በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሕይወት የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?

በሕይወት የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?

በሕይወት የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ ስሙ ይሖዋ እንደሆነና ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ እንዳለው ይናገራል። ይሖዋ በጠፈር አካላት ውስጥ ያለው ኃይል ሁሉ ምንጭና የጽንፈ ዓለም ፈጣሪ ነው። (መዝሙር 83:18፤ 92:5) በመጽሐፍ ቅዱስ መግቢያ ላይ ያለው ሐሳብ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” ይላል። ቀጥሎም አምላክ ሰውን ‘በመልኩ’ ማለትም እንደ እሱ ዓይነት ባሕርያት እንዲኖሩት አድርጎ ፈጠረው፤ ከዚያም አምላክ የሰው ልጆች እንዲባዙና ምድርን እንዲሞሏት አዘዛቸው።—ዘፍጥረት 1:1, 26, 28

ታዲያ አምላክ፣ ምድርንና በላይዋ ያሉትን በርካታ እንስሳትና ዕፅዋት ጨምሮ ጽንፈ ዓለምን በአጠቃላይ የፈጠረው ለሰው ልጅ መኖሪያ እንዲሆን ብቻ ብሎ ነው? በሕይወት የመኖራችን ዓላማ ለጥቂት አሥርተ ዓመታት መኖር፣ መብላትና መጠጣት እንዲሁም ዘር መተካት ብቻ ነው?

አምላክ የፈጠረን ለምንድን ነው?

ይሖዋ አምላክ ሰውን የፈጠረው ፍቅር ስላለው ይኸውም የሰው ልጆች በሕይወት መኖር የሚያስገኘውን ደስታ እንዲያጣጥሙ ስለፈለገ ነው። አምላክ፣ የሰው ልጅ ውብ የሆነና የተትረፈረፉ ነገሮችን የያዘ መኖሪያ እንዲያገኝ በማሰብ የተለያዩ ፍጥረታትን ሲፈጥር በጣም እንደተደሰተ ምንም ጥርጥር የለውም። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአምላክ ዓላማ የሰው ልጆች ከፈጣሪያቸው ጋር የጠበቀ ቅርርብ እንዲመሠርቱ፣ እሱን እንዲያውቁትና እንዲያነጋግሩት ነበር፤ ይህ ደግሞ ሕይወታቸው ዓላማ እንዲኖረው ያደርጋል። የሰው ልጆች የተፈጠሩት ሰላም በሰፈነበትና ፍጹም በሆነ ዓለም ላይ ለዘላለም ለመኖር ነበር።—ዘፍጥረት 3:8, 9፤ መዝሙር 37:11, 29

ይሖዋ ለሰው ልጆች አስደሳችና ትርጉም ያለው ሥራም ሰጥቷቸው ነበር። አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች እንደሚከተለው ብሏቸው ነበር፦ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው።” (ዘፍጥረት 1:28) አዎን፣ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እንዲሁም ልጆቻቸው መላዋን ምድር አስደሳች ወደሆነች ገነት እንዲለውጧት ታዘው ነበር።

እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ዓላማ በዚያን ጊዜ አልተፈጸመም። * ሆኖም አምላክ ለሰው ልጆች የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ መፈጸሙ አይቀርም።—ኢሳይያስ 46:9-11፤ 55:11

የሰው ልጅ የሕይወትን ዓላማ ለማወቅ ጥረት ማድረጉ፣ አምላክን የማወቅና ከእሱ ጋር ዝምድና የመመሥረት ፍላጎት እንዳለው እንዲያውም እንዲህ ማድረግ እንደሚያስፈልገው ያሳያል። ሰው የማሰብ ችሎታ እንዲኖረው ተደርጎ የተፈጠረ ሲሆን ነገሮችን የመመርመርና የመረዳት ፍላጎት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የሰው ልጅ ስለ አምላክና ስለ ፍጥረት ሥራዎቹ አስደሳች የሆነ እውቀት መቅሰሙ ለዘላለም የሚቀጥል ሂደት ነው።

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሰው ልጅ በሕይወት የመኖሩ ዓላማ ምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ይደክሙበት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ከባድ የሥራ ጫና አየሁ። ሁሉንም ነገር በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ በሰዎችም ልብ ዘላለማዊነትን አኖረ፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ማወቅ አይችሉም። ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሰኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው።” (መክብብ 3:10-13) ከዚህ ለማየት እንደምንችለው ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ፍጥረታቱ የሚቀስሙት እውቀት ፈጽሞ ማለቂያ አይኖረውም።

ስለ አምላክ ተማር

የይሖዋን ፍጥረታት በመመርመር ስለ እሱ መማር ትችላለህ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፦ “የማይታዩት [የአምላክ] ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።” (ሮም 1:20) አዎን፣ ስለ ይሖዋ ፍቅር፣ ጥበብና ኃይል ከፍጥረት ሥራዎቹ ብዙ መማር ይቻላል።

ስለ አምላክ ለመማር የሚረዳን ሌላው ጠቃሚ ነገር ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈው ይህ መጽሐፍ ስለ ይሖዋ አመለካከት፣ ባሕርያትና ዓላማ የፍጥረት ሥራዎቹን በመመርመር ከምናገኘው የበለጠ እውቀት እንድንቀስም ይረዳናል።

መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ዓላማ በተመለከተ “ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 115:16) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው በዚህ ጽንፈ ዓለም ላይ ለሰው ልጅ ብቸኛ ተስማሚ መኖሪያ የምትሆነው ምድር ትመስላለች፤ ይሖዋም ምድርን ያዘጋጃት ለዚሁ ዓላማ ነው።

ታዲያ ወሰን የሌለው የሚመስለውን ጽንፈ ዓለምን በተመለከተስ ምን ማለት ይችላል? በዙሪያችን ያሉት ከዋክብት በሙሉ የተፈጠሩበት ዓላማ እኛ ያለንበት ሥርዓተ ፀሐይ ሚዛኑን ጠብቆ እንዲቀጥል በማድረግ በምድር ላይ ሕይወት መኖር የሚችልበት ሁኔታ ማመቻቸት ብቻ ነው? የጠፈር አካላት የተፈጠሩት በምሽት ሰማዩን ለማስዋብ ብቻ ነው? በአሁኑ ጊዜ የማናውቃቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ መገንዘብ ይኖርብናል። ሆኖም ይህ ጥሩ ነገር ነው! ለምን?

የሰው ልጅ ለዘላለም ቢኖርም የአምላክን ዓላማና እሱ የሠራቸውን ነገሮች ሙሉ በሙሉ መረዳት አይችልም። አምላክ ሁልጊዜ አዳዲስ ነገሮችን እያወቅንና ማብቂያ የሌለው ደስታ እያገኘን እንድንኖር ይፈልጋል። ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ሲኖሩ ስለ ጽንፈ ዓለም ብዙ ነገር ለማወቅ ሰፊ አጋጣሚ ይኖራቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ

^ አን.7 ብዙ ሰዎች አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ እንዳለ ማመን እንዲከብዳቸው ያደረጋቸው በዓለም ላይ የሚታየው ክፋትና መከራ ነው። ይህን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሰው የማሰብ ችሎታ እንዲኖረው ተደርጎ የተፈጠረ ሲሆን ነገሮችን የመመርመርና የመረዳት ፍላጎት አለው

[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

መጽሐፍ ቅዱስ ምድር የተፈጠረችበት ዋነኛ ዓላማ የሰው ልጆች ተደስተው እንዲኖሩባት እንደሆነ ይጠቁማል