ዓላማ ያለው ንድፍ ወይስ ትርጉም የለሽ ሂደት?
ዓላማ ያለው ንድፍ ወይስ ትርጉም የለሽ ሂደት?
ዊልያም ፔሊ የተባሉ እንግሊዛዊ ቄስና የሥነ መለኮት ምሑር፣ ፈጣሪ መኖሩን እንዲያምኑ ያደረጓቸውን ምክንያቶች በ1802 አብራርተው ነበር። እኚህ ምሑር አንድን ጭው ያለ በረሃ ሲያቋርጡ ድንጋይ ቢያገኙ ድንጋዩ እዚያ ሊገኝ የቻለው በተፈጥሯዊ ሂደት ነው ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ እንደሚሆን ከተናገሩ በኋላ በረሃው ላይ ሰዓት ወድቆ ቢያገኙ ግን ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ እንደማይችሉ ገልጸዋል። እንዲህ ያሉት ለምንድን ነው? ሰዓት ንድፍ ወጥቶለትና በዓላማ የሚሠራ ነገር መሆኑ ግልጽ ስለሆነ ነው።
ፔሊ ያቀረቡት ሐሳብ ቻርልስ ዳርዊን በተባለው እንግሊዛዊ የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር። ይሁን እንጂ ፔሊ ከደረሱበት ድምዳሜ በተቃራኒ ዳርዊን፣ ሕያዋን ፍጥረታት ንድፍ ያላቸው የሚመስሉት “ተፈጥሯዊ ምርጦሽ” (natural selection) ብሎ በሰየመው ሂደት ምክንያት እንደሆነ ገልጿል። ብዙ ሰዎች የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ፣ ተፈጥሮ ንድፍ እንዳለው ማመን ስህተት መሆኑን የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ እንደሆነ ያስቡ ነበር።
ከፔሊና ከዳርዊን ዘመን ወዲህ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ብዙ ተጽፏል። ተፈጥሮ ንድፍ እንዳለው የሚገልጸውን ሐሳብና ተፈጥሯዊ ምርጦሽን የሚደግፈውን ጽንሰ ሐሳብ በተመለከተ የቀረቡት የመከራከሪያ ነጥቦች በተደጋጋሚ ጊዜያት ማስተካከያ ተደርጎባቸዋል፣ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል እንዲሁም ተሻሽለዋል። ሁለቱም አመለካከቶች ጽንፈ ዓለም፣ ዓላማ አለው ወይስ የለውም በሚለው ጉዳይ ረገድ ሰዎች ባላቸው እምነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። የምታምንበት ነገር ሕይወትህ ዓላማ ያለው በመሆኑ ወይም ባለመሆኑ ላይ ለውጥ ያመጣል። እንዴት?
የዳርዊን ጽንሰ ሐሳብ ያስከተለው ውጤት
ብዙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በዳርዊን ንድፈ ሐሳብ ማመናቸው ሕልውናቸው ዓላማ እንደሌለው እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል። መላው አጽናፈ ዓለምና በውስጡ ያሉት ነገሮች በሙሉ በቢሊዮኖች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ከተከሰተው “ታላቅ ፍንዳታ” (big bang) በኋላ ንጥረ ነገሮች በአጋጣሚ በመቀናጀታቸው ምክንያት የተገኙ ከሆኑ ሕይወት ምንም ዓላማ የለውም ማለት ነው። የኖቤል ተሸላሚና የባዮሎጂ ተመራማሪ የነበሩት ዣክ ሞኖ እንዲህ ብለዋል፦ “የሰው ልጅ በአጋጣሚ ወደ ሕልውና በመጣበት ግዙፍ ጽንፈ ዓለም ውስጥ ብቻውን መሆኑን በመጨረሻ ተገንዝቧል። የወደፊት ዕጣውም ሆነ ከእሱ የሚጠበቅበት ነገር በግልጽ አይታወቅም።”
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ፒተር ዊልያምስ አትኪንስ እንደሚከተለው በማለት ተመሳሳይ የሆነ አስተያየት ሰጥተዋል፦ “ዕፁብ ድንቅ የሆነው የዚህ ጽንፈ ዓለም መኖር በጣም አስደናቂ ነገር እንደሆነ ይሰማኛል። ግርማ ሞገስ የተላበሰ ቢሆንም ምንም ጥቅም የለውም።”
እንዲህ ባለው አስተሳሰብ የሚስማሙት ሁሉም ሳይንቲስቶች አይደሉም። ለዚህም ጥሩ ምክንያት አላቸው።
በጥንቃቄ መዋቀሩ ዓላማ ያለው ንድፍ ለመኖሩ ማስረጃ ይሆናል?
ብዙ ተመራማሪዎች የተፈጥሮን ሕግጋት በሚመረምሩበት ጊዜ ጽንፈ ዓለም ምንም ዓይነት ዓላማ የለውም የሚለው አስተሳሰብ አልዋጥ ይላቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ጽንፈ ዓለሙን የሚቆጣጠሩት መሠረታዊ ኃይሎች በጣም ያስደንቋቸዋል። ከእነዚህ ኃይሎች በስተጀርባ ያሉት ሕግጋት በጽንፈ ዓለም ውስጥ ሕይወት መኖር እንዲችል በጥንቃቄ ተስተካክለው የተቀመጡ ይመስላሉ። የጠፈር ተመራማሪ የሆኑት ፖል ዴቪስ “አሁን ያሉትን ሕግጋት በጣም በትንሹ እንኳ መለወጥ ሕይወት ያለው ነገር በሙሉ እንዲጠፋ ያደርጋል” ብለዋል። ለምሳሌ፣ የፕሮቶኖች ክብደት ከኒውትሮኖች በመጠኑ ያነሰ መሆኑ ቀርቶ ከኒውትሮኖች በትንሹ ቢበልጥ ፕሮቶኖች በሙሉ መልካቸው ተለውጦ ኒውትሮን ይሆኑ ነበር። እንዲህ መሆኑ ያን ያህል የከፋ ውጤት ይኖረዋል? “ፕሮቶኖችና እነሱ የሚያስገኙት ወሳኝ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሌሉ አተሞች ሊኖሩ አይችሉም” በማለት ዴቪስ አስረድተዋል።
የኤሌክትሮማግኔቲክ ኃይል፣ ኤሌክትሮኖች ወደ ፕሮቶኖች እንዲሳቡ በማድረግ ሞለኪውሎች እንዲፈጠሩ ያስችላል። ይህ ኃይል በጣም ከተዳከመ ኤሌክትሮኖች በአንድ አተም ኒውክሊየስ ዙሪያ በምሕዋራቸው ላይ ሊሽከረከሩ አይችሉም፤ ይህ ካልሆነ ደግሞ ሞለኪውሎች ሊፈጠሩ አይችሉም። በሌላ በኩል ደግሞ የኤሌክትሮማግኔቲክ ኃይል በጣም ከበረታ ኤሌክትሮኖች ከአንድ አተም ኒውክሊየስ ጋር ይጣበቃሉ። እንዲህ ከሆነ ደግሞ ኬሚካላዊ ለውጦች ሊኖሩ ስለማይችሉ ሕይወት አይኖርም ማለት ነው።
በኤሌክትሮማግኔቲክ ኃይል ላይ ትንሽ ለውጥ እንኳ ቢደረግ ይህ በፀሐይና ወደ ምድር በሚደርሰው የፀሐይ ኃይል ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። እንዲህ ያለው ለውጥ ተክሎች በፀሐይ ብርሃን አማካኝነት ምግባቸውን ለማዘጋጀት እንዲቸገሩ ወይም እንዲህ ማድረግ እንዳይችሉ ያደርጋል። ስለዚህ በምድር ላይ ሕይወት መኖር አለመኖሩ የተመካው የኤሌክትሮማግኔቲክ ኃይል *
ሳይዳከም ወይም በጣም ሳይበረታ በትክክለኛው መጠን በመኖሩ ላይ ነው።ሳይንስ ኤንድ ክርስቺያኒቲ—ፎር ቪውስ የተባለው መጽሐፍ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ኃይሎችና ንጥረ ነገሮች መጠናቸው በትንሹ እንኳ መዛባቱ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ ለማስረዳት ጥሩ ምሳሌ ተጠቅሟል። ፀሐፊው፣ አንድ አሳሽ “የመላው ጽንፈ ዓለም መቆጣጠሪያ የሚገኝበትን ክፍል” ሲጎበኝ በዓይነ ኅሊናቸው እንዲመለከቱ አንባቢዎቹን ይጠይቃል። በዚያም አሳሹ በማንኛውም መጠን ሊስተካከሉ የሚችሉ በጣም ብዙ የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ተደርድረው ይመለከታል፤ እንዲሁም በጽንፈ ዓለም ላይ ሕይወት እንዲኖር እያንዳንዱ የመቆጣጠሪያ መሣሪያ በትክክለኛው መጠን መስተካከል እንደሚኖርበት ይገነዘባል። እነዚህ መሣሪያዎች የስበት ኃይልን መጠን፣ የኤሌክትሮማግኔቲክ ኃይልን ጥንካሬ፣ በኒውትሮን ክብደትና በፕሮቶን ክብደት መካከል የሚኖረውን ሬሾ እና ወዘተ የሚቆጣጠሩ ናቸው። አሳሹ እነዚህን በርካታ የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ሲመለከት አሁን ካሉበት በተለየ መንገድ ሊቀመጡ ይችሉ እንደነበረ ያስተውላል። በተጨማሪም ጥንቃቄ የተሞላበት የሒሣብ ቀመር ከሠራ በኋላ መገንዘብ እንደቻለው ከመቆጣጠሪያ መሣሪያዎቹ መካከል በአንዱ ላይ እንኳ አሁን ካለበት መጠን ትንሽ ለውጥ ቢደረግ ጽንፈ ዓለም የሚሠራበት መንገድ ይለወጣል እንዲሁም ሕይወት ያለው ነገር በሙሉ ይጠፋል። ሆኖም እያንዳንዱ የመቆጣጠሪያ መሣሪያ አጽናፈ ዓለሙ አላንዳች ችግር እንዲንቀሳቀስና ሕይወት እንዲኖርበት በሚያስችል መንገድ በትክክለኛው መጠን ላይ የተስተካከለ ነው። ታዲያ ይህ ጎብኚ የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎቹ አሁን ባሉበት መጠን ስለተስተካከሉበት መንገድ ምን ድምዳሜ ላይ ሊደርስ ይችላል?
ጆርጅ ግሪንስታይን የተባሉት የሥነ ፈለክ ተመራማሪ እንዲህ ብለዋል፦ “መረጃዎቹን በሙሉ በምንቃኝበት ጊዜ ከሰው አቅም በላይ የሆነ አንድ ኃይል፣ እንዲያውም አንድ አካል መኖር አለበት የሚለው ድምዳሜ እያየለብን ይሄዳል። ከሁሉም በላይ የሆነ አካል መኖሩን የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ ማስረጃ ሳናስበው አግኝተን ይሆን?”
አንተስ ምን ይመስልሃል? በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ሕግጋት በጥንቃቄ ተስተካክለው የተቀመጡ መሆናቸው የትኛውን አስተሳሰብ ይደግፋል? ጽንፈ ዓለም ዓላማና ንድፍ ያለው መሆኑን ወይስ ትርጉም የለሽ የሆነ ሂደት ውጤት መሆኑን?
‘እዚህ ተገኝተናል፤ በቃ ይኸው ነው’
እርግጥ፣ በአምላክ መኖር የማያምኑ ሰዎች ከላይ የተመለከትናቸውን ነጥቦች የሚያስተባብል የመከራከሪያ ሐሳብ ይሰነዝራሉ። የተፈጥሮ ሕግጋት በጥንቃቄ የተስተካከሉ እንደሚመስሉ የሚገልጸው ሐሳብ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የማይገባ እንደሆነ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፦ ‘ሊታይ የሚችለው ጽንፈ ዓለም የሰው ልጆችን ሕይወት ሊያኖር የሚችል መሆኑ የሚካድ አይደለም። ባይሆንማ ኖሮ እዚህ ተገኝተን ስለዚህ ጉዳይ ስንጨነቅ አንገኝም ነበር። ስለዚህ ማብራሪያ የሚያስፈልገው ምንም ነገር የለም። እዚህ ተገኝተናል፤ በቃ ይኸው ነው።’ ይሁን እንጂ እዚህ ምድር ላይ የምንኖርበትን ምክንያት በተመለከተ እንዲህ ያለ አስተያየት ቢሰጥህ አጥጋቢ ሆኖ ታገኘዋለህ?
መሠረታዊ የሆኑት የተፈጥሮ ሕግጋት ሊሠሩ የሚችሉበት መንገድ አንድ ብቻ መሆኑና ሌላ አማራጭ አለመኖሩ ወደፊት ይረጋገጣል የሚል የመከራከሪያ ነጥብ የሚያነሱም አሉ። በሌላ አባባል ጽንፈ ዓለም ራሱ እንዲኖር ከላይ የተጠቀሱት የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች በትክክለኛው መንገድ መስተካከላቸው የግድ ነው። አንዳንዶች ‘የተፈጥሮ ሕግጋት በዚህ መንገድ የተቀመጡት ሌላ አማራጭ ስለሌለ ነው!’ ይላሉ። እንዲህ ያለው መጨበጫ የሌለው ክርክር እውነት ቢሆን እንኳ እዚህ የተገኘነው ለምን እንደሆነ አጥጋቢ መልስ ሊሰጥ አይችልም። በአጭሩ ጽንፈ ዓለሙ የኖረውና ሕይወት ሊኖርበት የቻለው እንዲሁ በአጋጣሚ ብቻ ነው?
ሌሎች ደግሞ በጽንፈ ዓለም ላይ ለሚታየው ንድፍ እንዲሁም የተፈጥሮ ሕግጋት በጥንቃቄ ተስተካክለው የተቀመጡ ለመሆናቸው ምክንያቱ የተፈጥሮ ሂደት እንደሆነ አድርገው ለመግለጽ ሲሉ ከአንድ በላይ ጽንፈ ዓለማት አሉ የሚል ጽንሰ ሐሳብ ያቀርባሉ። በዚህ መላ ምት መሠረት የምንኖርበት ጽንፈ ዓለም፣ የተለያየ ሁኔታ ካላቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጽንፈ ዓለማት አንዱ ሊሆን ይችላል፤ ከእነዚህ ጽንፈ ዓለማት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ዓላማ ወይም ንድፍ የላቸውም። በዚህ አመለካከትና ነገሮች በአጋጣሚ እንደሚከናወኑ በሚገልጸው ጽንሰ ሐሳብ መሠረት በቂ ቁጥር
ያላቸው ጽንፈ ዓለማት ከኖሩ ውሎ አድሮ በአንዳቸው ላይ ሕይወት ሊያኖር የሚችል ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም። ይሁን እንጂ ብዙ ጽንፈ ዓለማት እንዳሉ የሚገልጸውን ይህን መላ ምት የሚደግፍ አንድም ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም። እንዲሁ ግምታዊ ሐሳብ ብቻ ነው።የኖቤል ተሸላሚና ባዮኬሚስት የሆኑት ክርስቲያን ደ ዱቨ ይህን መላ ምት ፈጽሞ እንደማይቀበሉት ከገለጹ በኋላ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “እንደ እኔ አስተያየት፣ ሕይወትንና የሰውን አእምሮ ማስገኘት የማይችሉ በርካታ ሌሎች ጽንፈ ዓለማት ኖሩም አልኖሩ ሕይወትና የሰው ልጅ አእምሮ በጣም አስገራሚ ነገሮች በመሆናቸው ትርጉም ሊኖራቸው ይገባል። በትሪሊየኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ጽንፈ ዓለማት እንዳሉ የሚገልጸው ሐሳብ፣ ጽንፈ ዓለማችን ልዩ የሆኑ ገጽታዎች ያሉት መሆኑ የሚኖረውን ትርጉም አይለውጠውም፤ ጽንፈ ዓለማችን ያሉት ልዩ ገጽታዎች ከበስተ ጀርባ ያለውን ‘ወሳኝ ሐቅ’ [ማለትም ንድፍ አውጪ መኖሩን] የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች እንደሆኑ ይሰማኛል።”
የሰው ልጅ ንቃተ ሕሊና
ስለ ጽንፈ ዓለሙ ሕልውና የተለያዩ ንድፈ ሐሳቦችን ማቅረብ መቻላችን በራሱ አስደናቂ ነው። ጽንፈ ዓለም፣ ዓላማ የለውም ከተባለ እንዲህ ያለው የማሰብ ችሎታ በአጋጣሚ የተገኘ ነገር ሊሆን ነው ማለት ነው። ታዲያ እንዲህ ያለው አመለካከት ምክንያታዊ ይመስልሃል?
የሰው ልጅ አእምሮ “በመላው ጽንፈ ዓለም ውስጥ በጣም አስደናቂና እምብዛም የማይታወቅ ነገር” እንደሆነ ተገልጿል። በፊዚክስም ሆነ በኬሚስትሪ ምንም ያህል እውቀት ቢኖረን የሰው አእምሮ ረቂቅ የሆኑ ሐሳቦችን የማመንጨት ችሎታ ሊኖረው የቻለው እንዲሁም የሕይወትን ዓላማ ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርገው ለምን እንደሆነ አጥጋቢ በሆነ መንገድ ማብራራት አንችልም።
የሰውን አእምሮ የፈጠረውና የማወቅ ፍላጎት እንዲኖረው ያደረገው ከሰው በላይ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል አለ፤ አለዚያ እነዚህ ነገሮች በአጋጣሚ የተገኙ ናቸው። ከእነዚህ ሁለት አማራጮች ምክንያታዊ የሚሆንልህ የትኛው ነው?
ሌላ ማብራሪያ አለ?
ሳይንስ ስለ ጽንፈ ዓለም አሠራር እንዲሁም ስለ ምድራችንና ሕይወት ስላላቸው ፍጥረታት ብዙ እንዳሳወቀን አይካድም። አንዳንዶች ሳይንስ ብዙ ነገር እንድናውቅ ባደረገን መጠን “እዚህ መኖራችን ለማመን የሚከብድ” እንደሚመስል ይሰማቸዋል። እዚህ የተገኘነው በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ የምናስብ ከሆነ መኖራችን ለማመን የሚከብድ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሳይንሳዊ ጽሑፍ የሚያዘጋጁት ጆን ሆርገን እንዲህ ብለዋል፦ “በዙሪያችን የምንመለከተው ነገር በሙሉ እጅግ የተራቀቀ ንድፍ ያለው ይመስላል፤ ከአንዳንድ ነገሮች አንጻር ሲታይ በጭራሽ በአጋጣሚ ብቻ ሊገኝ የማይችል እንደሆነ [ይሰማኛል]።” በተመሳሳይም የፊዝክስ ሊቅ የሆኑት ፍሪማን ዳይሰን እንዲህ ብለዋል፦ “ጽንፈ ዓለምን ይበልጥ በመረመርኩና አሠራሩን በዝርዝር ባጠናሁ መጠን ጽንፈ ዓለም የእኛን መምጣት ያውቅ እንደነበረ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ አገኛለሁ።”
እስካሁን የተመለከትናቸውን ማስረጃዎች በሙሉ ይኸውም የተፈጥሮን ውስብስብነት፣ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ሕግጋት በጥንቃቄ ተስተካክለው የተቀመጡ መሆናቸውን እንዲሁም የሰውን ልጅ ንቃተ ሕሊና ግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ ቢያንስ ፈጣሪ ሊኖር እንደሚችል ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንም? እንዲህ ብለን እንድናስብ የሚያደርገን አንዱ ምክንያት ‘ሕይወት እንዴት ተገኘ? ዓላማስ አለው?’ የሚሉትን ጥያቄዎች ሊመልስልን የሚችለው ፈጣሪ በመሆኑ ነው፤ ሳይንስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አልቻለም።
እነዚህ ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ በሚባለው መጽሐፍ ውስጥ መልስ ያገኛሉ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ይህን መጽሐፍ ያሰፈሩት ፈጣሪ በመንፈሱ መርቷቸው እንደሆነ ገልጸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል ለምን አትመረምርም?
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.12 በዚህ ርዕስ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የሚለውን መጽሐፍ ከገጽ 10-26 ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የሰው ልጅ አእምሮ ትርጉም የለሽ የሆነ ሂደት ውጤት ነው?
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሳይንስ እንዲኖር ያስቻለው ምንድን ነው?
ሳይንሳዊ ምርምር ሊኖር የቻለው ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ሥርዓት ባለው መንገድ የተቀመጠ በመሆኑ እንዲሁም ኃይልና ቁስ አካል በአንድ ዓይነት ሁኔታ ሥር፣ ወጥ የሆነና አስቀድሞ ሊታወቅ የሚችል ባሕርይ ያላቸው በመሆናቸው ነው። ይህ ሥርዓት በሒሣብ፣ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪና ወዘተ መሠረታዊ ሕግጋት ሊገለጽ ይችላል። እንዲህ ያለ ሥርዓት ባይኖር ኖሮ ሳይንሳዊ ምርምር፣ ቴክኖሎጂና ሕይወት ራሱ መኖር አይችሉም ነበር።
በመሆኑም ‘የፊዚክስ ሕግጋት የመነጩት ከየት ነው? እነዚህ ሕግጋት አሁን በሚሠሩበት መንገድ የሚሠሩት ለምንድን ነው?’ የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ብዙ ሰዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች ምክንያታዊ የሚሆነው መልስ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል መኖሩ እንደሆነ ያምናሉ። አንተስ?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ከምንም የተገኘ ነው?
በእያንዳንዱ ሕያው ሴል ውስጥ የሚገኙት የዲ ኤን ኤ (ዲኦክሲራይቦኒውክሌይክ አሲድ) ሞለኪውሎች ለሕያዋን ፍጥረታት ትክክለኛ እድገት የሚያስፈልጉትን ዝርዝር መመሪያዎች በሙሉ ይይዛሉ። ዲ ኤን ኤ ይበልጥ ውስብስብ ቢሆንም በዲቪዲ ላይ ከተቀረጸ አኃዛዊ መረጃ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በዲቪዲ ላይ የተቀረጸ መረጃ በሚተረጎምበት ጊዜ ቪዲዮ ለማየት ወይም ሙዚቃ ለመስማት ያስችላል። በተመሳሳይም የተጠማዘዘ የገመድ መሰላል የሚመስል ቅርጽ ያላቸው የዲ ኤን ኤ ሞለኪውሎች፣ ሕይወት ላላቸው ነገሮች በሙሉ መሠረት የሆነውን እንዲሁም ሕያዋን ፍጥረታት አንዳቸው ከሌላው ለምሳሌ ሙዝ ከባቄላ፣ የሜዳ አህያ ከጉንዳን፣ ሰው ከዓሣ ነባሪ የተለዩ እንዲሆኑ የሚያደርገውን መረጃ ይይዛሉ።
በዲቪዲ ላይ የተቀረጸው አኃዛዊ መረጃ በአጋጣሚ የተገኘ ነው ለማለት የሚደፍር ሰው አይኖርም። ታዲያ ከዚህ ይበልጥ በጣም ውስብስብ በሆነው በዲ ኤን ኤ ላይ የሚገኘው መረጃ እንዲሁ ከምንም የተገኘ እንደሆነ ማመን ምክንያታዊ ይሆናል?
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Sombrero Galaxy: NASA and The Hubble Heritage Team (STScI/AURA)