በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጥልቅ ባሕር ውስጥ የሚኖሩ ግዙፍ ፍጥረታት

በጥልቅ ባሕር ውስጥ የሚኖሩ ግዙፍ ፍጥረታት

በጥልቅ ባሕር ውስጥ የሚኖሩ ግዙፍ ፍጥረታት

አንድ ግዙፍ ፍጡር በድንገት ከባሕር ውስጥ ወጣ፤ ከዚያም አንድን ጀልባ ጭምድድ አድርጎ በመያዝ በላዩ ላይ የተሳፈሩትን ሰዎች ጨምሮ ጀልባውን ቁልቁል ወደ ባሕሩ ጎትቶ አስገባ። ይህ ተቀንጭቦ የተወሰደ ሐሳብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ ለኖሩ አፈ ታሪኮች መነሻ ታሪክ ሆኖ አገልግሏል። ይሁን እንጂ ይህን ያህል ግዙፍ የሆኑ ፍጥረታት አሉ?

በ2007 ዓሣ አጥማጆች ከአንታርክቲካ ማዶ በሚገኘው በሮስ ባሕር ላይ ዓሣ እያጠመዱ እያለ ሳያስቡት ኮሎሳል ስኩዊድ የተባለ አንድ የባሕር ፍጡር ይዘው ነበር። ይህ ፍጡር ቴንታክሎቹን ጨምሮ 10 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከ500 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት አለው! የሳይንስ ሊቃውንት ይህ የስኩዊድ ዝርያ ከዚህም በላይ ማደግ እንደሚችል ያምናሉ።

ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነው ጃይንት ስኩዊድ ተብሎ የሚጠራው የባሕር ፍጡር ደግሞ የሰው ጭንቅላት የሚያህሉ ዓይኖች፣ የብረት ሽቦን ለመቁረጥ የሚያስችል ጥንካሬ ያለው የበቀቀንን የሚመስል ምንቃር፣ ቆንጥጠው ለመያዝ የሚረዱ የተደረደሩ መንጠቆዎች ያሉባቸው ስምንት እጆች እና ምግቡን የሚጎርስበት ሁለት ረጃጅም ቴንታክሎች አሉት። ይህ ፍጡር በውኃ ውስጥ በሰዓት 30 ኪሎ ሜትር መወንጨፍም ሆነ ወደ አየር ተወርውሮ መውጣት ይችላል!

ባለፈው መቶ ዓመት ውስጥ ከእነዚህ ግዙፍ ፍጥረታት መካከል በሰዎች የታዩት 50 አያክሉም፤ በመሆኑም እነዚህ ፍጥረታት ጥናት ተደርጎባቸው አያውቅም።

ግዙፍ የባሕር ዓሣ ነባሪዎች

ይሁን እንጂ ኮሎሳል እና ጃይንት የሚባሉት ስኩዊዶች እስከ 20 ሜትር የሚደርስ ቁመትና 50,000 ኪሎ ግራም የሚመዝን ክብደት ላለው ስፐርም ዌል ለተባለ ዓሣ ነባሪ ከአንድ ጊዜ ምግብ አያልፉም። የዚህ ዓሣ ነባሪ አንድ ጥርስ ብቻ 900 ግራም ይመዝናል! ሞተው በተገኙ አንዳንድ ስፐርም ዌሎች ሆድ ውስጥ የጃይንት ስኩዊድ የተወሰነ የሰውነት ክፍል ተገኝቷል። በተጨማሪም ሞተው በተገኙት በእነዚህ ዓሣ ነባሪዎች ግዙፍ ራስ ላይ የስኩዊድን መንጠቆ የመሰሉ ክብ ቅርጽ ያላቸው ጠባሳዎች ተገኝተዋል፤ ይህ ደግሞ ስኩዊዶቹ ከመበላታቸው በፊት የሞት ሽረት ትግል አድርገው እንደነበረ ያሳያል። በ1995 አንድ የሶቪየት ዓሣ ነባሪ አጥማጅ ቡድን አባላት፣ አንድ ጃይንት ስኩዊድ ከ40 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ከሚመዝን ስፐርም ዌል ጋር ሲፋለም እንዳዩ ተናግረዋል። በፍልሚያው ሁለቱም ሞተዋል። ታንቆ የሞተው ዓሣ ነባሪ የስኩዊዱ ራስ በሆዱ ውስጥ እንዳለ በባሕር ላይ ተንሳፎ ተገኝቷል።

ጃይንት ስኩዊድና ስፐርም ዌል ግዙፎች ቢሆኑም እንኳ ከአጥቢ እንስሳት መካከል በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ብሉ ዌል የሚባለው ዓሣ ነባሪ ከሁለቱም ይበልጣል። እስከ አሁን ከተመዘገቡት መካከል በርዝመት ተወዳዳሪ ያልተገኘላት በአንታርክቲካ የተያዘችው 33 ሜትር ርዝመት ያላት ብሉ ዌል ናት። ብሉ ዌል ክብደቱ እስከ 150,000 ኪሎ ግራም ሊደርስ ይችላል። የምላሱ ክብደት ብቻ እንኳ ከትልቅ ዝሆን ጋር እኩል ነው! እስቲ አስበው ገና የተወለደው ዓሣ ነባሪ እንኳ ከ3,000 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ሲሆን ርዝመቱ ከ7 እስከ 8 ሜትር ይደርሳል! ብሉ ዌል በጣም ብዙ ከመታደኑ የተነሳ በ1960ዎቹ ዓመታት ዝርያው ከምድር ገጽ ለመጥፋት ተቃርቦ ነበር፤ በአሁኑ ጊዜም ቢሆን የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል ከሚባሉት ዝርያዎች ዝርዝር ውስጥ ይገኛል።

አስፈሪ እና ገራም ፍጥረታት

ከሥጋ በል እንስሳ መካከል የሚመደበውና 3,000 አስፈሪ ጥርሶች ያሉት ታላቁ ነጭ ሻርክ ምናልባትም ከሁሉ የበለጠ አስፈሪ ዓሣ ሳይሆን አይቀርም። እስከ አሁን ከተመዘገቡት መካከል ትልቁ ነጭ ሻርክ 7 ሜትር ርዝመት የነበረው ሲሆን 3,200 ኪሎ ግራም ይመዝናል። ታላቁ ነጭ ሻርክ አስደናቂ የሆነ የማሽተት ችሎታ አለው፤ በ100 ሊትር ውኃ ውስጥ የገባን አንድ ጠብታ ደም እንኳ አሽትቶ መለየት ይችላል!

እስከ አሁን ዝርያቸው ካልጠፉት የዓሣ ዓይነቶች መካከል ትልቁ በአማካይ 7.5 ሜትር ርዝመት ያለው ዌል ሻርክ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ዌል ሻርኮች ርዝመታቸው የዚህን እጥፍ ሊያክል ይችላል። ይህ ሻርክ የአፉ ስፋት 1.4 ሜትር ሊደርስ የሚችል ሲሆን አንድን ሰው በቀላሉ መዋጥ ይችላል። ይሁን እንጂ ይህ ገራም ዓሣ፣ አስፈሪ ከሆኑት ከሌሎቹ ግዙፍ አዳኝ የባሕር ፍጥረታት በተለየ የሚመገበው በውቅያኖስ ላይ የሚንሳፈፉ ፕላንክተን የሚባሉ ጥቃቅን እፅዋትንና ትንንሽ ዓሦችን ነው።

ናሽናል ጂኦግራፊክ የተሰኘው መጽሔት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ነቢዩ ዮናስ በትልቅ ዓሣ እንደተዋጠ የሚገልጸውን ታሪክ በመጥቀስ “የዌል ሻርክ ለየት ያለ የምግብ አፈጫጨት ሥርዓት የዮናስን ታሪክ የሚደግፍ ነው” በማለት ዘግቧል። ዌል ሻርኮች “በድንገት የዋጧቸውን በቀላሉ የማይፈጩ ትላልቅ ነገሮች ያለምንም ጉዳት የሚያስወጡበት መንገድ” አላቸው።—ዮናስ 1:17፤ 2:10

ዓይናፋርና ግዙፍ የሆነው የባሕር ፍጥረት

ሌላው ግዙፍ የባሕር ፍጥረት እስከ 250 ኪሎ ግራም ድረስ ሊመዝን የሚችለው ጃይንት ኦክቶፐስ ነው። በአንድ ወቅት የዲያብሎስ ዓሣ ተብሎ ይጠራ የነበረው ይህ ፍጡር መርከቦችን ማስጠም ይችላል ተብሎ ይታሰብ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ኦክቶፐስ በዓለቶች እንዲሁም በባሕር ወለል ላይ ባሉ ስንጥቆች ውስጥ የሚደበቅ ዓይናፋር የሆነ ፍጡር ነው። ስምንት እጆቹ ሲዘረጋጉ እስከ 10 ሜትር ያህል ስፋት ሊኖራቸው የሚችል ሲሆን የአከርካሪ አጥንት ከሌላቸው ፍጥረታት ሁሉ ትልቅ አንጎል አለው። በእርግጥም ኦክቶፐስ በጣም ብልኅ በመሆኑ መውጫ መግቢያቸው በሚያደነጋግሩ መተላለፊያዎች እንደማለፍና በማዞር የሚከፈቱ ክዳኖችን እንደመክፈት ያሉ ውስብስብ ነገሮችን መማር ይችላል!

እንደ ጃይንት ስኩዊድ ሁሉ ጃይንት ኦክቶፐስም ቀለሙን በመቀየር ራሱን መሰወር፣ በውኃ ውስጥ ለመንቀሳቀስ እንደ ጀት መመንጠቅና ጥቅጥቅ ያለ የቀለም ደመና በመርጨት ከአደጋ ማምለጥ ይችላል። አልፎ ተርፎም ኦክቶፐስ ምግብ ለመፈለግ ከውኃ ወጥቶ የብስ ላይ ለአጭር ጊዜ መቆየት ይችላል!

በጥልቅ ባሕር ውስጥ የሚኖሩ እነዚህ ፍጥረታት በእርግጥም ፈጣሪያቸው ለሆነው ለይሖዋ ምስጋና ያመጣሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰ አንድ መዝሙራዊ “የባሕር ውስጥ ግዙፍ ፍጥረትና ጥልቅ ውሆች ሁሉ፣ እግዚአብሔርን [“ይሖዋን፣” NW] ከምድር አመስግኑት” ብሎ መዘመሩ ተገቢ ነበር።—መዝሙር 148:7

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

ምን ያህል ሊያድጉ ይችላሉ?

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ታላቁ ነጭ ሻርክ

ጃይንት ኦክቶፐስ

ዌል ሻርክ

ጃይንት ስኩዊድ*

ኮሎሳል ስኩዊድ*

*መጠኑ በግምት

ስፐርም ዌል

ብሉ ዌል

ጫማ 100 90 80 70 60 50 40 30 20 10 0

ሜትር 30 25 20 15 10 5 0

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታላቁ ነጭ ሻርክ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጃይንት ኦክቶፐስ

[በገጽ 16 እና 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ስፐርም ዌል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዌል ሻርክ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብሉ ዌል እና ግልገሏ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሻርክ፦ © Steve Drogin/SeaPics.com; ሥዕል፦ Getty Images; ኦክቶፐስ፦ © Brandon Cole

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ስፐርም ዌል፦ © Brandon Cole; ብሉ ዌል፦ © Phillip Colla/SeaPics.com; ዌል ሻርክ፦ © Steve Drogin/SeaPics.com