካከል ወደ 60 በመቶ የሚጠጉት የሚኖሩት በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ነው፤ በመሆኑም እጅግ ዘመናዊ ከሆኑት የመገናኛ ዘዴዎች መካከል በእነዚህ አገሮች በርካታ ተጠቃሚዎች በማፍራት ረገድ ሞባይል ስልክ የመጀመሪያው ሊሆን ችሏል። ለምሳሌ ያህል፣ በአፍጋኒስታን በ2008 በየወሩ 140,000 ገደማ ለሚሆኑ አዲስ ደንበኞች የሞባይል ስልክ አገልግሎት ይሰጥ የነበረ ሲሆን በአፍሪካ ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዚህ ስልክ ተጠቃሚዎች ብዛት በየዓመቱ 50 በመቶ ገደማ ጨምሯል።

ይሁን እንጂ በመገናኛ ዘዴዎች ረገድ የተገኘው እድገትና ስርጭቱ ያስከተላቸው ችግሮችም አሉ። ሞባይል ስልኮች፣ ፔጀሮችና ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች ሰዎችን በማንኛውም ጊዜና ቦታ ማግኘት እንዲቻል በማድረጋቸው አንዳንድ ተጠቃሚዎች ከዚህ የኤሌክትሮኒክ መረብ ማምለጥ የሚቻልበት መንገድ እንደሌለ ይሰማቸዋል። በሌላው ጽንፍ ደግሞ ቴክኖሎጂ ካስገኛቸው የመገናኛ መሣሪያዎች አልላቀቅ የማለትና ምን አዲስ ነገር እንዳለ ለማወቅ የመጓጓት አባዜ የተጠናወታቸው የቴክኖሎጂ “ሱሰኞች” አሉ።

ከዘመናዊ የመገናኛና የመልእክት መለዋወጫ ዘዴዎች ጋር ተያይዘው ከሚመጡት ችግሮች መካከል ዋነኞቹ የዚህ ቴክኖሎጂ “ሱሰኛ” መሆን፣ የትኩረት መከፋፈል እንዲሁም ከጀመሩት ነገር መስተጓጎል ሳይሆኑ አይቀሩም። * ይሁን እንጂ እነዚሁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ብዙ ጥቅምም አላቸው። ታዲያ ሚዛኑን በጠበቀ፣ ጥበብ በታከለበትና አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ በእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ልትጠቀም የምትችለው እንዴት ነው? የሚቀጥሉት ርዕሶች ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 እነዚህ ተከታታይ ርዕሶች የሚያተኩሩት እንደ ሞባይል ስልኮችና ኮምፒውተሮች እንዲሁም ቴሌቪዥንና ኢንተርኔት በመሳሰሉት ነገሮች ላይ ነው። እዚህ ላይ “ቴክኖሎጂ” የሚለው ቃል በተለየ መንገድ ካልተገለጸ በቀር የሚያመለክተው እነዚህን ነገሮች ነው።