በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለጦርነት የነበረኝ ፍቅር የጠፋበት መንገድ

ለጦርነት የነበረኝ ፍቅር የጠፋበት መንገድ

ለጦርነት የነበረኝ ፍቅር የጠፋበት መንገድ

ቶማስ ስቱበንቮል እንደተናገረው

ኅዳር 8, 1944 ኒው ዮርክ ሲቲ ተወለድኩ። ያደግኩት በደቡብ ብሮንክስ ሲሆን በወቅቱ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት ሰፈሮች በጎሳ ተከፋፍለው ነበር። በልጅነቴ አብዛኛውን ጊዜዬን ያሳለፍኩት በጎዳናዎች ላይ ነበር፤ በመሆኑም በጎሳ የተከፋፈሉት የተለያዩ የወሮበላ ቡድኖች የያዟቸውን ሰፈሮች ለይቼ ለማወቅና ከእነሱ ጋር ተከባብሬ መኖር የምችለው እንዴት እንደሆነ ለመማር ጊዜ አልወሰደብኝም። እነዚያ የወሮበላ ቡድኖች በሚፈጽሟቸው የወንጀል ድርጊቶችና በጠበኝነታቸው የተፈሩ ነበሩ።

የ12 ዓመት ልጅ ስሆን የአንዱ ወሮበላ ቡድን አባል ሆንኩ። ለቡድናችን ዘ ስከልስ (የራስ ቅሎች) የሚል ስም አወጣንለት። እኔና ጓደኞቼ የባቡር ፉርጎዎችን ሰብረን በመግባት የኦቾሎኒ ቅቤና ሌሎች የምግብ ሸቀጦችን የያዙ ትልልቅ እሽጎችን እንሰርቅ ነበር። በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ያቀፉ የወሮበላ ቡድኖች ደግሞ ከሌሎቹ የባሰ ዓይን ያወጣ ወንጀል ይፈጽሙ ነበር። እንደነዚህ ባሉ ቡድኖች መካከል የተደረጉት በርካታ ድብድቦች ለብዙ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆነዋል። በአንድ ወቅት፣ በጣም የምወደው ጓደኛዬ ዓይኔ እያየ በስለት ተወግቶ ሞቷል።

በጦርነት የመካፈል ጉጉት አደረብኝ

በወሮበላ ቡድን ውስጥ ያሳለፍኩት ሕይወት እውነተኛ ደስታ አላመጣልኝም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከተማውን ለቅቄ ለመውጣት ወሰንኩ። ኤዲ የተባለው አጎቴ ኮሪያ ዘምቶ በነበረበት ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሠራዊት ክፍል በሆነው ባሕር ኃይል ውስጥ አገልግሎ ነበር። አጎቴ ኤዲ ስለ ባሕር ኃይል ወታደሮች ሲነግረኝ እኔም እንደ እነሱ የመሆን ጉጉት አደረብኝ። እያንዳንዱ የባሕር ኃይል ወታደር ነገሮችን በሥርዓት የማደራጀት ብሎም የመምራት ችሎታ ያለው ከመሆኑም ሌላ ቆራጥ እርምጃ እንዲወስድ ተደርጎ የሠለጠነ ጠንካራ ተዋጊ እንደሆነ ነገረኝ። የባሕር ኃይሉ መፈክር በላቲን ቋንቋ ሴምፔር ፊዴሊስ ሲሆን “ምንጊዜም ታማኝነት” የሚል ትርጉም አለው፤ ይህ መፈክር በሠራዊቱ ዘንድ ታማኝነትና ቃል አክባሪነት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጣቸው ያሳያል። ብዙም ሳይቆይ የሠለጠነ የባሕር ኃይል ወታደር የመሆን ከፍተኛ ምኞት አደረብኝ።

ኅዳር 8, 1961 ልክ 17 ዓመት ሲሆነኝ በባሕር ኃይል ለመሠልጠን ተመለመልኩ። አራት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የባሕር ኃይል ወታደር ሆኜ ከማሠልጠኛው የጦር ሠፈር ተመርቄ ወጣሁ። በጦር ሠራዊቱ ውስጥ ያሳለፍኩትን የ11 ዓመት ወታደራዊ አገልግሎት ሀ ብዬ የጀመርኩት በዚህ ጊዜ ነበር።

የጦር ሠራዊት አባል የሆንኩት በሰላሙ ጊዜ ነበር። ያም ሆኖ የባሕር ኃይል ሕይወት የማያቋርጥ ሥልጠና የሚጠይቅ ነበር። መጀመሪያ ላይ ኦዋሁ፣ ሐዋይ ሄጄ እግረኛ ወታደርና የደፈጣ ተዋጊ እንድሆን የሚያስችለኝን ከፍተኛ ሥልጠና ለሁለት ዓመት ወሰድኩ። በ457 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝን ዒላማ አነጣጥሬ መምታት የምችል አልሞ ተኳሽ ሆንኩ። የማርሻል አርት፣ የፈንጂ አጠቃቀምና የካርታ ንባብ ሥልጠና የወሰድኩ ከመሆኑም በላይ ሕንፃዎችን ማውደምና የመልእክት ልውውጥ ማድረግ የምችለው እንዴት እንደሆነ ተማርኩ። እያንዳንዱን ጊዜ ደስ ብሎኝ አሳልፍ ነበር።

በሐዋይ ሥልጠናዬን ከጨረስኩ በኋላ ጃፓን ውስጥ በአትሱጊ የባሕር ኃይል አውሮፕላን ጣቢያ የሚገኙትን የጦር መሣሪያዎች እንድጠብቅ ለስድስት ወር ተመደብኩ። ብዙም ሳይቆይ በዩናይትድ ስቴትስና በሰሜን ቬትናም መካከል የነበረው ግጭት እየተባባሰ መጣ፤ እኔም ዩኤስኤስ ሬንጀር በተባለችው አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ላይ እንዳገለግል ተመደብኩ። አውሮፕላኖቻችን ቶንኪን ባሕረ ሰላጤ ላይ ከቆመችው መርከባችን በመነሳት ከሌሎች አውሮፕላኖች ጋር በመሆን ሰሜን ቬትናምን በቦምብ ደበደቧት። ጦርነት ውስጥ ለመካፈል የነበረኝ ጉጉት በመጨረሻ እውን ሆነ። ያም ሆኖ ሥራዬ መርከብ ላይ ብቻ በመሆኑ በምድር ላይ በመዋጋት የሚገኘው ደስታ እያመለጠኝ እንዳለ ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር።

የጦርነት እውነተኛ ገጽታ

በ1966 በጸደይ ወቅት ሬንጀር በተባለችው መርከብ ላይ እየሠራሁ ሳለ በወታደራዊ አገልግሎቴ አራት ዓመት ስለሞላኝ ሠራዊቱን እንድለቅ የስንብት ደብዳቤ ደረሰኝ። አብዛኞቹ ወታደሮች በእኔ ቦታ ቢሆኑ ኖሮ ከሚመጣው ደም መፋሰስ ለማምለጥ ሲሉ በደስታ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። እኔ ግን ለሙያዬ ከፍተኛ ፍቅር ስለነበረኝና ፕሮፌሽናል ተዋጊ ስለሆንኩ ሥራዬን ለመልቀቅ ምንም ፍላጎት አልነበረኝም። ስለዚህ ድጋሚ ለመመዝገብ ወሰንኩ።

የሠለጠንኩት ለመዋጋት እስከሆነ ድረስ ውጊያ ውስጥ መግባት እንዳለብኝ ተሰምቶኝ ነበር። ስለዚህ በእግረኛ ጦር ውስጥ ለማገልገል ራሴን በፈቃደኝነት አቀረብኩ። በባሕር ኃይል ውስጥ የእግረኛ ጦር አባል ልሁን እንጂ የትም ብመደብ ምንም ግድ አልነበረኝም። የሕይወቴ ዋነኛ ዓላማ የተዋጣለት የባሕር ኃይል ወታደር መሆን ነበር፤ ጦርነትም አምላኬ እየሆነ መምጣት ጀመረ።

ጥቅምት 1967 ወደ ቬትናም በተላክሁ ጊዜ ፍርሃትና ደስታ የተቀላቀለበት ስሜት ተሰማኝ። እዚያም እንደደረስኩ በክዋንግ ትሪ ጠቅላይ ግዛት ወደሚገኘው ጦር ግንባር ተወሰድሁ። አንድ ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተጧጧፈ ጦርነት ውስጥ ገባሁ። በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች ሲገደሉና ተመተው ሲቆስሉ እመለከት ነበር። ከጠላት ወገን የሚተኮሱ ጥይቶች መሬት ላይ ሲያርፉ አቧራውን ያቦኑት ነበር። ከጥቂት ቁጥቋጦዎች በቀር መጠለያ የሚሆን ምንም ነገር አልነበረም። እኔም መተኮስ ጀመርኩ። ሁኔታው በጣም አሰቃቂ ነበር። የምሞት መስሎ ተሰማኝ። በመጨረሻም ውጊያው አበቃ። እኔ በሕይወት ተረፍኩ፤ ይሁንና ሕይወታቸውን ለማዳን ተሸክሜ የወሰድኳቸው ወታደሮች ከሞት ሊተርፉ አልቻሉም።

በቀጣዩ አንድ ዓመት ከስምንት ወር ጊዜ ውስጥ በቬትናም ከተደረጉት ጦርነቶች ሁሉ እጅግ አሰቃቂ በሆነው ውጊያ ላይ ተካፍያለሁ። ሌት ተቀን ማለት ይቻላል ሙሉውን ሳምንት ያሳለፍኩት አንድም ስተኩስ በሌላ በኩል በጥይት እንዳልመታ ስሹለከለክ እንዲሁም በአንድ በኩል ላጠቃ ሳደፍጥ በሌላ በኩል ደግሞ ጥቃት እንዳይሰነዘርብኝ ስደበቅ ነበር። በእነዚያ ጊዜያት በአብዛኛው ከጠላት ጋር የምታኮሰው ጉድጓዶች ውስጥ ሆኜ ሲሆን እነዚህ ጉድጓዶች ዝናብ ሲጥል ወዲያውኑ ይጨቀዩ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ጉድጓዶቹ በጣም የሚቀዘቅዙና ምንም የማይመቹ ነበሩ። የምበላውም ሆነ የምተኛው እንደነዚህ ባሉት ጉድጓዶች ውስጥ ነበር።

የተሰጠኝን ጠላትን አድኖ የመግደል ተልእኮ ለመፈጸም እርጥበት አዘል አየር ያለውን ጫካ አንድ ሳይቀር ማዳረስ ይጠበቅብኝ ነበር፤ ይህ ደግሞ በማንኛውም ጊዜ ጥቅጥቅ ካለ ጥሻ ውስጥ በመውጣት ጥቃት ለሚሰነዝሩ የጠላት ወታደሮች እንድጋለጥ የሚያደርግ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ያለሁበት አካባቢ ለብዙ ሰዓታት በመድፍ ይደበደብ ነበር። ኬ ሳን በሚባል መንደር አካባቢ በተደረገ አንድ ውጊያ ላይ እኔ ካለሁበት ብርጌድ ውስጥ ሦስት አራተኛው የሚሆነው ወታደር ቆስሎ አሊያም ተገድሎ የነበረ ሲሆን የቀረነው 13 ብቻ ነበርን።

ጥር 30, 1968 ወደ አንድ ወታደራዊ ጦር ሠፈር ሄድኩ፤ ከአንድ ዓመት ለሚበልጡ ጊዜያት በጫካ ውስጥ ካሳለፍኩ በኋላ በድንኳን ውስጥ መተኛት የቻልኩት እዚህ ቦታ ስመጣ ነበር። ማለዳ ላይ የሰማሁት ጆሮ የሚያደነቁር የሞርታር ፍንዳታ ከእንቅልፌ ሲያባንነኝ ግን ያገኘሁት አንጻራዊ ምቾት በአጭሩ ተቀጨ። በፍንዳታው የተነሳ ቆስዬም ነበር። በርካታ የቦምብ ፍንጣሪዎች በትከሻዬና በጀርባዬ ላይ ተሰንቅረውብኝ ነበር። ያን ዕለት ጠዋት ጠላት መጠነ ሰፊ ወረራ ማካሄድ ጀምሮ ነበር።

በዚያ ጊዜ ፐርፕል ሃርት የሚባለውን በጦር ግንባር ለቆሰሉ ወታደሮች የሚሰጠውን ኒሻን ተሸለምኩ፤ ይሁን እንጂ የደረሰብኝ ጉዳት እንደገና ወደ ውጊያ እንዳልገባ እንቅፋት አልሆነብኝም። የሕክምና ባለሙያዎቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቦምብ ፍንጣሪዎቹን ያወጡልኝ ሲሆን እኔም ወዲያውኑ ከፍተኛ ውጊያዎች ከተካሄደባቸው የጦር ግንባሮች መካከል አንዱ ወደሆነው ወደ ሕዌ ከተማ አቀናሁ። በርካታ ሰዎችን በአንዴ እንደሚረፈርፍ የጦር መሣሪያ ያገኘሁትን ሰው ሁሉ ከመጨረስ ወደኋላ አልልም ነበር። ጠላትን መግደል ምንም አይመስለኝም ነበር። ለ32 ቀናት እያንዳንዱን ዕለት ያሳለፍኩት ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ጠላትን እያደንኩ በመግደል ነበር።

በወቅቱ የማደርገው ነገር ቅንጣት ታክል ሕሊናዬን ቆርቁሮኝ አያውቅም። እንዲህ እያልኩ አስብ ነበር፦ ‘ደግሞም ጠላት በሕዌ ከተማ የሚኖሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰላማዊ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን ሲገድል አልነበር። በየጎዳናውና በየመንገዱ በሺህ የሚቆጠሩ ሬሳዎች ተረፍርፈው ይታዩ ነበር። በየቦታው ሌላው ቀርቶ በአንዳንድ ሬሳዎች ሥር እንኳ ፈንጂዎች ተቀብረው ነበር። ጠላት ለሚያደርስብን ስውር አደጋ ዕለት ዕለት የተጋለጥን ነበርን።’ ይህ ሁሉ ወደኋላ እንድል አላደረገኝም። በእኔ አስተሳሰብ ጠላትን መግደል ትክክለኛ እርምጃ ነበር።

ለጦርነት የነበረኝ ከልክ ያለፈ ፍቅር

በሕዌ የተደረገው ውጊያ ካበቃ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለ13 ወር የሚቆየውን የመጀመሪያ ዙር ግዳጄን አጠናቀቅኩ። ይሁን እንጂ ጦርነቱ የተባባሰ ሲሆን እኔም በጦርነት የመካፈል ፍላጎቴን ይበልጥ ማርካት ፈልጌ ነበር። ስለዚህ በቬትናም ሌላ ዙር ለመቆየት ራሴን በፈቃደኝነት አቀረብኩ። በወቅቱ የባሻነት ማዕረግ የነበረኝ ሲሆን ልዩ ተልእኮ ተሰጠኝ። ይህም በትንንሽ የገጠር መንደሮች ውስጥ የሚዘምቱ የባሕር ኃይል ወታደሮችን መምራትን ይጨምር ነበር። እዚያም ከነዋሪዎቹ ጋር በመነጋገር ማኅበረሰባቸውን ከጥቃት መጠበቅ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እናሠለጥናቸው ነበር። ጠላት ብዙውን ጊዜ የአካባቢውን ሰው መስሎ ሊቀላቀል ስለሚችል ዘወትር ንቁ ሆነን እንጠብቅ ነበር። የሌሊት ሥራችን ጠላትን በጥንቃቄ እያደንን በመያዝ መግደል ነበር። ሥራው ከፍተኛ ውጥረት የሚያስከትል ቢሆንም ለጦርነት የነበረኝ ፍቅር እየጨመረ ሄደ።

በቬትናም ያሳለፍኩት ሁለተኛው ዙር ግዳጄ ምንም ሳይታወቀኝ አለፈ። አሁንም ለተጨማሪ ዙር በጦር ግንባሩ እንድቆይ ፈቃድ ጠየቅኩ። በዚህ ጊዜ ግን አለቆቼ ለጦርነት የነበረኝን ከልክ ያለፈ ፍቅር ስላስተዋሉ ሳይሆን አይቀርም ጥያቄዬን ውድቅ አደረጉት። ይሁን እንጂ ከባሕር ኃይል ሠራዊት ሙሉ በሙሉ አልተሰናበትኩም። ከዚህ ይልቅ ምልምል ወታደሮችን እንዳሠለጥን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተላክሁ። ለሦስት ዓመት ተኩል ትኩረቴ ሁሉ ያረፈው ተማሪዎቼን በሚገባ በማሠልጠን ላይ ነበር። ለተማሪዎቼ የማካፍላቸው ብዙ ነገር ነበረኝ፤ በተቻለኝ መጠን ሁሉም ልክ እንደ እኔ ሰው ጨራሽ መሣሪያ እንዲሆኑ ጥሬያለሁ።

የሕይወትን ዓላማ አገኘሁ

እንደ እኔ አሠልጣኝ ከሆነ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ጋር ወዳጅነት መሠረትኩ። ይህ ወዳጄ ሚስቱ ጥላው የሄደችው በቅርቡ እንደሆነ ነገረኝ። በዚህ ወቅት የይሖዋ ምሥክር ከሆነች ብዙም ያልቆየችው ክሪስቲን አንቲስዴል የተባለችው እህቱ እሱ ቤት መጥታ ሁለት ትንንሽ ልጆቹን መንከባከብ እንደምትፈልግ እንደነገረችውም አጫወተኝ። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በዚህ ጊዜ ነበር።

ያደግሁት በካቶሊክ እምነት ውስጥ ሲሆን ለስምንት ዓመታት የተማርኩት በካቶሊኮች ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። እንዲያውም በቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ አገለግል ነበር። ያም ሆኖ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። ከክሪስቲን ጋር ስተዋወቅ ግን ሁኔታው ተቀየረ። ከዚህ በፊት ሰምቼ ከማላውቀው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር አስተዋወቀችኝ። ትክክለኛ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከሐሰት ትምህርቶች ለይቼ ማወቅ ቻልኩ።

ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ሰዎችን በገሃነመ እሳት ያቃጥላል የሚለውን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ እንደማይደግፍ ተማርኩ። (መክብብ 9:5, 10) መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ሥላሴ እንደሆነ አያስተምርም። (ዮሐንስ 14:28) በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ክፋትን፣ ሥቃይንና ሞትን እንደሚያስወግድ እንዲሁም ታዛዥ የሰው ዘሮች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ያስተምራል። (መዝሙር 37:9-11፤ ራእይ 21:3, 4) በተጨማሪም የአምላክ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምን እንደሆኑ ተማርኩ። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አምላክ ይሖዋ የሚባል ስም እንዳለውም አወቅኩ። (መዝሙር 83:18 NW) እነዚህን ሁሉ በማወቄ በጣም ተደሰትኩ!

ኅዳር 1972 ወታደሮችን የውጊያ ስልት እንዳሠለጥን ወደ ሌላ የጦር ካምፕ ተዛወርኩ። እዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ የተገኘሁ ሲሆን በመካከላቸው ባለው ወዳጃዊ መንፈስና እውነተኛ የወንድማማችነት ፍቅር ተደነቅሁ።

ይሁን እንጂ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ በተማርኩ መጠን ሕሊናዬ የዚያኑ ያህል ይረብሸኝ ጀመር። አኗኗሬ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር በእጅጉ የሚቃረን ነበር። ሕይወቴን ያዋልኩት የዓመፅ ድርጊቶችን በመፈጸምና በብሔራዊ ስሜት ተነሳስቼ በጦርነት በመካፈል ነበር፤ እነዚህ ደግሞ አምላክ የሚጠላቸው ነገሮች ናቸው።

የባሕር ኃይል ወታደር ሆኜ የይሖዋን አምልኮ ማራመድ እንደማልችል ተገነዘብኩ። ለጦርነት የነበረኝ ፍቅር የጠፋው በዚህ ጊዜ ነው። በመሆኑም ሥራዬን ለመልቀቅ ወሰንኩ። መልቀቂያዬን ለማግኘት አንዳንድ ጉዳዮችን ማስፈጸም እንዲሁም ቃለ ምልልስና የአእምሮ ጤንነት ምርመራ ማድረግ የተወሰኑ ወራት ወሰደብኝ፤ በመጨረሻም ከሠራዊቱ በክብር እንድሰናበት ተፈቀደልኝ። በዚህ ጊዜ የተሰናበትኩት ግን ከሕሊና የተነሳ በውትድርና ለማገልገል ፈቃደኛ ባለመሆኔ ነው። በባሕር ኃይል ጦር ሠራዊት ውስጥ ያሳለፍኩት የ11 ዓመት ወታደራዊ አገልግሎት በዚህ መልኩ አበቃ።

አሁን በኢሳይያስ 6:8 ላይ እንደተጠቀሰው ለይሖዋ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ማለት እችላለሁ። አዎን፣ ጉልበቴንና ተግቶ የመሥራት ፍላጎቴን የባሕር ኃይል ሠራዊቱን ለማገልገል ከመጠቀም ይልቅ እውነተኛውን አምላክ ለማገልገል ላውለው ዝግጁ ሆንኩ። በመሆኑም ሐምሌ 27, 1973 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ከአምስት ወራት በኋላ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘኋትን የይሖዋ ምሥክር ማለትም ክሪስቲን አንቲስዴልን አገባሁ።

እኔና ክሪስቲን አብረን የቆየንባቸውን 36 ዓመታት ያሳለፍናቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት እንዲያገኙና ወደ አምላክ እንዲቀርቡ በመርዳት ነው። ለስምንት ዓመታት በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በሚስዮናዊነት አገልግለናል። ላለፉት 18 ዓመታት ወደተለያዩ አካባቢዎች በመጓዝ የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች ሳገለግል ቆይቻለሁ። እኔና ባለቤቴ በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ በስፓንኛ ቋንቋ የሚመሩ ጉባኤዎችን ጎብኝተናል።

እኔ እስከማውቀው ድረስ በጦርነት ያሳለፍኳቸው ጊዜያት የአእምሮ ሕመምም ሆነ የስሜት ቀውስ አላስከተሉብኝም። በጦርነት በመካፈልና አሰቃቂ ነገሮችን በማየት ሳቢያ የሚመጣ የመንፈስ ጭንቀት፣ ቅዥትና መጥፎ ትዝታ አጋጥሞኝ አያውቅም። ወደ ይሖዋ አምላክ ከቀረብኩ ወዲህ ግን በጦርነቱ ወቅት የሰዎችን ሕይወት ማጥፋቴ በጣም ይጸጽተኛል።

ብዙ ጥረት ቢጠይቅብኝም እንዲህ ያለውን ከፍተኛ ለውጥ በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ። በቀድሞ ሕይወቴ ለሠራሁት ጥፋት የአምላክን ምሕረት እንዳገኘሁ ይሰማኛል። በአሁኑ ጊዜ የተቀበልኩት ተልእኮ የሰዎችን ሕይወት ማጥፋት ሳይሆን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖርን ተስፋ ለሰዎች ማወጅ ነው። የባሕር ኃይል ወታደር በነበርኩበት ጊዜ ማንኛውንም ነገር የፈጸምኩት ባለማወቅና በተሳሳተ ቅንዓት ነበር። አሁን የይሖዋ ምሥክር እንደመሆኔ መጠን መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር በትክክል ተገንዝቤያለሁ። በመሆኑም ማንኛውንም ነገር የማደርገው አንድ እውነተኛና ሕያው አምላክ እንዳለ፣ እሱም አፍቃሪ አምላክ እንደሆነና ወደፊት ጥሩ የሆኑ ነገሮችን የሚያገኙት እሱን የሚወዱና የሚታዘዙ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ባለኝ ጽኑ እምነት የተነሳ ነው።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሌት ተቀን ማለት ይቻላል ሙሉውን ሳምንት ያሳለፍኩት አንድም ስተኩስ በሌላ በኩል በጥይት እንዳልመታ ስሹለከለክ እንዲሁም በአንድ በኩል ላጠቃ ሳደፍጥ በሌላ በኩል ደግሞ ጥቃት እንዳይሰነዘርብኝ ስደበቅ ነበር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወደ ይሖዋ አምላክ ከቀረብኩ ወዲህ በጦርነቱ ወቅት የሰዎችን ሕይወት ማጥፋቴ በጣም ይጸጽተኛል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በአሠልጣኝነት ሥራ ላይ እያለሁ (ከላይ) እና በቬትናም በእግረኛ ጦር ውስጥ ሳለሁ (በስተ ግራ)

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፐርፕል ሃርት የሚባለውን በጦር ግንባር ለቆሰሉ ወታደሮች የሚሰጠውን ኒሻን ተሸለምኩ፤ ይሁን እንጂ የደረሰብኝ ጉዳት እንደገና ወደ ውጊያ እንዳልገባ እንቅፋት አልሆነብኝም

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ክሪስቲን አብረን የቆየንባቸውን 36 ዓመታት ያሳለፍናቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት እንዲያገኙ በመርዳት ነው