በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“መጨነቃችሁን ተዉ”

“መጨነቃችሁን ተዉ”

“መጨነቃችሁን ተዉ”

“በባንክ የነበረን ገንዘብ ተሟጠጠ፤ በልጆቻችን ስም ያጠራቀምነው ተቀማጭ ገንዘብም አለቀ። ለብዙ ወራት ምንም ገቢ አልነበረንም።”

በሕንድ አገር ውስጥ ገጠራማ በሆነ አካባቢ የሚገኝን አንድ ትምህርት ቤት በኃላፊነት አስተዳድር ነበር። በአንድ ወቅት በግምት 500 የሚያህሉ ልጆች በትምህርት ቤቱ ይማሩ ነበር። ከዚያ በኋላ በከተማ የሚገኝ አንድ ታዋቂ ትምህርት ቤት አካባቢያችን ድረስ አውቶቡሶችን መላክ በመጀመሩ ልጆች እዚያ ትምህርት ቤት ለመግባት ሁኔታው አመቺ ሆነላቸው። አብዛኛዎቹ ተማሪዎቼ ከተማ ወደሚገኘው ወደዚህ ትምህርት ቤት እንደተዛወሩ መገመት አያዳግትም። እንዲያውም የተማሪዎቼ ቁጥር ከ500 ወርዶ 60 ገደማ ደረሰ። ይባስ ብሎም በዚያ ወቅት አካባቢ አንድ ሰው ቃሉን በማጠፍ ያበደርኩትን ገንዘብ ያስቀረብኝ ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስም ገንዘቤን አልከፈለኝም። ደሞዝ ልከፍላቸው የሚገቡ ብዙ የትምህርት ቤት ሠራተኞች ስለነበሩኝ ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ አጋጠመኝ።

በቤተሰብ አንድ ላይ ቁጭ ብለን ስለ ሁኔታው ተወያየን። ኢየሱስ፣ በገንዘብ ረገድ ‘አጥርቶ የሚያይ ዓይን’ እንዲኖረን የሰጠውን ምክር ለመከተል ጥረት በማድረግ በሌላ አባባል ባጀታችን ከሚፈቅደው በላይ ገንዘብ ባለማውጣት ሁላችንም የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ አሳይተናል። (ማቴዎስ 6:22, 25) ለነዳጅና ለጥገና የምናወጣውን ገንዘብ ለመቆጠብ ስንል ለተወሰነ ጊዜ መኪና ላለመያዝ ወሰንን። በጣም ሲመሽ የምግብ ሸቀጣሸቀጥ ዋጋ ስሚረክስ በዚህ ጊዜ በመሸመት የምግብ ወጪያችንን ለመቀነስ ጥረት አደረግን። በተጨማሪም የምንበላቸውን የምግብ ዓይነቶች ቀነስን።

የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መካፈል አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማናል። (ዕብራውያን 10:25) በመሆኑም በገንዘብ ረገድ ችግር ላይ ብንሆንም እንኳን ከጉባኤና ከትላልቅ ስብሰባዎች ላለመቅረት ቁርጥ ውሳኔ አደረግን፤ በእርግጥ ረጅም መንገድ መሄድ የሚያስፈልገን ጊዜ ነበር። ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ የማስተማር ሥራን ጨምሮ መንፈሳዊ አገልግሎታችን ርቀው ወደሚገኙ አካባቢዎች መሄድን ይጠይቃል። ይህን ሥራ ለማከናወን ከመኪና ይልቅ ሞተር ብስክሌት እንጠቀም ነበር። እርግጥ ነው፣ ብስክሌቱ ከሁለት ሰው በላይ መጫን አይችልም።

ይህም ቢሆን በአገልግሎቱ የምናሳልፈውን ጊዜ እንድንቀንስ አላደረገንም። እንዲያውም በተቃራኒው ባለቤቴና ሴት ልጃችን ለሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በመናገር ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ ጀመሩ። ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት ሲሉ ደርሶ መልስ ከ12 እስከ 16 ኪሎ ሜትር በእግራቸው የሚጓዙበት ጊዜ ነበር። እኔና ወንዱ ልጄም ሌሎችን መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ተጨማሪ ጊዜ ለማሳለፍ ጥረት አድርገናል።

በገንዘብ ረገድ አሁን ሁኔታችን በመጠኑ ተሻሽሏል። የሆነ ሆኖ ሁላችንም ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ሥፍራ መስጠት እንደሌለብን ከደረሰብን ችግር ተምረናል። በተጨማሪም ከቁጥጥራችን ውጪ የሆኑ ነገሮች ሲያጋጥሙን ከልክ በላይ መጨነቅ እንደሌለብን ትምህርት አግኝተናል። በተለይ መዝሙር 55:22 በጣም የሚያጽናና ሆኖ አግኝተነዋል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል፤ የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።” የገንዘብ ችግር በገጠመን ወቅት እነዚህ ቃላት መቶ በመቶ እውነት እንደሆኑ ተመልክተናል!—ተጽፎ የተላከልን